Saturday, 25 March 2023 17:46

ሁለት ገጠመኞች

Written by  በከድር ነብሶ
Rate this item
(4 votes)

 አስታውሳለሁ፤ በአንድ ብራማ ቀን አንዲት ልጅን እየጀነጀንኳት  ከፊት ለፊታችን  ወደምትገኝ  አንዲት ምግብ  ቤት  ዎክ እያደረግን ሳለ  ነበር፤አንድ ፖስተራዊ አለባበስ የለበሰ ሰውዬ፣ በፈገግታ ፊቱን አሸብርቆ ወደ እኛ ሲራመድ ያየሁት።
እንዳየሁት በኪሴ ጎዶሎነት ልጅቷን ወደ ሽሮ ቤት ይዤ እየሄድኩ በመሆኔ የተሰማኝን መሸማቀቅና የኪሴን ጎዶሎነት በኩራት ረስቼ፣ በከተማይቱ ታዋቂ ስለሆንኩኝ ከሰውዬው አድናቆት በልጅቷ ፊት ልሸለም እንደ ተሸላሚ ፊቴን በፈገግታ አቅልሜ ስጠባበቅ  ሰውዬው አጠገቤ ደርሶ፤
“ሰላም ነህ ወንድሜ?” ሲለኝ፤ “አለን” በማለት አድናቆት መስሎኝ ከመሸማቀቄ ለመላቀቅ እየሞከርኩ  በኩራት ተሞልቼ፤ “ተመልከቺ ከማን ጋር እንዳለሽ!”  በሚል ስሜት ዓይኖቼን ወደ ልጅቷ ሳነጣጥር  ነው፣ ሰውዬውም ከፈገግታው ሳይናጠብ፣  ጥሪቴን አስታውሶኝ፣ ትካዜ ያስታቀፈኝ።
“ዋናው ጤና ነው። የደቡብ ግሎባል ባንክ አካውንት ከፍተሃል? ካልከፈትክ ያስቆምኩህ  ላስከፍትህ ነው?”
በነገራችን ላይ የከተማ ገጠመኜ ብዙ ነው። ደግሞ ባንዱ ቀን ነው፣ እኔና አንድ ጓደኛዬ  ስሟን የማልጠቅሳት ከተማ ሄደን፣ እንደ ጤና ጉድለት የብር ጉድለት፣ እንደ ሆስፒታል አልጋ ሳይወዱ ለሚተኙበት አልጋ የዳረገን።
አስታውሳለሁ፤ አልጋውን ልንከራይ እንደገባን ነው አከራያችን መታወቂያ ሲጠይቀን፣ ”መጀመሪያ አልጋውን እንይ” ብለን ወደ ውስጥ የገባነው።
ታዲያ ገብተን ስናየው አልጋው እንደተቸ ስክሪን ሲነኩት፣ ተናጋሪ ከመሆንም አልፎ በህመሙ ሌላ አልጋ የሚያሲዝ ቁንጫ ነበረው፤ ተናድፎ።
ጓደኛዬም  አል ጋውን እያየ ነበር፡፡
‹ወንድሜ፤ ከዚህ መውጣት ነው የሚሻለው› አለኝ፡፡
‹ለምን?› ጠየኩት፡፡
‹ይሄን አልጋ የያዝነው ብር ለመቆጠብ ነበር› መለሰለኝ
‹ታዲያ አሁን ምን ሆነ?›  ገርሞኝ ጠየኩት፡፡
በሹክሽክታ እንዲህ አለኝ፤ ‹ሰውዬ! እዚህ ብርድ ልብስ ውስጥ ለመግባት ወንጀል ውስጥ እንደሚገባ ሰው ለመጠጥ ወይም ለአደንዛዥ እጽ ከዚህ ሳንወጣ ለሆስፒታል አልጋ የሚዳርግ ወጪ ማውጣታችን  ነው፤ ስለዚህ ብንወጣ ነው የሚሻለው!››
(“እንዚራ ቲዩብ” ላይ ከተለቀቀ የወግ እና የግጥም ቪዲዮዬ የተቀነጨበ፡፡)



Read 1648 times