Monday, 10 April 2023 00:00

ለምንድነው ቀውስ የበዛብን መፍትሄ የጠፋብን?

Written by  -ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)

በሰሜንና በደቡብ፣ በምስራቅም ሆነ በምዕራብ፣…በየቦታው የሚከሰተውን እዩ።  
በየእለቱ በየወሩ የሚፈጠሩ ቀውሶችንና ጥፋችን ተመልከቱ።
አብዛኞቹ ከዘረኝነት አስተሳሰብና ከብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ የሚመነጩ መዘዞች ናቸው። አንዳንዶቹ ሃይማኖትን ከፖለቲካ ጋር የማቀላቀል ጥፋቶች ናቸው።
ሌሎቹ ደግሞ፣ ኢኮኖሚን ከጉልበት ጋር የማቀላቀል ጣጣዎች ናቸው።
ከእነዚህ ውጭ የሚመጣ  የሀገር ውስጥ ቀውስ የለም። የሶስቱ ጥፋቶች የጋራ ባህርይ ደግሞ መርህ አልባነት ነው። እንደ እስስት የመሆን ምኞት አድሮብናል። ብልጥ የሆንን መስሎናል።
ውሎ የሚያድር፣ ከአንድ ቀን አልፎ የሚሰነብት፣ ወንዝ የሚያሻግር፣ በሁሉም ቦታ የሚያገለግል፣ ቅጥ የያዘ ሃሳብ ጠፍቶብናል።
የሕግ አዋጅና የፖለቲካ ሃሳብ እየተነተንን ትናንት ያልተፈላሰፍንባቸው ያህል፣ ዛሬ ከአእምሯችን የተፋቁ ያህል ከሃሳባችን እንሰርዛቸዋለን። ጨርሰው ከሰው አንደበት እንዲጠፉ እንመኛለን። ጭምጭምታ ከሰማንም አጣጥለን እናዳፍናቸዋለን።
ትናንት ያወቅነውን ለዛሬ እንዳይሰራ አንቋሽሸን ለማጥፋት መቅበዝበዛችን፣ እውቀታችንን የማምከን ዘመቻ እንደሆነ አይገባንም? ወይስ ግድ አይሰጠንም?…
በሰሜን ወይም በምስራቅ አቅጣጫ ለተፈጠረው ክስተት እንደዋና መከራከሪያ ያቀረብነው መርህ፣ በደቡብና በምዕራብ በኩል ለተመሳሳይ ጉዳይ እንዲያገለግል አንፈልግም። ጭራሽ፣ በተቃራኒ ሃሳብ እናፈርሰዋለን። ባይፈርስ እንኳ፣ በአእምሯችን ውስጥ ያፈራረስነው እስኪመስለን ድረስ እየደጋገምን እንሳደባለን።
እውቀትን እያመከንን፣ መርህን እያራከስንና በርቀት እያባረርን፤ እንደ አየር ሁኔታው (የየእለቱን ፊት እያየን)፣ ስሜታችን እየተዘበራረቀ፣ መልካችን ይቀያየራል። ረፋድ ላይ ከፀሐይዋ ጋር እየፈካ፣ ከቀትር በኋላ ከደመናው ጋር እየጠቆረ፣ እንደ ነፋሱ አቅጣጫ በስሜት መገላበጥን ተላምደናል።
ከስካር ከቅዠት አይተናነስም።
ለእያንዳንዱ ሰው፣ በየትኛውም የአገሪቱ አካባቢ ተወልዶ ላደገ፣ በመሃል አገርም ሆነ በጠረፍ ዳር ለሚኖር ሁሉ የሚያገለግል መርህ፣… እንዲያውም ለየትኛውም አገር ከልብ የምንመኘው ትክክለኛ መርህ፣… ማለትም ሁሉን አቀፍ መልካም የስነምግባር መርህ፣ እንዲሁም ከዚህ የሚመነጭ ትክክለኛ የፖለቲካ ሃሳብ ይዘናል?
ባንይዝ እንኳ፣ እንዲኖረን እንፈልጋለን?
እንዲያው ለመሆኑ፣ ሁሉን አቀፍ መልካም የስነምግባር መርሆችንና ትክክለኛ የፖለቲካ ሃሳቦችን መጨበጥ ይቻላል ብለንስ እናምናለን?
ወይስ፣ በአላዋቂነት አልያም በጠማማ ብልጣብልጣነት፣ ያለ መርህ፣ ያለ አንዳች የሃሳብ መልህቅ፣ በዘፈቀደ መደናበርና መቅበዝበዝን ነው የምንመርጠው? ከደቂቃ ደቂቃ፣ ከቦታ ቦታ እንዳሰኘን፣ ምስክርነታችንና ፍርዳችንን በቀላሉ እያገላበጥን ለመኖር ነው ወይ ምኞታችን?
“እውነት ነው ወይስ ውሸት” ብለን ለማጣራትንና ለማረጋገጥ የምንጥረው፤ የተናጋሪውን ዘር እየቆጠርን፣ የፓርቲውን ታርጋ እየለየን፣ የሃይማኖት ምልክቶችን እያየን ነው? የአማራ “እውነት”፣ የኦሮሞ “እውነት”፣ የትግራይ “እውነት”፣ የሶማሌ “እውነት”  እያልን “የእውነት ትርጉምን” ማጥፋት እንደ ጥሩ የፖለቲካ ዘዴ ሆኖ ይታየናል ወይ?
ዛሬ የሰላምና የእርጋታ ታማኝ ተቆርቋሪ፣ ሆነን እንታያለን። ባንሆን እንኳ መስለን እንሰለፋለን። ዛሬ የህግና የስርዓት “ፅኑ” አክባሪ ሆነን መናገርና መከራከር ያሰኘናል። መንገድ ተዘጋ ብለን እንኮንናለን። አገር በዘር እየተከለለ ዜጎች ተፈናቀሉ ብለን እናወግዛለን። ቤት ንብረት ተቃጠለ። ሰዎች ተገደሉ። በዘር መቧደን አገርን እያጠፋ ነው ብለን አምርረን እንቃወማለን። መልካም ነበር፡፡…
በሌላ ቦታ ወይም በማግስቱ ግን፣ ህግና ስርዓት፣ ጨርሶ እንደቁምነገር እንዳይቆጠርና እንዳይነሳ እንፈልጋለን። ከዚያም አልፈን፣ ሕግና ሥርዓትን፣ እንደ አፈና እንቆጥረዋለን። መንገድ የሚዘጉና ከአገር እስከ መንደር በዘር ለመከለል የሚቧድኑ ሰዎችን ስንመለከት፣… አላማቸውን እንደ ስህተት ተግባራቸውን እንደወንጀልና እንደ ጥፋት ሳይሆን እንደ ጀግንነት እናሞግሰዋለን።
 እንዲህ እንዳሻን የመናገርና የመፍረድ “ነጻነት” እንዲቀርብን አንፈልግም።
በእርግጥ አላዋቂነትም ያሳስታል። መርሆችን እንደየዓይታቸው አሟልቶና እንደየልካቸው አዋህዶ ለማገናዘብ ያልቻለ ሰው፤ በነጠላ መርሆችና በቅንጥብጣቢ ሃሳቦች መሃል እየተላተመ፣ ዛሬ የአንድ መርህ አቀንቃኝ፣ ነገ ደግሞ ይህን ጥሎ የሌላ መርህ ዘፋኝ ይሆናል።
ሕግን እያጣጣለ፣ የነጻነት አርበኛነቱን የሚያስመሰክር ይመስለዋል። ሌላ ጊዜ ደግሞ “ህጉ ተጽፏል” ይላል።
ነፃነትን እንደ ስርዓት አልበኝነት እየቆጠረ ያንቋሽሻል።
 ከሳምንት በኋላ ደግሞ፤ ለነጻነት ሲባል ሕገ-ወጥነት ያስፈልጋል እያለ ይሰብካል። መርህና ነጻነትን ሕግና ስርዓትን ያዋሃደ ትክክለኛ አስተሳሰብ ለመያዝ አይሞክርም፡፡
ምናለፋችሁ የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካን እየተቀለብን፣ የሃይማኖት ወይም የጉልበት ፖለቲካን እየተጋትን የስነ-ምግባር መርህ መያዝ አቅቶናል።
እንዲያውም ለመርህ ዋጋ መስጠት፣ የዋህነትና ሞኝት ይሆንብናል” ይልቅስ እንዳሰኘን በዘፈቀደ ለመደገፍና በጭፍን ለመቃወም፣… ሰበብና ማመካኛ እንደረድራለን።
አትዋሽ፣ የሰውን ሕይወትና ንብረት አትንካ የሚሉ የስነ-ምግባር መርሆች፣ መልካም መርሆች መሆናቸው ተረስቶ፣ ተቀናቃኝ ለማጥቃት የተነጣጠሩ የጥላቻ መሳሪያዎች ሆነዋል።
የዚህኛው ብሔረሰብ ተወላጅ፣ የወዲህኛው ፓርቲ ፖለቲከኛ፣… እውነትን ቢክድ፣ የሐሰት ውንጀላ ሲፈበርክ ቢውል ችግር የለውም፡ ለበጎ አላማ ነው ብለን እንደግፈዋለን። ወይም እንደ ጥበብ እንደ ችሎታ ይቆጠርለታል። ህይወት ሲያጠፋና  ንብረት ሲያወድም እንኳ፣… ጥፋት ሰርቷል አይባልም። በሰበብና በማመካኛ ብዛት፣ የክፋት ተግባሩ በይሁንታ ይታለፍለታል።
የስነምግባር መርህና የሕግ ሥርዓት፣ በተቀናቃኝና በሚጠሉት ሰው ላይ ብቻ እንዲሰሩ ነው ምኞታችን? እንደ ሸክም እንደ እስርና ጉዳት ሆነው ነው የሚታዩን- መርህና ሥርዓት። እውነትን አስክደን በውሸት ለውጠን፣ ውሸትን ቀባብተን እውነት እንደሆነ አስመስለን፣ እንዳሻን እንደፈቀድን እንዳንናገር የሚያግድ አስሮ የሚያስቀር ሆኖ ይታየናል-መርህ ማለት።
ህግና ስርዓት ሌሎች ፓርቲዎችን ጠልፎ ለማስቀረትና ለመቅበር የሚያገለግል  ወጥመድ እንዲሆንልን እንመኛለን። የምንደግፈው ፓርቲ ግን፣… ህግና ስርዓት የማይገዛው፣ በተቃራኒው እንዳሻው እንዲጋልብበት ነው ምኞታችን።

Read 1260 times