Saturday, 08 April 2023 19:37

ሳህሉ ቢጠፋ አብረን በላን

Written by 
Rate this item
(4 votes)

ከእለታት አንድ ቀን አንድ አንበሳ፣ አንድ ነብር፣ አንድ ጅብ እና አንድ አህያ ችግር ገጥመዋቸው ተሰባስበው ሁኔታውን ለመገምገም ይቀመጣሉ፡፡ የውይይታቸው ርዕስ ‹‹አገሩን ለምን ድርቅ መታው? ዝናብ ለምን አቆመ? ምግብስ ለምን እጥረት ገጠመን?›› የሚል ነበር፡፡ በተደጋጋሚ፤ ‹‹እንዲህ እየተሰቃየን እስከ መቼ እንቆያለን? ያለ ምግብስ በባዶ ሆድ እንደምን ይዘለቃል?›› ይሉ ጀመር፡፡
ከመካከላቸው አንዱ አንድ ሀሳብ ሰነዘረ፡፡
‹‹ምናልባት እኮ ከእኛ መሀል ሀጥያት የሰራ ይኖር ይሆናል፡፡ በዚህ ምክንያት እግዚሀር ለቅጣት የፈረደብን ፍርጃ ሊሆን ይችላል፡፡ አይመስላችሁም?›› ሲል ጠየቀ፡፡
‹‹እውነት ነው›› አለ ሌላኛው፡፡ ‹‹ምናልባት ሁላችንም የሰራነውን ሀጥያት ብንናዘዝና እግዚያብሄርን ይቅርታ ብንጠይቅ ይሻላል፡፡›› በሚል ሀሳብ ሁሉም ተስማሙና  አንበሳ ኑዛዜውን ማሰማት ጀመረ፡፡
‹‹ወንድሞቼ በጣም የሚፀፅተኝን አንድ ሀጥያት ፈፅሜያለሁ፡፡ አንድ ጊዜ አንድ ወይፈን መንደር ውስጥ አግኝቼ፣ ወገቡን በክርኔ ሰብሬ አንድም አጥንት ሳላስቀር በልቼዋለሁ፡፡ ለዚህም ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡››
ሌሎቹ እንስሳት ኑዛዜውን ካዳመጡ በኋላ የአንበሳን ሀይለኝነት ስለሚያውቁና ስለሚፈሩ እራሳቸውን በአሉታ ነቀነቁና፤
‹‹የለም አቶ አንበሳ፤ በጭራሽ ጥፋት አልፈፀምክም፡፡ የሰራኸው ስራም ምንም ሀጥያት የለበትም! እግዚሀር እንድትፈፅም የሚፈልገውን ተግባር ነው ያከናወንከው›› አሉት፡፡
ቀጥሎ ነብሩ ተናዘዘ፤
‹‹ወንድሞቼ፤ በጣም አዝናለሁ፤ እጅግ የሚፀፅተኝን አንድ ሀጥያት ሰርቻለሁ፡፡ ይኸውም አንድ ቀን አንድ ሸለቆ ውስጥ አንድ ከከብቶች ተነጥሎ የሚንከራተት ፍየል አግኝቼ፣ ቁጥቋጦ ውስጥ አድፍጬ ቅርጭምጭም አድርጌ በልቼዋለሁ፡፡ ለዚህም እግዚሀርን ይቅርታ እጠይቃለሁ›› አለ፡፡
ሌሎቹ እንስሳት የነብርን የአደን ችሎታ አድንቀው ሲያበቁ፤ ‹‹በጭራሽ ሀጥያት አልፈፀምክም አቶ ነብር፡፡ እንዲያውም ያንን ፍየል ባትበላው ኖሮ እግዚሀር ይቆጣ ነበር›› አሉት፡፡
ቀጥሎ ተራው ያያ ጅቦ ነበር ‹‹እኔ ሀጥያተኛ ነኝ ወንድሞቼ›› ሲል ጀመረ፡፡ ‹‹አንዴ አንዲት ትንሽ መንደር ውስጥ ገብቼ አንዲት ዶሮ አግኝቼ ቅርጥፍጥፍ አድርጌ በልቻታለሁ››
እንስሳቱም፤ ‹‹ይሄ በጭራሽ ሀጥያት አደለም፡፡ እንዲያውም እግዚሀር ደስ የሚለው ሁለት ሦስቱን ብትበላቸው ነበር›› አሉት፡፡
ለመጨረሻ አህያ ኑዛዜዋን አሰማች፡-
‹‹ከእለታት አንድ ቀን ጌታዬ ጭነት ጭኖብኝ እየነዳኝ ሳለ፤ አንድ ጓደኛውን አግኝቶ ቆም ብሎ መጨዋወት ጀመሩ፡፡ እኔ ሆዬ የመንገዱ ዳር ዳር እያልኩ አጎንብሼ እዚያ ያገኘዋትን ትንሽ ሳር ስግጥ ቆየሁ፡፡ ይሄንን ሀጥያት ሰርቻለሁ ወንድሞቼ፡፡ ለዚህም እግዚሀርን ይቅርታ እጠይቃለሁ›› አለች፡፡
ሌሎች እንስሳ አህያን ተመለከቷት። አህያን የሚፈራትም ሆነ የሚያደንቃት ማንም የለም፡፡ ከጥቂት ጊዜ ቆይታ በኋላ ሁሉም እራሳቸውን ነቀነቁና፤
‹‹ይሄ በአለም ላይ ከተሰሩ ሀጥያቶች ሁሉ እጅግ በጣም የከፋው ነው፡፡ በሀገራችን ላይ ለሚደርሰው ስቃይና መከራም ዋናው ምክንያት ያንቺ ሀጥያት ነው፡፡ ቀንደኛዋ ሀጥያተኛም አንቺ ነሽ!›› በሚል ወነጀልዋት፡፡
ስለዚህም አንበሳ፣ ነብርና ጅብ ዘለው አህያይቱ ላይ ሰፈሩባት፡፡ አንድም አጥንት ሳያስቀሩ ተቀራመቷት፡፡ ሚስኪኗ አህያ  በዚህ ሁኔታ ተሰዋች፡፡
***
ለግፍ ከዚህ ወዲያ ምሳሌ የለም፡፡ ሀይለኛ ይፈራል፡፡ ሀይለኛ ይደነቃል ሀይለኛ የሰራው ስራ ሁሉ እንደ ትክክል ይወሰድለታል፡፡ ሀጥያት መፈፀሙም ቢታወቅም እንደ ፅድቅ ስራ ይቆጠርለታል፡፡ ውይይቶች እና ግምገማዎች ሁሉ የሱን ንፅህና፣ የእሱን ብፅእና የሚያረጋግጡ እንዲሆኑ ይደረጋል፡፡ በዚህም ምክንያት ደካሞች የሀይለኞች ሲሳይ እንደሆኑ ይኖራሉ፡፡ ደካሞች ምንም አይነት ቅን አገልገሎት ቢሰጡም፣ ምንም አይነት ሸክም ቢሸከሙም ድካማቸው ሁሉ እንደ ከንቱ ተቆጥሮ እንዲያውም ሀጥያተኛ ነው ተብሎ እርምጃ ይወሰድባቸዋል፡፡ የሰሩትን መልካም ነገር ሁሉ እንደ ሀጥያት ይናዘዛሉ፡፡ ከዚያም ይሰዋሉ፡፡ ከዚህ ወዲያ ጭቦኛ ስርአት የለም፡፡ ከዚህም ወዲያ ግፍ አይኖርም፡፡ በሀገራችን ሀይለኞች ተፈጥረው አይተናል። ሀይለኞች ደካሞች ላይ ግፍ ሲፈፅሙም አይተናል፡፡ እንዲህ ባለው ሁኔታ፤ ዲሞክራሲም፤ ሰላምም፤ እድገትም ሊመጣ እንዳልቻለና እንደማይችልም ተገንዝበናል፡፡ አስገራሚው ነገር፤ ደካሞች ሁሉ ከተሰዉት ደካሞች አለመማራቸው ነው፡፡ ሌላው አስገራሚ ነገር፤ ደግሞ ሀይለኞች ሁሉ ከሌሎች ሀይለኞች ታሪክ አለመማራቸው ነው፡፡
ሀይለኞቹ፤ ‹‹ከዚህም ወዲያ አኩሪ ድል የለም›› ብለው እንዲያስቡ የሚያደርጋቸው፡፡ ምናልባትም የደካሞቹ ከተሰውት አለመማር ሳይሆን አይቀርም። በግፍ የሚገኝ ማናቸውም ነገር የኋላ ኋላ ግፍ መሆኑ መረጋገጡም አይቀርም፡፡ የኋላ ኋላ ማስጠየቁ አይቀርም፡፡ እስከ ዛሬ በታሪክ የታየውም ይኸው ሀቅ ነው፡፡
በአንድ ወቅት በአዲስ አበባ ወህኒ ቤት ታስሮ የነበረ አንድ እብድ፣ ጠዋት መናገር የጀመራትን አንድ አረፍተ ነገር ቀኑን ሙሉ ሲደጋግማት ይውል ነበር፡፡ ሰው የማይረዳለት ስለሚመስለው ይሆናል፡፡ ወይም በሌላም እብደታዊ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ ከነዚህ ከሚደጋግማቸውም አባባሎች መካከል፤ ‹‹ሞኝ ያስራል ብልጥ ይማራል›› የሚል ነበረበት፡፡ ግፍ የሚፈራ ሞኝ ነው፡፡ ግፍ የተሰራበት ደግሞ ከተማረ ብልጥ ነው፤ ማለት ነው፡፡ ዋናው ማማሩ ነው፡፡ ግፍ የሚፈፅም ሹም፣ አለቃ፣ የአለቃ ቀኝ እጅ፣ ቡድን፣ ፓርቲ ወይም መንግስት ይዋል ይደር እንጂ የእጁን ያገኛል፡፡ መጨረሻው አያምርም፡፡ ‹‹የሚደርቅ ውሀ ውሻ ይበላል›› እንደሚባለው በትንሽ በትልቁ ማኩረፍ፣ መቆጣት፣ ዘራፍ ማለት፣ ማስፈራራት እና ‹‹እርምጃ እወስዳሁ!›› ማለትን ይደጋግማል፡፡በአንድ አገር ጭቦና እኩይ ተግባር፣ ሙስናና ዘረፋ ከበረከተ ቋንቋ ለቋንቋ መጠፋፋት ግድ ይሆናል፡፡ አንዱ በቀኝ የተናገረው ለሌላው ግራ ይሆናል፡፡ መደማመጥ ይጠፋል፡፡ ባለ አንድ አቅጣጫ መንገድ (one way road) እንዲሉ፣ በዚህ በኩል ብቻ ሂዱ ማለት ይበዛል፡፡ ጉዞ ሁሉ ‹‹የተከለከለ መንገድ›› የሚል ፅሁፍ እና መፈክር ይበረክትበታል፡፡ ህዝብ እራስ አቀፍ (Self-censorship) ስርአትን ያዘወትራል፡፡ አለቃው የሚናገረው ለምንዝሩ ካለመግባቱም ሌላ አለቃ እና አለቃ እንኳ በአንድ ልሳን መነጋገር ይሳናቸዋል፡፡ ‹‹መልካም ጋብቻ ይሁንልህ!›› ቢለው ‹‹እግዜር ነው እንዲህ ያደረገኝ!›› ይላል፤ እንደተባለው የወላይታ ተረት መሆኑ ነው፡፡ አዩ ሌላ ወዮ ሌላ ነውና የተዘበራረቀ አሰራር ይሰፍናል፡፡ አቃጅና ፈፃሚ በተለያየ መንገድ ይሄዳሉ፡፡ ይገኛል የተባለው ውጤት፤ እናፈራለን የተባለውን ፍሬ፣ ወይ ጥሬ ይሆናል ወይ ይረግፋል፡፡ለዚህ ጥፋት ወይም ሀጥያት ደግሞ ባለተራ፤ ‹‹ይሰዋል››፡፡
ከቶውንም ዲሞክራሲያውነት የጎደለው እና ጭቦ የበዛበት ስርአት ካለ ግልደፅነት ዘበት ነገር ነው፡፡ ግልፀኝነት ከሌለ ደግሞ የሚሰራው ከማይሰራው፣ ግፈኛው ከቀናው፣ አምራቹ ከአውዳሚው፤ ሀቀኛውና አዋቂው ከአስመሳዩና ከደንቆሮ የሚለይበት ሚዛን ይጠፋል፡፡ ሚዛን አለ ቢባል እንኳ ይሸቅባል፡፡ አዳዲስ ኮሚሽን፣ ባለስልጣን፣ ኮሚቴ ይበዛል፡፡ ‹‹በኮሚቴ ቢወስን ኖሮ ሙሴ ቀይ ባህርን አያቋርጥም ነበር›› እንደተባለው ቁርጥ ያለ እቅድ፣ ቁርጥ ያለ መመሪያ፣ ዕቅጩነት ያለው ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማግኘት ከንቱ ድካም ይሆናል፡፡ መልካም ውጤት ሲጠፋ ተጠያቂ ይፈጠራል፡፡ በአድሎ ይፈረዳል፡፡ ‹‹ፋቂ ቆዳ መፋቅ ቢያቅተው ውሻ ይሰድባል›› እንዲል መፅሀፉ፤ አንደኛው ወገን ላይ ሀጥያቱም፤ ይደፈደፋል፤ ይደመደማል፡፡
የኢ-ዲሞክራሲያዊነት፣ የመልካም-አስተዳደር (good Governance ) እጦት፣ የፖለቲካ ቡድኖች ገዢ ተገዢነት ሹኩቻ፣ ወዘተ አንዱ እና ዋነኛው ምንጫቸው አለመተማመን ነው - ‹‹ከጀርባው ምን ይኖር ይሆን?›› የሚል ስጋት እና ጥንቃቄ። ‹‹ያጎረሰኝ እንዲያንቀኝ ፈልጎ ሊሆን ይችላል!›› የሚል አመለካከት ነው፡፡ ይህንን ሁሉ የጎሽ ሂደት ቀለል አድርገን ስንመለከተው እንግዲህ ወትሮውንም በፖለቲካው ጨዋታ ላይ የተሰለፉ ቡድኖች እና ግለሰቦች ከዋና ተጫዋቾች ይልቅ ተለዋጮች (Bench እንዲሉ መፅሀፈ ካምቦሎጆ) የበዙባቸው መሆኑንና በአለመተማመን  የሚጋዙ መበርከታቸውን እናስተውላለን፡፡ አለቃ አለቃን፣ ባለስልጣን ባለስልጣንን፣ ቡድን ቡድንን፣ ፓርቲ ፓርቲን የሚጠራጠርበት ሁኔታ ካለ ለማናቸውም እንቅስቃሴ ልባዊ አንድነት አይኖርም ማለት ነው፡፡ አብሮ መጋዝ ይቻላል እንጂ በአንድ ልብ ለመጓዝ አይቻልም፡፡ የይስሙላ እንጂ የልብ አንድነት አይኖርም፡፡ ቢቸግር ነው እንጂ ከአንድ ገበታ አይቆርሱም ማለት ነው፡፡ ‹‹ሳህን ቢበዛ አብረን በላን›› ማለት እንግዲህ ይሄው ነው፡፡
መጪው የህማማት ጊዜ ከራሳችን ጋር የምንጋገርበት፤ በጥሞና የምናሳልፍበትና ሃጢያታችንን የምንናዘዝበት ያድርልን። በተለይ ደግሞ ለፖለቲከኞቻችንና መሪዎቻችን።
ቅቱ ጥቅስ
‹‹ዛፍ ላይ ወጥቼ ልግደልህ፣ መሬት ሆኜ?›› ቢባል
‹‹ዛፍ ላይ ወጥተህ›› ብሎ መለሰ፡፡
‹‹ለምን?›› ቢለው፤
‹‹ዛፍ እስክትወጣ በህይወት እቆያለሁ…››
የወላይትኛ ምሳሌያዊ አነጋገር

Read 1348 times