Saturday, 22 April 2023 19:10

አሜሪካ ኤምባሲ፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት እና የዉጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ተከሰሱ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

 የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ጉዳዩን እንዲከታተልለት ፍትህ ሚኒስቴር ወክሏል


አሜሪካ ኤምባሲ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት፣ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴርና በኢትዮጵያ የኬኒያ ኤምባሲ ክስ ቀረበባቸው። እነዚህ ተቋማት የተከሰሱት ከአንድ አመት ተኩል በፊት በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ውስጥ በፀጥታ ሀይሎች ታፍኖ በተወሰደው በአቶ ሳምሶን ተክለሚካኤል ቤተሰቦች ነው፡፡
የአቶ ሳምሶን ተክለሚካኤል ባለቤት ወይዘሮ ሚለን ሀለፎምና ጠበቃቸው ዳባ ጩፋ (ዶ/ር)፣ ሀሙስ ሚያዚያ 12 ቀን 2015 ዓ.ም ረፋድ ላይ በሳሮማሪያ ሆቴል ለጋዜጠኞ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው ተቋማቱን መክሰሳቸውን ያስታወቁት። ክሱ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለተኛ የሰብአዊ መብት ችሎት መቅረቡንም ጠበቃ ዳባ ጩፋ (ዶ/ር) አብራርተዋል። የውጪ ጉዳይ  ሚኒስቴር ፍርድ ቤት የቀረበ ሲሆን የክስ መዝገቡ ዘግይቶ የደረሰው በመሆኑ አንብቦ ምላሽ ለመስጠት ጊዜ እንዲሰጠው በጠየቀው መሰረት ፍርድ ቤቱም ለሚያዚያ 13 (ትላንት) ቀጠሮ መስጠቱን የገለጹት ጠበቃው፤ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ጉዳዩን እንዲከታተልለት ፍትህ ሚኒስቴርን መወከሉንም ጠቁመዋል።
ላለፉት 19 ዓመታት በኬኒያ ናይሮቢ ነዋሪነቱን አድርጎ በጋዝ ንግድ ላይ በመሰማራት ሲሰራ የነበረው አቶ ሳምሶን እስካሁን በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ ልጆቹና ቤተሰቡ እንደማያውቁና ከዛሬ ነገ ይመጣል እያሉ በመጠበቅ በስቃይ ላይ መሆናቸውን የገለጹት ባለቤቱ ወ/ሮ ሚለን ሀለፎም፤ ባለቤቴ ከመያዙ በፊት ከወንጀል ነጻ የሚል ሰርትፍኬት ያለው፣ እጅግ ደግና ለተቸገረ ቀድሞ ደራሽ እንጂ የባህሪም ሆነ የሰብዕና ችግር  ያለበት አይደለም ብለዋል።
“ወንጀል ሰርቶም ከሆነ በ48 ሰዓት ውስጥ ፍ/ቤት መቅረብ ሲገባው እስካሁን በምን ሁኔታ ላይ  እንዳለ አለማወቃችን ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት ነው” ብለዋል።
የታሳሪው ቤተሰቦች በኬኒያ ኤምባሲ በኢትዮጵያ፣ በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴርና በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በኩል ጉዳዩ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲፈታ ብዙ ርቀት መጓዛቸውን የገለጹት ጠበቃው፣ ሆኖም እስካሁን የተገኘ ውጤት አለመኖሩን አብራርተዋል። የአሜሪካ ኤምባሲ በኢትዮጵያና የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በ3 ወር ውስጥ እናስለቅቀዋለን ብለው መግለጫ ቢያወጡም ጠብ ያለ ነገር አለመኖሩን የገለጹት ጠበቃ ዳባ ጩፋ (ዶ/ር) ደንበኛቸው ከተያዘበት ጊዜ ጀምሮ የተያዘበት ምክንያት ሳይገለጽ፣ በ48 ሰዓት ፍ/ቤት ሳይቀርብ ከልጆቹ፣ ከጠበቃውና ከሀኪሙ ጋር የመገናኘት መብቱ ተጥሶ እየተጉላላ መሆኑ በእጅጉ እንዳሳዘናቸውና ይህንን ክስ በተቋማቱ ላይ ለመመስረት እንደተገደዱ አብራርተዋል።
 የቀረበውም ክስ ከላይ በተዘረዘሩት የሰብአዊ መብት  ጥሰቶች የተነሳ ከመደበኛው ክርክር ከፍ ያለና “ስልተ-ሙግት” እንደሆነ ያስረዱት የአቶ ሳምሶን ጠበቃ፤ ይህ ሁሉ ችግር የተፈጠረው በኢትዮጵያ የኬኒያ ኤምባሲ  ድክመት እንደሆነም አብራተዋል።
“ምንም እንኳን የኢትዮጵያ መንግስት ሊረዳን ቢሞክርም የእስከዛሬ እንቅስቃሴው  ውጤት ስላላመጣ አሁን ተጨማሪና ከእስከዛሬው ጠንከር ያለ እንቅስቃሴ አድርጎ ባለቤቴ ያለበትን ሁኔታ ያሳውቀኝ” ያሉት ወ/ሮ ሚለን፤ “ወንጀልም ሰርቶ ከሆነ ክስ ተመስርቶበትና  ፍርድ ቤት ቀርቦ ቅጣት ይቀጣ፤ ያለጥፋቱም ከሆነ የታሰረው በነጻ ይለቀቅልኝ፤ ይህን ለመጠየቅና ለመማጸን ከኢትዮጵያ መንግስት ውጪ የማንኳኳው በር የለም” ሲሉ ተማጽነዋል።
አቶ ሳምሶን ተክለሚካኤል በኬንያ ናይሮቢ ባለፉት 19 ዓመታ በጋዝ ንግድ ላይ ተሰማርተው ከኬንያ ጋዝ በማምጣት ኢትዮጵያ ውስጥ በማከፋፈል ስራ ላይ የቆዩ መሆናቸው የተብራራ ሲሆን ከአንድ አመት ተኩል በፊት በናይሮቢ ውስጥ በጸጥታ ሀይሎች ታፍነው  በመኪና ሲወሰዱ የሚያሳይ ቪዲዮ ከታየ በኋላ በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ እንደማይታወቅ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተጠቁሟል።

Read 1920 times