Sunday, 12 March 2023 11:48

ተማሪው ሰይጣን (ትርጉም)

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(4 votes)

 ነሐሴ ስምንት ልደቴ ነበር፡፡ ልደቴን ለማክበር የመረጥኩት መንገድ የማላውቀውን ሰው ፈልጌ በንትርክ መጥመድ ነው፡፡
 ከቀኑ አስር ሰዐት ገደማ ሲሆን ፍሎሪዳ ካርዶባ ኩርባ ላይ አንድ ሰውን ጠርቼ  አስቆምኩት፡፡ እድሜው ወደ ስልሳዎቹ ገደማ የሚገመት፣ የእጅ ቦርሳ ያንጠለጠለ ሰውዬ ነው። ጠበቃዎችና ስልጣን ያላቸው ሰዎች ላይ ብቻ የሚገኝ ንቃት ይታይበታል፡፡
“ይቅርታ ጌታዬ” አልኩት፤  “ፕላዛ ደ ማዮ ወደ የት አቅጣጫ እንደሆነ ልትጠቁመኝ ትችላለህ?”
ሰውየው ቆም አለ፡፡ ከእግር እስከ ራሴ በደንብ አድርጎ በዐይኑ አዳረሰኝ፡፡ እና ከጠየቅሁት ጥያቄ ጋር ምንም የማይገናኝ ሌላ ጥያቄ ጠየቀኝ፤ “መሄድ የፈለከው ወደ ፕላዛ ደ ማዮ ነው ወደ አቫንዳ ደ ማዮ?”
“ለነገሩ፤ መድረስ የፈለኩት ወደ ፕላዛ ደማዮ ነው፤ ግን እሱ የማይቻል ከሆነ ሌላ ቦታ ብሄድም ጉዳዬ አይደለም”
“ጥሩ እንደዛ ከሆነ” አለና፣ እኔ የተናገርኩትን ለመስማት ሳይሞክር፣ እኔንም ልብ ብሎ ሳያስተውል… አቅጣጫውን መጠቆም ቀጠለ፡፡
“በዚህ ታደርግና” ወደ ደቡብ አቅጣጫ እያመለከተ… “ቫያሞንትን፣ ታኩማንን፣ ላቫሊን… አቋርጠህ እለፍ”
የስምንት መንገድ ስሞችን መዘርዘር ደስታ የሚሰጠው ሰውዬ መሆኑን ተገነዘብኩኝ፡፡ ስለዚህ ላቋርጠው ወሰንኩኝ፡፡
“ስለምትናገረው ነገር እርግጠኛ ነህ?” አልኩት፡፡
“በጣም እርግጠኛ ነኝ”
“ስለ ተጠራጠርኩህ ይቅር በለኝ” አልኩት፣ ለማስረዳት እየሞከርኩኝ፤ “ግን አየህ ከጥቂት ደቂቃዎች ቀደም ሲል አንድ መልኩ የብልህ እንደሆነ የሚያስታውቅ  ሰው የፕላዛ ደ ማዮ አቅጣጫ በሌላ በኩል እንደሆነ ጠቁሞኝ ነበር” … እጄን ወደ ሳን ማርት አቅጣጫ እያመለከትኩ።
“ከተማውን የማያውቅ ሰው መሆን አለበት እንደዚህ የጠቆመህ” ብቻ ነው ሰውየው ማለት የቻለው፡፡
“ቢሆንም ቅድም እንዳልኩህ ሰውየው የብልህ ፊት ነው ያለው፤ እናም አንተን ከማምን እሱን ማመኑን እመርጣለሁ”
የተኮሳተረ መልክ መጣበትና፤ “ ከእኔ የበለጠ እሱን ለማመን ለምን መረጥክ እስቲ ንገረኝ?”
“እሱን ካንተ የበለጠ ለማመን ስለፈለግሁ አይደለም፡፡ ግን ቅድም እንዳልኩህ እሱ የተማረ ሰው ፊት ነው ያለው”
“አትለኝም… የእኔስ ታዲያ የመሃይም ፊት ነው?”
በጣም ደንግጬና ተገርሜ፤ “በፍፁም! በፍፁም! እንደዛ መች አልኩኝ?”
“የዛኛው ሰው ፊት የተማረ ነው ስላልክ የኔ ደግሞ…”
“መቼም እውነት ለመናገር ከሆነ ያንኛው ሰውዬ ብሩህ አእምሮ ያለው እንደሆነ ባኳሁዋኑ ያስታውቃል”
በንትርክ ወጥመዴ ውስጥ የያዝኩት ሰለባዬ፣ ትዕግስቱን እየጨረሰ እንደሆነና ትዕግስት እያጠረው እንደመጣ ያስታውቃል፡፡
“በጣም ጥሩ ወዳጄ” አለኝ፤ “እኔ ጊዜ የተረፈኝ ሰው አይደለሁም፤ ደህና ዋል”
“መልካም፣ ግን ወደ ፕላዛ ሳን ማርት በየት በኩል እንደምሄድ አሁንም አልጠቆምከኝም…”
***
ድንገት ንዴት ፊቱን ወረሰው፡፡
“ወደ ፕላዛ ማዮ መሄድ ነው የምፈልገው አልነበረም ቅድም ያልከው?”
“በፍፁም! ወደ ፕላዛ ደ ማዮ መሄድ ነው የምፈልገው አላልኩም፡፡ እኔ መሄድ እፈልጋለሁ ያልኩት ወደ ፕላዛ ሳን ማርት ነው”
“እንደዛ ከሆነ” አለ አሁን እጁን ወደ ሰሜን እያመለከተ፤ “ ካሌ ፍሎሪዳ የሚለውን ይዘህ ፓጉዌይን አልፈህ ሂድና….”
“አንተ ሰውዬ ልታሳብደኝ ነው” ብዬ በተቃውሞ አቋረጥኩት፡፡ “ቅድም ወደ ደቡብ እየጠቆምክ… በተቃራኒ አቅጣጫ ሂድ እያልክ ስታሳየኝ አልነበር?”
“ወደ ፕላዛ ደ ማዮ እሄዳለሁኝ ብለኸኝ ስለነበር ነዋ”
“እንዴት አድርጌ ላስረዳህ ሰውዬ… እኔ ወደ ፕላዛ ደማዮ መሄድ አልፈለኩኝም… ወይንስ የምንነጋገርበትን ቋንቋ አታውቀውም? አለዚያ ከእንቅልፍህ በደንብ አልነቃህም ማለት ነው”
የሰውዬው ፊት ወደ ቀይ ተቀየረ፡፡ የቀኝ እጁ በያዘው ቦርሳ ላይ ሲጠብቅና ሲጠነክር አየሁኝ። ባልደግመው የሚሻል የሆነ ቃል ተናገረኝና… በፈጣን የተናደዱ እርምጃዎች መንገዱን ቀጠለ። ትንሽ ሳይበሳጭብኝ አልቀረም፡፡




Read 1135 times