Saturday, 08 April 2023 19:45

የ”ኦፕራ ሾው” የምንጊዜም ተወዳጅ እንግዳ!

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ጥቁር አሜሪካዊቷ ኦፕራ ዊንፍሬይ፣ በአሜሪካ ከምንም ተነስተው፣ በራሳቸው ጥረትና ትጋት ቢሊየነር መሆን ከቻሉ እንስቶች መካከል አንዷ ናት፡፡ ፎርብስ መጽሄት እንደሚጠቁመውም፤ የኦፕራ ወቅታዊ የተጣራ የሃብት መጠን 2.46 ቢ. ዶላር ይገመታል፡፡
 ኦፕራ ለ25 ዓመታት ገደማ በስኬት በመራችውና ከፍተኛ ተወዳጅነት በነበረው “ኦፕራ ሾው” ላይ ለ35 ሺ ሰዎች ገደማ ቃለ-ምልልስ  ማድረጓን በከራት ትናገራለች፡፡
በቅርቡ ለኦፕራ ቃለ-ምልልስ  ያደረገላት አንድ ጋዜጠኛ፤ “የኦፕራ ሾው የምንጊዜም ተወዳጅ እንግዳ ማን ነው?” ሲል ጠይቋት ነበር፡፡
የዚህን ጥያቄ መልስ ለመመለስ ኦፕራ፣ በዝነኛው የኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጠኛ ኒኮላስ ክሪስቶፍ፣ የተጻፈውንና ያነበበችውን አንድ መጽሐፍ መጥቀስ ነበረባት፡፡ የታሪኩ ባለቤት አንዲት የዚምቧቡዌ ልጃገረድ ናት - ተዓምረኛ ልጃገረድ! ተወልዳ ያደገችው፤አግብታ የወለደችው እዚያው ዚምቧቡዌ ነው፡፡ ቴራይ ትባላለች፡፡
ቴራይ በልጅነቷ ከወንድሟ ጋር ት/ቤት ለመግባት ሳትታደል ነው ያደገችው፡፡ አባቷ ወንድ ልጃቸውን ት/ቤት እየላኩ፣ እሷ ግን ቤት ውስጥ ቀርታ እንድታገለግል ፈረዱባት፡፡  የሚያስገርመው ደግሞ ት/ቤት እየዋለ ለሚመጣው ወንድሟ፣ የቤት ሥራ የምትሰራለት እርሷ ነበረች - ትምህርቱ  እየከበደው፡፡
ቴራይ ገና በህጻንነቷ ነበር ባል እንድታገባ የተገደደችው - በ11 ዓመቷ  ግድም፡፡ በ18 ዓመት ዕድሜዋ የአምስት ልጆች እናት ነበረች፡፡ ልጅነቷን ሁሉ የሰጠችው ለሚስትነትና ለእናትነት ነው ቢባል ፍጹም እውነት ነው፡፡
በዚህ ጊዜ ነበር  ሄይፈር  የተባለ መንግሥታዊ  ያልሆነ ድርጅት ውስጥ የምትሰራ አንዲት ሴት ወደ እነ ቴራይ መንደር ጎራ ያለችው፡፡ ስለ ቴራይ በጥልቀት ካወቀች በኋላ፤”ህልምሽ ምንድን ነው?” ስትል  ጠየቀቻት። ከባድ ጥያቄ ነበር፤ ለቴራይ፡፡ ከዚያ ቀን በፊት ይሄንን ዓይነት ጥያቄ ተጠይቃ አታውቅም፡፡ በመጨረሻም፣ ከሄይፈር የመጣችው ሴት፣ ህልሟን በወረቀት ላይ እንድታሰፍር ትመክራታለች፡
ቴይራም  በተባለችው መሰረት፣ በብጣሽ ወረቀት ላይ ማሳካት የምትፈልገውን ግብ ትጽፍና፣ በትንሽዬ ጣሳ ውስጥ በመክተት፣ አንድ  ትልቅ ድንጋይ ሥር ትደብቀዋለች፡፡ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ቴይራ ራሷን ያገኘችው፣ ከአንድ የአሜሪካ ዩኒቨርስቲ በመጀመሪያ ድግሪ ስትመረቅ ነው፡፡
 በርግጥም የመጀመሪያ ግቧ አድርጋ የጻፈችው፣ከአሜሪካ ዩኒቨርስቲ የመጀመሪያ ድግሪዋን ማግኘት ነበር። ወደ ዚምባቡዌ ተመልሳ ሁለተኛ ግቧን በብጣሽ ወረቀት ጽፋ እዚያው ድንጋይ ሥር ወሸቀችው። የማስተርስ ድግሪዋን ከአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ ማግኘት ነበር -ሁለተኛው ግቧ፡፡ ይህንንም አሳካች። ሁለተኛ  ድግሪዋን ከአሜሪካ ዩኒቨርስቲ ተቀበለች። አሁንም ወደ ትውልድ መንደሯ በመመለስ፣ ሦስተኛውንና የመጨረሻውን ግቧን ጻፈች። በዚህ ጊዜ ደግሞ የዶክትሬት ድግሪዋን ለማግኘት ነበር ያለመችው። ባለፈው ዓመት ታዲያ ከአሜሪካ ዩኒቨርስቲ የፒኤችዲ ድግሪዋን አጠናቃ፣ ዶ/ር ቴራይ  ለመባል በቅታለች፡፡
ቴራይ በልጅነቷ የተከለከለችውን ትምህርት፣ እስክትጠግብ ድረስ በአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ተማረች፡፡ ትምህርት ሀ ብላ የጀመረችው እጅግ ዘግይታ በ18 ዓመቷ  ቢሆንም፣. እስከ ዶክትሬት ድግሪዋ ከመማር ያገዳት ምንም ነገር የለም፡፡ኦፕራ የዚህችን ወጣት አስደማሚ ታሪክ አንብባ ከጨረሰች በኋላ ነው፣ለቃለመጠይቅ ያፈላለገቻት፡፡ሆኖም በመላው አሜሪካ ተፈልጋ አልተገኘችም። በመጨረሻም አገሯ - ዚምባቡዌ እንዳለች ለማረጋገጥ ተቻለ፡፡
 ኦፕራ አውሮፕላን ተሳፍራ፣ ባህር ተሻግራ ዚምባቡዌ ገባች፡፡ በታሪክ  ብቻ የምታውቃትን ወጣት በአካል ተዋወቀቻት፡፡ ከዚያ በኋላ ነው በ”ኦፕራ ሾው” ላይ ቃለመጠይቅ ያደረገቻት።
ኦፕራ ዊንፍሬይ ቴራይን፤”የምንጊዜም ታላቅ እንግዳዋ” ያለችበትን ምክንያት ስትገልጽ፤ “እኔ ለ25 ዓመት በእያንዳንዱ ፕሮግራም ላይ ለተመልካቾቼና ተሳታፊዎቼ ስነግራቸውና ስመክራቸው የኖርኩትን ነው፣በዚህች ወጣት ታሪክ ውስጥ ቁልጭ ብሎ ያገኘሁት፡፡
 ሁሌም  ትችላላችሁ- ሙከራችሁን ቀጥሉበት፤ ፈጽሞ አታቋርጡ እያልኩ ነው ሳስተምር የኖርኩት፡፡” ብላለች፡፡በዚምባቡዌ  የተወለደችውና በገዛ አባቷ የትምህርት ዕድል የተነፈገችው ቴራይ፤  ዘግይቶም ቢሆን ህልሟን አሳክታለች - በሙሉ ልብ፣ በጥልቅ መንፈስ፣ በቁርጠኝነትና በዲሲፕሊን ተሞልታ!!


Read 1391 times