Sunday, 12 March 2023 10:30

“ሸክላ ሲሰበር ገል ይሆናል። መኳንንትም ሲሻሩ ህዝብ ናቸው” አንጋረ ፈላስፋ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

በአንድ ቤተ-መንግሥት ውስጥ ሁልጊዜ የሚከበር አንድ ስነስርዓት ነበር። ማታ እራት ተበልቶ ገበታው ከፍ ካለ በኋላ ወይን ጠጅ በማብረጃ ይቀርብና ወግ ይወጋል። ጨዋታ ይመጣል። ቤተሰባዊ ውይይት ይደራል። ታዲያ ሁሌ ልዑሉ ከንጉሱ ጋር የሚያደርገው ክርክር አለ። ንጉሱ አስፈሪና ጨካኝ ናቸው ብሎ የሚያምነው ልዑል፤ አስተዳደራቸው ግፈኛ መሆኑን ሊያስረዳ ሁሌ ይሟገታቸዋል።
ልዑል፡- እኔ መንግስቴን በምወርስበት ጊዜ አስተዳደሬ ከርስዎ የተለየ ነው የሚሆነው።
ንጉሥ፡- እንዴት?
ልዑል፡- በምንም ዓይነት ህዝቡን አልቆጣም። አላስፈራራም። አልጫንም። “ይሄን ካላደረክ” እያልኩ አዋጅ አላውጅም። ጥቁር ወተት፣ ነጭ ኑግ አምጣ እያልኩ አላስጨንቀውም።
ንጉሥ፡- ተው የዋዛ ህዝብ አይደለም ይሄ! እንደተልባ ሙልጭልጭ ነው። በእግርህ የረገጥከውን ምንጣፍ አንተ ሳትሰማ ከእግርህ ስር ስቦ ሊያወጣ የሚሞክር ምስጥ ህዝብ ነው።
ልዑል፡- ቢሆንም ቢቸግረው እንጂ ከመሬት ተነስቶ አልታዘዝም ብሎ አያምጽም።
ንጉሥ፡- እንግዲህ እኛ በእድሜያችን ያየነው ህዝብ፤ ስትተኛለት አልጋ የሚገለብጥ፣ ስትተኛበት የሚጎረብጥ፣ ዝም ካለ የሚያስፈራ፣ ከተናገረ የሚሸነቁጥ ነው። ሼክስፒር “ዘውድ የጫነች ጭንቅላት ወዮላት!” ያለው በግምት እንዳይመስልህ። በትክክል ተገንዝቦ ነው።
ልዑል፡- ምንም ይባል ምንም እኔ በበኩሌ ህዝብ ይሰቃይ ይረገጥ አልልም። እኛ እጅግ ጥቂት ነን። እኛ አልጋ ይጎረብጠናል ብለን ህዝቡ እንዲጉላላ ማድረግ በጭራሽ ልክ አይደለም።
 እንዲህ እንዲህ ያለ ሙግት በየቀኑ ይሟገታሉ። ብዙ ታሪክ እያነሱ ያወሳሉ። ቆይ ንጉሡ እለተ-ሞታቸው ደረሰና ሙሉ መንግስታቸውን ለልዑሉ ባርከውለት አለፉ። ስርዓተ ንግሱ ተፈጸመና የልዑሉ ዘመነ መንግስት ጀመረ። አዲሱን ንጉስ ህዝቡ ጥያቄ መጠየቅ ጀመረ። እንቅልፍ ነሳው። አንዱን ጥያቄ ሲመልስ ሌላ ይቀጥላል። አንድ አዋጅ አውጆ “አሁን አረፍኩ! ህዝቡ ፈነጠዘ!” ሲል ወዲያው ቤተመንግስቱ ደጃፍ ታድሞ አቤት ሲል ያገኘዋል። መንፈቅ ሳይሞላ ተማረረ።
ባለሟሎቹን ሰብስቦ፡- “በሉ እንግዲህ በአገሩ በጠቅላላ ያለውን ማረሻ ነሽ፣ ማጭድ ነሽ፣ መዶሻ ነሽ፣ የወዳደቀ ብረታ ብረት ሁሉ አንድም ሳይቀር ሰብስቡና አምጡልኝ” አለ። ባለሟሎቹ እንደታዘዙት አደረጉ። በአገሩ ያለውን ብረታ ብረት አንዲት ብሎን ሳትቀር አመጡ።
ንጉሡም፡- “በሉ ይህን ሁሉ ብረት ቀጥቅጣችሁ፣ አቅልጣችሁ የእጅ ሰንሰለትና የእግር ብረት ስሩ” አላቸው።
ባለሟሎቹም፡- “ ምነው ንጉሥ ሆይ ህዝቡን ላያስቀይሙ፣ ላያጉላሉ፣ ላያስሩ፣ ላይገርፉ ቃል ገብተው ነበር እኮ?! ለምን ቃልዎን ይሽራሉ?” ብለው ጠየቁት።
ንጉሡም፡- “እሱ መሬት ሆኜ ያሰብኩት ነው። አልጋው ላይ ስወጣ የተገላቢጦሽ ሆኖ ነው ያገኘሁት። አባቴ እንደዚያ እረግጦ እየገዛ ያቃተውን ህዝብ እኔ ባዶ እጄን አልችለውም። ከብት ህዝብ ነው!! ፈርገጥ ሲል ጥፍር አርጎ ማሰር፣ እምቧ ሲል እምሽክ፤ ማድረግ ያስፈልጋል!” አለ በኃይለ-ቃል።
አንዱ ባለሟልም፤
“ኧረ ንጉሥ ሆይ፤ መክረን ዘክረን ለጥያቄው መልስ ብንሰጥ ይሻላል”
ንጉሱም፤ “ህዝብ እንደ ብዛቱም ሁሉ እንቆቅልሹ አያልቅም። ጥያቄውም አያቆምም። ስለዚህ ትዕዛዜን ፈጽሙ። እናንተም እምቢ ካላችሁ ያው ህዝብ እንደምትሆኑ አትርሱ!” ብሎ አሰናበታቸው።
***
በንግስም ይምጣ በውርስ፣ በምርጫም ይምጣ በርግጫ፣ በትግልም ይገኝ በእድል፣ ስልጣን ከፍተኛ ጭንቀት አለበት። ስልጣን፤ ላወቀው፣ በጥንቃቄ ተዘጋጅቶ፣ ተደጋግፎ፣ አስቦና አስልቶ የሚረከቡት እንጂ ወይ ተሻምተው፣ ወይ አድፍጠው አልያም አድብተው በጮሌነት የሚመነትፉት ከካርቶን የተሰራ ዘውድ አይደለም።
በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ምስቅልቅል የአስተሳሰብና  የአስተዳደር ችግር እንዲሁም ያልተፈቱ አንቆቅልሾች መነሀሪያ በሆነች ሀገር ውስጥ ስልጣን ከጽድቁ ጭንቁ ይበዛል!! እጅግ በተለይም ደግሞ አልጋው አድሮ እንደሚጎረብጥ፤ ወንበሩ ሲሞቅ እንደሚቆረቁር፣ የህዝብ አይን ሲፈጥ  እንደሚቆጠቁጥ፣ ከታሪክ ፍርድ እንደማይመለጥ ልብ ሳይሉ፤ የየግለሰብና የድርጅቶችን እኩይ አላማ ለማሳካትና የየራስ እንጀራን ለመጋገር መሯሯጥ የኋላ ኋላ ከላይ እንደተጠቀሰው ልዑል “እግር ብረት ስሩልኝ! ወደማለት ማምራቱ አይቀርም። ቃልን ለመጠበቅ ቃል የሚገቡበትን ጉዳይ በቅጡ ማወቅና ለራስም ሆነ ለህዝብ ታማኝ መሆንን ይጠይቃል። ሰዎች ወንበር በተለዋወጡ፣ የየራሳቸውን ቄጤማ በቆረጡና በጎዘጎዙ ቁጥር የተሻለ አስተዳደርና የተባ ራዕይ መጠበቅ አይቻልም። ማንንም ቢሆን ከአባይ ድልድይ ጠባቂነት አንስተው የአዋሽ ድልድይ ጠባቂነት ቢሾሙት ለውጥ የለውም። “አሮጌ ጠላ በአዲስ ጋን” ከመጥለቅ የተለየ ነገር አይሆንምና። አሮጌ ጋን ውስጥ አዲስ ጠላ ለመጥመቅ ካሻን ደግሞ አሮጌውና የኮመጠጠው ጠላም ሆነ ቅራሪ ከአሮጌው ጋን ውስጥ መፍሰስ አለበት። ከዛ ጋኑ መታጠብ፣ በጭንቅላቱ ተደፍቶም በወይራ መታጠን ይኖርበታል። ከዚያ የማያጋድልበት ጠንካራ ቦታ መቆም አለበት። ከዚያ ደግሞ የጥሩ ባለሙያ እጅ  መገኘት ይኖርበታል ወዘተ…። ይሄ ሁሉ ለህዝብ ሲባል ነው። ጥዋው የህዝብ እንጂ የሹሙ ስላልሆነ ነዋ!!
ለክልልና ለፌደራል ምክር ቤት የተመረጡ፣ ነገም ለየወረዳውና ለየቀበሌው በሚደረገው ምርጫ ከፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆነ ከግል ሊመረጡ የተዘጋጁ ሁሉ ጥዋውን ለመንጠቅ ሳይሆን ለመረከብ፣ ተረክበውም በአግባቡ ማህበራቸውን ለመደገስ ንጹህ ልቦና ሊኖራቸው ይገባል። አለበለዚያ “ሳያውቁ በስህተት አውቀው በድፍረት ለሚሰሩት ስህተት” እነሱ እንጂ ሌላ ማን ተጠያቂ ይሆናል?
“ሸክላ ሲሰበር ገል ይሆናል። መኳንንትም ሲሻሩ ህዝብ ናቸው!” እንዲል አንጋረ ፈላስፋ፤ እንደ ሸክላ ላለመፈረካከስ የሕዝብን አደራ አለመብላት ብልህነትም ግዴታም ነው።Read 1826 times