Saturday, 25 March 2023 17:37

ሕዳሴዎች ያስፈልጉናል - ሰው አይደለንም እንዴ?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(2 votes)

 ከብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ መራቅ፣… ቢያንስ ቢያንስ መቆጠብ፣… መቀነስ፣… ቢያንስ ቢያንስ አለማባባስ… ማስወገድ እስኪቻል ድረስ።
አምስት የቀውስ፣ የትርምስና የምስቅልቅል ዓመታት ከበቂ በላይ ናቸው።
የሃሳብ፣ የኑሮ፣ የመንፈስ ሕዳሴዎች ያስፈልጉናል። የግድ ነው - በሕይወትና በአገር እንደ ሰው በክብር ለመኖር።
ሕይወታችን፣… “መልክ፣ ትርጉምና ጣዕም” እንዲኖረው፣ እስከዛሬ ከተዘፈቅንባቸው የቅዠትና የስካር ሃሳቦች መባነን አለብን።
ከአንድ ቀን በላይ የሚጓዝ፣ ውሎ የሚያድር፣ ወንዝ የሚያሻግር፣ ቅጥ ያለው ሃሳብ ጠፍቶብናል። ለዛሬ “የተገለገልንበትን” አንድ ሃሳብ፣ ለነገ እንዳሻን በሌላ ተቃራኒ ሃሳብ እንለወጣለን - እንደፈቀድን። ያለ ከልካይ፣ ማለትም ያለ ሕሊና።
የትውልድ ቦታ እየተጠቋቆምን፣ የብሔር ብሔረሰብ ተወላጅነትን እየቆጠርን፣ አማራ ወይስ ኦሮሞ፣ ትግራይ ወይስ ሶማሌ እያልን፣ በየወንዙ የተለያየ “መርህ” እያገላበጥን፣… ከሰው ተራ ወጥተናል። ሃሳባችን ከቅዠት የማይተናነስ ሆኗል።
ከወንዝ የማይሻገር “መርህ”፣ ጨርሶ መርህ አይደለም። ሊሆንም አይችልም። እንዲያውም፣ መርህ አልባነት ነው። ከዚያ ከባሰም፣ ህሊና ቢስ ስነ-ምግባር የለሽ “ፀረ-መርህ” ይሆናል።
ተግባራችንም፣… በመደናበርና በጥፋት መሃል የሚመላለስ አዙሪት፣ መንፈሳችንም ጭፍን ጥላቻና የክፋት ጭካኔ የሚፈራረቅበት ጨለማ ሆኗል። በቅራኔና በጥላቻ፣… ኑሮ ተበላሽቶ፣ ሕይወት ረክሷል።
የሃሳብ፣ የኑሮ፣ የመንፈስ ሕዳሴዎች ያስፈልጉናል። የግድ ነው - ሕይወታችን፣… “መልክ፣ ትርጉምና ጣዕም” እንዲኖረው። ሰው ሆነን እንደ ሰው በክብር ለመኖር፣ የሃሳብ፣ የኑሮ፣ የመንፈስ ሕዳሴዎች ያስፈልጉናል።
እንዲህ በአምስት ቃላት የመግለጽ ያህል፣ ነገሮች ሁሉ በእውንና በተግባር ቀላል ቢሆኑ እንዴት መልካም ነበር? ግን ቀላል አይደሉም። እንዲያውም፣ ከእነዚህ የከበደ ሌላ ቁም ነገር የለም ማለት ይቻላል።
ደግሞስ ቁምነገር የተባለ ሁሉ፣ በእነዚሁ ውስጥ የሚካተት አይደል! ታዲያ ምንም ቢከብዱ፣ ሌላ ምን አማራጭ አለ- መልካም ቁምነገር ከመስራት በቀር። “ለስጋም ለነፍስም”፣ ወይም “ለአካልም ለመንፈስም” እንደሚባለው፣ ከዚህ በላይ የላቀ ከዚህ ሌላ የተቃና መንገድ የለም። ለውጤትም ለጀግንነትም፣ ለትርፍም ለክብርም ነው።
ካሰቡና ከተመኙ አይቀር፣ አላማ ከያዙና በጽናት ከታገሉ አይቀር… ከዚህ የበለጠና ከዚህ የተለየ መልካም ቁምነገር የለም።
የሃሳብ፣ የኑሮና የመንፈስ ማንሰራሪያ መንገድ ነው የሁሉም መልካም ነገር እናት።
ታዲያ ምነው? ምን እንጠብቃን? ምን ትጠብቃላችሁ? የመባነን፣ የማንሰራራት፣ የመታደስ መንገድ እንዲህ እንደ ንግግር አይቀልልም። እንደ ቀላል የእግር ጉዞ አይደለም።
ቀላል አይደለም ማለት ግን፣ ስህተት ነው ማለት አይደለም። ቀላል ባይሆንም ትክክል ነው የሃሳብ፣ የኑሮና የመንፈስ ህዳሴ ያስፈልገናል።
በእርግጥ በጥቅሉ ሲታይ ትክክልና መልካም ቁምነገር ቢሆንም፣ ሲፍታታ ሲዘረዘር ግን ጣጣው ብዙ ነው። ከስንት አይነት ሃሳብ፣ ከእልፍ የኑሮ እቅድ፣ ከስንቱ የመንፈስ ትምህርት የትኛው መልካም የትኛው ክፉ እንደሆነ ለይተን ብናውቅ ኖሮ፣- እሺ።…
 በእልፍ የሃሳቦች ግርግር እየተሳከርን፣… የሃሳብ ትንሳኤንና የመባነን መንገድን እንፈልጋለን ብለን በደፈናው ብንናገር የት እንደርሳለን? እውነት ነው ነገሩ ከባድ ነው። ነገር ግን፣ የተሳከሩ ሃሳቦች እጅግ ስለበዙ፣ ሃሳባችንን ማስተካከል የለብንም ማለት አይደለም። እንዲያውም፣ በተሳከሩ ሃሳቦች ተተብትበን እየተደናበርን ስለሆንን ነው ሃሳባችንን ለማስተካከልና ቅጥ ለማስያዝ መበርታት የሚኖርብን።
ይህም ግን በቂ አይደለም። ገና ምኑን አይተን!
የሃሳብ ትንሳኤ ብቻውን ባለብዙ ቅርንጫፍ አስቸጋሪ ስራ ከሆነ፣ የኑሮ የኢኮኖሚ ህመምን መፈወስና ማንሰራራትማ እንዴት ይሞከራል?
አዎ፤ የኑሮ ችግር መራራ ነው። በይደር ይቆይ አይባልም። የምግብ እጦት፣ እሺ ብሎ ጊዜ አይሰጥም። አጣዳፊ አደጋ ነው። በዚያ ላይ የእለት ተእለት ፋታ የለሽ የዘወትር ፈተና ነው። እናም፣ ሃሳብን የማስተካከል ጥረት ሳይሆን ኑሮን የማሻሻል መከራ ይመስላል ከባዱና አስቸጋሪው ስራ። አዎ ይመስላል።
የተጎሳቆለውን ኑሮ እንዲያገግምና፣ የማሰነው ኢኮኖሚ እንዲያንሰራራ ማድረግ ይቻላል ወይ የሚለው ጥያቄ፣ ሃይለኛ ራስ ምታት ነው። ይቻላል ወይ?… ብለን ብንሰጋም አይፈረድብንም። አዎ፣ የዜጎች ኑሮ በክፉ ስብራቶች ሳቢያ አፈር ቢበላም፣ ማገገምና መነሳት ይችላል። የማይችል መምሰሉ ግን እውነት ነው። የኑሮ ችግር ከመብዛቱና ከመክበዱ የተነሳ፣ ተስፋዎቻችንን ያጨልምብናልና።
የዶላር እጥረት እየተባባሰ፣ በሌላ በኩል የብር ሕትመት አለቅጥ እየጨመረ፣ እየረከሰ፣ የዋጋ ንረት በላይ በላዩ እየተቆለለ፣ ኑሮ የማይቀመስ ሆኗል።
የተገነባ እየፈረሰ፣ የተሰራ እየወደመ፣ በየትኛው ተዓምር ኢኮኖሚ ያገግማል? በየት በኩል የዜጎች ኑሮ ያንሰራራል? በሰላም መኖር፣ ሰርቶ መግባት፣ ወጥቶ መመለስ አደገኛ እየሆነ፣ ከቤትም ከመንገድም፣ በውድቅት ሌሊትም በጠራራ ጸሐይም ሰው እየተገደለ፣ ንብረት እየተዘረፈ፣… አዲስ ኢንቨስትመንት እንዴት ይታሰባል? ነባሩንም ማቆየት ያስቸግራል።
ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ፣ አዲስ የስራ እድል የሚያስፈልጋቸው ሰባት ስምንት ሚሊዮን ተጨማሪ ወጣቶች ተፈጥረዋል።
ለዚህ ሁሉ ወጣት የሚበቃ በሚሊዮኖች የሚቆጠር የሥራ እድል ከየት ይመጣል? ብዙ የኢንቨስትመንት ግንባታ ያስፈልጋል። ግን፣ ምንን ተማምነው ይገቡበታል? የንብረት ባለቤትነት መብትን ተማምነው ፋብሪካ ይተክላሉ ወይ? ነገ ተዘርፎ፣ ከነገወዲያ በአመፅ ወድሞ፣ ወይም በመንግስት ፈርሶ ባዶ እጃቸውን ቢቀሩስ? የእያንዳንዱን ሰው ሕይወት የሚያስከብር ሕግና ስርዓት ነው መተማመኛቸው? ህግና ሥርዓት ከወዴት ይገኛል!
ድሮስ ቢሆን ሕግ እና ስርዓት መች ነበረ እንል ይሆናል። አዎ ድሮም እንደጎደለን ነው። አሁን ግን ለወጉ ያህልም እየራቀን ነው። እንደ ነገሩ ውለን ለማደር የምንተማመንበት ሕግና ስርዓት ሲጠፋ ምን እንበል?
ቢያንስ ቢያንስ፣ የተረጋጋ አገር ከሌለ፣ ከሳልስት የሚሻገር ሰላም ከሌለ፣ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች በምን ስሌት ይታሰባሉ? በሚሊዮን የሚቆጠሩ የስራ እድሎችስ እንዴት ይፈጠራሉ?
የተረጋጋ ሰላም ያስፈልጋል። ከዚያም አልፎ ለታይታም ሆነ ለወጉ ያህል፣ በተወሰነ ደረጃ ሊታይ የሚችል፣ ቢጠሩት አቤት የሚል የሕግና የሥርዓት ጭላንጭል ጭምጭምታ ሊኖረን ይገባል። ከዚያም ቀስ በቀስ፣ ሕግና ስርዓቱ፣ በአካልም በመንፈስም መጎልበት ይችላል። አቅጣጫው ሲስተካከል፣ ከስህተት እየጠራ እየታነጸ ሲሄድስ? ሁነኛ የስልጣኔ ጅምር እንደማየት ቁጠሩት።
ያኔ፣ የእያዳንዱን ሰው ሕይወትና ንብረት ለማስከበር ያለመ ጠንካራ መተማመኛ ይሆናል- ህግና ሥርዓት። የግለሰብ ነጻነትና መብትን በማክበር ላይ የተመሰረተና ይህን ለማስከበር ያለመ ሕግና ሥርዓትም ነው፤… የሕግ የበላይነት ተብሎ የሚታወቀው። ይሄው ነው ስልጡን ፖለቲካ።
አሁን ችግሩ፣ የሕግ የበላይነት ወይም ስልጡን ፖለቲካ በአገሬው መታጣቱ አይደለም። ጨርሶ በሃሳባችንም በሕልማችንም መጥፋቱ ነው አስፈሪው ነገር።
ታዲያ፣ የሃሳብ ሕዳሴ አያስፈልግም ትላላችሁ? ተግተህ ስራ፣ ንብረት አፍራ ከሚሉ የስነ-ምግባር መርሆች ጋር፣ የሰው ህይወትና ንብረትን አትንካ የሚሉ የስልጡን ፖለቲካና የፍትሕ፣ የሕግና የሥርዓት መርሆች… መሠረታዊና ትክክለኛ ሃሳቦች መሆናቸውን ካተገነዘብን፣ ምን ሌላ ተስፋ ይኖረናል?
እውነትም፣ የተሳከሩ ሃሳቦችን ማስተካከል፣ ትልቅ ስራ፣ የተከበረ ሃላፊነት ነው።
ያለ ሃሳብ ሕዳሴ፣ ሕግና ስርዓትን ማነጽ አይቻልም።
ሕግና ስርዓት ሳይኖርስ፣ እንዴት ብሎ ስራ ይቃናል? እንዴትስ ኑሮ ያገግማል? በምን ሂሳብ በአዲስ ኢንቨስትመንት አዳዲስ የስራ እድሎች ይከፈታሉ?
አገሬው ባያስተማምንም ሌላ አማራጭ እንደሌለው በማሰብ አዳዲስ ስራዎችን የሚጀምር ይኖራል። አይጠፋም። ግን ጥቂት ነው። እሱም ይደናቀፋል።
ከምር ለመስራት ሳይሆን፣ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ለማምታታት የሚታትርና አሰፍስፎ የሚጠብቅ ደግሞ አለ።
በአንዲት አቋራጭ መንገድ፣ በአደባባይ አየር ባየር፣ አልያም በጓዳ በጉራንጉር፣… ከመንግስት ባለስልጣትና ከፓርቲ ካድሬዎች ተጠቃቅሶም ሆነ ተቃቅፎ፣… እዚህም እዚያም መሬት ተቀራምቶ ቦታ አስከልሎ፣ ብድር በገፍ ተቀብሎ፣ በሌለ ዶላር በጎን በኩል አስፈቅዶ፣… ሃብታም ለመሆን ይነሳል።
“በዚህም በዚያም ሃብትን ካገኘሁ በኋላ… ያኔ ደፍሮ የሚነካኝንና የሚሆነውን አያለሁ፤ ገፍቶ ከመጣም፣…ምንም ቢሆን ያገኘሁትን ይዤ በጊዜ አመልጣለሁ” ይላል። እንዲህ አይነት ሰዎች ብቻ ናቸው መድረክ ላይ የሚቀሩት- ሰላም በደፈረሰበት አገርና ዘመን።
አየር ባየር የሚያምታቱ፣ በዘር እየተደቧደኑ፣ በፓርቲ እየተዳበሉ፣ በአንዱ ፓርቲ ተገን ከሌላው ፖለቲከኛ ጋር እየተሻሹ ሃብታም ለመሆን፣ በባለስልጣን ልሳን የሚቀባጥሩ የሚቀላውጡ ሰዎች በታሪክ ሁልጊዜ ነበሩ፤ ወደፊትም ይኖራሉ።
ሕግና ስርዓት በተፍረከረከበት ዘመንና ሰላም በደፈረሰበት አገር ውስጥ ግን፣ አምታቾች ብቻ ናቸው፣ ከመድረኩ ላይ እየገነኑ የሚቀሩት።
በጥረት ፍሬያማ ከመሆንና አዲስ ሃብት ከመፍጠር ይልቅ፣ ከዚህም ከዚያ እየተቀራመቱ ይሻማሉ።
የነሱ አልበቃ ብሎ፣ ሌላ ሌላውንም እየበከሉ፣ የስራ ሰዎችም ጭምር ተስፋ እየቆረጡ ወደ ቅሚያና ወደ ሽሚያ እንዲቀላቀሉ ይገፋፏቸዋል።
አገሪቱን ሁሉ የሸፍጥና የንጥቂያ ቅርጫ ያስመስሏታል።
ምን ይሄ ብቻ! የደፈረሰውን ሰላም ከናካቴው ያናውጡታል። በዘርና በትውልድ ቦታ፣ በሃይማኖትና በፓርቲ ቲፎዞነት እየተቧደኑ ሲቀራመቱ፣ በየጎራው በተቀናቃኝነትና በልወደድ ባይነት፣ ጭፍን ጥላቻን ያዛምታሉ። የመጠፋፋት ውዝግብን በየእለቱ እየፈለፈሉ አገሬውን ያለእረፍት ያምሱታል።
የሕግና የሥርዓት ጭላንጭሎችን ሁሉ እያዳፈኑ፣ መጫወቻና መቀለጃ እንዲሆንላቸው፣ ወይም ደብዝዞ እንዲጠፋ ያደርጋሉ።
በሌላ አነጋገር፣ ሰላም ሲደፈርስ፣ ህግና ሥርዓት ሲፍረከረክ፣ እንደ አሸዋ ክምር እለት ተእለት ሲንሸራተት፣ ከነፋስ ጋር እየተንሳፈፈ፣ ባደረበት ቦታ የማይገኝ፣ በዋለበት አካባቢ የማያመሽ፣ የማይጨበጥ የማይተማመኑበት፣ ከንቱ የቃላት ድምጽ ብቻ ሆኖ ይቀራል።
ይህም ለወንጀለኞች፣ ለዘራፊዎች፣ ለአውዳሚ ለአጥፊዎች፣ ለአምታች አሳባቂዎች ይመቻቸዋል። እነዚህም በተራቸው፣ ይባስኑ ሰላምን የሚያደፈርስ የሰበብ መዓት ይፈጥራሉ። በቅርምትና በውድመት ብዛት፣ በግጭትና በጥቃት መዛመት የተነሳም የሕግና የስርዓት አቅሞች ይሽመደመዳሉ። ቅሪታቸው ይፈራርሳል። ተስፋዎች ይጨልማሉ።
ይህም ከእለት ተእለት ጋጠወጥነትና ስርዓት አልበኝነትን፣ ጭካኔንና ክፋትን ያስፋፋል።
ነገሩ ቁልቁል የሚያወርድ አዙሪት ነው። እዚህም ላይ ነው ሙስና ክፋቱ። ሃብትን ንብረትን፣ ኑሮንና ኢኮኖሚን ብቻ የመቦጨቅ የመዘንጠል ጉዳይ አይደለም።
ከነአካቴው፣ የአገር ህልውናንና ሰው የመሆን ክብርን የሚበክል፣ እንደነቀዝ ቋሚ መሰረቶችንና ምሰሶዎችን የሚበላ ነው- አዙሪቱ።
አሳዛኙ ነገር፣ መሰረታዊና የሚያዘልቁ መፍትሄዎችን ለማሰብ፣ በውጤታማ መንገድም እውን ለማድረግ፣ በሃሳብና በተግባር ከመትጋት ይልቅ፤… የኑሮ ችግርንና የኢኮኖሚ ቀውስን የሚፈውስ መድሃኒት ከማበጀት ይልቅ፣… የፖለቲካ መጫወቻ፣…ጭራሽ የፖለቲካ ትንቅንቅ ማባባሻ ማራገቢያ ሰበብ ያደርጉታል።
መንግስትን ለማሳጣት ገዢውን ፓርቲ ለማጥላላት ስለሚያገለግላቸው፣ የኢኮኖሚ ቀውስን ሲያዩ ይጎመጃሉ- አንዳንድ የቅራኔ ፊታውራሪዎች።
የገዢ ፓርቲ ሃላፊዎችና የመንግስት ባለስጣልናት ደግሞ፣ ከቻሉ እውነታውን ለማስካድ ላይ ታች ይላሉ። ኢኮኖሚ ሲቃወስ እንደተቃና፣ ኑሮ ሲጎሳቆል እንደተነቃቃ እንዳማረበት ለማሳመን ይሟሟታሉ። የተመሳቀለውን ኢኮኖሚ ማዳነቅ፣ የተራቆተውን የዜጎች ኑሮ በዲስኩር አንቆጥቁጠው ማሳማር ባይችሉ እንኳ፣ ነገሩን ለማስተባበልና ለማድበስበስ የሚሞክሩ አይጠፉም። እውነታውን የማስካድም ሆነ የማስተባበል ጥረት፣… ጊዜንና አቅምን በከንቱ ያባክናል እንጂ፣ ቅንጣት መፍትሄ አይሆንም።
ከዚህ የሚከፋም አለ።
በማያዛልቅና በማያዋጣ በጭፍን ስሜት፣ ተጨማሪ በሽታዎችን የሚፈጥር፣… የዋጋ ተመንና የዋጋ ቁጥጥር ለማወጅ የሚሽቀዳደሙ ባለስልጣናት ሞልተዋል። በስሚንቶ ገበያ ላይ የተሞከረው የኮታ አሰራር ብዙ እጥፍ ችግሮችን ወልዷል- እስኪሰረዝ ድረስ። የእህል ንግድን አስረው አንቀው መፈናፈኛና መተንፈሻ የሚያሳጡ ኬላዎችን በየወረዳው እየተከሉ እልፍ የሙስና እድሎችን መፍጠርስ? እንዲህ የመሳሰለ የመንግስት ውሳኔና ተግባር፤… ህመምን ከመፈወስ ይልቅ ያባብሳል፤ ያዛምታል።
ከዚህ የከፋም አለ- ብታምኑን ባታምኑም።
የኑሮ ችግሮችን ከመፍታት ይልቅ፣ ኑሮን የሚያስረሱ ሌሎች የፖለቲካ ቀውሶችን በየእለቱ መፈብረክ ይሻላል ብለው የሚያሰቡ ፖለቲከኞች ይኖራሉ - ቁጥራቸው ብዙ ባይሆንም።
እና፣ ከኑሮ ለማዘናጋትና የፖለቲካ መድረኮችን ለመቆጣጠር፣ በላይ በላዩ የፖለቲካ ውዝግቦችንና የቅራኔ ሰበቦችን በእሩምታ እያከታተሉ አገሬውን ያለፋታ ይቀውጡታል። የኢኮኖሚ ቀውስንና የኑሮ ችግርን እንደገና እያባባሱ ቁልቁል እንደመገፍተር ነው። እንጦሮጦስ የሚያወርድ ነው አዙሪቱ።
እናም የሃሳብ፣ የኑሮና መንፈስ ሕዳሴዎች ያስፈልጉናል። ዋና ዋና የሃሳብ ሕደሴዎችን በማንሳት ሳምንት ብንጀምረውና ብንነጋገርበትስ?

Read 1007 times