Sunday, 26 March 2023 00:00

የሐብት ክፍፍሉ በመዘግየቱ ኪሳራችን 100 ሚሊዮን እየተጠጋ ነው

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

 ኪሳራው የኔ ብቻ ሳይሆን የሀገርም ጭምር ነው” - አቶ አለምሰገድ ይፍሩ
                        
            አቶ አለምሰገድ ይፍሩ የ”አለምሰገድ ይፍሩ ጠቅላላ ህንፃ ሥራ ተቋራጭ ድርጅት ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው። እ.ኤ.አ ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ ኑሯቸውን በሰሜን አሜሪካ ኮሎራዶ አድርገዋል። ከሀገር ከመውጣታቸው በፊት በወላይታ ዞን የአረካ ከተማ ከንቲባ ከመሆን ጀምሮ በርካታ አገልግሎት ሲሰጡ መቆየታቸውን ይናገራሉ። ወደ አሜሪካ ከሄዱም በኋላ የደቡብ ኢትዮጵያ የዲያስፖራ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ በመሆን ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር ለሀገራቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሲያበረክቱም እንደቆዩ ይናገራሉ።
እንደ አቶ አለምሰገድ ገለጻ ከሆነ የደቡብ ክልል ባለስልጣናት ወደ አሜሪካ በማቅናት  ዲያስፖራው ወደ ሀገር ቤት መጥቶ ልምዱን፣ እውቀቱን የዶላር ሬሚታንሱንም ሆነ ኢንቨስትመንቱን እንዲያበረክት ግብዣ ባቀረቡ ጊዜ ይህን አጋጣሚ ተጠቅመው ወደ ሀገር ቤት በመምጣት በደረጃ አምስት የኮንስትራክሽን ዘርፉ መሰማራታቸውን ይናገራሉ። በወቅቱ የደቡብ ብሄር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ደሴ ዳልኬ በቀናነት ግብዣውን እንዳቀረቡላቸውም ነው የገለጹት።
እ.ኤ.አ በ2016 ህጋዊ ንግድ ፈቃድ በማውጣት በደረጃ 5 ተቋራጭነት ስራ ተሰማርተው ሲንቀሳቀሱ እንደነበር የተናገሩት ዲያስፖራው ባለሃብት ባለቤቱ የደቡብ ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን የሆነ ባለ ስድስት ወለልና ሌላ ተጨማሪ ህንጻ 60 አባዎራዎችን ሊይዝ የሚችል ባለሁለትና ባለሶስት መንታ ቅንጡ አፓርታማ ህንጻዎችን በቁርጥ ዋጋ ማለትም በ109 ሚሊዮን ብር ገንብቶ ለማስረከብ ከደቡብ ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ንዑስ ተቋራጭ ከሆነው ከደቡብ ክልል ቤቶች ኢንተርፕራይዝ በንዑስ ተቋራጭነት ተረክበው ከሶስት ዓመት በፊት ወደ ግንባታ መግባታቸውን አጫውተውናል። ጨረታውን ከአራት ደረጃ አንድ ተቋራጮች ጋር ተወዳድረው የውጪውን ሀገር ተሞክሮ ቀምረው በማቅረባቸው ማሸነፋቸውንም ነግረውናል።
በሃዋሳ ከተማ በተለምዶ ዶሮ እርባታ በሚባው አካባቢ የተጀመረው ይህ ግንባታ የሲዳማ የክልልነት መብት መረጋገጡን ተከትሎ በመንግስት ፕሮጀክትነት የሚገነቡ ግንባታዎች ባሉበት እንዲቆሙ ክልሉ ባወረደው መመሪያ መሰረት ሀምሌ 16 ቀን 2012 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ አለምሰገድ ይፍሩ ጠቅላላ ህንፃ ሥራ ተቋራጭም ግንባታውን እንዲያቆም በንዑስ ተቋራጭነት ስራውን እንዲሰሩ ያስረከባቸው የደቡብ ቤቶች ኢንተርፕራይዝ ግንባታ እንዳስቆማቸው ይናገራሉ።
የመኖሪያ አፓርታማ ህንጻዎቹ ሁለት ሲሆኑ የሚሰሩትም ለደቡብ ክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት መኖሪያነት በኪራይ ለማስረከብ እንደነበር ሰምተናል። ህንጻዎቹ ባለፉት ሁለት ዓመታት ዝናብና ፀሀይ እየተፈራረቀባቸው አሸዋና ጠጠር መቀላቀያ አራት ማሽኖችን ጨምሮ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ወጥቶባቸው በኪራይ የመጡ ፓኔሎች፣ የተለያዩ የግንባታ ግብዓት የሆኑ ብረቶች፣ አሸዋና ሲሚንቶ በሙሉ ከጥቅም  ውጪ ሆነው ህንጻዎቹም በመፈራረስ ላይ መሆናቸውን በስፍራው ተገኝተን ለመታዘብ ችለናል። ግንባታው በቆመ በአንድ አመት ውስጥ የደረሰውን ኪሳራ አስጠንተው ከ33 ሚሊዮን ብር በላይ ደርሶ እንደነበር የሚናገሩት ዲያስፖራው ባለሀብት የዛሬ ዓመት አካባቢ ለደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳው አቤቴታ አቅርበው ይህ ፕሮጀክት ወደ ሲዳማ ክልል ንብረትነት እንዲካተት ኮሚቴ አዋቅረው ትዕዛዝ ቢያስተላልፉም ትዕዛዙ ተፈጻሚ ባለመሆኑ ሌላ ተጨማሪ አንድ ዓመት ያለውሳኔ መቆየቱ ህንጻዎቹን ለተጨማሪ ብልሽትና ኪሳራ፣ በህንፃው ግቢ ውስጥ ያሉ ንብረቶች ለዘረፋ መዳረጋቸውንና ተቋራጩ በርካታ ጥበቃዎችን ቀጥረው ጅምር ህንጻዎቹን በማስጠበቅ ለተጨማሪ ወጪ መዳረጋቸውን ይናገራሉ።
“እኛ ንዑስ ተቋራጭ ሆነን ስራውን ስንረከብ የብረት ዋጋ በኪሎ 52 ብር የነበረ ቢሆንም የክልሉ መንግስት አስተያየትና ታሳቢ እናደርጋለን በማለቱ ስራውን የብረት ዋጋ በኪሎ 26 ብር ተረክበናል። አሁን ላይ የ1ኪሎ የብረት ዋጋ እስከ 180 ብር ደርሷል” የሚሉት አቶ አለምሰገድ ይህን ሁሉ ጊዜ ህንጻው በጅምር ተገትሮ እየበሰበሰ፣ በውስጡ ያለው የግንባታ ግብዓት በሙሉ ከጥቅም ውጪ ሆኖ፣ ለጥበቃ ደሞዝ እየከፈልን ያለመፍሄ ተቀምጠናል። ይህም ኪሳራችንን ወደ 100 ሚሊዮን ብር ከፍ አድርጎታል ሲሉ ያማርራሉ።
“እኛ በሀገራችን አንድ አስተዋጽኦ ለማድረግ መንግስት ባደረገልን ጥሪ መጣን እንጂ ትርፍ ለመሰብሰብ አይደለም” ያሉት ባለሀብቱ ሁኔታው በእጅጉ እንዳሳዘናቸው ገልጸው ኪሳራው የራሳቸው ብቻ ሳይሆን የሀገርም ጭምር በመሆኑ አስቸኳይ እልባት እንዲያገኝ ጠይቀዋል፡፤
“ጉዳዩን ወደ ህግ ያልወሰድነው በሆደሰፊነትና በትዕግስት እንዲያልቅ ከመመኘት ጭምር ነው” ሲሉም እየሄዱበት ያለውን እልህ አስጨራሽ ጉዞ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። እንደ ባለሃብቱ ገለጻ እርሳቸው የጀመሩት ፕሪጀክት ኪሳራ አንዱ ማሳያ ይሁን እንጂ ከሁለቱ ክልሎች ሀብት ክፍፍል ውሳኔ መዘግየት ጋር ተያይዞ እንዲህ አይነት በርካታ ፕሮጀክቶች ለኪሳራ ሳይዳረጉ እንደማይቀሩ ስጋታቸውን ይልጻሉ።
እኛም ጉዩን ለማጣራት ስራውን ለዲያስፖራው በንዑስ ተቋራጭት ወደሰጠው የደቡብ ክልል ቤቶች ኢንተርፕራይዝ ጽ/ቤት ጎራ ብለን ነበር። የኢንተርፕራይዙ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አያሌው በየነ በጉዳዩ ላይ በሰጡን ማብራሪያ በቀድሞው አጠራሩ የደቡብ ብሔር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል አሁን ወደ አራት ክልልነት የተከፋፈለውን ሁሉንም ይዞ በሚመራበት ጊዜ የተለያዩ ከፍተኛ አመራሮች ወደ ሃዋሳ ሲመጡ የነበረውን የመጠለያ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት አፓርትመንት እንዲገነባ በወቅቱ በነበረው የክልል መንግስት ውሳኔ ተሰጥቶ ከላይ በተገለጸው ሳይት ላይ ባለ 6 ወለልና አንድ ተጨማሪ ህንፃ እንዲገነባ መወሰኑን ያብራራሉ።
እሳቸው የሚመሩት የክልሉ ቤቶች ኢንተርፕራይዝ ደግሞ የመንግስት ተቋም እንደመሆኑ ፕሮጀክቶችን በድርድርም ሆነ በጨረታ እየወሰደ እንዲሰራ በሚፈቅድለት የህግ ማዕቀፍ አማካኝነት ይህ ፕሮጀክት በክልሉ ቤቶች ልማትና ኮንስትራክሽን እንዲሰራ ተወስኖ በ2009 ዓ.ም አሰሪያችን በቤቶች ልማትና ኮንስትራክሽን ስር የቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲ በሚባል ክፍል ወደውለታ መግባታቸውን ይናገራሉ።
በወቅቱ ፕሮጀክቱ አስቸኳይ ስለነበረና ቶሎ መድረስ ስለነበረበት ጠንካራና የተሻሉ ተቋራጮች በሚመለከተው አካል ተመልምለው አሸናፊው ተቋራጭ እንዲገነባ በቦርዱ በተላፈው አቅጣጫ መሰረት ለአለምሰገድ ጠቅላላ ህንጻ ሥራ ተቋራጭ ድርጅት ንዑስ ኮንትራት መስጠታቸውን ተናግረዋል።
በዚህ ሂደት የሲዳማ ክልል ሆኖ ሲወጣ በሲዳማ ክልል ያሉ የመንግስት ፕሮጀክቶች ግንባታዎች ባሉበት እንዲቆሙ ትዕዛዝ መተላፉን ተከትሎ ኢንተርፕራይዙም ለንዑስ ተቋራጩ ግንባታቸውን ባለበት እንዲያቆም በደብዳቤ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውንም ስራ አስኪያጁ ነግረውናል።
ይሁን እንጂ ተቋራጩ ዲያስፖራ ፕሮጀክቱ ባለቤት አግኝቶ ከዛሬ ነገ ይጀምራል በሚል ተስፋ ወደ ኢንተርፕራዙም ሆነ ወደ ሌሎች ቢሮዎች ሲመላለሱ መቆታቸውን አስታውሰው፣ የሁለቱን ክልሎች የሀብት ክፍፍል የሚያስፈጽም የሀብት ክፍፍል ፕሮጀክት ጽ/ቤት መቋቋሙንና የጽ/ቤቱ የቴክኒክ ኮሚቴ ይህ ፕሮጀክት ባለበት ሁኔታ ርክክብ እንዲደረግ መወሰኑን አቶ አያሌው ተናግረዋል።
ሆኖም ባለሀብቱ “ካሳ ካልከፈላችሁ በህግ እጠይቃለሁ። ውሳኔ ሳትሰጡ በመቆየታችሁ ወደ 33  ሚሊዮን ብር ኪሳራ ደርሶብኛል ካሳ የመጠየቅ መብት አለኝ” የሚል ቅሬታ ማቅረባቸውን ያስታወሱት የኢንተርፕራይዙ ዋና ስራ አስኪያጅ “በወቅቱ ፕሮጀክቱ ከእኛ እጅ ወጥቶ ስለነበር ውሳኔ መስጠት አልቻልኩም” ካሉ በኋላ የተቋራጩን ቅሬታ የቴክኒክ ኮሚቴው አብሮ እንዲያይለት ሁለቱ መንግስታት በሁኔታው ላይ ተነጋግረው ምላሽ እንዲሰጡና ውሳኔ እንዲያገኝ የሚል ሪፖርት ለሀብት ክፍፍል ፕሮጀክት ጽ/ቤት የቴክኒክ ኮሚቴ ማቅረባቸውን ተናግረው ከዚህ በላይ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ መስጠት እንደማይችሉ ገልጸውልናል።
ቀደም ሲል 5 ሺህ ካሬ ሜትር ተረክበውና ከሁለቱ 60 አባወራ ከሚያስተናግዱ ቅንጡ አፓርታማዎች በተጨማሪ ክሊኒክና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን ለማሟላት ታቅዶ የነበረው ቦታ ተሸርፎ ተሸርፎ 2 ሺህ ካ.ሜትር ብቻ እንደቀረ የገለጹት ተቋራጩ  እስካሁንም ውሳኔ ባለማግኘቱ አሜሪካ ያሉ ሌሎች ስራዎቻቸውን፣ ቤተሰባቸውንና ሌሎች ጉዳዮቻቸውን ትተው ከቢሮ ቢሮ እየተንከራተቱ ለከፍተኛ የገንዘብ፣ የጊዜና የሞራል ኪሳራ መዳረጋቸውን ገልጸው የክልሉም ሆነ የፌደራል መንግስት ጉዳዩን ተመልክተው ውሳኔ እንዲሰጧቸው ጠይቀዋል።
ዲያስፖራው አክለውም “መንግስት የሚያደርገውን ጥሪ ተከትሎ በሀገሩ ኢንቨስት ለማድረግ የሚመጣውን ዲያስፖራ ተስፋ የሚያስቆርጥ ተግባር መከናወን የለበትም ለሀገርም አይበጅም ኪሳራው የደረሰው እንደግለሰብ በኔ ላይ ብቻ ሳይሆን በሀገርም በመሆኑ አስቸኳይ እልባት ይሰጠኝ” ሲሉ በምሬት ጠይቀዋል።
እኛም ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ያልናቸውን የሲዳማ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ኃላፊዎችና የሀብት ክፍፍል ፕሮጀክት ኃላፊዎችን ለማነጋገር በአካል በመገኘትም ሆነ በተደጋጋሚ ስልክ በመደወል ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ ባለመሳካቱ ምላሻቸውን ማካተት አልቻልንም።

Read 1574 times