Saturday, 29 April 2023 20:00

ከማህበራዊ ሚዲያ በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

 ሸበተ መሰለኝ!
               (በድሉ ዋቅጅራ)


        ሸበተ መሰለኝ፣ እውቀትም አረጀ፤
ጡት ተጣባውና፤
አበልጅ ሆኑና፤
ከድንቁርና ጋር፣ በወግ ተወዳጀ፡፡
ብርሃኑ ጠፋ፣ አይኑ ደነገዘ፤
መቅኒው በረዶ ሆነ፣ በቁሙ ፈዘዘ፡፡
ይኽው እውቀት ጃጅቶ፤
ከድንቁርና ላይ፣ በሊዝ ቦታ ገዝቶ፤
ጎጆ ቀለሰና፣ መስሎ ጎረቤቱን፤
ፀሐዩን ይሞቃል፣ እያሻሸ ሪዙን፡፡
መጥኔ ለዚች ሀገር!
‹‹የት ይደርሳል›› ስንል በወጣትነቱ፤
እዚህ እቅርባችን፣ ይኽው ተመልከቱ፤
እውቀት ተመፃድቆ፤
ማወቁን አድምቆ፤
ህፀፁን ደብቆ፤
ከድንቁርና ጋር፣ ከጠላቱ ታርቆ፡፡
ደባልነት ገባ፣ አብሮ ቤት ቀለሰ፤
አንዱ ሲገነባ፣ አንዱ እያፈረሰ፡፡
ውሃ እያፈሱ፤
ጤፍ እየቆጠሩ፤
ውሃ እየወቀጡ፤
ባንድ ተቀመጡ፡፡
ይብላኝ ለዚች ሀገር!
የሀገር ጥሪት ነጥፎ፤
የሕዝብ ሀብት ባክኖ፤
የእድሜ ሻማ ነዶ፤
ስልጣኔ ብሎ፤ ፈረንጅ ሀገር ሄዶ፤
ሩቅ… ባህር ማዶ፤
የተገኘን እውቀት፤
ወይም
እዚሁ ሀገር ውስጥ፣ ኮሌጅ ተኮልጆ፤
የተገኘው እውቀት፤
ይኽው ተመልከቱ…
ከውጭ ሲመለስ፣ ከኮሌጅ ሲወጣ፤
ቦቃ በግ ሰውቶ፤
ዛፍ ቂቤ ቀብቶ፤
ንፍሮውን በትኖ፣ እጣኑን አጢሶ፤
ይኽው ተመልሶ፣
ተንበርክኮ ሽቅብ፣ ቱፍታ ይቀበላል፤
መርፌውን ሰክቶ፤
ከድንቁርና ጋር እውቀት ይማማላል፡፡
መጥኔ ለዚች ሀገር!
እውቀትም እንደ ሰው፣
ያለ እድሜው አረጀ፤
ከጠላቱ ጋራ፣ በወግ ተወዳጀ፡፡
አያት ድንቁርና፣ ለምለም አስጨብጠው፤
ለጋ የጊደር ቂቤ፣ ግንባሩን ቀብተው፤
በአምሳላቸው ቀርጸው፣
አውራ ጣት አጠቡት፡፡
ልጃቸውም ሆነ፣ አባት አያት ሆኑት፡፡
ከዚያማ ጋለቡት፣
ሉጋም አበጅተው፣ ለህሊናው መግቻ፤
ለራዕዩ መቀጨት፣ ለህልማቸው መፍቻ፡፡
ለእኩይ እጣ ብሎት፣
 እውቀትም አርጅቶ፤
ይኸው ተመልከቱ፤ ደጅ ተጎልቶ፤
ከድንቁርና ጋር፣ እሳት እየሞቀ፣
እውቀት ተጃጅሎ፡፡
ለአድባር ይሰዋል፤
ለአውልያ ይሰግዳል፤
ያማል፣ ያማል፣ ያማል፣
እውቀት ተጃጅሎ፤
የኦክስፎርድ ዲግሪ፤
ያለማያን ካባ፣ ግርግዳው ላይ ሰቅሎ፡፡
ይብላኝ ለዚች ሀገር!
ይብላኝ ለኢትዮጵያ!
እውቀት ድንቁርና ለተወዳጁባት፣
አንዱ ሲገነባ፣ ሌላው ለሚንዳት፡፡
መጥኔ ለዚች ሀገር፡፡
(1989- ፍካት ናፋቂዎች)




Read 1921 times