Print this page
Saturday, 18 March 2023 20:14

ከአዳም ማስታወሻ

Written by  ደራሲ፡- ማርክ ትዌን (ሳሙኤል ክሊመንስ) 1982 እኤአ። ትርጉም፡- ቢንያም ኃይለመስቀል ኪዳኔ
Rate this item
(4 votes)

 [የደራሲው መግቢያ — የእዚህን ዲያሪ ከፊል አካሉን የተረጎምኩት ከትንሽ አመታት ቀደም ብሎ ነበር፣ አንድ ጓደኛዬም ባልተሟላ መልኩ ትንሽ ቅጂዎችን አተማቸው፤ ህዝብ ግን ከቶ አላገኛቸውም ነበር። ከእዛም በኋላ ግን ጥቂት ተጨማሪ የአዳም ሄይሮግሊፊክስ ጽሁፎቹን ለመተርጎምም በቅቻለሁ፣ በአሁኑ ሰዓት ደግሞ እንደ አደባባይ ገጸባህሪይ በበቂ መጠን ተወዳጅ በመሆኑ ይህን ለማሳተም እሚፈቅድልኝ ይመስለኛል። ማርክ ትዌይን]
ሰኞ
ይሄ ባለረዥም ጸጉር አዲስ ፍጥረት የለየለት አደናቃፊ ሆኖብኛል። ሁልጊዜም ዝም ብሎ ይንቀዋለልብኛል፣ ይከታተለኛል። ከቶ አልተመቸኝም፤ ከብጤ ጋር መሆንም አላቅበትም። እንደኔ እንደኔ፣ ከሌሎቹ እንስሳት ጋር ቢኖር ደስ ይለኝ ነበር።
ዛሬ ቀኑ ደመናማ ነው፤ ነፋሱ በምስራቅ በኩል አለ፤ ዝናቡ ሳይዘንብልን አይቀርም… እኛ ያልኩትን ከየት አምጥቼ ተናገርኩት ጃል!? አሁን ትዝ አለኝ፤ ያ ፍጥረት ነው እሚገለገለው።
ማክሰኞ
ታላቁን ፏፏቴ ሳጠና አረፈድኩ። በእርስቱ ውስጥ ካሉ ነገሮች ሁሉ መልካሙ ነገር እሱ ነው። አዲሱ ፍጥረት ናያግራ ፏፏቴዎች ብሎ ይጠራዋል—ለምን እንዲያ አለው ቢባል፣ አለማወቄ ላይ እርግጠኛ ነኝ። እሚለው፣ ናያግራ ፏፏቴዎችን ይመስላል ነው። ያ መነሻ ምክንያት አይደለም፤ እንዲያ ማለት መቼም አለማስተዋል እና ደደብነት ነው። ለምንም ነገር ስም እንድሰጥ ለእኔ እድል አይሰጠኝም። እኔ አማራጭ የማቅረብ እድል እንኳ ሳላገኝ የታየውን ነገር ሁሉ እራሱ ይሄ አዲስ ፍጥረት ስም ያወጣለታል። ይብስ ብሎ ደግሞ ሁሌም ያ ተመሳሳይ ሰበብ ይቀርባል—ስሙ ያን የተሰየመውን ነገር ይመስላል ይለኛል። ለምሳሌ ዶዶ ግብዴው ወፍ ነበር። እሚለኝ፤ እንስሳውን አንድ ሰው ባየው ቅጽበት ወዲያው “አንድ ዶዶ ይመስላል” እሚለውን መመልከት ይቻለዋል ነው። ጥርጥር የለኝም፣ መቼም አውሬው ያን ስም መውሰድ አለበት። በርግጥ ስለ ነገሩ መጨነቅ በራሱ ይደብረኛል፣ ምንም ዋጋም የለውም፤ ምን ተሰየመ ምን ምን። ዶዶ! እንስሣው እኔ ዶዶ ከመሰልኩት እሱ የተለየ የመሰለ አይመስለኝም።
ረቡዕ
ከዝናቡ ለመጻረር አንድ መጠለያን ገነባሁ፣ ለነገሩ ግን በሰላም ለራሴ ላደርገው አልቻልኩም። አዲሱ ፍጥረት ዘልቆ ገባ። ላስወጣው በሞከርኩ ጊዜ፣ በሚመለከትበት ቀዳዳዎች ዉሃ አመነጨ፣ ቀጠለና በመዳፉ ጀርባ ጠረገው፣ ከእዛ አንዳንድ እንስሶች ሲጨነቁ እሚያወጡት ድምጽን አሰማ። ቢያንስ ባያወራ ደግሞ እመኛለሁ፣ ግን ሁሌም እንደለፈለፈ ነው።
አንዳች ርካሽ ሐሜት ሊባል ይችላል፣ የሆነ ክፉ የጥላቻ ጉርምርምታም፤ ግን እንዲያ እንዲመስል ብዬ አይደለም። የሰው ድምጹን ከዚህ ቀደም መቼም ቢሆን ገጥሞኝ ሰምቼው አላውቅም፣ ስለዚህ ማንኛውም አዲስ እና እንግዳ ድምጽ በበረታው ህልም መሰል ብቸኛነት መሀል እራሱን ሲያመጣብኝ ጆሮቼን ስለሚያበሳጭ እና ሃሰተኛ ስለሚመስለኝ ብቻ ነው። እናም ደግሞ ይህ አዲስ ድምጽ በጣም ቀርቦኛል፤ ልክ በትከሻዬ ላይ ነው፣ ልክ በጆሮዬ ላይ፣ መጀመሪያ በአንደኛው ጆሮዬ ቀጣይ በሌላው እሚለቅብኝ፣ በበኩሌ ከሞላጎደል ከእኔ ራቅ ያሉ ድምጾችንም ማድመጥ ስለለመድኩም ጭምር ነው።
አርብ
ምንም እንኳ ብዙ ባደርግም አልቆመም፣ ስያሜ መስጠቱ በግዴለሽነት እንደለመደው እንደቀጠለ ነው። ለርስቱ ደህና ስም ነበረኝ፣ ሲጠሩት ሙዚቃ መሣይ እንዲሁም ቆንጆ ነበር—ኤ.ደ.ን-ገ.ነ.ት.። ተደብቄ፣ እንዲያ እያልኩ መጥራቴን እንደቀጠልኩ ነኝ። ነገርግን ያ አብቅቷል፣ በይፋ እንዲያ ብዬ ልጠራው ካሁን በኋላ አልተቻለኝም። አዲሱ ፍጥረት እሚለው ስፍራው እንጨቶች እና ቋጥኞች እንዲሁም ለእይታ ማራኪ ገጽታ ብቻ ነው ያለው፣ ስለዚህ ምንም የገነት ምስያ የለውም ነው።  መናፈሻ ብጤ ነው እሚመስለውና ከመናፈሻ በቀር ምንም መምሰል አይችልም አለኝ። ያን ብሎኝ፣ ከእኔ ጋር ከመማከር ውጭ አዲስ ስያሜ አበጀለት—የናያግራ ፏፏቴዎች መናፈሻ አለው። ይሄ የተሟላ ንቀት ነው፣ ለኔ መስሎኛል። እንደገናም፣ ካሁኑ የሰቀለው ማስታወቂያ አለ፡
“ሣሩ ላይ  መራመድ የተከለከለ ነው!”
ህይወቴ ይሆን እንደነበረው ደስተኛ መሆኑ ቆሟል።
ቅዳሜ
አዲሱ ፍጥረት ፍራፍሬ በገፍ በሊታ ነው። መቼም ማለቁ ነው። “እኛ” አልኩኝ በድጋሚ—ያ እኮ የእሱ ቋንቋ ነው፤ አሁንማ ደጋግሜ ከመስማቴ የተነሳ ብቻ የኔም አደረግኩት።
ብዙ ጭጋግ ነበረን ዛሬ ጧቱን። እኔ ራሴው በጭጋጉ ወደ ውጭ አልወጣሁም። አዲሱ ፍጥረት ወጥቶ ነበር። በሁሉም አየር ንብረቶች ወደ ውጭ ዝም ብሎ ይወጣል፣ ሲመለስ ደግሞ ኮራ እያለ ጭቃ በጭቃ እግሮቹን ድም ድም እያደረገ ሰተት ብሎ ይገባል። ይህ ስፍራስ አስደሳች እና እማይረብሽ ቦታ ነበር።
እሁድ
እንደምንም ተገፍቶ አለፈ። ይህኛው ዕለት ግን የበለጠ እና የበለጠ ፈታኝ መሆኑን ተያይዞታል። ባለፈው ህዳር ላይ ተመርጦ እና የተለየ እንዲሆን ተደርጎ የእረፍት ቀን ተደርጎ ነበር። እኔ በሳምንት ስድስቱንም ቀኖች አስቀድሜምም ማረፊያ አድርጌያቸው ነበር።
ዛሬ ጧት ደግሞ ከተከለከለው ዛፍ ያን አዲስ ፍጥረት አፕሎች ለመውሰድ ሲታገል አገኘሁት።
ሰኞ
አዲሱ ፍጥረት ስሙ ሔዋን ነው አለ። ያስ ይሁን ምንም ተቃውሞ የለኝም። እንዳለው ከሆነ፣ እንዲቀርበኝ ስፈልግ  በእዛ እጠራዋለሁ። ያማ አላስፈላጊ ትርፍ ነገር ነው ብዬው ነበር። ቃሉ በግልጥ እንዳከብረው አደረገኝ፣ አዎ በርግጥም ትልቅ፣ ጥሩ እና ስለሚደጋገምም እሚቆይ ስም ነው።
እንዳለኝ ከሆነ አንተ ሳይሆን አንቺ እሚባል ፍጡር ነው። ይህ ምናልባት አጠራጣሪ ነው፤ ቢሆንም ለኔ ግን ሁለቱም ያው ነው፣ ራሷን ብትችል እንዲሁም ባታዋራኝ ለኔ ሌላው ምኔም አይደለም።
ማክሰኞ
እርስቱን እንዳለ በአስቀያሚ ስሞች እና እሚደብሩ ምልክቶች አጥለቅልቃዋለች ፤
“በእዚህ በኩል ወደ ዌርልፑል።”
“በእዚህኛው መንገድ ወደ ፍየል ደሴት።”
“የንፋሶች ዋሻ በእዚህኛው በኩል።”
አንዳች ህጎች ቢፈጠሩለት ኖሮ፣ ይህ መናፈሻ ለበጋ ንጹህ ሪዞርት ይሆን ነበር፣ አለች።  የበጋ ሪዞርት—ሌላው ፈጠራዋ ነው—ሌላ ምንም ትርጉም የሌለው ቃል። አሁን የበጋ ሪዞርት ማለት ምንድነው? ብቻ እሚሻለው ነገር እርሷን አለመጠየቁ ነው፣ አብራሪ ካሏት እጅግ በጣም በረዥሙ ለመለፍለፍ ትበረታለች።
አርብ
አሁን ደሞ ወደ ፏፏቴዎቹ መሄዴን እንዳቆም ፍላጎት አሳድራለች። ቆይ ምን ጉዳት አለው? ስቅጥጥ ያደርገኛል አለች። ለምን እንዲያ እንደተሰማት ባውቅ ደስ ባለኝ። አኔ ሁሌም እማደርገው ነበር—ምንጊዜም ዉሃው ሿ… ሲል እና መዝናኛነቱን ሲቸር፣ እንዲሁም ፈታ ሲአደርግ እንደወደድኩት ነበር። እሚገባኝ ፏፏቴዎች ለእዛ ነበር አፈጣጠራቸውም። እኔ ማየት የምችለው ሌላ አገልግሎት አሊያዙም፣ እንዲሁም ለሆነ ኢላማ መሰራታቸውም ግልጥ መሆን አለበት። እሷ እምትለው፣ ናያግራ ለእይታ ብቻ ነው የተፈጠረው—ልክ እንደ ራይኖሰረስ እና ማስቶደን ነው። ወደ ፏፏቴዎቹ በአንድ መዋኛ ባረል ሆኜ ሄድኩ—ለእሷ አላስደሰታትም። በአንድ ሌላ ገንዳም ሆኜ ሄድኩ—ያም አላስደሰታትም። ቀጥዬ ወርልፑል እና ፈጣኑ-ፏፏቴን በሾላ-ቅጠል ልብስ ዋኘሁ። ብዙ ጉዳት ግን ደረሰብኝ። ስለእዚህ፣ እጅግ ረዥም ቅሬታ በገንዘብ አባካኝነቴ ላይ ተመስርቶ ቀረበብኝ። ካለቅጥ፣ እየገደበችኝ ነው። እምፈልገው ነገር ቢኖር ይህን አኳኋን መቀየር ነው።
ቅዳሜ
ባለፈው ማክሰኞ ማታ አመለጥኩኝ፣ ከእዛም ሁለት ቀኖችን ሳላቋርጥ ተጓዝኩ፣ ከእዛም በተገለለ ቦታ ሌላ መጠለያ ለራሴ ገነባሁ፣ ቀጥዬ በተቻለኝ ሁሉ እየተመለስኩ ዱካዬን አጠፋሁ፣ ነገር ግን አድና ደረሰችብኝ፣ ያም የሆነው ባለመደችው እና ስሙን ተኩላ ብላ በሰየመችው እንስሣ አማካኝነት ነበር፤ ከእዚያም አሳዛኝ ድምጽ በድጋሚ እያሰማችኝ እና ከምትመለከትበት ቦታ ዉስጥ ዉሃ እያፈለቀች መጣችብኝ። ከእርሷ ጋር ለመመለስ ተገደድኩ፣ ነገር ግን ሁኔታዎች እንደፈቀዱልኝ ደግሜ በቶሎ እመለሳለሁ።
ሰሞኑን እራሷን በብዙ ሰነፍ ጉዳዮች ትይዛለች፡ ከሌላዎቹ መሀከል፣ አንበሳ እና ነብር ለምን በሳር እና አበባዎች እንደሚኖሩ ታጠናቸዋለች፣ እንደምትለው፣ የተሰጧቸው ጥርሶች እርስበርስ እንዲበላሉ እንደሆነ ስለሚጠቁም ነው። ይህ ነፈዝነቷ ነው፣ ያን ቢያደርጉ እርስበርስ መገዳደል ነው፤ ያም እንደገባኝ ከሆነ “ሞት” እሚሉት ነው፤ እናም እንደተነገረኝ ከሆነ ደግሞ ወደ መናፈሻው ሞት ገና አልገባም። ምንም እንኳ ካንዳንድ ሁኔታዎች አኳያ በራሱ ያ አሳዛኝ ቢሆንም።
እሁድ
እንደምንም ታለፈ።
ሰኞ
ሳምንት ለምኑ እንደተፈጠረ አሁን የተገነዘብኩ መሰለኝ፡ እሁድ ላይ ከድካም ለማረፍ ጊዜውን ማስተካከያ መሆኑ ነው። ደህና ሃሳብ ይመስላል…. ያን ዛፍ ደግሞ መልሳ ትወጣበት ጀምራለች። ከልክዬ አወረድኳት። እምትለው ማንም እኮ እያየ አይደለም ነው። ያንን ማንኛውም አደገኛ ነገር ለመሞከር ብቁ ማብራሪያ አድርጋ ተቀብላዋለች። ይህን ያሰብኩትን ቃል ነገርኳት። ብቁ ማብራሪያ እሚለው ቃሌ አድናቆቷን ቀሠቀሰው—ቅናቷንም፣ እንደገባኝ ከሆነ። ደህና ቃል ነው መሠል ለነገሩ።
ሀሙስ
እሷ የተበጀችው ከተሠነጠረ አንድ ጎድኔ እንደሆነ ነገረችኝ። ከእዛም በላይ አይደለም ቢባል እንኳ፣ ቢያንስ ቢያንስ ግን አጠራጣሪ ነው። ከእኔ ምንም የጎደለ ጎድን የለም….
ከቡዛርድ ወፉ ጋር ብዙ ችግር ገብቷታል፤ የሣሩ መብል ከእርሱ ጋር አይናበብም ትላለች፤ ስለማታሳድገውም ታዝናለች፤ በሙት አካሎች ብስባሽ ላይ እንዲኖር የታቀደለት ነው ብላ አስባለታለች። ከቀረበለት ሣር ጋር አብሮ ለመጓዝ የተቻለውን መጣር ግን ግዴታው ነው። መቼም ያለውን የሁነቶች ሂደት በሙሉ ለቡዛርድ ወፉ ስንል ማጠፍ አይቻለንም።
እሁድ
ትላትና ሁሌም እንደምታደርገው እራሷን ዝቅ ብላ ስታይበት ኩሬው ዉስጥ ወደቀች። ታፍና ነበር ማለት ይቻላል፣ ያም ፈጽሞ ምቾት እንደነሳት ነገረችኝ። ያ ደግሞ በዉሃ ዉስጡ ለሚኖሩት ፍጥረቶች ሃዘን እንዲሰማት አደረጋት፤ በማይፈልጉት ሲጠሩበትም ሰምተው በማይመጡበት ስምን ሰይማ ትጠራቸው ቀጥላለች እና እነርሱንም ዓሣ ብላ ሰይማቸው ነበር፤ ዞሮ ዞሮ የማታሰላስል በመሆኗ  አለማድመጣቸው ለእሷ ምንም ፍንጭ አልሰጣትም ማለት ነው፤ ስለእዛ ብላ ብዙዎቹን አውጥታ ባለፈው ማታ ምሽት አካባቢ ወደ እኔ አልጋ እንዲሞቁ ብላ አመጣቻቸው፣ ነገር ግን አሁንም አያቸዋለሁ፤ ቀኑን ሙሉም አስተዋልኳቸው፣ በፊት ከነበሩበት የበለጠ በእዚህ ስለሆኑ ደስተኛ አይደሉም፣ የበለጠ ዝምተኞች ግን ሆነዋል። ምሽቱ ሲበረታ አውጥቼ ወደ ዉሃቸው እወረውራቸዋለሁ። ሙልጭልጭ ስለሚሉ እና የምለብሰውን ከተጋሩኝ መሀከላቸው ለመተኛቱም በደፈናው ደስ ስላላለኝ ድጋሚማ አብሬያቸው አልተኛትም።
እሁድ
እንደምንም ተገፍቶ ታለፈ።
ማክሰኞ
አሁን ደግሞ ከእባብ ጋር ገጥማለች። ዘወትር ስለምትመራመርባቸው እና ስለምታስጨንቃቸው ሌሎቹ እንስሶች በዛ ተደስተዋል፤ አብሬ እኔም ደስተኛ ሆኛለሁ ምክንያቱም እባቡ መናገር ስለሚችል እና ከእዛ የተነሣ እኔ እረፍት እንዳገኝ ስለሚያስችለኝ ነው።

አርብ
ከእዛ ዛፍ ፍሬ እንድትሞክር እባቡ ምክር እንዳቀበላት ነገረችኝ፣ ዉጤቱም ታላቅ እና ደህና እንዲሁም ምርጥ ትምህርት እንደሚያስገኝ ነገረችኝ። ሌላም ዉጤት እንደሚኖር ነገርኳት—ወደ አለሙ ሞትን ያስገባል። መናገሬ ግን ስህተት ሆነ—የሞት ነጥቡን ለራሴ ደብቄ መያዙ ሳይሻለኝ አይቀርም ነበር። ምክንያቱም አንድ ሃሳብ ነው ያመነጨላት—የታመመውን ቡዛርድ ለማዳን ያስችላታል፣ በተጨማሪም ቅሬታ ለማያጣቸው አንበሳ እና ነብርም ስጋ ለማቅረብ ያገለግላታል። ከዛፉ እንዳትቀርብ መክሬያታለሁ። አልቀርበውም ትላለች። እኔ ግን ጉዳት ሲከተል እየታየኝ ነው። ርቄ መሰደድ ይበጀኛል።
ረቡዕ
የተደበላለቀ ሰሞን ላይ ነኝ። ያን ምሽት አመለጥኩ፣ ጉዳቱ ከመጀመሩ አስቀድሜ በሌላ ሀገር ለመደበቅ በሚል  ከመናፈሻውም ርቄ ለመጥፋት፣ አንድ ፈረስ ይዤ ሌቱን ሙሉ በተቻለው ፍጥነት ጋለብኩት፣ ግን የሚሳካ ነገር አልነበረም። ጸሀይ ከወጣች አንድ ሰዓት በኋላ፣ እልፍ እንስሳዎች አበባማ ለጥ ያለ መሬት ላይ ሲግጡ፣ አረፍ ብለውም ወይም እርስበርስ ሲጨዋወቱ በመሀከላቸው እጋልብ ነበር፤ በድንገት አንዳች ቅጽበት ላይ ግን፣ እንደየልማዳቸው፣ የድንጋጤ ጫጫታ ማእበል ተፈጠረ፣ በእዛም ቅጽበት ለጥ ያለው ምድር በጭንቅ ሁከት ተሞላ፣ እያንዳንዱ አውሬ ጎረቤቱን እሚያጠፋው ሆነ።
ምን ማለት እንደሆነ ገብቶኛል—ሔዋን ያን ፍሬ በልታዋለች፣ ስለእዚህ ወደ አለሙ ሞት ገብቷል…. ፈረሴን ነብሮቹ በሉብኝ፣ እንዲያቆሙ ባዛቸውም እኔን ከቁብ አልቆጠሩኝም። ብቆይማ ጨምረው እኔንም ባነከቱኝ ነበር—ዳሩ አልቆየሁም፣ በበዛ ችኮላ ሆኜ አመለጥኩ...
ከመናፈሻው ውጭም ለትንሽ ቀኖች ተስማሚ እሚሆን ሥፍራን አገኘሁ። ነገር ግን ፈልጋ አገኘችኝ። ፈልጋ ስትይዘኝ ስፍራውን ቶናዋንዳ ብላ ሰየመችው—እንደልምዷ ቶናዋንዳን መሳይ ነው ብላ ታብራራለች። በርግጥ፣ ስለመጣች አላዘንኩም፣ እሚለቀሙ ነገሮች እምብዛም ባለሁበት አካባቢ አልነበሩም። እሷ ከእነዛ አፕሎችም ጥቂት ስላመጣችልኝ ልበላቸው ተገደድኩ፣ በጣም ተርቤ ነበር እና። ያ ከመርሆቼ ውጭ ነበር፣ ነገር ግን አንድ ሰው በበቂ ካልጠገበ መርሆዎች ጉልበት ከምር እንደማይኖራቸው ተገነዘብኩ….
በቅጠላቅጠሎች እና ቅርንጫፎች መጋረጃ አገልድማ መጣች፣ በእዛ አጉል ድርጊቷ ምን ማለቷ መሆኑን ስጠይቃት እና መንጭቄ ስወረውርባት ሳቅ ብላ ፊቷ ፍም መሰለ። ከዚህ በፊት ሰው ሲሽኮረመም እና ፊቱ ሲያፍር ተመልክቼ አላውቅም ነበር፣ ስለእዚህ ለእኔ ያላማረ እና ስንፍና ድርጊት ሆኖ ታየኝ። እራሴ እንደነበርኩ እማውቅ እንደሆነ ነገረችኝ። ያ ልክ ነበር። ተርቤ እንደ ነበረው ያክል፣ አፕሉን በግማሽ ተውኩት—መብቀያ ወቅቱ ማለፉን በመገመት ሰሞኑን ካየኋቸው አፕሎች ይህኛው ደህና ነበር—አካሌንም ባመጣችው የቅጠላቅጠሎች እና ቅርንጫፎች  ልብስ ከተትኩት፣ ከእዛም በመረረ ቁጣ ተናግሬያት ሳበቃ ሄዳ ትንሽ ተጨማሪ ለራሷ እንድትሰበስብ አዘዝኳት፤ አያይዤም እራሷን እንዲህ ያለ ነገር በማድረግ በማይረባ ትኩረት አጉል ተመልካች እንዳትስብ ዳግመኛ እንድትጠነቀቅ ነገርኳት።
ያልኳትን ሄዳ አደረገች፣ በኋላ ግን ቆይተን የዱር እንስሣዎቹ የተዋጉበት አውድማ መንደር በታላቅ ጥንቃቄ ሆነን በመደበቅ ሄድን። ከእዛም ትንሽ ቆዳዎችን ሰበሰብን፣ እና ሁለት ልብሶችን እንድትሰፋ እና የክት አድርጋ እንድትጠቀመው ያም እንዲስማማት አስለመድኩ። እውነት ነው ምቾት አልተሰማትም፣ ነገርግን ስልታማ ነው፣ የልብስ ቁምነገሩ ደግሞ እንዲያ ፋሽን ማሳየቱ ነው።.…
በደንብ ጥሩ አጋር መሆኗን ተገነዘብኩት። ንብረቶቼን አጥቻለሁ እና፣ ካለሷ ብቸኛ እምሆን እና ጭንቀት የሚይዘኝ ነኝ። ሌላው ነገር፣ ከእዚህ በኋላ ለኑሯችን እንድንሰራ መታዘዙን ነገረችኝ። ጠቃሚ መሆኗ አይቀርም። እኔ እንደሆነ ተቆጣጣሪዋ እሆናለሁ።
ከአስር ቀናት  በኋላ
የውጥንቅጣችን መነሾ ብላ እኔን ከሳኛለች! የተከለከለው ፍሬ አፕሉ ሳይሆን ቸስትነት የተባለው ፍሬ እንደነበረ እባቡ በሚታይ ትህትናው እና አለመዋሸት ተናግሮ እንዳረጋገጠላት ትናገራለች። ስለዚህ እኔ ደግሞ ምንም ቸስትነት ስላልተመገብኩ ንጹህ ነኝ ማለት ነው ብዬ ነገርኳት። እባቡ መልሶ “ቸስትነት” ማለት እኮ ያረጀ እና ያፈጀ ቀልድን ፈሊጥ አርጎ ያለ ቃል ነው ብሎ አስታወቃት። ያን እንዳሰማችኝ ክው ብዬ ገረጣሁ፣ ምክንያቱም ደባሪ ጊዜውን ለማሳለፍ ብዬ ብዙ ቀልዶችን እኔም ራሱ ፈጥሬ ነበር፣ ምንም እንኳ ከልቤ አዲስ ቀልድ ናቸው ብዬ ባምንም፣ ከእነርሱ መሀከል ግን አንዳንዶቹ እንዲያ ያሉ ቀልዶች ሊሆኑ ቢችሉስ። ልክ አደጋው ሲከሰት፣ ምንም ይሁን ምን ብቻ ቀልድ ፈጥሬ ከነበረ ጠየቀችኝ። ድምጼን ሳላሰማ ለራሴ አንድ ቀልድ ፈጥሬ እንደነበር ለማመን ተገደድኩኝ። እርሱም የሚከተለው ነበር።
ስለፏፏቴዎቹ በማሰብ ላይ ሳለሁ ነበር፣ ከዛ ለራሴ እሚከተለውን አልኩት፣ “እንዲህ ያለ የበዛ የዉሃ አካል ወደዚያ ወደታች ሲከነበል መመልከት እንዴት ያስደስታል!” በዛች ቅጽበት አንዳች ደግ ሃሳብ ለአእምሮዬ ብልጭ አለለት፤ ከእዛም ደፍሬ አወጣሁት “ወደላይ ሲፈስ ደግሞ ቢመለከቱት ኖሮ የተለየ አስገራሚ ይሆን ነበር!”—እና ተፈጥሮ ሙሉ በጦርነት እና ሞት ስትሠበር፣ እየተመለከትኩ በቀልዴ በሳቅ ልሞት ድረስ ሳቅኩበት፣ ቀጥሎ ስለነፍሴ እግሬ አውጪኝ ማለት ነበረብኝ። “ያው፣” አለች፣ በድል፣ “ያ እራሱ ነው፤ ያንኑ ቀልድ እባቡም ገልጧል፤ ከእዛም የመጀመሪያው-ቸስትነት ብሎ ሰይሞታል እናም በስነፍጥረቱ መሀከል መሰል ያረጀ እና ያፈጀ ነው” ብሎታል። ወይ ጉድ፤ እኔው ነበርኳ ተወቃሹ። እኔስ ቀልደኛ አልነበርኩም ማለት ነው፤ አወይ ያንን ደግ ሃሳብ ባላመነጭ ይሻለኝ ነበር!
ቀጣዩ አመት
ስሙን ቃየን ብለን ሰይመነዋል። ከኤሪ ግዛት ውስጥ ከሀገር ወጣ ብዬ በሰሜን ወንዝ ዳርቻዎቹ ላይ በማጥመድ ላይ ሳለሁ ነበር እሷ ያደነችው። ከእኛ ቤት መውጫ በቀደድንው ቦይ በኩል ሁለት ማይሎች አካባቢ ርቆ ባሉት ግንዶች ውስጥ ነበር ያጠመደችው—ምናልባት አራት ማይሎችም ሊሆን ይችላል፤ በእዛ እርግጠኛ አልነበረችም። በአንዳንድ ነገሮች እኛን ይመስላል፤ እናም ምናልባት እሚዛመደን ሊሆን ይችላል። እሷ እምታሰላስለው ያንን ነው፤ እንደኔ ውሳኔ ከሆነ ግን ያ ስህተት ነው። በቁመት መለያየታችን እሚደግፈው ድምዳሜ ቢኖር የተለየ እና አዲስ የእንስሣ አይነት ነው—ምናልባትም ዓሣ ነው፤ ለመሞከር ብዬ ወደ ዉሃ ስጨምረው ወደ ውስጥ ሰመጠ፣ እሷም ተወርውራ በመግባት ሙከራው ጉዳዩን ለመወሰን እድል ከማግኘቱ በፊት በመቅደም መንጭቃ አወጣችው። ያም ቢሆን ዓሣ ነው ብዬ ነው የምገምተው፣ እሷ ግን ምን ይሁን ምን ግድ አይሰጣትም፣ እንዲሁም ለእኔ ልሞክርበት እንድወስደው አትፈቅድልኝም። ይህስ ሊገባኝ አልቻለም። የፍጡሩ መምጣት መላ ነገረ ስራዋን ቀያይሯታል፤ እንዲሁም ስለ ሞክሮ-መገንዘብ ጥረቶች ምክንያታዊ እንዳትሆን አድርጓታል። ሌላ እንስሳዎችን ከምታስብበት ድግግሞሽ በበለጠ ደጋግማ ይኼኛውን ታስበዋለች፣ ግን ለምን ያን እንደምታደርግ ማብራሪያ አትሰጥም። አእምሮዋ አልሰከነም—ሁሉም ነገሯ እሚያሳየን ያንን ነው። ዓሣው ቅሬታ ካሰማ እና ወደ ዉሃው መመለስ ከፈለገ እሷ ግን በእጇ እስከ እኩለ ሌሊቱ ትሸከመዋለች። እንዲህ ሲሆን ግን በምትመለከትበት የፊቷ ክፍል በኩል ዉሃ ይፈልቃል፣ ከእዛም በጀርባው ቸብቸብ እያደረገችው ልስልስ ድምጽ በማውጣት ታባብለዋለች፣ በአንድ መቶ መንገዶች ሃዘን እና ብቸኛነትን ታባርራቸዋለች። ይህን አይነቱን ነገር ግን ከሌላ ማንኛውም ዓሣ ጋር ስታደርገው አላየኋትም፣ ያም በብርቱ ያስጨንቀኛል። የነብር ደቦሎቹን ተሸክማ ዞር ዞር ትል፣ አብራቸውም ትጫወት ነበር፣ ያኔ ንብረቶቻችንን ከማጣታችን በፊት ማለት ነው፤ ቢሆንም ግን ቅርርቧ ጨዋታ ብቻ ነበር፤ እራታቸው ካልተስማማቸው ማስገደድ ድረስ ግን አትገዳደራቸውም ነበር።
እሁድ
እሁዶች ላይ ስራ አትሰራም፣ ደካክማ እረፍት ለማድረግ ነው እምታርፈው፣ ዓሣውንም በአካሏ እንዲንቀዋለል ስታደርገው ደስ ይላታል፤ ልታዝናናው በማለት ሰነፍ ድምጾችንም ታወጣለታለች፣ ሽሆናውንም እምትበላ እየመሰለችበት ታሳስቀዋለች። ከእዚህ ቀደም መሣቅ እሚችል ዓሣ ተመልክቼ አላውቅም። ይህኛውን እንድጠራጠር ያደርገኛል….
እኔው ራሴም እሁድን እንድወድድ አድርጎኛል። ሁሉን ነገር ሳምንቱን ሙሉ መቆጣጠር፣ አንድን አካል በደንብ ያደክመዋል። ብዙ እሁዶች መኖር አለባቸው። በቆዩት ጊዜዎች ከባድ ነበሩ፤ አሁን አሁን ግን ጠቃሚ እየሆኑ ነው።
ረቡዕ
ኧረ ዓሣ አይደለም። ምን እንደሆነ ከነአካቴውም ሊገባኝ አልቻለም። ካልተደሰተ አንዳች ትንግርት፣ ክፉ ድምጾችን በማውጣት ይጮኻል፤ ቀጥሎም የልቡ ሲሟላለት “ጉ-ጉ” ይላል። ከኛ ወገን አይደለም፣ መራመድ አይችልም እና፤ ከወፎችም አይደለም፣ መብረር አይችልም እና፤ ከእንቁራሪቶችም አይደለም፣ እንጣጥ አይልም እና፤ ከእባቦችም አይደለም፣ አይሳብምና፤ ይዋኝ አይዋኝ ለማረጋገጥ እንድችል እድሉን አላገኘሁም ቢሆንም ግን ዓሣ እንዳልሆነ እርግጠኝነት ተሰምቶኛል። እንዲሁ ተጋድሞ ይውላል፣ በብዛት በጀርባው ተንጋሎ እግሮቹንም ወደ ላይ እንደሰተረ ነው። እንደዛ እሚያረግ ሌላ ምንም እንስሣ ከዚህ ቀደም ተመልክቼ አላውቅም። ግርታ ነው ብዬ አምኛለሁ አልኳት፤ ግን ያልኩትን ከመረዳት ይልቅ እንዲሁ አስተያየት መስጠቴን ብቻ ወዳዋለች። እንደኔ ብያኔ ከሆነ፤ ወይም ልዩ ትንግርት ነው ወይም የሆነ አይነት ተሳቢ እንስሳ ነው። ከሞተ፣ ፈታትቼ አቀነጃጀቱን እመለከተዋለሁ። እስካሁን እንዲህ አዲስ የሆነብኝ ነገር አልነበረም።
ከሶስት ወራት  በኋላ
ከመቀነሱ ይልቅ እሚያደናግረኝ ነገር ጨምሯል። እተኛለሁ ግን ትንሽ ብቻ ነው። አሁን መተኛቱን አቋርጦ በአራት እግሮቹ ይንቀሳቀሳል። ከተለመደው  ውጭ የፊት እግሮቹ አጠር በማለታቸው ከሌሎቹ እንስሳዎች ግን አሁንም ቢሆን የተለየ ሆኗል፤ ከእዛ የተነሳም ደግሞ ዋናውን ሰውነቱን ምቾት በሚነሳው መንገድ አበጥ እንዲልበት እና ወደ አየር ከፍ እንዲል አድርጎታል፣ ያም ምንም አያምርም። እኛ የተገነባነውን መሰል አገነባብ እንደተገነባ ነው፤ የመጓጓዝ ዘዴው ግን ፈጽሞ የኛ ዘር አለመሆኑን አስመልካች ነው። ያጠሩት የፊት እግሮች እና የረዘሙት የኋላ እግሮች እሚጠቁሙት፣ የካንጋሩ ቤተሰብ መሆኑን ነው፣ ቢሆንም ከእዛ ዘርም የተለየ ነው፣ ምክንያቱም እውነተኛው ካንጋሩ እንጣጥ እንጣጥ ባይ ነው፣ ይህኛው ግን አንዴም እንጣጥ አላለም። ከእዚያ ባሻገር፣ ከእዚህ በፊት ያልተለመደ ትንግርት እና አስገራሚ ፍጥረት እየሆነ ሄዷል። እኔ ቀድሜ እንዳገኘሁት፣ አዲስ ግኝት ቀድሞ የማግኘቱን ሽልማት - ስምን ከግኝቱ የማያያዝ ነገሩን - ለእራሴው ለመውሰድ የተፈቀደልኝ መስሎኛል፤ ስለእዚህ ስሜን አጣምሬው ካንጋሩም አዳሚንሲስ ብዬ ጠርቼዋለሁ…. አሁን ላይ በከፍተኛ መጠን በማደጉ፣ ሲመጣ እጅግ ልጅ ነበር ማለት ነው። በፊት ከነበረበት አሁን አምስት እጅ ያደገ መሆን አለበት፣ ካልተደሰተም በፊት ከነበረው ከሃያ ሁለት እስከ ሰላሳ ስምንት እጥፍ የጎላ ጩኸቶችን ይጮኻል። ቢያስገድዱትም ይሄን ለማስተካከል አልተቻለም፣ እንዲያ መጣጣሩ ይልቁንም ተቃራኒ ውጤት እየሰጠ ነው። ያን በመመልከት ጸጥ እንዲል ማስገደዱን ተውኩት። እሷ በማባበል እና በፊት አልሰጥህም ትለው የነበሩትን ነገሮች በመልቀቅ ታስማማው አለች።
ቀድሞም እንዳልኩት፣ መጀመሪያ ሲመጣ እኔ ቤት አልነበርኩም፣ እሷም ከጫካዎቹ እንዳገኘችው ነግራኝ ነበር። ከመሰሎቹ አንድ እና ብቸኛ መሆኑ እሚገርም ነው፣ ግን የምርም ብቸኛ ቢሆን ነው፣ ላለፉት ብዙ ሳምንታት መሰሉን ለመፈለግ እና የእንስሣቶች ስብስቤ ውስጥ ላካትተው ስሞክር ከእዚህኛው ጋር ግን ልጫወት አስቤ፤ ያኔ በርግጠኝነት የተሻለ ጸጥታ ይኖራል፤ እንደገናም በተሻለ ለማዳ እንስሣ ሊያደርጉትም ይቀላል፣ በበለጠ ቅለት እምናረባውም ይሆናል በማለት ጣርኩ። ግን ከሱ ውጭ ያለ አንድም ተጨማሪ አላገኘሁ፣ የተተዉ ፍንጮችንም ራሱ አላየሁም፤ ከሁሉ በሚገርም ደግሞ ዱካውን ራሱ አንድ እንኳ ማደን አልተቻለኝም።
እራሱን ለማገዝ ስለማይችል፣ በየብስ እሚኖር ይመስለኛል፣ ከሆነ ደግሞ እንዴት አርጎ ዱካ ሳይተው መኖር ተቻለው? ደርዘን ወጥመዶችን ባስቀምጥም ግን አንዳቸውም አልበጁኝም። እንደሚመስለኝ ምን እንደሆነ ለማወቅ ከመጓጓት ብቻ እሚጓዙ ናቸው ብቻ ፈጽመው ባይጠጡትም ወጥመዱ ዉስጥ ወተቱ ለምን እንደተቀመጠ ሊያዩ እሚመጡትን ሁሉንም አነስ አነስ ያሉ እንስሣዎች ሁሉ ማጥመድ ችያለሁ፣ ብቻ ከእዚህኛው በስተቀር ሆነብኝ።
(ቅንጭብ ከአዳም ማስታወሻ ውስጥ)
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢሜይል ድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡




Read 947 times