Monday, 24 April 2023 18:41

ኢቲኬር የግማሽ ቀን አውደ ጥናት በጌትፋም ሆቴል አካሄደ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ኢቲኬር የውበት መጠበቂያ ምርቶች ሽያጭ ኃ.የተ.የግ.ማህበር፣ "የቀጥተኛ ሽያጭ ገበያ ሥርዓትና ህገወጥ ፒራሚዳዊ አሰራር ሥልት በኢትዮጵያ የህግ ማዕቀፍ አጠቃላይ ዕይታ" በሚል ርዕስ፣ በዛሬው ዕለት ለግማሽ ቀን የዘለቀ አውደ ጥናት በጌትፋም ሆቴል አካሄደ፡፡

የአውደ ጥናቱ ዓላማ፣ በቀጥተኛ ሽያጭ ገበያ ሥርዓትና ህገወጥ ፒራሚዳዊ አሰራር ሥልት መካከል ስላሉ ጉልህ ልዩነቶች  ግንዛቤ ለማስጨበጥ ነው ተብሏል፡፡

በአውደ ጥናቱ ላይ የኢቲኬር መሥራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ማቲዮስ መባን ጨምሮ የኢኮኖሚና የህግ ባለሙያዎች በርዕሰ ጉዳዮቹ ዙሪያ ጥናታዊ ጽሁፍና ማብራሪያ ለታዳሚዎች ሰጥተዋል፡፡

ኩባንያው ባዘጋጀውና ለግማሽ ቀን በተካሄደው በዚህ አውደ ጥናት ላይ፤ በቀጥተኛ ሽያጭ የገበያ ሥርዓትና ህገወጥ ፒራሚዳዊ አሰራር ስልት መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው፣ የቀጥተኛ ሽያጭና ፒራሚዳዊ አሰራር ሥልት በኢትዮጵያ ህግ እንዴት ይታያል፣ በገበያው የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችና የመፍትሄ አቅጣጫዎች ምንድን ናቸው፣ እንዲሁም የቀጥተኛ ሽያጭ የገበያ ሥርዓት ለሃገር የሚያበረክተው የኢኮኖሚ ጠቀሜታ--- የሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ተዳስሰዋል፡፡

የኢቲኬር መሥራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ማቲዮስ መባ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፍ፣ የቀጥተኛ ሽያጭ የገበያ ሥርዓትና ፒራሚዳዊ አሰራር ስልት ያላቸውን ልዩነቶች በዓለም አቀፍ ተሞክሮ አስደግፈው ያብራሩ ሲሆን፤ የቀጥተኛ ሽያጭ የገበያ ሥርዓት ለአገር  ኢኮኖሚ የሚያበረክተውን  ጥቅምና ፋይዳ  የራሳቸውን ኩባንያ በማስረጃነት በመጥቀስ አስረድተዋል፡፡
በግንዛቤ ማስጨበጪያ አውደ ጥናቱ ላይ እንደተገለጸው፤የቀጥተኛ ሽያጭ ሥርዓትን የሚከተሉ ድርጅቶች የሚታወቅና በህግ የተመዘገበ አድራሻና የንግድ ፈቃድ ያላቸው ሲሆኑ፤ ለመንግሥትም ተገቢውን ግብር ይከፍላሉ፤ ፒራሚዳዊ አሰራርን የሚከተሉቱ ግን  አድራሻቸው የማይታወቅና ህጋዊ ፈቃድ የሌላቸው በመሆኑ ለመንግሥት ግብር የማይከፍሉና በአየር ላይ የሚንቀሳቀሱ ናቸው ተብሏል፡፡

ኩባንያው በአውደ ጥናቱ ላይ ያሰራጨው አጭር የቅኝት ጽሁፍ፤"የቀጥተኛ ሽያጭ የገበያ ሥርዓት የሚከተሉ ድርጅቶች ጥራት ያላቸውን ምርቶች ለገበያ የሚያቀርቡ ሲሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ባለው ልምምድ እነዚህ ድርጅቶች የሰዎችን የአኗኗር ዘይቤና ፍላጎቶች ለማሟላት ለፈጠራ ሥራና ለምርምር ከፍተኛ ገንዘብ ይመድባሉ፡፡ በአንጻሩ በፒራሚድ ሥልት የተሰማሩት ደግሞ ምንም ዓይነት ምርት የሌላቸው ወይም ቢኖራቸውም ለይስሙላና የገበያ ዋጋ የሌላቸው ሲሆን ዋነኛ ዓላማቸው ከሰዎች የገንዘብ መዋጮን መሰብሰብ ነው፡፡" ይላል፡፡

የቅኝት ጽሁፉ አክሎም፤"የቀጥተኛ ሽያጭ ሥርዓት በአቋራጭና በፍጥነት በአንዴ ሃብት የሚሰበሰብበት ሳይሆን በዚህ የገበያ ሥርዓት ውስጥ ጠንክሮ በመሥራት፣ ብዙ ደንበኞችን በማፍራትና ብዙ ሽያጭ በማስመዝገብ ኮሚሽን የሚገኝበት ሲሆን፤ የፒራሚዳዊ አሰራር በአንጻሩ፣ በአንድ ጊዜ የሚከበርበት እንደሆነና ሃብት ለማፍራት ብዙ የገንዘብ መዋጮ የሚያደርጉ ሰዎችን መመልመል እንደሚያስፈልግ ይታወቃል፡፡" ሲል ያብራራል፡፡

Read 1475 times