Print this page
Saturday, 18 March 2023 19:51

እሱ ሰጠ፤ እሱ ነሣ ያስብላል - የዘመኑ ቴክኖሎጂና የዘፈን አልበም።

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

 • ሙሉ የሙዚቃ አልበም እንደ ሕይወት ነው። ነጠላ ዜማ እንደ ገጠመኝ ነው።
   • አዲስ ዘፈን በዜማ ጥበብ አሳምሮ መስራት ሌላ ነው። አስመስሎ መዝፈን ሌላ ነው።
         
        ሙዚቃ እንደ ልብ አማርጦ፣ የፈለጉትን ያህል መስማት፣… ዛሬ ነው። ሁሉም ሞልቶ! ሁሉም ተትረፍርፎ። ቴክሎጂ ምን ይሳነዋል? የልብ በሚያደርስ እንከን በማይወጣለት ጥራት ሙዚቃ ለማዳመጥ፣ እንደዛሬ ዘመን እጅግ የተመቸ ጊዜ፣ በታሪክ ታይቶ ተሰምቶ አይታወቅም።
ታዲያ ይሄን ጊዜ ጠብቆ፣ የሙዚቃ ጥበብ ቢሳሳ አልበም ቢጠፋ፣ ምን የሚሉት ምቀኝነት ነው? ዘንድሮ ስንት አዲስ አልበም ሰምታችኋል? ብዙ አይደለም። ወይስ፣… ጥቂት ቢሆንም ይበቃል?
“የአስቴር አወቀ አዲስ አልበም ለብቻው ብዙ ነው” የሚሉ አድናቂዎች ይኖራሉ። እውነት ነው። እንደ ሁልጊዜው፣  እንደ ብቃቷ ልህቀት፣ የጥበብ በረከቷ ብዙ ነው። ለወራት፣ ለዓመታት የደከመችበት አልበም፣ በሙዚቃ ባለሙያዎች የታጀበው የአስቴር አወቀ ጥበብ፣… ድንቅ ስጦታ ነው።
በተለይ በግርግር ለታመሰ አገር፣ አልበሟ ፈውስ ባይሆነው እንኳ፣ ነፍስን የሚያድስ መሰንበቻና ማስታገሻ ይሆንለታል። ተገኝቶ ነው? በተቃወሰ ዘመን ጤናማ የጥበብ በረከት ማግኘት እንደ እድል እጅግ ብርቅ ነው።
ወራትን የምናስታውሰውኮ፣ ጥቅምትና መጋቢት በሚሉ ስሞች አይደለም። ድሮ ቀረ። ዛሬ ዛሬ ወራትን የምናስታውሰው፣ በጦርነትና በነውጥ ሆኗል። ጦርነት የፈነዳበት ወራት፣ ቤተክርስቲያን ጥቃትና መከራ የከበዳት ወራት እንላለን። የወር ስያሜዎች በረብሻና በቀውስ ዓይነቶች የሆነበት ዘመን፣ ምን መላ አለው? በዚህ መሃል፣… አልፎ አልፎ የጥበብ በረከት ሲገኝ፣ ተመስጌን ነው። መንፈስን ያድሳል፤ ሰውነትን ያነጻል።
የአስቴር አወቀ አልበም ለአደባባይ በበቃ ማግስት፣… አዳሜ ሳንቲም ሳያወጣና አንዲት ብር ሳይከፍል፣ በጠዋት በምልዓት አደመጠው። ምስጋና ለጥበበኞች፣ እድሜ ለቴክኖሎጂ እንበል። ጥበበኞችን ማመስገንና መመረቅ ደግ ነው።
ግን በምርቃት ብቻ አልበም መስራት አይችሉም። በአልበም ሽያጭ ሳንቲም ማግኘት እንደሆነ ምኞት ብቻ ሆኖ እየቀረ ነው- ይህ የቴክኖሎጂ ነገር!
ታዲያ፣ ዘንድሮ ብዙ አልበም ባናይ ምን ይርማል? ለሙዚቃ ጥበበኞችና ለአድማጮች እጅግ አመቺ የሆነ የቴክኖሎጂ ዘመን፣ በሙዚቃው ውበት ዓለማቸውን የሚያዩበት፣ ጥበብን ከነሙሉ ጣዕሙ የሚያጣጥሙበት ድንቅ የቴክኖሎጂ ዘመን፣… የአልበም ስራዎችን የሚያመናምን ሆኗል።
ሰርተው ደክመው፣ ሁለመናቸውን ሰጥተው የፈጠሩት የጥረት ፍሬ፣… ያለ ዋጋ በቴክኖሎጂው የሚበተን ከእጃቸው የሚያመልጥ ከሆነ፣… ስንቶቹ አልበም ሊሰሩ ይችላሉ?
አልበም የመስራት አቅምና ፍላጎት ሲጠፋ፣… በጣም ያሳዝናል። ለሙዚቃ አፍቃሪዎችም ለጥበበኞቹም ትልቅ ኪሳራ ነው።
አልበም እንደ ሕይወት ነው። ነጠላ ዜማ እንደገጠመኝ።
አስቴር አወቀን በነጠላ ዜማዎች ብቻ፣… አንድ ጠጠር አንድ ጠብታ እያልን የምናደምጣት ቢሆን ብዙ ይጎድልብናል። አንድ ዛፍ ወይም አንድ ክፍል ብቻ ማየት፣… ሰፊውን እርሻና የተሟላውን ህንጻ ከነከተማ ከማየት ጋር አነጻጽሩት። የነጠላ ዜማና የአልበም ልዩነት እንደዚያው ነው።
የዘሪቱ ከበደ ድንቅ የጥበብ በረከቶችን በወጉ እንዳናጣጥም ፈተና ይሆንብናል- የነጠላ ዜማዎች ነጠብጣብ።
ቴዲ አፍሮ ባለብዙ ገጽታ ጥበበኛ ሆኖ ሳለ፣ በነጠላ ዜማዎች ሳቢያ አንድ ገጽታው ብቻ እየተገነጠለ ሌሎቹን የፈጠራ በረከቶች ይሸፍንብናል። ያስቀርብናል።
ነጠላ ዜማ መጥፎ ሆኖ አይደለም። ግን አይበቃም። አዎ፣…የዘሪቱ ወይም የቤቲጂ የዘፈን ድንቅ ብቃት በአንድ በሁለት ዘፈን ማወቅ ይቻል ይሆናል።
ግን፣ የብቃታቸው ድንቅ ህብር ደምቆ የሚወጣው በነጠላ ዜማ ሳይሆን በአልበም ነው።
የስለሺ ደምሴን የጥበብ ነፍስ ለመረዳት፣ የሙዚቃዊ ድራማ ዝንባሌውን ለማጣጣም ጥሩ እድል የምናገኘውም፣ አልበሞቹን በማድመጥ ነው።
አብነት አጎናፍር፣… ዜማ የሚያውቅና ማዜም የሚችል ሙዚቀኛ እንደሆነ ለማወቅ፣… አልበሙን ሙሉ መስማት ያስፈልጋል። ምናልባት፣ አሪፍ ግጥሞችን፣ የሙዚቃ አቀናባሪዎችንና የዜማ ደራሲዎችን በጥንቃቄ መምረጥ ስለሚችል ነው የተሳካለት የሚልም ሊኖር ይችላል።
ነገር ግን፣ ከሁሉም በላይ “ዜማ” ያውቃል ቢባል የአብነትን ጥበብ የሚገልፅ ይመስለኛል። “ዜማውን ከነስሜቱ፣ ከነመንፈሱ ማወቅ” ማለቴ ነው።
የዜማ ጥበብ አስመስሎ መዝፈን አይደለም።
ምናለፋችሁ! አዲስ ዘፈን በድንቅ የዜማ ጥበብ መዝፈንና ሰውን ነባር ዘፈን አስመስሎ ማንጎራጎር ምን ያህል እንደሚለያዩ ለማወቅ፣ የአልበም ስራዎችን ማድመጥ ያስፈልጋል። አዳዲስ ድንቅ የጥበብ ፈጠራዎችን በእጅጉ እንድናከብር ያግዙናል- የአልበም ስራዎች። የዜማ ጥበብ በልሕቀቱ ይለያልና። አስመስሎ ከመዝፈን በጣም ይርቃልና።
በእርግጥ፣ አብዛኞቻችንም “እንደ ነገሩ” ዜማዎችን ማንጎራጎር እንችላለን። የዜማውን መንፈስ አፍክተን አጥርተን ማውጣትና መግለፅ ባንችል እንኳ፣ እንሞካክረዋለን። አዝማሚያውና አካባቢው ይገባናል። ለሚሰማን ሰው፣ በከንቱ የምናጉረመርም የምናልጎመጉም ሊመስለው ይችላል።  ጣዕመቢስ ይሆንበታል፣ ይጎረባብጠዋል፤ ይሻክረዋል። ቢሆንም ግን በትዕግስት በጨዋነት ይታገሰናል። ባይጥመውም ይችለናል።
ዜማዎችን መዝፈን የሚችሉ ድምጻዊያን እንኳ፣ አንዳንዴ ከውስጣቸው ጋር ያላዋሃዱትን ዜማ ሲዘፍኑ፣… ጣዕሙ ይጠፋል። ሌላ ሌላ ነገር እያሰቡ ወይም እያነበቡ የሚዘፍኑ ሊመስለን ይችላል። ቶሎ ዘፍነው ለመጨረስ የፈለጉና የሆነ ቦታ ለመሄድ የቸኮሉ ያህል አይነት ይሆንብናል።
ከዜማ ደራሲ የተቀበሉትን ፈጠራ፣ ከውስጣቸው ጋር አዋህደው፣ የዜማውን የሕይወት ኃይል አሟልተው መዝፈን፣…ቀላል ጥበብ አይደለም።
አንዳንዴ፣ “ለዜማው ነፍስ ዘራበት”፣ “ዜማውን ሕያው አደረገችው”… ያስብላል። ከዚያ በኋላ፣ አስመስለው ለሚዘፍኑ ጀማሪዎች፣ ይመቻቸዋል።
አስመስሎ መዝፈን፣… ጥሩ መለማመጃ ዘዴ ቢሆንም፣ አለቅጥ ከደጋገሙትና ካበዙት ግን፣… ያሳስታል። ከኦሪጂናሉ ዘፋኝ የበለጡ፣ እንደ ዘበት በቀላሉ፣ ያለ ብዙ ጥረት፣ ምርጥ ዘፋኝ ለመሆን የቻሉ ይመስላቸዋል።
አስመስሎ የመዝፈን ልምድ ግን፣ አሳምሮ የመዝፈን ጥበብ አይደለም። የሚመስላቸው ሰዎች ግን አሉ። የዜማውን የከፍታና የዝቅታ፣ የፍጥነትና የዝግታ መስመሮችን ሁሉ በጥምረትና በሕብር፣… በቅደም ተከተል እንደፍሰታቸው እንደ አረማመዳቸው የዜማውን መስመሮች አዋህዶ አሳምሮ የመዝፈን ጥበብ፣ ቀላል የድምፅ ችሎታ ብቻ መስሎ ይታያቸዋል። ተሳስተዋል።
አዲስ ዘፈን መስራት፣ አስመስሎ እንደመዝፈን አይደለም። አዲስ የዜማ ፈጠራ ተቀብሎ፣ የዜማውን እምቅ ጥበብ ተረድቶ፣ ያንን በሚመጥን የዜማ እውቀትና ጥበብ ወደተዋጣለት ድንቅ ዘፈን ማድረስ፣ ትልቅ ጥበብ ነው።
ከጠለላ ከበደ እስከ አስቴር አወቀ፣ ከዘሪቱ እስከ ቤቲ ጂ፣ በርካታ ዘፋኞች የዜማ አዋቂዎችና የዜማ ጥበብ ባለቤቶች ናቸው።
ከዜማ ጥበብ ጋር የድምጽ ልህቀት ሲጨምሩበትም ነው ድንቅ ዘፋኝ ሆኑት። እንደ ጥላሁን ገሰሰና እንደ ማህሙድ አህመድ ማለት ነው።
ወደ ዜማ ጥበብ ስንመለስ ሌሎች በርካታ ዘፋኞችንም… ለምሳሌ ስለሺ ደምሴ፣ ፍቅር አዲስ ነቅዓጥበብ፣ እነ አብነት አጎናፍርን መጥቀስ ይቻላል። የዜማን ስሜትና መንፈስ ያላሟላና ያላዋሃደ ዘፈን በስለሺ ወይም በአብነት አልበሞች ውስጥ አታገኙም ቢባል ይሻላል። የዘፈኑን ስሜት የማደብዘዝና የማራቆት ስህተት አይሰሩም።
ምናልባት፣ የዜማዎችን ስሜት ያጋንናል ካልተባለ በቀር ማለቴ ነው። እንዴት ልበላችሁ? እንግሊዛዊው ዘፋኝ… ማይክል ቦልተን፣… በአዘፋፈኑ፣… ለዜማዎቹ ከመጠን ያለፈ የተጋነነ ስሜት ያሸክማቸዋል ይባል ነበር። አብነት እንዲህ አይነት ስህተት አይሰራም። ዜማ ያውቃል። ደግሞም በቀላሉ የሚገኝ ጥበብ አይደለም።
በወጉ ለማዜም የሚከብዳቸው ድምጻውያን አሉ።
አንዳንዶቹ፣ ወይ ከግጥም ንባብ አልሆኑ፤ ወይ ከግጥም ዜማ አልሆኑ። በመንጠቆ እንደተያዘ ነፍስ፣…”ራፕ” ውስጥ ተቀርቅረው የመንገጫገጭና የመወራጨት ሰለባ ይሆናሉ። ልማዳዊ ጭፈራ ላይ ብቻ መጠመድም የዜማ ጥበብን በአጭሩ ቀጭቶ ሊያስቀር ይችላል።
በሰርግ፣ በሌሎች በዓላትና በድግሶች ላይ የማስጨፈር ሃይለኛ ችሎታ ያለውና ይህንኑ ብቻ ሲቀጠቅጥ የኖረ ዘፋኝ፣… አዳዲስ ዜማዎችን በቅጡ ለመዝፈን በጣም ይቸገራል። እንደ ጅረት መፍሰስ፣ እንደ ተወርዋሪ ኮኮብ መምጠቅ የሚኖርበትን ዜማ ወስዶ ሲያበቃ፣ በአጭር በአጭር እየከታተፈ፣ ድንጋይ እንደመወራወር፣ ዱላ እንደመሰናዘር፣ ተቀባይ አጃቢዎች የሚያስፈልጉት ማስጨፈሪያ ያስመስለዋል።
ሁሉም ዜማ የጭፈራ ዜማ ይሆንበታል። ሳያውቀው፣ ወደ ጭፈራ ስሜት ይወስደዋል።
የዜማ እውቀትና ችሎታ ያስፈልጋል ለማለት ነው ነገሩ። ዜማዎችን እንደአፈጣጠራቸው ከነስሜታቸው መገንዘብ፣ መንፈሳቸውን ከራስ ጋር አዋህዶ፣ በሚመጥናቸው ጥበብ የመዝፈን ችሎታ ያስፈልጋል - ከማህሙድ አህመድና ከጥላሁን ገሰሰ፣ እስከ እንዳለ አድምቄና አብነት አጎናፍር፣ ዘሪቱ ከበደ፣ ቤቲ ጂ… የዜማ የጥበብ ጌቶችና እመቤቶች ናቸው።
የዜማ ጥበብና የድምፅ ጥበብ ሲዋደዱ ምርጥ ዘፈን ይወልዳሉ።
ዜማ ያውቃሉ ማለት፣ ሌሎች ጥበቦችንና ችሎታዎችን በመዘንጋት አይደለም። እንዴት ተደርጎ? የድምፅ ጥበብና ችሎታም ያስፈልጋል። ዜማዎችን ከነመንፈሳቸው የመረዳት ጥበብ፣ የድምፅ ችሎታ ከጎደለው፣ ዘፈንን ያበላሻል። የዜማ ጥበብ ለብቻው ዋጋ የለውም ወይም በከንቱ ይባክናል ማለት ግን አይደለም።
ብዙ የሙዚቃ አስተማሪዎች፣ የዘፈን አዘጋጅና አቀናባሪዎች፣ ጥሩ የዜማ እውቀትና ጥበብ ሊኖራቸው ይገባል። የድምጽ ጥበብና ችሎታን እያሳደጉ ካከሉበት ደግሞ፣ አሪፍ ዘፋኝ ይሆናሉ።
እነ ጥላሁን፣ ከዚያም እነ አስቴር አወቀ፣ እነ ዘሪቱና ቤቲጂ … የዜማ ጥበብን ከድምጽ ብቃት ጋር ያዋሃዱ፣ ድንቅ ዘፋኞች ናቸው- ማለትም፣…የዜማ ጥበበኞች፣ እንዲሁም የድምጽ ጥበበኞች።
 ይሄ ራሱ የተዓምር ያህል ድንቅና ብርቅ ነው።
ነገር ግን፣ ከዚህም ያልፋል- ጥበባቸው። ግጥም ይጽፋሉ፤ ዜማ ይፈጥራሉ።
በእርግጥ፣ የግጥምና የዜማ ደራሲ መሆን፣… ለዘፋኞች የግድ አይደለም። ከሌሎች ጥበበኛ ባለሙያዎች አሪፍ ግጥምና ዜማ መርጠው መሥራት ይችላሉ።
ዘፋኞች፣… አሪፍ ዜማ ፈጣሪዎች ከሆኑም ግን እሰየው ነው። ቴዲ አፍሮ ድንቅ የግጥም ጥበበኛ ነው። ዜማም ይፈጥራል።
ሃሳቦችን የመመርመርና የማፍለቅ ዝንባሌም አለው።
ከሙዚቃ ባሻገር ምን ያስፈልጋል?
ከቴዲ አፍሮ እና ከአብዱ ኪያር የተገኙ አባባሎችን እንደገና በምሳሌነት ለማስታወስ የፈለግኩት፣ የሆነ ሃሳብ ሲሰነዝሩ፣ ከሙዚቃ ጥበባቸው ጋር እንዳይምታታ በማሰብ ጭምር ነው። በፖለቲካ ጉዳይ ላይ መናገር ለዘፋኝ ግዴታ አይደለምና። ዝንባሌው ወይም ሙያው ካልሆነ በቀር ማለቴ ነው።
የአገራችን ፖለቲካ ላይ የሚታይ አንድ ባሕርይ ለመግለፅ ቴዲ አፍሮ የተጠቀመበትን ምርጥ አባባል አስታውሳለሁ። “የብሽሽቅ ፖለቲካ” የሚል አባባል ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁት፣ ከቴዲ አፍሮ ነው።
ብሽሽቅን እየዘራን ጠላትነትን እናጭዳለን። ለምን? አንዳች ፍሬ የምናገኝበት መስሎን አይደለም። ብሽሽቅ ከጥላቻ በቀር፣ ሌላ ትርፍ ሌላ አላማ የለውም።
ተቀናቃኝ መፍጠርና ማብሸቅ ብቻ ነው የብሽሽቅ ትርፉ። መነሻውና መድረሻው ጥላቻ ነው። ታዲያ ምን ሊጠቅመን? ምንም! የምን ጥቅም? እንዲያውም ጠላት ነው የምንፈጥረው፣ የሚያበሽቅ ተቀናቃኝ። ጉዳትና ኪሳራ እንጂ ጥቅምና ትርፍ አይደለም የብሽሽቅ አላማ።
ተጎድተንም ከስረንም ቢሆን፣ ዋናው ነገር ተቀናቃኞችን ማብሸቅ! እንዲህ አይነት የብሽሽቅ ረሃብና ሱስ የተጠናወተው ነው የአገራችን ፖለቲካ። ምናልባት መፍትሄ የምንፈልግ ከሆነ፣ ችግሩን ለመገንዘብ የሚረዳ ገላጭ አባባል ነው - “የብሽሽቅ ፖለቲካ” የሚለው የቴዲ አፍሮ አገላለፅ።
አብዱ ኪያር በበኩሉ፣ መልካም ታሪኮችንና ባሕሎችን በክብር እያደነቀ ከመዝፈን ጋር፣… ስህተትንና ጥፋትን ደግሞ በበጎ እንድንቀይር ይመኛል። ዘረኝነትን አይወድም። በዘር ቢሆንማ ሁሉም ሰዎች የአዳም የሄዋን ልጆች እንደሆኑ የሚገልጽ ዜማውን አስታውሱ።
 “ይቅርብን” ልንለው የሚገባ ሌላ የአገራችን መጥፎ ዝንባሌ ምን እንደሆነ ሲናገርም ሰምቻለሁ። አንዳንዱ ሁኔታችን፣ “የኩርኩም ውርርድ” ይመስላል ብሏል አብዱ ኪያር።
ሕፃናትስ፣… “በኩርኩም” እያሉ ቢወራረዱ፣…እሺ ካለማወቅ ነው። ልጅነት ነው። በአገር ደረጃ፣ አዋቂዎች ሁሉ፣ “የኩርኩም ውድድር” የሚመስል እልህ ውስጥ የሚጠመዱበት ልማድ ግን፣… ወይ ስካር ነው። ወይ ቅዠት። ወይ በሽታ ነው። ይሄ ይቅርብን ይላል አብዱ ኪያር። ለማንም አይበጅም።
የተኮረኮመም ህመም ነው። የኮረኮመም የህመሙ መጠን አነስ ቢልም፣ ከህመም ውጭ ምንም አያተርፍም።
አንዱ ጭንቅላት በኩርኩም ስለተናጋና ስለተናወጠ፣ የሌላው ጭንቅላት እርጋታና ሰላም አያገኝም። የሌላኛውን አናት ማፍረስ፣ የራስን አናት መገንባት አይደለም። የኩርኩም ውርርድ እንዲህ ነው። ውጤቱ ህመምና ጥላቻ ብቻ ነው። የአገራችን ፖለቲካም እንደዚህ አይነት ባህርይ አለው።
በሳንቲም መወራረድን እንኳ እንወቅሳለንኮ፣ “ቁማር” ነው ብለን እናናንቀዋለንኮ።
ሳንቲም በውርርድ ለማግኘት መመኘት አያዛልቅም። የሳንቲም መፍጠሪያ ሙያዎችንና ስራዎችን እንድንዘነጋ ያደርጋል እንጂ ቁማር አይጠቅምም።
 ነገር ግን፣ ቢያንስ ቢያንስ፣ የሆነ ጥቅም፣ የሆነ ትርፍና ጥቂት ሳንቲም አገኛለሁ በሚል ስሜት እንጂ፣ ሰውን በኩርኩም ለማሳመም፣ ወይም ኪሱን ለማራቆት በመጓጓት የሚደረግ ነው።
የኩርኩም ውርርድ ግን፣ ሰውን ከማሳመም ውጭ ትርፍ የለውም፤ እንዲያውም ኮርኳሚም ያመዋል።
ሌላ ሰው ለማሳመም እስከሆነ ድረስ ግን፣ እያመመውም ይኮረኩማል። ይሄ እየተጠላለፉ እየተያያዙ ወደ ገደል የመግባት ዝንባሌ ይቅርብን ለማለትም ነው - “የኩርኩም ውርርድ” የሚለው አገላለፅ የመጣው - ከአብዱ ኪያር።
ከንቱ የእርስ በርስ ግጭትና ከንቱ ጦርነትም የዚህ አይነት ባሕርይ አለው። ጥግ ድረስ የሄደ የኩርኩም ውርርድ እንደማለት ነው። ያው ከንቱ ጦርነት፣ ከኪሳራ ውጭ ትርፍ የለውም። መሸነፍ ብቻ ሳይሆን፣ ማሸነፍም በኪሳራ ነውና።
ዘሪቱም፣ ከዜማ ጥበቧና ከድንቅ ድምጻዊነቷ በተጨማሪ፣ አሪፍ የዜማ ደራሲ እንደሆነች ታውቃላችሁ። ምርጥ ዘፋኝ ለመሆንኮ፣ ዜማን የመረዳት ችሎታዋና የድምፅ ጥበቧ ብቻ በቂ ነው። በቂ ነው ማለት ግን ግጥም መፃፍ፣ ዜማ መፍጠር የለባትም ማለት አይደለም። ምርጥ እስከሆነ ድረስ፣ የዘፈን ጥበቧን የሚያዘናጋ እስካልሆነ ድረስማ፣ የጥበብ በረከቷ ቢበዛ ተገኝቶ ነው? የመፈላሰፍ ዝንባሌም አላት እንጂ።
ይሄ ይሄ ግን ከሙዚቃ ጥበብ ጋር የግድ መቆራኘት የለበትም። እንደ ተጨማሪ ዝንባሌ ነው።
በእርግጥ፣ ምርጥ ሙዚቃ ወይም ድንቅ ዘፈን፣ ከዜማ እውቀትና ከድምጽ ችሎታ በተጨማሪ በርካታ ባለሙያዎችንና ጥበቦችን ማሟላት፣… ማሟላት ብቻም ሳይሆን ሁሉንም በትክክል አቀናብሮ ማዋሃድን ይጠይቃል።
የዜማዎችን ስሜትና መንፈስ ፈልቅቆና አድምቆ፣… እንደሚፈነዳ እምቡጥ አበባ አፍክቶ በድንቅ ድምፅና በውብ ዜማ ለጆሮ ለአእምሯችን የማድረስ ጥበብ ለጥበበኞች ይብዛላቸው።… እንደ አስቴር አወቀ የጥበብ በረከታቸው ይብዛልን።
የቴክኖሎጂው ነገር መቼስ፣… በጎ አገልግሎቶቹ እየበለጸጉ፣… ፈተናዎቹ ደግሞ መፍትሔ እየተበጀላቸው መንገዱ እንዲቃና እየተመኘን፣… ለዚህ የሚተጉ ሰዎችም እንዲሳካላቸው ይበርቱ እንበል።


Read 890 times