Saturday, 15 April 2023 20:12

“እድል”፣ “እጣ” እና “ፈንታ”… - በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

“መወለድ”፣ እንደ ፀሐይ፣ እንደ ዝናብ ነው። የብቃት ወይም የድክመት ውጤት አይደለም። ፀሐይ የሚወጣው፣ ዝናብ የሚወርደው፣… ለሁሉም ሰው ነው። መወለድም እንደዚያው። እገሌ፣ በራሱ ጥበብና ምርጫ አልተወለደም። እከሊት፣ በትጋቷና በበጎነቷ አልተወለደችም። በሞኝነትና በስንፍና ሳቢያ፣ “መወለድህ ተሰርዟል”፤ “መወለድሽ ቀርቷል” ብሎ ነገር የለም። ጥበብና ሞኝነት፣ ትጋትና ስንፍና፣ መልካምነትና ክፋት፣ የእኔነት ክብርና የግል ኃላፊነት፣… ከልደት በኋላ የሚመጡ የማንነት ገፅታዎች ናቸው።
በሌላ አነጋገር፣ የእገሌ ብሔር የእገሊት ብሔረሰብ ተወላጅነት አያሳፍርም፤ አያኮራም። ሃሳብን፣ ተግባርንና ማንነትን አያመለክትም። ለዳኝነት አይቀርብም - ለአድናቆትና ለሽልማት ይቅርና፣ ለወቀሳና ለክስ የሚሆን ነገር የለውም። እና፣ በሌለ ነገር ነው፣… ሰዎች በዘር እየተቧደኑ በጎራ እየተሰዳደቡ የሚወነጃጀሉት፤ ሰዎችን ለጥቃትና ለሞት፣ አገርን ለውድመትና ለትርምስ የሚዳርጓት። በሌለ ነገር መነዳትም ነው፣ ጭፍንነት ማለት። “ቅዠት” የሚለው ስያሜም ትክክለኛ ነው።
የጥንት ታሪክ አይለወጥም። ወደ ኋላ ተመልሰን ማበላሸትም ሆነ ማሻሻል አንችልም። በብዙ ዘመናት በእልፍ አእላፍ ሰዎች አማካኝነት እየተሸበላሸም ሆነ እየተሻሻለ የመጣ ነባር ባህል፣ ወደ ፊት ማሻሻል ይቻል እንደሆነ እንጂ፣ ወደ ኋላ ተመልሰን ልንቀይረው አንችልም። የድሮ ታሪክና ነባር ባህል፣ ለወደፊት ተግባር መማሪያና መነሻ ይሆናል እንጂ፣ መበሻሸቂያና መወነጃጀያ ሰበብ መሆን አልነበረበትም።
የድሮ ዘመን ሰዎች፣ የጥንታዊው ታሪክና ባህል ተዋናዮች፣… በአንዳች ተዓምር አፅማቸው ስጋ ለብሶ ቢነሳ እንኳ፣… አሁን የምናየው ያህል ጭቅጭቅና ንትርክ አይፈጥሩም ነበር። ባልነበርንበት ዘመንና ባልዋልንበት ቦታ፣ በባዶ መፎከርና የክስ እሮሮ ማንጋጋት ምንድነው? የጊዜ መንኮራኩር ሰርተው ወደ ጥንቱ ዘመን ተመልሰዋል እንዳንል፣ የዚያን ያህል እውቀትና ጥበብ ቢኖራቸው እንዲህ በከንቱ የጥላቻ መዓት ለመዝራት የሕይወት ዘመናቸውን የሚያባክኑበት የስድብና የውንጀላ ጊዜ ባልተረፋቸው ነበር።
ይልቅስ፣… በድሮ ታሪክና ባህል ሰበብ፣… ዛሬ ውንጀላና ጥላቻ የሚያራግቡት፣… የጥንት ዘመን ጉዳይ ስለቆረቆራቸው አይደለም። በዚያ ሰበብ ዛሬ በዘመናችን፣ ከድሮ የባሰ ጥፋትና ግፍ የመፈፀም ፍላጎትና ዝግጅት ነው ማለት ይቻላል።

+++++++++++++++++++++++++++

“እድል፣ እጣና ፈንታ”፣… በተለያየ ትርጉም የሚያምታቱና ለጭፍን አስተሳሰብ ተጋለጡ ቃላት መሆናቸው አያጠራጥርም። ነገር ግን፣ በምሳሌያዊ ዘይቤ ቁምነገረኛ ፍሬ ሃሳቦችን ለመጨበጥ መነሻ ቢሆኑልንስ? እስቲ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ጋር እያዛመድን እንያቸው።
እድል ማለት፣… ለክፉም ለደጉም፣ በጊዜውና በቦታው፣ ከናንተ ቁጥጥር ውጭ የሆነ ነገር ማለት ነው? ብትፈልጉም ባትፈልጉም፣ ወደዳችሁም ጠላችሁም፣ የሚለወጥ ነገር አይደለም ማለት ነው።
ወላጆቹን የሚመርጥ ሰው የለም። የመሬት ስበትን፣ በዲሞክራሲያዊ ምርጫ፣ በፓርላማ አዋጅ የመሻር ወይም የማፅደቅ፣ የስበት ኃይሉን የመቀነስ ወይም የመጨመር ስልጣን የለም።
ወደ ኋላ ተመልሶ ታሪክን ማስቀረትና መፍጠር፣ ማሻሻልና ማበላሸት የሚችልም የለም። ስለማይቻልም ነው፣ ለማስመሰል መከራቸውን የሚያዩት።
ካንተ ወይም ካንቺ ምርጫ ውጭ የሆኑ ነገሮች ብዙ ናቸው። የቢሊዮን ሰዎች የእለት ተእለት ውሳኔና ተግባር፣ ካንተ ጥረት ወይም ካንቺ ምርጫ ውጭ ነው። ንፁሐንን የሚያጠቁ፣ በጭካኔ ነፍስ የሚያጠፉ ወንጀለኞች አሉ። አንተ ወይም አንቺ እጃችሁ የለበትም። ወንጀልን ለመከላከልና አጥፊዎችን ለመቅጣት፣ ሕግና ሥርዓትን በትክክል ለማስፋፋት የምትችሉትን ያህል ጥራችኋል ወይ የሚል ጥያቄ ግን፣ በቀጥታ ይመለከታችኋል። የወንጀለኞች ተግባር ውስጥ ግን፣ ቅንጣት ድርሻ አልነበራችሁም።
ነፃነትንና መብትን የሚያከብር ባህል፣ በዚህ የተቃኘ ሕግና ስርዓት የተስፋፋበት ዘመን ላይ ብትወለዱ፣ “መታደል” ነው። ግን የሚያኮራ አይደለም - የናንተ ውጤት አይደለምና። ወንጀለኞችና ነውጠኛ ሽፍቶች፣ ወይም አምባገነን አሰራርና ሕግ የማይገዛቸው ባለስልጣናት የበዙበት ዘመንና አገር ውስጥ መወለድም፣… የናንተ ልማትና ስኬት፣ ወይም ጥፋትና ውድቀት አይደለም። የአጋጣሚ፣ የእድል ጉዳይ ነው ልንለው እንችላለን።
ይልቅስ፣ “ከትናንቱ ባህልና ስርዓት ለመማር፣ ጥሩ ጥሩውን ለመጠበቅና ለማፅናት፣ የወደፊቱን ደግሞ ለማሻሻል ምን አይነት ድርሻ ይኖርሃል? ምን ያህል ድርሻ ይኖርሻል?” የሚለው ነው ዋናው ጥያቄ። ይሄ ነው ያንተና ያንቺ ፈንታ።
የጥበበኞች ድንቅ የእውቀት ግኝትና የፈጠራ ውጤትስ? በአካል ባታውቋቸውም፣ በምርምራቸውና በቤተሙከራቸው ውስጥ ድርሻ ባይኖራችሁም፣… ከአዋቂዎቹ መማር፣ ከሙያተኞቹ ልምድ መቅመስ፣ የቴክኖሎጂያቸውና የምርታቸው ተጠቃሚ ገበያተኛ መሆን ትችላላች። በእርግጥም፣ የጥበበኞች ፍሬ ለብዙ ሰዎች በረከት ይሆናል። መታደል ነው። እውቀትና ቴክኖሎጂ በተበራከተበት አገርና ዘመን መወለድ፣ የሚያኮራ ወይም የሚያሳፍር አይደለም። “አጋጣሚ” ወይም “እድል” ብንለውስ?
አንተስ ምን ሰራህ? አንቺስ ምን ፈጠርሽ? ይሄ የየግል ኃላፊነትና ፈንታ ነው - በግል ምርጫና በግል ጥረት የሚወሰን።
የሌሎች ሰዎች የዛሬ ተግባር ብቻ ሳይሆን፣ የዛሬ ተፈጥሯዊ ክስተቶችም ከእያንዳንዱ ሰው ምርጫ ውጭ ናቸው። የጥንት ታሪኮችና የቀድሞ ተፈጥሯዊ ክስተቶችም እንዲሁ።
በዘመናት የታነፀ ባሕል እንዲሁም የተፈጥሮ ዑደትና ሕግስ?
የመሬት ስበት፣… የሚያኮራም የሚያሳፍርም አይደለም ብለናል። የስንፍና ወይም የጉብዕዝና፣ የበጎነት ወይም የክፋት ውጤት አይደለም። ለሁሉም የሚታደል ነው። ፀሐይ የምትወጣው ዝናብ የሚጥለው፣ ለጥበበኛም ለሞኝም ነው። ለአጥፊም ለአልሚም ያው ናቸው - ፀሐይና ዝናብ።
በዝናብና በፀሐይ ማምረት፣ እንዲሁም መጠለያ መስራት ግን ለሁሉም የሚታደል ጉዳይ አይደለም። መስራትና አለመስራት የሚያኮራ የሚያሳፍር ነው። የመሬት ስበት ተፈጥሯዊ ገፅታዎችን ተምሮ ከዚያም ተመራምሮ ማወቅ፣ በዚያው ልክ ያኮራል። በእርግጥ፣ ጥበበኛ አስተማሪ የማግኘት እና ያለማግኘት ጉዳይ፣ የእድል ጉዳይ ሊሆን ይችላል። ከኒውተን በፊት፣… የስበት ትምህርት ብዙም አልነበረም።
ከ300 ዓመት በፊት የነበሩ ሰዎች፣ የስበት ቀመሮችን የሚያስረዳ መፅሀፍና የሚያስተምር አዋቂ አለማግኘታቸው አያሳፍርም። እኛ ከኒውተን በኋላ መወለዳችንም አያኮራም። በምርጫችንና በጥረታችን የተገኘ ውጤት አይደለም።
ይልቅ እንደየ ዝንባሌያችን በተገቢው መማር አለመማራችን ነው - ከኮራንበትም ካፈርንበትም። በእርግጥ ለመማር መምረጥና ከልብ መትጋት፣ የእያንዳንዱ ሰው ድርሻ ቢሆንም፣ እንደ ልብ ጎበዝ አስተማሪ ይገኛል ማለት አይደለም። በጥንቃቄ የተዘጋጀ የመማሪያ መጽሃፍ፣ እጅ በመሰንዘር ብቻ ከመዳፋችን ማስገባት እንችላለን ማለትም አይደለም። እድሉ ግን ተፈጥሯል። ጎበዝ አስተማሪዎችና ጥሩ መፃህፍት በሌላ ዘመን አልነበሩም። ዛሬ ግን ጥቂት ቢሆኑ እንኳ አሉ።
ከጣርን እናገኛቸዋለን። መፅሐፍና አስተማሪ ፍለጋ ስንጀምር፣ “እጣው ውስጥ እንደ መግባት” ቁጠሩት። ዛሬውኑ በቅርባችን ባናገኛቸው እንኳ፣ ዞር ዞር ብለን ካየን ወዲያውኑ ባይሳካልን እንኳ፤ ውለን አድረን በፍለጋ እናገኛቸዋለን። እጣው ውስጥ ከገባንበት፣ ቀን ቆጥሮ ግራ ቀኝ ዞሮ ይደርሰናል። ወይም እንደርስበታለን።
እቁብ እንደ መግባት ነው። በሚቀጥለው ሳምንት እጣው ባይደርሳችሁ እንኳ፣ መምጣቱ አይቀርም - የተበላ እቁብ ካልሆነ በቀር ማለቴ ነው።
በእርግጥ፣… እድሉ ካለ፣ እጣውም ከደረሰ፣… ጥሩ መፅሐፍ ለማግኘት ወይም እቁብ ለመግባት ስለወሰንክ ብቻ፣ ስኬታማ ባለሀብት፣ አዋቂና ጥበበኛ ሆንክ ማለት አይደለም። እያንዳንዱ ሰው፣ ፍሬያማ ለመሆን ከፈለገ፣ ከእድልና ከእጣ ባሻገር፣ በየፊናው የየራሱን ድርሻ ማከናወን አለበት። የተማረውን ማጥናትና ገቢ መፍጠር፣… የእድልና የእጣ ጉዳይ አይደለም። እነዚህን የግል ኃላፊነቶች የአቅሙን ያህል መወጣት፣ የእያንዳንዱ ሰው ፈንታ ነው።
ይሄኔ፣ እድል፣ እጣ እና ፈንታ ተሟልተዋል ማለት ይቻላል።
ዓለማትና ከዋክብት ተገጣጠሙ ያስብላል።
ሁሉም በዓይነታቸው ተሟልተው፣ በየልካቸው ስክትክት ሲሉ፣… መስመር ሲይዙ፣ አላማ ተሳካ፣ ኑሮ ሰመረ ያሰኛል።
ጥንታዊ ትረካዎች፣ የሰውን ህይወት ከጨረቃ (ከወር) ዑደት ጋር ያመሳስሉታል።
ጨረቃ፣ የወሩ መግቢያ ላይ ትንሸ ሆና ትወለዳች። እያደገች የወሩ መንፈቅ ላይ ሙሉ ትሆናለች። ወደ ወሩ መገባደጃ እያነሰች ትከስማች። የመወለድ፣ የማደግና የማርጀት ዑደት መሆኑ ነው። ዑደቱ እየተመላለሰ ይሸከረከራል - ሁሉም ሰው ላይ።
አንዳንድ ሰባኪዎች፣ ይህን ምሳሌ የህይወትን ወረትነት ለመግለፅ ይጠቀሙበታል። በዘይቤ ለማስረዳትም፣ “ፎርቹን” የተሰኘችውን አምላክ ይጠቅሳሉ። “ቨርቱ” ከሚል ቃል የተዛመደው የአምላኪቱ ስያሜ፣ መዘወር ወይም ማሾር እንደማለት ነው። በምስል ለመግለፅም፣ መዘውር አስይዘው ይስሏታል። ሐውልት ይሰሩላታል።
አንዳንዴ፣ መዘውሩን ታፈጥነዋለች፡፡ የኑሮ መከራዎችን እየደራረበች ያለ እድሜው ታጎሳቁለዋለች፡፡ ወደ እርጅና ትጠመዝዘዋለች። ሲያሰኛትም፣ በተደላደለ ኑሮና በድንቅ ስኬት፣ የሰዎችን ሕይወት ታድሳለች - የያዘችውን መዘውር በመጠቀም። ትርጉሙ፣ የሰው ሕይወት፣ ከሰዎች ቁጥጥር ውጭ ነው ለማለት ሊሆን ይችላል - በጭፍን አስተሳሰብ። የሰውን ሕይወት የሚያሻሽሉ ወይም የሚያበላሹ አጋጣሚዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ የሚል መልዕክትም ሊኖረው ይችላል።
በመዘውር፣ ወይም በዑደት ላይ ተጨማሪ እንቅስቃሴ በመጨመር የሰውን ሕይወት የሚገልጹ ሌሎች ጥንታዊ ትረካዎችም አሉ።
የህይወት ዑደት በሁሉም ሰው ላይ ተመሳሳይ እንደሆነ ቢያምኑም፣ ህይወት ማለት ዑደት ብቻ… መሽከርከር ብቻ አይደለም። እየተሸከረከረ ይጓዛል። እየሾረ ይጠቀለላል፤ ይመዘዛል።
ሕይወት፣ እንደ መንኮራኩር እየተሸከረከረ፣ ረዥም ርቀት ይጓዛል፤ ወይም አንድ ቅያስ ሳይሻገር በአጭር ይቋጫል።
ሕይወት እንደ እንዝርት እየሾረ በቀጭን ወይም በወፍራሙ፣ በረዥሙ ወይም በአጭሩ፣ የተለያየ ዓይነት ፈትል ይወጣዋል።
ይህን የሚገልፅ ይመስላል የሶስቱ ወይዛዝርት ትረካ። እህትማማች ናቸው ይባላል። የሰውን እድል፣ እጣና ፈንታ ያዘጋጃሉ፤ ይመዘግባሉ፤ ይዘጋሉ።
የሰው ህይወት እንደ እንዝርት ሆነና፤ አንዷ ታሾረዋለች፤ ፈታይ ናት። “ኮለቶ” ይሏታል።
ሁለተኛዋ የየዘመኑን ፈትል ትመትራለች። በማስመሪያ በመለኪያ ዘንግ ርዝመቱንና እጥረቱን ትመዘግባች። “ለከሲስ” ይሏታል።
ሦስተኛዋ መቋጫውን ትቆርጣለች - አጥሮፓስ ናት።የሕይወት ዑደት፣ ከውልደት እስከ ሞት፣ የዓመታትና የወራት፣ የየእለቱ ውሎና አዳር ተመሳሳይ ተፈጥሯዊ ዑደትና ተደጋጋሚ ዙረት ቢሆንም፤… ይህ ብቻ አይደለም።
የሕይወት መኪና ይጓዛል፤ እንዝርቱ ይፈትላል። ከጉዞው ርቀት ጋር ከፍታውና ዝቅታው፣ ከፈትሉ ርዝመት ጋር ንጣቱና ጥቁረቱ በሁሉም ሰው ህይወት ላይ ተመሳሳይ አይደለም። እንዝርቱ ይሾራል፤ የጋሪው እግር ይሽከረከራል። ነገር ግን ምንም አዲስ ነገር የለም የሚያስብል አይደለም።
የሕይወት ዑደት ከጨረቃ የየወሩ ሂደት ጋር መመሳሰሉ እውነት ቢሆንም፤ ወረት ብቻ ግን አይደለም። ቀንና ሌሊት፤ ነቅቶ መነሳት፤ ተኝቶ ማረፍ፤ ነባር እውቀትና አዲስ ነገር ማየት፤ … እንደጨረቃ ዑደት ከወር ወር ያው ነው። አይለወጥም።
ነገር ግን፣ መሽቶ ሲነጋ ተኝተን ስንነቃ በየቀኑ እንደ ህፃን አንሆንም። በየቀኑ አእምሮ በላጲስ እየተፋቀ ሀሁ ብለን ከባዶ አንጀምርም። እያፈረሱ መገንባት አይደለም። በየቀኑ ሽቅብ እያንከባለሉ ከኮረብታው ጫፍ አናቱ ላይ ለመድረስ መውተርተር፤ ተመልሰው ቁልቁል እየተንሸራተቱ መውረድ፣ የደከሙበት ስራም ቁልቁል እየተንከባለለ ወደ ትናንትናው መመለስ አይደለም-ሕይወት።
በእለታዊውም ሆነ በዓመታዊው ዑደት የተሰራውን ቁም ነገር ከንቱ እንዳይሆን መጠበቅ፣… የትናንቱን እየተንከባከቡና እያደሱ፤ ተጨማሪና የተሻለ ቁምነገር ማከናወን… በዚህ መንገድ ሲገለፅ፣ የሰው ህይወት የዑደትና የሂደት፣ የነባርና የአዲስ፣ የአላማና የውጤት ገጽታዎችን አዋህደን እንድናይ ይረዳናል።
ተፈጥሯዊ እውነታን፤ ተመልሰን የማንቀይራቸው የዘመናት ታሪኮችንና የትናንት ተግባራትን፣ በረዥም ጊዜ የተዋቀሩ ልማዶችንና ዝንባሌዎችን፣… ከዛሬ የስራ እቅድና ድርጊት፣ ከዛሬ ክስተቶችና ከአዲስ መረጃዎች፣… ከሕይወት ዘመን አላማና ምኞት፣ ዘመን ከማይገድበው የስነ ምግባር መርህና ከሩቅ ራዕይ ጋር ማዋሀድ፣ ትልቁ የህይወትና የጥበብ ምስጢር ነው።
ተፈጥሯዊውን እውነታና ዑደት በአወንታ መቀበል እንጂ ሌላ አማራጭ የለም። በዚያ ላይ ጥፋትም ልማትም አይደለም። በዚያ ላይ የክፋት ወይም የመልካምነት ውጤት አይደለም።
አያስቀጣም፤ አያሸልምም። አያኮራ፤ አያሳፍርም። በሰው ምርጫና ተግባር አማካኝነት የመጣ አይደለም- ተፈጥሯዊ እውነታ።
መወለድም የምርጫ ጉዳይ አይደለም።
የጥንት ታሪክና በረዥም ዘመን የተፈጠረ ባህል፤ የእልፍ አእላፍ ሰዎች ውጤት ነው- አውቀውም ተሳስተውም፣ በድክመትም በብቃትም፣ ተፀፅተው በተሻሻሉ እጥፊዎችም፤ ፅናታቸው እየላላ በተበላሹ አልሚዎችም፤ በብዙ አይነት ሰዎች፤ የተገነባ፤ የተሸረሸረ፣ የተጠገነ፣ የተጎሳቆለ፣ እየተሻሻለ፣ እየተበላሸ… ብዙ እያየ የመጣ ነው- ነባር ባህል፤ የጥንት ታሪክ።
ወደኋላ ተመልሰን ልናሻሽለው ወይም ልናበላሸው ግን አንችልም። ልንማረርበት ግን እንችላለን። የወደፊት ታሪክንና ባህልን የማሳመር እድል አለ። ከጥንቱ ታሪክ በመማርና ነባሩን ባህል በመጠቀም የወደፊት ሕይወትን ማሻሻልና ማነፅ ነው የዘመናችን ሕያዋን ፈንታ።
የጥንቱን ታሪክ ዛሬ ማዕረግ ሰጥተን ልንሸልመው ፍርድ ቤት ልናቀርበው አንችልም። በነባሩ ባህል ማፈርና መኩራት፤ አይገባም። ወደኋላ ተመልሶ ነባሩን ባህል መቀየር የሚችልም የለም። ያማ፣ የጥንቱ ዘመን ሰዎች ፈንታ ነው። ወደኋላ ተመልሶ በራሱ ምርጫ ለመወለድ እንደመሞከር ነው።
የሰው ክብሩና ውርደቱ፣ ማንቱና ኃላፊነቱ፣… በሆነ ዘመን በሆነ ባሕልና አገር ውስጥ መወለዱ አይደለም። ያማ የሌሎች ሰዎች ስራ ነው። ከተወለደ በኋላ ነባሩን ባህል ተጠቅሞ በሕይወት ዘመኑ ምን ፋይዳ ሰራ? ምን አይነት ብቃትና ስብዕናን ተቀዳጀ? የሚሉ ጥያቄዎች ናቸው የእያንዳንዱ ሰው ፈንታና ድርሻ። ማፈርና መኩራ መምጣት ያለበት ከግል ኋላፊነትና ፈንታ ጋር ነው።Read 2404 times