Saturday, 29 April 2023 18:48

አቃፊ የለውጥ ክንፎች- የማጣፋትና የመደመር

Written by  -ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(2 votes)

 እየተቃቀፉ የመጠፋፋት አዙሪት፣ የሰው እጣ ፈንታ እንደሆነ የሚያምኑ መሪዎች ምን ዓይነት ዓለም እንደሚፈጥሩ አስቡት። ሀንገር ጌምስ ይህን ዓለም ያሳየናል። ፖለቲከኞች የሚፈጥሩት የመጠፋፋት ዓለም ነው፤ በመጀመሪያው መጽሐፍ የተገለጸው የሀንገር ጌምስ ታሪክ። ቀላል አይደለም።ይህን የመጠፋፋት አዙሪት የሰበረችው ጀግናዋ “ካትነስ አበርዲን” እንኳ፣ ሰዎችን እያቧደነ ለማጠፋፋት ከተቃኘው የማጣሪያ አዙሪት ለመውጣት፣ ከጥሎ ማለፍ ወጥመድ ለማምለጥ በጣም ተቸግራለች።
  

         “ለውጥ” የሚሉት ነገር፣… ስንት ሰዎች እንዳልተጨነቁበት፣ እንደ ቀላል ነገር… “የጥሎ ማለፍ ፍልሚያ”፣ “የመተቃቀፍና የመጠፋፋት አዙሪት” ብለን ልንገልጸው ሞክረናል። “ግፍ” ነው። ስንት አዋቂዎች እየተመራመሩ የተፈላሰፉበትን ጉዳይ፣ አቅልለን ወይም አጥቁረን ማየት የለብንም።
በእርግጥ፣ ሌኒን የለውጥን ጉዞ ለማስረዳት፣ የአዙሪትና የመሰላል ቅይጥ እንደሆነ ጽፏል።
እንዲያም ሆኖ፣ ለውጥ ማለት፣… እየተቃቀፉ የመጠፋፋት አዙሪት፣… ወይም አንዱ ሌላውን መወጣጫ ለማድረግ የሚራገጥበት ሽሚያ ብቻ አይደለም።
የጥበብ ልሕቀትንና የትጋት ጽናትን የሚጠይቅ ቢሆንም፣” የመከባበርና መተቃቀፍ አዲስ ታሪክ” ሊሆን ይችላል- መልካም የለውጥ ዓይነት።
ያለፉት 150 ዓመታት ይህን ይመሰክራሉ። በፖለቲካ ብቻ አይደለም። በኑሮና በእውቀት ጭምርም እንጂ።፡
በበርካታ የምዕራብ አገራት ውስጥ፣ እያንዳንዱ አዲስ ትውልድ፣ ከቀዳሚዎቹ የተሻለ የኑሮ ደረጃ እየፈጠረና እየተሸጋገረ፣… አስደናቂ የብልፅግና ታሪክ ተመዝግቧል። ለጥቂቶች የነበረ የሕይወት እድል ወደ ብዙዎች እየተዛመተና በሰፊው ሚሊዮኖችን እያቀፈ ባለዲግሪና ባለመኪና አድርጓል- አስገራሚው የለውጥ ዘመን።
ሰረገላ፣ የጥቂት ባለጸጎች ቅንጦት ነበር። የዛሬ 120 ዓመት የተሻለ ቴክኖሎጂ መጣ- መኪና የሚሉት። ዛሬ ከቢሊዮን በላይ መኪኖች በዓለም ዙሪያ ይሽከረከራሉ።
የመጀመሪዎቹ የሞባይል ስልኮችም በጊዜያቸው ብርቅና ውድ ነበሩ። በኒውዮርክና በኤልኤ፣ በሆንክ ኮንግ እና በሲንጋፖር፣ ለጥቂት ሚሊዮኖች የተፈበረኩ ናቸው። የዛሬ እጅግ ርካሽ ተራ ሞባይሎች ከያኔዎቹ “ብርቅና ድንቅ” ሞባይሎች፣ በብዙ እጥፍ ይሻላሉ። በዋጋቸው ግን የድሮዎቹ አይቀመሱም። 10ሺ ዶላር ነበር የያኔው ዋጋ። በገበያ ምንዛሬ፣ 1 ሚሊዮን ብር ማለት እንደሆነ አስቡት። ዛሬ በመቶ ብር ገዢ አያገኙም።
የቴክኖሎጂው ለውጥ፣ በሺ እና በሚሊዮን እጥፍ እጅግ የተሻሻሉ ሞባይሎችን አስፋፍቷል። ለዚያውም ቢሊዮነሮችን ብቻ ሳይሆን ቢሊዮን ሰዎችን የሚያቅፍ ለውጥ ነው።
በእርግጥ፣ ከዚሁ ጋር የቴክኖሎጂ ግስጋሴ ለብዙ አደጋዎች ሰፋፊ እድሎችን ፈጥሯል። አለምን አሰባስቦና አስተቃቅፎ ሲያበቃ፣ የብሽሽቅና የጥላቻ መቆስቆሻ፣ የግጭትና የጥፋት ማዛመቻ እየሆነ መጠፋፋትን ሊያበራክት ይችላል።
ቢሆንም ግን፣ በቴክኖሎጂ ለውጥ ሳቢያ የተፈጠረ አይደለም- ችግሩ።
ሞባይልና ኮምፒውተር በራሳቸው ምርጫ፣ ስድብና ጥላቻ፣ የሃሰት ውንጀላና የጥቃት ዘመቻ አያሰራጩም። ለክፉም ለደጉም እንደ አጠቃቀማችን ያገለግላሉ- ለመማርም ለማማረርም፣ ለማጥቃትም ለማዳንም፣… ለመተቃቀፍና ለመከባበር ወይም ለመተቃቀፍና ለመጠፋፋት ሊውሉ ይችላሉ።በዚህም ተባለ በዚያ፣ ለማልማትም ለማጥፋትም፣ የለውጥ ሃሳብ ወይም የቴክኖሎጂ ለውጥ በሰፊው ይዛመታል፤ ብዙዎችን ይነካል፤ ያነካካል። “ከትውልድ አገሬ አልወጣም” የሚል የቴክኖሎጂ ፈጠራ የለም። ሃሳቦችም እንደዚያው ክንፍ አላቸው። አቃፊ ናቸው- ሁሉንም ለማዳረስ የሚከንፉ።
በአጭሩ፣ “ማዕቀፍ” ሁሌም ከለውጥ ጎን አይጠፋም።
 “ፀረ- ማዕቀፍ” ተብሎ የተሰየመው የዘመናችን መንፈስ እንኳ፣… ነገሮችን የመሰንጠቅና የመሰንጠር፣ የማፍረክረክና የማፈራረስ ረሃብ የተጸናወተው የዝገት ቅኝት ቢሆንም፣… የሆነ አገር ላይ ብቻ፣ የሆነ የኑሮ ዘርፍ ላይ ብቻ ታጥሮ የሚቀር አልሆነም። ስንጥቅጥቁ እየተስፋፋ የዓለም አገራትን ለማዳረስ እየተስፋፋ ነው። በሌላ አነጋገር “ፀረ-ማዕቀፍ” የአስተሳሰብ ቅኝት፣ ማዕቀፉን እያሰፋ መጥቷል።
የሀንገር ጌምስ ዓለም- እየተቃቀፉ መጠፋፋት።
የፖለቲካ ለውጥ ሲከሰት፣ ዋናዎቹ መሪዎችና ደጋፊዎች፣… አባሪ ተባባሪ፣ ስንቅ አቀባይና አጃቢ ለማብዛት፣ በዙሪያቸውም ለማሰባሰብ ይፈልጋሉ። መተቃቀፍ ይስፋፋል። ዳሱ እና አዳራሹ የአገር ያህል ይለጠጣል። በነጋታው ግን ቅራኔ ይፈነዳል። በለውጡ ማግስት፣ ገሚሶቹ ለብቻ ተቃቅፈው ገሚሶቹን ያጠፏቸዋል። “ጠላት” ብለው የፈረጅዋቸውን ቡድኖችና ፓርቲዎችን እያሳደዱ ያጠፏቸዋል። “ጠላት” ብለው የፈረጁትን ቡድን፣ ፓርቲ ወይም ተቋም እስኪደመስሱት ድረስ፣
እርስበርስ አይዋቀሱም። ለጊዜው፣… “የጋራ ጠላት” ላይ ነው ጅራፋቸው።
በጠላታቸው ሳቢያ ለጊዜው ይዋደዳሉ።
ነጥለው ባሳደዱት ቡድን ሳቢያ በአጋርነት ተሰባስበው ይተቃቀፋሉ።
ጠላት ሲጠፋ ነው ችግሩ።
የጠመዱት ገዢ ወይም ያሳደዱት ጠላት ከስልጣን ሲሸሽ፣ ሲወድቅ፣ ሲሟሽሽ፣… ዘመቻው ሲጠናቀቅ፤ የሚያዋድድ የጋራ ጠላት ያጣሉ። እንደገና ከመሃከላቸው ከፊሎቹ ተቀራርበው ከፊሎቹን ነጥለው ይዘምቱባቸዋል።
በዚህ የጥሎ ማለፍ አዙሪት፣ የድንኳኑ የአዳራሹ አውራ ታዳሚዎች ይመናመናሉ። የሚተቃቀፉ መሪዎች ቁጥራቸው ይቀንሳል። የለውጡ ማዕቀፍ እየጠበበ ነው ማለት ይቻላል። ነገር ግን፣ እየተስፋፉም ነው ይላሉ። እንዴት?
በየዙሩ፣ ቁጥራቸው ሲቀንስ፣ ስልጣናቸው እየበዛ መዋቀራቸው እየሰፋ ከዳር እስከ ዳር መላ አገሪቱን በመዳፋቸው ውስጥ እያስገቡ ይሄዳሉ።
የገዢው ፓርቲ ወይም የመሪው የስልጣን ማዕቀፍ ከእለት ወደ እለት እየተስፋፋ ይለጠጣል። አገሬው ሁሉ በአንድ ጥላ ስር ይታቀፋል ልንል እንችላለን።
 አዎ፣ በመጠፋፋት የሚመጣ ማዕቀፍ ነው።
አዎ፣ በአንድ በኩል የአምባገነንነት መንገድ በሌላ በኩልም ወደ አመጽ የሚወስድ ጎዳና ነው።
ግን ያው ሰፊ ማዕቀፍ ነው።
ምን ለማለት ፈልጌ ነው? የማዕቀፉ አይነት ይለያያል እንጂ፣ ለክፉም ለደጉም፣ ለድህነትም ለብልጽግናም፣ ለነጻነትም ለአፈናም የማዕቀፉ ዓይነት ይለያያል እንጂ፣… የመጠፋፋትም ሆነ የመከባበር ማዕቀፍ እየተስፋፋ አገሬውን ለማዳረስ መዛመቱ አይቀሬ ነው።
“The Hunger Games” የተሰኘው ልብወለድ ድርሰት ውስጥ፣ “እየተቃቀፉ የመጠፋፋት አዙሪት”፣… በጥበብና በምሳሌያዊ ዘይቤ እንዴት እንደተገለጸ ማንበብ ይቻላል።
የማጥራትና የማዋሃድ ዘመቻ፣ በጊዜያዊና በተለዋዋጭ የጎራዎች አሰላለፍ እየተቧደኑና እየነጠሉ፣ እየተቃቀፉ እና፣ እየጣሉ የማለፍ የመጠፋፋት ሴራ ይመስላቸዋል - አንዳንድ ሰዎች። እንዲያውም፣ እየተቃቀፉ የመጠፋፋ አዙሪት፣… ማብቂያ የሌለውና የማይቋረጥ የለውጥ ሕግ ነው ይላሉ። እንዴት ብላችሁ ጠይቋቸው። በአንድ በኩል፣ “በልዩነት ውስጥ የመተቃቀፍ አንድነት ይኖራል” ብለው ይጀምራሉ። ተቃራኒ ቡድኖች፣ የጋራ ጠላትን ለማጥቃት በአንድነት ይሰባሰባሉ፤ ይተቃቀፋሉ። በሌላ በኩል ደግሞ፣ “የመተቃቀፍ አንድነት ውስጥ፣ የመጠፋፋት ቅራኔ ሁሌም ይኖራል” በማለት የጥሎ ማለፍ ፍልሚያ ምስጢርን ይልጹልናል። “ዲያሌክቲክ” ብለው የሚጠሩትም አሉ።
እየተቃቀፉ የመጠፋፋት አዙሪት፣ የሰው እጣ ፈንታ እንደሆነ የሚያምኑ መሪዎች ምን ዓይነት ዓለም እንደሚፈጥሩ አስቡት። ሀንገር ጌምስ ይህን ዓለም ያሳየናል። ፖለቲከኞች የሚፈጥሩት የመጠፋፋት ዓለም ነው፤ በመጀመሪያው መጽሐፍ የተገለጸው የሀንገር ጌምስ ታሪክ። ቀላል አይደለም።
ይህን የመጠፋፋት አዙሪት የሰበረችው ጀግናዋ “ካትነስ አበርዲን” እንኳ፣ ሰዎችን እያቧደነ ለማጠፋፋት ከተቃኘው የማጣሪያ አዙሪት ለመውጣት፣ ከጥሎ ማለፍ ወጥመድ ለማምለጥ በጣም ተቸግራለች።
24 ናቸው “የጨዋታው ተሳታፊዎች”። ጨዋታው የሞት ሽረት ፍልሚያ ነው። የፍልሚያው አውድማ፣ ጫካው፣ በረሃው፣ ገደልና ሜዳው ተፈጥሯዊ አይደለም። የፖለቲከኞች ፈጠራ ነው። እንደ ትያትር መድረክ፤ እንደ ፊልም ቀረጻ ይመስላል።
ፍልሚያው ግን የምር ነው። አንድ ሰው እስኪቀር ሌሎቹ ሁሉ እስኪያልቁ ድረስ ይፋለማሉ።
አንዳንዶቹ ለጊዜው ይቧደናሉ፤ ባይዘልቅም ይተቃቀፋሉ።
በጊዜያዊ ትብብር ተቀናቃኞችን እያስወገዱ፣ እርስ በርስ የመገዳደል “የአደን ጨዋታ” ነው። በሁለተኛው መጽሐፍ “ጨዋታው” ባሰበት እንጂ አልበረደም። ነገር ግን፣ ሌላ አይነት የመተቃቀፍና የመከባበር፣ የውሕደትና የትብብር ቅኝትም ይዟል - ድርሰቱ።
የፍቅርና የወዳጅነት፣ የቤተሰብና የጓደኝነት፣ የመተጋገዝና የመረዳዳት፣ የልግስናና የግብይት፣ የጨዋነትና የመከባበር፣…
ከሽንገላና ከማስመሰል፣ በስድብና ከሃሰት ውንጀላ፣ መቆጠብ፣ ከሽፍጥና ከስርቆት፣ ከዝርፊያና ከውድመት፣ ከጸብና ከግድያ ጥቃቶች መታቀብ፣…
መከባበርና አጥር አለማፍረስ፣ የግል መስመርን አለመጣስ…
እነዚህ ሁሉ በአንድ ማዕቀፍ የሚካተቱ የስነምግባር መርሆች ናቸው። ከእነዚህ የስነ-ምግባር መርሆች ውስጥ ነው የህግ መርሆችን የምናገኘው።
ለሰው ተፈጥሮ የሚመጥን የመከባበር መርህ- አቃፊ ስልጣኔ።
 ስልጡን የነጻነት ፖለቲካ፣ የዛሬ 240 ዓመት በአሜሪካ ብልጭ ብሎ አልቀረም። በየአህጉሩ ለመዛመትና ማዕቀፉን ለማስፋት ጊዜ ወስዶበት ይሆናል። ግን፣ ዛሬ ሕገ-መንግስት የሌለው አገር ስንቱ ነው? ዛሬ አምባገነን ስርዓቶች እንኳ፣ “ሕገ-መንግሥት” አዘጋጅተው ያውጃሉ። ሕገ-መንግሥት ለዓለማችን ብርቅ ነበር። “ለሕግ ተገዢ የሆነ መንግስት” የሚል አስተሳሰብ ገና አዲስ ሙከራ ነበር ያኔ። ይህም ብቻ አይደለም።
ሰው ሁሉ በተፈጥሮው፣ “የሕይወት መብት፣ የነጻነት መብትና በጥረቱ የመደሰት መብት አለው” የሚል ነው የያኔው የለውጥ መርህ።
ለወንዶች ብቻ፣ ለሴቶች ብቻ፣ ለነጮች ወይም ለጥቁሮች፣ ለክልል ወይም ለወንዝ ማዶ፣ ለእገሌ ብሔር ተወላጅ፣ ለእገሊት ብሔረሰብ ቋንቋ… የሚል አይደለም- መሰረታዊው አሜሪካ የነፃነት መግለጫ።
እያንዳንዱ ሰው በተፈጥሮው፣…
አካላዊና አእምሯዊ አቅሙን የመጠቀም ነጻነት፣…
የህይወቱና የግል ማንነቱ ብቸኛ አዛዥ ሆኖ የመምራት፣… ኑሮውን ለማሻሻል የማምረትና የንብረቱ ባለቤት የመሆን መብት አለው።…
ምንኛ ሰፊ ማዕቀፍ እንደሆነ አስቡት።
የዚህ አገር ነዋሪ፣ የዚያ መንደር ተወላጅ፣ የባሕር ማዶና የወንዜ፣… የጥንት፣ የዘንድሮ፣ የመጪው ዘመን ሰዎች… እያለ የሚሰነጣጥር አይደለም- የስልጡን ፖለቲካ መሰረታዊ ሃሳብ።
የአሜሪካው አብዮት፣… የያኔው ለውጥ፣ ሰፊ የሃሳብ ማዕቀፉን በትክክል ዘርግቶ ነው የመጣው።
ሁሉን አቀፍ አስተሳሰብ ቢሆንም፣… በእያንዳንዱ ሰው ሕልውና ላይ የተመሰረተ አስተሳሰብ ስለሆነ፣ እንትናን፣ አንቶኒትን፣ እገሌን፣ እከሊትን ሁሉ ጨፍልቆ፣ ሁሉንም የሚጠቀልል፤ ሁሉን የሚወክል “ሰው” ይፈጥራል ማለት አይደለም።
እያንዳንዱን ሰው ያቀፈ ስልጡን የፖለቲካ መርህ፣… ትክክለኛ ሃሳብ ቢሆንም፣ “የግለሰብ መብት” የተሰኘው መርህ ከመነሻው ተፈጥሯዊውን እውነታ በማስተዋልና በማገናዘብ የተገኘ እውቀት ቢሆንም፣… በሁሉም ቦታና ዘመን፣ ሁሉም ሰዎች ያውቁታል ማለት አይደለም። ሁሉም ሰዎች የትክክለኛ መርህ ደጋፊዎች ናቸው ማለት አይደለም።
እንደማንኛውም እውቀት፣ ትክክለኛ የመርህ እውቀትም የእንዳንዱን ሰው ጥረት ይፈልጋል። የመተባበርና የመማማር፣ መረጃና ሃሳብ የመለዋወጥ ፈቃደኝነትን ይጠይቃል።
እንደማንኛውም እውቀት፣ ስልጡን የፖለቲካ መርህና አስተሳሰብም፣ በጥረት ሊስፋፋና ሊጎለብት ይችላል።
ድንበርና ዘመን፣ ጾታና ዘር ሳያግደው ብዙዎችን የሚያቅፍ አስተሳሰብ ሊሆን ይችላል።
በአንድ ጊዜ በሁሉም ቦታ የመገኘት አቅም አላቸው- መሰረታዊ ሃሳቦችና መርሆች። ነገር ግን፣… አንድ ሰው ስላወቃቸው፣ እዚያው በዚያው፣ የሁሉም የጋራ እውቀትና አቋም ይሆናሉ ማለት አይደለም።
አቃፊ ናቸው፤ ነገር ግን አቅፈው አይወስዱም።
አንዴ ከተዛመተ በኋላ፣… ቅርንጫፉን አብዝቶ፣ ክንፉን ዘርግቶ በሰፊው የተንሰራፋ የሃሳብ ማዕቀፍ፣… በቀላሉና በአጭር ጊዜ አይፈርስም፣ አይጠፋም።
ካናናቁትና ካጥላሉት ግን፣… ቸል ካሉትም፣ ቀስ በቀስ ቅርንጫፎቹ ሊጠወልጉ፣ የክንፎቹ ላባዎች እየተነቀሉ ሊረግፉ ይችላሉ።
እውነተኛ እውቀትና ትክክለኛ መርህ፣… ሊወገዝ ይችላል።
የሰበብና የማመካኛ መንገዶች ደግሞ እልፍ ናቸው። ጥቂት የማናናቂያ አባባሎችን ተመልከቱ። “ጊዜው አልፎበታል፤ አርጅቷል፤ ጽንፈኛ ሆኗል፤ የፈጠራ ዝንባሌዎችን ያከሽፋል፤ ለሕዝብ ፍላጎት ቦታ አይሰጥም፤ የመንግስትን ስልጣን ይገድባል፤ ለ21ኛው ክፍለ ዘመን አዲስ ሃሳብ ያስፈልጋል፤ ያልተሞከሩ ሌሎች መርሆች እኩል እድል ማግኘት አለባቸው፤ የባሕር ማዶ እውቀት በአገር በቀል እምነት ይለወጥ፤ በየወንዙ በብሔር ብሔረሰብ ብዛት የተለያዩ መርሆችንና ተቃራኒ “እውቀቶችን” እንደውበት የሚቀበል ብዝሃነት ይስፈን”…
ማለቂያ በሌላቸው ሰበቦች አማካኝነት፣ እውነተኛ እውቀትና ትክክለኛ መርህ ሊፈራርስ ይችላል።
እውነተኛ እውቀት መሆኑን መሻር አይቻልም።
ነገር ግን አዋቂዎችን እያመናመኑ፣ አላዋቂ የጭፍን አስተሳሰብ ምርኮኞችን ማበርከት ግን ይቻላል።
ትክክለኛ መርህ፣ ትክክለኛነቱ አይሰረዝም።
ነገር ግን፣ እየተንቋሸሸ ተጥላልቶ ከብዙ ሰዎች አእምሮ ተጠራርጎ ሊራገፍ ይችላል።
በሌላ አነጋገር ሰፊውን ዋርካ ማራቆትና መገንደስ፤ አቃፊ ክንፎችን መንጨትና ከነጭራሹ ሰባብረው መጣል የሚፈልጉ ሰዎች ይኖራሉ። አንዳንዴም ይሳካላቸዋል (ሌሎች አዋቂዎች ለእውቀትና ለመርህ በጽናት ካልተጉ፤ ቸል ካሉ)።
በእርግጥም፤ ሰልጡን የፓለቲካ መርሆች፤… .. ከጊዜ ወደ ጊዜ ከአገር አገር ክንፋቸው እየተዘረጋ በሰፊ ማዕቀፍ፤… “ተዓምረኛ” የሚሰኝ መልካም የአኗኗር ለውጥ ቢያመጡም፤… . ዛሬ ዛሬ በፍጥነት እየተፍረከረኩ ብዙ አገራት ለትርምት እየተጋለጡ ናቸው።
እና፣… “የግል መብት” የተሰኘው መሰረታዊ መርህ (“ካፒታዝም” ተብሎ የሚታወቀው ሥርዓት) ክንፉ ከተሰበረ ማን ይተካዋል?
ጥንታዊዎቹ ቅኝቶች አሉ። ሃይማኖታዊ መንግስት፣ የጎሳ መሪ እና አፄ በጉልበቱ ጨርሰው ጠፍተዋል ማለት አይደለም።
የካፒታሊዝም ተቀናቃኝ ሆነው የተፈጠሩት ሁለት ዘመነኛ ማእቀፎችም አሉ- ሁለቱም የሶሻሊዝም ቅኝቶ ናቸው። አንዱ መደባዊ ወይም ወዛደራዊ ሶሻሊዝም ነው። አለማቀፋዊ ኮሙኒዝም ልንለው እንችላለን። ሌላኛው ደግሞ አገርኛ ወይም ብሔርተኛ ሶሻሊዝም ነው የሞሶሎኑ ፋሺዝም፣ የሂትለር ናዚዝም ዓይነት። ሁለቱም በጋራ፣ “የግለሰብ መብት” የሚለውን መርህ ያፈርሳሉ።
እያንዳንዱ ሰው የህዝብ ማገዶ፣ ነው ይላሉ። ግለሰብ፣… ማለትም ሁሉም ሰው የመንግስት ጭሰኛ ነው ይላሉ። የአገር ወይም የብሔር ብሔረሰብ ባሪያ እንደሆነ ያውጃሉ። አቃፊ ናቸው። ምንም አይቀራቸውም። ግን የመጠፋፋት ነው ማእቀፋቸው።
አምባገነንነትንና አመፅን እያነገሱ፣ በዓለም ዙሪያ ድህነትንና ረሃብን፣ ስቃይና እልቂትን፣ አፈናንና ትርምስን ሲያዛምቱ በተግባር እየተደጋገመ ከተረጋገጠ በኋላ ነው ክንፋቸው መርገፍ የጀመረው። ነገር ግን፣ በእነዚሁ ምትክ የመጣ ሌላ አቃፊ አስተሳሰብ የለም። ፈላስፋዋ አየን ራንድ እንደምትለው፣ የካፒታሊዝም አስተሳሰብ የተሰናከለው አስደናቂ ውጤት ካስመዘገበ በኋላ ነው። የካፒታሊዝም መርህ የጠወለገው፣በአላዋቂነት፣ በፍርሃት እና በምቀኝነት መንፈስ ነው።የሶሻሊዝም ቅኝቶች (ከፋሺዝም እስከ ኮሙኒዝም) እርቃናቸው የቀሩት፤ ክንፋቸው የተሰበረው በ1940ዎቹ ነው። በሁለተኛው የአለም ጦርነት ላይ ያስከተሉት መዓት፣ የብሔርተኝነትና የሶሻሊዝም አጥፊነትን አጋልጧል ትላለች ፈላስፋዋ። ከዚያ በኋላ የሶሻሊስት መንግስታት ውድቀት የጊዜ ጉዳይ ብቻ እንደሆነም ገልፃ ነበር። በእርግጥም፣ ከሃያ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ነው የራሺያ ኮሚኒዝምና የበርካታ አገራት ሶሻሊዝም የተፍረከረከው (የኢትዮጵያን ጨምሮ)።
ነገር ግን፣ እንደ ድል መቆጠር እንደሌለበትም ራንድ ገልፃ ነበር።
የተሳሳቱ መጥፎ አስተሳሰቦች ስለከሰሩ፣ ትክክለኛ መልካም አስተሳሰቦች ይለመልማሉ ማለት አይደለም። እንዲያውም የአስተሳሰብ ማዕቀፍን የሚፈርስ ቅኝት እየተስፋፋ መሆኑን በመጥቀስ፣ የትርምስ አደጋ እየተባዛ እንደሚዛመት ገልፃ ነበር- ከ50 ዓመት በፊት። የፓለቲካ ምሁሩ ሳሙኤል ሃቲንግተን የዛሬ 30 ዓመት ያቀረቡት ትንታኔ፣ በበርካታ ጉዳዮች ከአየን ራንድ ሃሳቦች ጋር ይራራቃል። ነገር ግን፣ ተመሳሳይ ቁም ነገርም ይዟል። የሃሳብ ማዕቀፎች በጥቅሉ፣ በተለይ ደግሞ የፓለቲካ መርሆች፣ ትክክለኛም ይሁኑ ስህተት፣ ሁሉም ማዕቀፎች እንደተዳከሙና እንደተፍረከረኩ ይገልጻል የሃቲንግተን ታሪካዊ ትንታኔ። የማዕቀፎች ወይም የመሰረታዊ መርሆች መንኮታኮት፣ የዓለምን ታሪክ በአዲስ አቅጣጫ የሚወስድ እጅግ ከፍተኛና አደገኛ ለውጥ እንደሆነም የምሁሩ ጥናት ያትታል።
ፍልስፍናዊ ማእቀፎችና የፓለቲካ መርሆች፣ በጎዎቹና ክፉዎቹ ሲፈራርሱ፣ ለጊዜው ተዳክመው የነበሩ ጥንታዊ ቅኝቶች፣ ያቆጠቁጣሉ።… የዘርና የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ፣ የጥንታዊ ባህልና የሃይማኖት ፓለቲካ ያንሰራራሉ ብለዋል-ሃቲንባተን።ታዲያ እንዲሁ በፍሬ ሃሳብና በንድፈ ሃሳብ ላይ ብቻ ያተኮረ ትንታኔ አይደለም። የብሔር ብሔረሰብና የሃይማኖት ፖለቲካ ሲያቆጠቁጥ፣ ብዙ አገራትን እንደሚያተራምስ ሃቲንግተን በዝርዝር ጠቅሰዋል። ከሳዑዲ አረቢያና ከኢራን ተቀናቃኝነት ጀምሮ፣ ኢራቅና የሶሪያ፣… ምን ያልተናገሩት አለ? ምንስ እንደተነበዩት ያልሆነ ይገኛል?
ዘመነኛው የመፍረክረክ ቅኝት፣… ሱዳንን ከሰሜንና ከደቡብ የሚሰነጥቅ፣ ከዚያም ሰላም የማይሰጥ ይሆናል ብለው ነበር ሃቲንግተን። ያሉት አልቀረም።
የዩክሬን የውስጥ ችግር እንደሚባባስና ከራሺያ ጋር ቅራኔ እንደሚፈጠር የተናገሩትስ ከ25 ዓመት በፊት አይደለም?
ለትንቢያ ከሚያስቸግሩ የዓለማችን አገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ እንደሆነች የጠቆሙት ሃቲንግተን፣ የብሄር ብሄረሰብ ፖለቲካ ሲጦዝ ለውጥረትና ለግጭት የምትጋጥ አገር መሆኗን ግን ገልፀዋል። የሰጉት ደርሷል።
ይህም ብቻ አይደለም። ሶሻሊዝም በተፍረከረከ ማግስት በበርካታ አገራት የፖለቲካ ማሻሻያ ለውጦች ቢታዩም፣ ወደፊት ግን የለውጥ አብዮቶች፣ ዘመቻዎችና አመፆች፣ ለትርምስና ለውድቀት የተጋለጡ እንደሚሆኑ ተናግረው ነበር-ምሁሩ።
በተለይ የአሜሪካና የአውሮፓ መንግስታት፣ “ዴሞክራሲን በዓለም ለማስፋፋት” በሚል ሃሳብ የሚያካሂዱት ጥረት ወይም የሚሰጡት ድጋፍ፣ ከእንግዲህ በጎ ውጤት አያመጣም። ከመጣም፣… ከውጤቱ ይልቅ መዘዙ እንደሚበዛ በመግለፅ ቁጥብነትን መክረዋል።
ይልቅስ፣ የአሜሪካና የአውሮፓ የፖለቲካ ነባር ስርዓት፣ መሰረታዊ መርሆቹ ስለተሸረሸሩ ከናካቴው እንዳይፈራርስ በጥንቃቄና በትኩረት ለመጠበቅ ቢተጉ ይሻላል ሲሉ አሳስበው ነበር።
የአሜሪካና የአውሮፓ መንግስታት የሃቲንግተንን ምክር የተገነዘቡ ወይም ለመቀበል የፈለጉ አይመስሉም።
ሃቲንግተን እንዳሉት፣ በበርካታ የአረብ አገራት የተፈጠሩ የለውጥ ሙከራዎችና አመፆች፣ መልካም ውጤት ሳይሆን የትርምስና የግጭት መዘዝ አምጥተዋል። የአሜሪካና የአውሮፓ ከመንግስታት ግን፣ ድጋፍ ለመስጠት መሯሯጣቸው አልቀረም።
ቢሆንም፤ ሃቲንግተን እንደተነበዩት፣ የለውጥ አመፆችና የምእራብ አገራት ድጋፍ ለመልካም ውጤት አልበቁም።
መርሆችን የሚያፈራርስ፣ ማዕቀፎችን የሚበታትን የዘመናችን የአስተሳሰብ ቅኝት፣… ሁሉንም አገር እያዳረሰ የትርምስ አደጋዎችን ማስፋፋቱ አልቀረም። “ጸረ-ማዕቀፍ” ቢሆንም እንኳ፣ እንደማንኛውም አስተሳሰብ፣ “አቃፊ” ነው። አፍራሽነቱና በታኝነቱ ሁሉን አቀፍ ነው።
በዚያው ልክ ትክክለኛው የስልጡን ፖለቲካ መርህም፣ ሁሉን አቀፍ ነው። “የእያንዳንዱ ሰው መብት” የሚለው መሰረታዊ የፖለቲካ ሃሳብ ሁሉንም ሰው ያቅፋል።በእርግጥ ለጊዜው በአንድ አገር ውስጥ ብቻ የተለኮሰ ችቦ ሊሆን ይችላል- በአሜሪካ እንደታየው። ትክክኛውን መሰረታዊ መርህ አጥርተው ከተገነዘቡ ግን፣ “የግለሰብ መብት” የሚለውን የፖለቲካ ማዕቀፍ አጽንተው ከያዙ ግን፣ የጊዜ ጉዳይ እንጂ ክንፎቹን እየዘረጋ ወደ በርካታ አገራት ችቦው እየተቀጣጠለ፣ ሁሉንም ሰዎች እያቀፈ መስፋፋት ይችላል- በአሜሪካና በሌሎች አገራት ታሪክ እንደታየው።
Read 1287 times