Saturday, 18 March 2023 20:05

የእስከዳር ግርማይ - “የፈረንጅ ሚስት”

Written by  ቢኒያም አቡራ
Rate this item
(4 votes)

 አውቶ ሜካኒኮች “Troubleshooter” የሚሉት የመኪና ሕመም የት እንደሆነ የሚያገኙበት መሣሪያ አላቸው። “የፈረንጅ ሚስት” የተሰኘው የእስከዳር ግርማይ መጽሐፍ በኢትዮጵያ መኪና ላይ ካሉ ሕመሞች አንደኛውን የሚጠቁም ባለ 119 ገጽ መጽሐፍ ነው፡፡ የመኪና አንዱ ብልሽት መኪናውን በሂደት ከጥቅም ውጭ እንደሚያደርገው ሁሉ በሀገር ላይ የተሰነቀረ አንድ ሳንካም ጉዞን ለመግታት አቅም ማደርጀቱ አይቀሬ ነው፡፡ የሀገራችን ግብድዬ ሳንካ ሚጢጥዬ የምትመስል የግለሰብ እንቅፋት መሆኑን በአዳም ረታ “እቴሜቴ ሎሚ ሽታ” የተሰኘው ድርሰት ላይ ማስተዋል እንችላለን፡፡ በዚህ ድርሰት ውስጥ ምስራቅ የተሰኘች ገጸሰብ አለች፡፡ ልጇን “በኔ ሕይወት ቀዳዳ ብትገባ ሀገርህን ታያለህ!” ትለዋለች። እስከዳር ግርማይ የራሷን የሕይወት ሽንቁሯን ለማሳየት ምኩራብ ላይ ተሰይማለች፡፡ በዚህ የሕይወት ሽንቁር ስናጮልቅ በሀገራችን ካሉ ደዌዎች አንደኛውን እናገኝበታለን፡፡ እንጀምር! (ለካስ ከጀመርን ቆየን!)
ነገረ-ሴትን ከሎሬት ጸጋዬ ገ/መድኅን እይታ ጋር ትፈክራለች፡፡ ጋሽ ጸጋዬ አድባርን ከባዕድ አምልኮ ይልቅ ከሴትነት ጋር ያቋልፋል፡፡ በቲያትሮቹም ላይ የጡዘቱ ማርገቢያ፣ የልቀቱ መላ ፈጠሪ፣ የእውቂያው አብሳሪ(ተራኪ) እና ደምዳሚ ያደርጋቸዋል፡፡ “በአባቶቻችን ሥልጣኔ ውስጥ መሪዎቹ ሴቶች ናቸው” ባይ ነው - ጋሽ ጸጋዬ፡፡ የእስከዳር የሙግት ወንጭፍ እሚወረወረው ከዚህ ለጥቆ ነው፡- “በጋሽ ጸጋዬ ሥራዎች ውስጥ ያለችዋ ሴት አሁን በመካከላችን አለች ወይ? የፈረንጅ ሚስትስ ምድቧ ከወየት ነው?” ትለናለች፡፡
የእስከዳር ጥያቄ CATCH 22(መልስ የሌለው ጥያቄ) አይደለም፡፡ ጥናት እሚጠይቅ እንጅ፡፡ “በጋሽ ጸጋዬ ሥራዎች ውስጥ ያለችዋ ሴት አሁን በመካከላችን አለች ወይ?” የሚለውን ጥያቄ በትዝብት መልክ ለእኛው ትተወውና የፈረንጅ ሚስት ምድቧን ግን ራሷ እንዲህ ስትል ትመልስልናለች፡- “ማኅበረሰባችን ለፈረንጅ ሚስት የሚሰጣት ሥፍራ ከምናውቃቸው ሴቶች ሁሉ ዝቅ ያለ ስለሆነ ከሁሉም ሴቶች ታንስብኛለች፡፡ ከሴቶች ሁሉ ታንሳለች ስል፣ ከሐበሻ ሚስት፣ ከኃብታም ቅምጥ፣ ከሴተኛ አዳሪ ወዘተ ሁሉ ማለቴ ነው፡፡” ጉድ በል ጎንደር! እንዴት ለሚለው ጥያቄ የመጽሐፉ መሶብ ውስጥ ከተሰነጉት ውስጥ “ገጠመኝ አንድ” በተሰኘው ምዕራፍ ከገጽ 21 – 30 ባለው ውስጥ ሁነኛ አስረጅ የሆኑ ሰበዞች ተዘርዝረዋል፡፡
ወደ መስታወት እስካፍንጫችን በመቅረብ ሙሉ ፊት አይታይም፡፡ መጽሐፍ ራሱ መጽሐፍ ውስጥ ተሆኖ ሳይሆን ከውጭ ነው የሚነበበው። እንዲሁም ደግሞ ለዐይን እጅግ ቅርብ ቅንድብ ቢሆንም ዐይን ያለመስታወት ቅንድብን ማየት አይችልም፡፡ እናም ጉዳዩን አንድም ከውጭ ሆነን፣ አንድም “ነገሩ ለኛ ይበልጥ ቅርብ ነው!” ከማለት ተቆጥበን እስኪ በእስከዳር መስታወት ቅንድባችን ላይ ያለውን ጉድ እንይ፡፡ የፈረንጅ ሚስት ላይ የሚደረጉ ጫናዎችን አንድ በአንድ እንይ!
የሐበሻ ሴት ከፈረንጅ ወንድ ጋር ስትታይ ልጅቷ ጥቅምን ፍለጋ የምትከተል እንጂ፣ ሕጋዊ ሚስት እጮኛ ወይም ጓደኛ አልያም የሥራ ባልደረባ ልትሆን እንደምትችል አይታሰብም። ስለሆነም ከፈረንጅ ጋር የታየች ሴትን ሁሉ እንደ ሴተኛ አዳሪ ብቻ እያዩ በየካፌው፣ በየመንገዱ፣ በየሆቴሉ፣ በየመንገዱ መዝለፍ ደረጃ አንድ የጽድቅ አገልግሎት የሚመስላቸው ሰዎች ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ተው የሚልም የለ! በሰው ሀገር ተንከራታ ለፍታ ጥራ በገዛችው መኪና ስትጓዝ “እንዴት ብትሰጪ ነው የተገዛልሽ?” የሚል ውረፋ ማስተናገድ የየዕለት ቀለብ ነው፡፡ “የሐበሻ ወንዶች ሆይ! እባካችሁ ገበታ ላይ እንደቀረበው ገበታ ተቋደሱኝ!” ያለች ይመስል “የፈረንጅ ሚስት የሐበሻ ያምራችኋል አይደል ለሚል ጾታዊ ጥቃት ያሰፈሰፈ የአባወራ ቁጥር ቤቱ ይወቀው፡፡ እነዚህንና መሰል ጥቃቶችን ያካተተ ተረክ እጅግ ግላዊ ከሆኑ ገጠመኞች ጋር ታጅቦ በመጽሐፉ ውስጥ ተከትቧል፡፡ የፈረንጅ ሚስት ላይ የምንለድፈው የተለነቆጠ ጭቃ በዚህ ቢያበቃ ምንኛ መልካም በሆነ! ግና የነውር በትራችን ይለጥቃል፡፡
“ሰው” እንዳገባች ማኅበረሰቡ ስለሚዘነጋ የእሷም “ሰው” መሆን እርስ በራስ ይጣፋል፡፡ ለማኅበረሰቡ ከባሏ ሰዋዊነት ይልቅ “ፈረንጅነቱ” ስለሚገዝፍባቸው የሷን “ሐበሻዊነት” የሚቃኙት በ”ሰው”ኛ የመሆን ዕድሉ የተመናመነ ነው። ስለሆነ  መስተጋብራዊው ቅኝቱ ይፋለሳል፡፡ ስለሆንም የሃያ ዓመት ትዳሯን በአንድ መናኛ ዓረፍተ-ነገር በማጠልሸት፣ ጫና ለማድረስ ይታትራሉ፡፡ የሐበሻ ሴት አዲስ ሐሳብ ባፈለቀች ቁጥር “እሷማ ከየት አምጥታው ድስት ውስጥ የሌለን ወጥ መቼም ጭልፋ አያወጣው፡፡ ባይሆን ሐሳቡን ፈረንጁ አፍልቆት ነው እንጅ!” በማለት የፈጠራ አቅሟን ያኮስሱታል፡፡ የስኬቷን ሁሉ አኮቴት ለፈረንጁ በመስጠት ጥረቷን የከንቱነት ባሕር ውስጥ ይሞጅሩታል፡፡ በእሳት ዳር ተረኮች የብላቴናዎችን አዕምሮ “ፈረንጅ፣ ደሃ ሴትን የሚያገባው በሀገሩ ባለው መንግሥት ፍራንክ ስለሚያሸልመው ነው!” በማለት ሕጻናት ሳይቀሩ የፈረንጅ ሚስቶችን በተንሸዋረረ እይታ እንዲመለከቷቸው ይመረዛሉ - በተለይ በገጠር። “የሐበሻ ሴቶችን ከነጭ ወንድ ጋር ስመለከት የምናደድ እና ራሴን የሀገር ቅርስ አስመላሽ ኮሚቴ አድርጌ የማይና አስመልስ አስመልስ የሚለኝ እኔ ብቻ ነኝ” በማለት በየማኅበራዊው ሚዲያ ግድግዳ ላይ እየለጠፉ በኢሞጂ ማሽካካትና ሥነ ልቦናዊ ጥቃት ማድረስ የተለመደና እንደ ተገቢ ድርጊት እየተቆጠረ ነው፡፡
የፈረንጅ ሚስት ምን እድሜዋ ቢገፋም የዚህ ውረፋ ሰለባ ከመሆን አረጋዊነቷ እንኳ አያስጥላትም፡፡ ለዚህም የሚሆን ሁነኛ ምሳሌ እስከዳር ግርማይ ከገጽ 103 ጀምሮ አስፍራልናለች፡፡ አንዲት በሳባዎቹ መጀመሪያ አከባቢ የምትገኝ ደርባባ እናትን በመጥቀስ ነውራችንን ታሳየናለች፡፡ እግዚዖ! እኚህ ደርባባ ኢትዮጵያዊት እመቤት የሚደርስባቸውን ጥቃት አንገብግቧቸው በውጭ ሀገር መኖር ከጀመሩ ወደ አርባ ስምንት ዓመታት የሆናቸው ሲሆን ፈረንጁ ባለቤታቸው ግን የሚኖረው እዚሁ ኢትዮጵያ ነው፡፡
የፈረንጅ ሚስትን ከመደብ ወለል በታች ማድረጋችን ሳያንስ እርስ በራስ ተደራጅተው እንዳይታገሉን ነው መሰል የፈረንጅ ሚስትን እንኳ በሁለት መደብ እንከፍላለን፡፡ እኩያዋን ያገባችና፣ እኩያዋን ያላገባች በሚል እንመድባታለን፡፡ እኩያዋን ያላገባች ሴት እኩያዋን ካገባች ሴት ይልቅ በማኅበረሳበችን ዘንድ ይበልጥ ቦታ ይቸራታል፡፡ በእድሜ ገፋ ያለውን ፈረንጀ ያገባች ሴት ከሴተኛ አዳሪ ምድብ ውስጥ እንድለድላትና እኩያዋን ካገባች ሴት እናስበልጣታለን፡፡ ታዲያ ግን በእድሜ ገፋ ያለውን ፈረንጅ ያገባች ሴት እኩያዋን ካገባች ሴት ላስበለጥንበት ትግላችን ክፍያ እንፈልጋለን፡፡ “እስኪ ካገኘሽው የዶላር ጎተራ ላይ ለኔም ቀንሺልኝ!” በማለት እርቧችንን ይዘን እንኮለኮላለን፡፡ በቸሮታዋ ምከንያትም ካለችበት እርከን ከፍ እናደርጋትና ከሴተኛ አዳሪነት ምደባ ውስጥ በማስረግ ክብራችንን እንገልጻለን፡፡ በተቃራኒው እኩያዋን ፈረንጅ አግብታ በፍቅር ሰንሰለት ለተጋመደችው ናዲር(የታችኛው ታችኛው) እናሰርጋታለን፡፡
በፈረንጅ ሚስት ላይ ማኅበረሰባችን እየተፋ ያለው ቅርሻት በጥቂቱ ይሄን ይመስላል፡፡ መጋቢ ሀዲስ እሸቱ ዓለማየሁ “አሲድ የተደፋበት ፊት ብቻ ሳይሆን አሲድ የተደፋበት ልብን ጭምር የሚያይ ማኅበረሰብ መፈጠር አለበት።” ይላል። ይሄን ልብ ያስተዋለ የተገዘገዘውን አንጀት በፍቅር መዳሰስ አለበት አሊያ ቆርጦ ለመለየት አንዲት ስንዝር በቂ ነው፡፡ ይሄ የገባው ጋሽ ጌትነት እንየው እንዲህ ይላል፡-  
በደል ያሰለለው ጥቃት የበዛበት
የተገዘገዘ የተጀመረ አንጀት
ባልጎለደፈ ቃል ባልገረጀፈ ጣት
በስሱ ካልነኩት፣ በፍቅር ካልዳሰሱት
በስስት ካልያዙት፣ በእውቀት ካላገሙት
በበደል በጥቃት ዳግም ከደፈቁት
ደፍቀው ከጓጎጡት
የተብሰከሰከ፣ የተጀመረ አንጀት
እንኳንስ ሊቀጥል፣
ጥቂት ይበቃዋል፣ ቆርጦ ለመለየት።
ግን ይሄ የተገዘገዘ አንጀት እንኳን ሊያባብሉትና በፍቅር ሊነኩት ይቅርና ይበልጡኑ ሌላ ይጨመርበታል በማለት እስከዳር ግርማይ ደግሞ “የፈረንጅ ሚስት” በሚለው መጽሐፏ ትለጥቃለች፡፡ የውጭ ሀገር የቢሉ ቢለዋ ሲገዘግዛት፣ የኑሮ ቀንበር ሲከብዳት፣ ወደ እንግዳ ተቀባይዋ እናት ሀገሯ ኢትዮጵያ፣ ከፈረንጅ ባሏ ጋር ስትመጣ የሚጠብቃት ፈጽሞ ያልገመተችው ይሆናል፡፡ ፈረንጅ ብሩን ከጓሮ ቀንጥሶ እንደሚያመጣው የሚያስቡ የሩቅ የቅርብ ዘመድ አዝማድ ደጅ ላይ ይኮለኮላሉ፣ አከራዮች ፈረንጁን ሲያዩ የኪራዩን ዋጋ ይቆልሉታል፡፡ የትኛውም የግዢ ዕቃ ሦሰት አራት እጥፍ ማድረግ ተገቢ ተግባር ሆኖ ይገኛል፡፡ ሁለገቧ አርቲስት አዜብ ወርቁ ለልጇ ለመሸመት ብላ በገባችው ሱቅ ውስጥ ያሳለፈችው ጸያፍ ክስተት ነገርየው የለየለት ቀውስ መሆኑን በመጽሐፉ ውስጥ ተጠቁሟል፡፡ ነጋዴው እምር ብሎ አዜብን “የሚከፍለው ፈረንጁ እስከሆነ ድረስ አንቺ ምን ቸገረሽ? ከፈረንጁ ባልሽ እኔ ሐበሻው ወገንሽ አልበልጥብሽምና ነው?” ብሏታል፡፡  “ከባልሽ ባሌ ይበልጣልና ሽሮ አበድሪኝ!” እንዳለችዋ ወፈፌ፡፡
በየሆቴሎቻችን እና በጉብኝት ስፍራዎቻችን ለፈረንጅና ለሐበሻ ያለው የዋጋ ልዩነት ደግሞ ሌላ አስቂኙ ቂልነታችን መሆኑን እስከዳር በብዕሯ ትጠቁመናለች፡፡ ይሄ ጉዳይ በጊዜ እልባት ካላገኘ የጎብኚዎችን መቀነስ ሊያስከትል እንደሚችል እንኳ አናስብም፡፡ ምንም እንኳ ኢትዮጵ ውስጥ ያሉ የቱሪስት መስህብ ሥፍራዎችና ሆቴሎች ከሌላው ዓለም አንጻር ርካሽ ቢሆኑም ለሐበሻ እና ለፈረንጅ ተገልጋይ ያለው የዋጋ ተመን መለያየት የውጭ ሀገር ጎብኚዎችን የሚያበሳጭ ነገር መሆኑን በመጽሐፉ ውስጥ ተጠቅሷል። በጊዜ ጥናት ተደርጎ እልባት ሊሰጠው አይገባምን?
ሌላው የፈረንጅ ሚስት በሀገር ውስጥም ብቻ ሳይሆን በውጭውም ዓለም የዚህ ገፈት ቀማሽ ናት፡፡ የሰባ ሰባቱን ድርቅ እየተዘቱ የፈረንጁን ባል ከርሃብ እንዳዳናት ይቆጥሩታል፡፡ ከእርስበርስ ጦርነት  ያመለጠችው በፈረንጁ ባሏ መሰላልነት እንደሆነ ይታወጃል፡፡
ዶ/ር ተስፋዬ ሮበሌ “ሥነ አመክንዮ” በተሰኘ መጽሐፉ “በምዕራቡ ዓለም የመማሪያ መጻሕፍት ከመብዛታቸው የተነሳ፣ የመብዛቱ “በረከት” ተጠቃሚውን በምርጫ “መርገም” ውስጥ ከቶታል።” ይላል፡፡ እኛ ሀገር ግን በተቃራኒው በብዙ ጉዳዮች ላይ የተሰነደ ሥራ ባለማግኘት ድርቅ እንናውዛለን፡፡ ዶ/ር እጓለ ገብረዮሐንስ “የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ” በተሰኘ መጽሐፉ እንዲህ ይላል፡- “ብዙ እናቶች ጎመን በድስት ጥደው ማብሰልን ለአዕላፍ ቀናት ከውነውታል። ከእንፋሎቱ መብዛት የተነሳ የድስቱ ክዳን ሲገለበጥ ለአያሌ ቀናት ተመልክተዋል፤ ግን ከዚህ መነሾ የእንፋሎት ሞተር ሊሰራበት የሚችልበትን መሠረታዊ ጉዳይ ያስተዋለች አንዲትም እናት የለችም፡፡” ይሄን ሁሉ ገፈት እየቀመሱ የነበሩ ብዙ ኢትዮጵያውያን የፈረንጅ ሚስቶች ነበሩ፡፡ አንዳቸውም ግን እንዲህ ባለ ሰፋ ያለ ሀተታ አላጋሩንም፡፡ በዝምታ ዛጎላቸው መጠቅለልን መርጠው ነበር፡፡ ጉዳዩን ለአደባባይ ላበቃቸው እስከዳር ግርማይ ገለታ ይግባት ከማለት በቀር ምን ቃል አለን? ክብረት ይስጥልን!


Read 2366 times