Saturday, 01 April 2023 20:22

የቢሊዮን ዶላር ኮንሰርት -የታይለር ስዊፍት!

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

 በሙዚቃው አለም፣ በዘፈኖች አልበም፣ በሽያጭና በሽልማት አዲስ ታሪክ መስራት፣ ሪከርዶችን መስበር፣ ለታይለር ስዊፍት፣ የሕይወት ዘመን ገጠመኝ አይደለም። በየዓመቱ ከእስከ ዛሬው የላቁ ከፍታዎች ላይ አዳዲስ ታሪኮችን ትሰራለች፡፡
በአልበምና በዘፈኖች ሽያጭ የቢልቦርድ ሰንጠረዥ የዘወትር ቤተኛ ናት፡፡ በተወዳጅ ስራዋ እንደ ዓውደ ዓመት በግራሚ ሽልማት ስሟ ሳይጠራ፣ የክብር ዋንጫ ሳታነሳ አያልፍም፡፡ አንዳንዴም ከግማሽ ደርዘን በላይ ሽልማቶች ትታቀፋለች። ምርጥ ዘፋኝ፣ ምርጥ አልበም፣ ምርጥ ዘፈን እየተዘረዘረ፡፡
በቅርቡ ጥቅምት ላይ ያወጣችው አልበም፣ ያው… እንደተለመደው ተወዳጅነትን አግኝቷል፡፡ በሽያጭ የቢልቦልድ ሰንጠረዥ አናት፣ የታይለር ስዊፍት ዙፋን ሆኗል፡፡ ከሌሎች አልበሞች ስለበለጠ ብቻ አይደለም፡፡ እስከዛሬ ታይቶ በማይታወቅ ፍጥነት በብዛት ስለተሸጠም ነው፡፡ተወዳጇ ዘፋኝ ባለፈው ሳምንት ደግሞ ሌላ አዲስ ታሪክ ሰርታለች፡፡
በስድስት ወራት 52 ግዙፍ የሙዚቃ ድግሶችን (ኮንሰርቶችን) በአሜሪካ ከተሞች ለማቅረብ ሀ ብላ ጀምራለች፡፡
በአዳራሾች ቢሆን ብዙም አያስቸግርም።በቂ ተመልካች ይኖራል።
የስታዲየም ኮንሰርት ግን፣ ሁለት ሶስት ዘፋኞች ካልተጋገዙ በቀር፣ ለአንድ ዘፋኝ ከባድ ነው፡፡ ለሙዚቃው ዓለም ከዋክብት ብቻ፣ ለገናናዎቹ በጣት ለሚቆጠሩት ለዝነኞቹ ለጥበብ እመቤቶችና ጌቶች ብቻ ነው የስታዲዮም ኮንሰርት፡፡
ስታዲዮሙ ከአፍ እስከ ገደፉ ጢቅ ብሎ ካልሞላ፣ መንፈሱን ያደበዝዘዋል፡፡10ሺ ሰው ለአዳራሽ ከበቂ በላይ ሊሆን ይችላል።ለስታዲየም ግን፣የመራቆት ያህል ነው። ድምፃቸውን ውጦ ጭር በሚያሰኝ በረዶ መንፈስ የሙዚቃውን ስሜት ያኮማትረዋል። የስታዲየም ኮንሰርት የሚደምቀው የሚሞቀው፤ ከሙዚቃና ከአቀራረቡ ጋር፣ ዳር እስከ ዳር በተመልካች ሲጥለቀለቅ ነው።               የሙዚቃ አፍቃሪ እንዲያ እንደማእበል የሚጎርፍላቸው ዘፋኞች ጥቂት ናቸው፡፡
ታይለር ስዊፍት ‹‹የዘመናት ጉዞ›› ብላ በሰየመችው የኮንሰርቶች ድግስ የመጀመሪያውን ትርኢት ስታቀርብ፣…ምን ጥያቄ አለው? ስታዲዮሙ ከጫፍ እስከ ጫፍ ሞልቷል፡፡
እንዲያውም፣ የመግቢያ ትኬት አለቀ፤ ቦታ የለም ተብሎ የቀረ ብዙ ነው፡፡ አንድ ቲኬት በ750 ዶላር… (በባንክ ምንዛሬ ከ40 ሺ ብር በላይ መሆኑ ነው)፡፡ ያው፣ የአስር ዓመት ልጇዋንም ይዛ ኮንሰርቱን ለማየት ተጨማሪ የ350 ዶላር ትኬት እንደገዛች ትገልፃለች አንዷ አድናቂ፡፡ ባለቤቷ ግን፣ ወጪው ቀላል አይደለም ባይ ነው፡፡ እናትና ልጅ፣ ኮንሰርት ለማየት 1100 ዶላር..( በገበያ ምንዛሬ መቶ ሺ ብር በሉት!)፡፡ እናም፣ ልጃቸው ይህን ታሪክ መቼም እንዳይረሳ አባትዬው ብዙ ተጨንቆ ለማስረዳት ሞክሯል፡፡
ለእናትዬው የጨነቃት ደግሞ ሌላ ነው፡፡ የሙዚቃ ድግሱ ረጅም ነው የሶስት ሰዓት። በዘፈን ብዛት እንደ ሁለት ኮንሰርት ነው። ስታዲየም ለመሄድና ለመግባት ሁለት ሰዓት፣ ለመውጣት አንድ ሰዓት ይፈጃል።
ታይለር ስዊፍት ተከታታይ ኮንሰርቶችን ከአምስት ዓመት በፊት በየከተማው አሳይታለች፡፡ ሌሎች ዝነኛ ዘፋኞችም በየፊናቸው በየስቴዲዮሙ ዘፍነዋል፡፡
የዘንድሮው የታይለር ስዊፍት ኮንሰርት ግን ይለያል፡፡ እንደዚህ ታይቶ አይታወቅም፡፡ አንድ ዘፋኝ ከ3 ሰአት በላይ ፣ በአንድ መድረክ 44 ዘፈኖችን፣ የሚያቀርብበት ኮንሰርት፣… ካሁን በፊት አልታየም ይላል የዎልስትሪት ጆርናል ዘገባ፡፡
ታሪከኞቹ የሮክ ከዋክብት እነ ቦብ ዳይለን፣ እና ብሩስ ስፓሪንግስተን፣ በረዣዥም ኮንሰርቶች በየፊናቸው አድናቂዎቸውን በዘፈን በማንበሽበሽ ይታወቃሉ፡፡ ነገር ግን በዛ ከተባለ፣ በአንድ መድረክ 30 ዘፈን ነው፡፡
ይህን ሪከርድ የሰበሩ፣ ፕሪንስ እና ቢዮንሴ ናቸው፡፡ በተከታታይ ኮንሰርት፣ በየመድረኩ በአማካይ 32 ዘፈኖችን በማቅረብ ተመልካች አድማጮቻቸውን አጥግበዋል፡፡ ታይለር ስዊፍት፣ በ44 ዘፋኞች መጣች፡፡ በዚያ ላይ፣ በመሀል አንድ ሁለቴ የእረፍት ጊዜ፣ በሙዚቃ መሳሪያ ብቻ ወይም በዲጄ ብቻ የሚደመጥበት ፋታ የለም፡፡ ሶስት ሰዓት ሙሉ ዘፈኟ መድረክ ላይ ናት፡፡ 10 ጊዜ ልብስ ትቀይራለች። ግን በሴኮንድ ነው። የእስከዛሬውን የኮንሰርት ታሪክ በረዥም ርቀት የሚያስከነዳ አዲስ ታሪክ እንደሆነ ሲገልፁ፣… ለዚያውም፣ ሂል ጫማ ነው ያደረገችው በማለት የመገረም አስተያየታቸውን አክለውበታል፡፡
ሁለት ኮንሰርት በአንድ ጊዜ እንደመስራት ነው ብለውታል፡፡ በዳንስ የደመቀ ነው፡፡ ከመድረኩ ግራ ቀኝ እየተመላለሰች ታዳሚዎቿን ታዝናናለች፡፡ ይሄ ብቻውን የሁለት ኪሎሜትር መንገድ እንደ ሆነ ተገልጿል። መድረኩ ላይ ወዲህና ወዲያ የምትራመደውን ቆጥረው ደምረው አስልተውታል።
በየሳምንቱ ሁለት ወይም ሶስት ቀን እስከ ነሐሴ ድረስ 52 ኮንሰርቶችን በዚህ ሁኔታ ትወጣዋለች ወይ ነው ጥያቄው፡፡
እንግዲህ፣ ጀምራዋለች፡፡ በጣም ሃብታም በጣም ዝነኛ የመሆኗ ያህል፣ በጣም ታታሪ ናት፡፡ አልበም ባወጣች ቁጥር በቢልቦርድ ሰንጠረዥ አንደኛ መሆኗ ብቻ ስኬትዋን ይናገራል፡ ነገር ግን፣ በአንድ ሳምንት ውስጥ ከሚሊዮን በላይ አልበሞችን በመሸጥ፣ እሷን የሚስተካከል አልተገኘም፡፡ አምስት አልበሞቿ የዚህ ማእረግ ባለቤቶች ናቸው፡፡
ምናለፋችሁ በአልበም ሰንጠረዥ ማንም ያልደረሰባቸው ታሪኮችን ሰርታለች፡፡
አሁን ደግሞ፣ በአሜሪካ በስድስት ወራት በ52 ቀናት በኮንሰርት ከ700 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ታገኛለች ተብሏል፡፡ አብዛኛው ቲኬት ገና ድሮ ተሽጦ አልቋል፡፡ የሌሎች አገራት ሲጨመርበት አንድ ቢሊዮን ዶላር ይሻገራል፡፡ ይሄ አዲስ ታሪክ ነው ተብሎለታል።
አስገራሚው ነገር፣ ብዙ የኪነጥበብ ምሁራንና አፍቃሪዎች፣ ታይለር ስዊፍትን በዘፋኝነቷ ብቻ ሳይሆን፣ ይበልጥ ደግሞ በግጥምና በዜማ ደራሲነቷ ያደንቋታል። እንዲያውም፣ በዘመኗ ከመሰሎቿ ልቃ የወጣች በግጥምና በዜማ ፈጠራዎቿ የደመቀች ጥበበኛ ናት ይላሉ አድናቂዎቿ። ከአዲስ አልበሟ፤ ከአንድ ዘፈኗ፣ ጥቂት ስንኞችን በማየት እንጨርሳ።
 “Midnight Rain”
…My town was a wasteland
Full of cages, full of fences
Pageant queens and big pretenders
But for some it was paradise
My boy was a montage
A slow motion, love potion
Jumping off things in the ocean
I broke his heart ‘cause he was nice
He was sunshine
I was midnight rain…
It came like a postcard
Picture perfect shiny family
Holiday peppermint candy
But for him it’s every day
So I peered through a window
A deep portal, time travel
All the love we unravel
And the life I gave away…
‘Cause he was sunshine
I was midnight rain
He wanted it comfortable
I wanted that pain
He wanted a bride
I was making my own name
Chasing that fame
He stayed the same…


Read 1056 times