Saturday, 08 April 2023 19:44

ከሶሻል ሚዲያ በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በእውቀቱ ስዩም)
ማዳበርያ

 እንደ ድሮው ብዙ  የሰውነት እንቅስቃሴ አላደርግም፤  ሲነሽጠኝ፥ በሁለት ሳምንት አንድ ቀን ዢም ( gym) እሄዳለሁ፤ ወደ አዳራሹ እንደገባሁ  አሰልጣኙ ሳያየኝ ፥ ኮቴየን  “ ሳይለንሰር “ ላይ አድርጌ፥  ወደ ጥግ ሄድኩና የመጨረሻውን ሚጢጢ ዳምቤል አነሳሁ፤  ዳምቤሉ ከማነሱ የተነሳ   ሁለት ራስ ያለው ትልቅ ቢስማር ነው እሚመስለው! ብዙም አልቆየም፤ የሆነ ድርብ ጭቆና የሚያህል መዳፍ   ትከሻዬ ላይ ወደቀ፤  ዞር ስል አሰልጣኙ ነው፤ እኔን ለማሰልጠን ሳይሆን ለማሰቃየት የተመደበ ነው እሚመስለኝ::  
“ብረት ከማንሳትህ በፊት ማሟቂያ ስራ” ሲል አዘዘኝ::
 “ ምን ልስራ?”
ትንሽ ሲያስብ ከቆየ በሁዋላ እንዲህ አለ፥
“ግራ እግርህን  አንስተህ ፥ በማጅራትህ  በኩል አሳልፈህ ተረከዝህን  ሳም! “
እንደጀመርኩ አካባቢ ከጂሙ ሁለት ጊዜ በዊልቼር እየተገፋሁ ወጥቻለሁ::
 ሰባት ፑሽአፕ ሰራሁና ሰባት ደቂቃ ከመስታወቱ ፊትለፊት ቆምኩ፤ እዚህ ጂም መምጣት ከጀመርሁ ወዲህ  ለውጥ አለ፤ አንገቴ ዙርያ ሲክስ ፓክ አውጥቻለሁ፤  ጥቂት ቆይቶ፥  አሰልጣኙ “ ስኳት”  አሰራኝ!  ጂም ሄደህ ለማታውቅ አንባቢ፤  “ስኳት”  ማለት ሽንት ቤት ልትቀመጥ ፈልገህ ቁጢጥ ማለት ከጀመርክ በሁዋላ ሽንት ቤቱ መበላሸቱን አይተህ ሀሳብህን ፥ቀይረህ ከመንገድ ስትመለስ ማለት ነው::
   “ ስኳት ቢቀረብኝስ “ አልኩት የተንሸራተተ ዲስኬን ወደ ቦታው እየመለስኩ::
  “ የግድ አስፈላጊ ነው” አለኝ አሰልጣኙ፤
 “ምን ያደርግልኛል!”
“ እግርህንና መቀመጫህን ያዳብረዋል”
“ እግሬን ከመቀመጫዬ  ነጥሎ እሚያዳብር ስፖርት የለም?”
 “ የለም!“ አለኝ ኮስተር ብሎ፤” ተያያዥ ስለሆኑ አብረው ነው እሚዳብሩት!“
 ስተክዝ እንዲህ ብሎ አጽናናኝ፤
 “ አትጨናነቅ! መቀመጫህን  ወደ ነበረበት ለመመለስ  በሚቀጥለው አመት  ሌላ ስፖርት እንሰራለን”
 እንቅስቃሴን ስጨርስ ገላዬን ታጠብኩ፤ ከዛ ብብቴን ወይባ ታጠንኩ፤ በአስር አመት ወደ ወጣትነቴ የተመለስኩ መሰለኝ! የሸሚዜን ሦስት ቁልፎች ፈታሁና ሩብ ደረቴን ለብርድና ለህብረተሰቡ እይታ አጋለጥኩት፤ ከ”ሮዛ”  የሞዴል  ማሰልጠኛ ለሻይ እረፍት  የወጡ ኮረዶች፤  “He is out of my league” በሚል አይነት እሚያዩኝ መሰለኝ፤  በዚህ ቅርጽ ላይ ትንሽ ዝነጣ ልጨምርበት ብዬ፥ እግሬን  በስታይል ፥ ጎተት አያደረግሁ መራመድ ጀመርኩ፡፡
  ግቢያችን በር ላይ ስደርስ ፥ ዘበኛው በአዘኔታ  ከንፈራቸውን አስጩኸው መጠጡና ፥
  “ሪህ ነው ልጄ?”

Read 1443 times