Saturday, 06 May 2023 17:50

54 ኤፍ.ኤም.ሲ.ጂ፤ ስያሜውን ወደ” ሳማኑ” መቀየሩን አስታወቀ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ግዙፍ የካፒታል ኢንቨስትመንትና የዕድገት ማስፋፊያ  ዕቅዶችንም ይፋ አድርጓል

ጤና የምግብ ዘይት፣555 የጽዳት መጠበቂያ፣ ኦራ የግል ንጽህና መጠበቂያ ሳሙና፣ሼፍ ሉካ ፓስታና አኳሴፍ የተፈጥሮ ማዕድን ውሃ የመሳሰሉ በርካታ ታዋቂ ምርቶችን ለኢትዮጵያውያን ደንበኞች በማቅረብ የሚታወቀው 54 ኤፍ.ኤም.ሲ.ጂ. የቢዝነስ ግሩፕ፣ ስያሜውን ወደ ሳማኑ መቀየሩን አስታውቋል፡፡
የቢዝነስ ግሩፑ አዲሱን ስያሜውን ያበሰረው፣ ባለፈው ረቡዕ በሃያት ሬጀንሲ፣ የሚዲያ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው፡፡ በዚህ መግለጫ፤ ግዙፍ የካፒታል ኢንቨስትመንትና የወደፊት የዕድገት ማስፋፊያ ዕቅዶችንምኩባንያው ይፋ አድርጓል፡፡ መግለጫውን  የሰጡት የ54 ኤፍ.ኤም.ሲ.ጂ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ሚ/ር ጆአኪም ኢቡዌት፣ የኩባንያው  ማርኬቲንግ ማናጀር ወ/ሮ ዳርቻ መኮንንና  የኩባንያው ማኑፋክቸሪንግ ዳይሬክተር አቶ ኢዩኤል ሸዋንግዛው በጋራ በመሆን ነው፡፡
ኩባንያችን  ጥራታቸውን የጠበቁ የደንበኞች ምርቶችን በማቅረብ ይታወቃል ያሉት ግሩፕ ማርኬቲንግ ማናጀሯ ወ/ሮ ዳርቻ መኮንን፤ “ከምርት እስከ ገበታ ከኢትዮጵያውያን ለኢትዮጵያውያን የሚል መርህ ነው የምንከተለው” ብለዋል፡፡
“ደረጃቸውን የጠበቁ ምርቶችን ለኢትዮጵያውያን ማቅረብ ዋና ዓላማችን ነው” ሲሉም አክለዋል፤ወ/ሮ ዳርቻ መኮንን፡፡ ባለፉት ዓመታት ኩባንያቸው በስኬትና በዕድገት ጎዳና ላይ ሲጓዝ መዝለቁን የገለጹት ግሩፕ ማኑፋክቸሪንግ ዳይሬክተሩ አቶ ኢዩኤል ሸዋንግዛው በበኩላቸው፤ በእነዚህ ዓመታት የተደረጉ የፋብሪካና ማምረቻ ማስፋፊያዎች፣ የተገነቡ አዲስ ፋብሪካዎች፣ እንዲሁም ራሳቸው ማምረት የጀመሯቸው ለድርጅቱ የሚያስፈልጉ ጥሬ ዕቃዎችን በዝርዝር አብራርተዋል፡፡
54 ኤፍ.ኤም.ሲ.ጂ በቅርቡ ኖርፈንድ ከተባለው ታዳጊ አገሮች ላይ አተኩሮ የሚሰራ የኖርዌይ ኢንቨስትመንት ፈንድ የ21 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ማግኘቱ የተገለጸ ሲሆን፤ ይህ ኢንቨስትመንት አዲስ የኤክስፖርት ፋብሪካ ለመገንባትና ከገበሬዎች ጋር በቀጥታ አብሮ በመሥራት የአግሮ ፕሮሰሲንግ አቅሙን ለማስፋት እንዲሁም  በኢትዮጵያ ለምግብነት የሚውል የዘይት ምርትን ለማሳደግ እንደሚውል ተጠቁሟል፡፡
 “በዚህ ኢንቨስትመንትና ተጨማሪ የንግድ ማስፋፊያ ዕቅዶች ምክንያት፣ 54 ኤፍ.ኤም.ሲ.ጂ  የኮርፖሬት ስያሜውን ወደ ሳማኑ መቀየሩን በደስታ ያበስራል” ብሏል፤ ኩባንያው  ዛሬ ባሰራጨው መግለጫ፡፡ ‘ሳማኑ ፕራውድሊ ኢትዮጵያን - ሳማኑ በኩራት የኢትዮጵያውያን’ የሚል ነው አዲሱ ሙሉ ስያሜ፡፡ የሳማኑ አርማ መነሻ ተደርጎ የተወሰደው ከህይወት ምንጭ ‘አባይ ወንዝ’ እና ሣ ከሚለው የአማርኛ ፊደል መሆኑን የሚያብራራው መግለጫው፤ዲዛይኑ የሳማኑን ኢትዮጵያዊ መሰረት ለማጠናከር ያለመ ነው ይላል -ይህም ከፍተኛ ጥራት ያለው የፍጆታ እቃዎችን በማምረት ግንባር ቀደም ኢትዮጵያዊ በመሆን ለዕድገትና መስፋፋት ያለውን ጠኝካራ ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ በመግለጽ፡፡
የሳማኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሚ/ር ጆአኪም ኢቡዌት በሰጡት መግለጫ፤ “ስለመጪው ጊዜ በጣም ደስተኞች ነን፤ ይህ አገሪቱ ያላትን የተትረፈረፈ የተፈጥሮ ሃብትና ተሰጥኦ በመጠቀም የኢትዮጵያውያንን ህይወትና ኑሮ ለማሻሻል ራዕያችንን የምናጎለብትበት መንገድ ነው” ብለዋል፡፡
ከውጭ የተገኘውን ኢንቨስትመንትም በተመለከተ ሲናገሩ፤”አዲሱና ከፍተኛው የውጭ ኢንቨስትመንት በኢትዮጵያ ውስጥ ያለንን ቆይታ በማጠናከር ለሰፋፊው የልማት መንገድ አስተዋጽኦ እንድናደርግ ያግዘናል፡፡ ቀዳሚ ሂደቶችን ወደ ኋላ በማቀናጀት  የኢትዮጵያን ግብርና በሚያዳብርበት ወቅት የተዋቀረ የአገር ውስጥ የምግብ ዘይት ለማምረት ያስችላል፡፡” በማለት አብራርተዋል፡፡“ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት እያደረግንና የማምረት አቅማችንን እያሰፋን ባለንበት በዚህ ወቅት የኩባንያችንን ስያሜና ምልክት መቀየር ለድርጅታችን ዕድገት አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው” ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ “ግባችን በአገር ውስጥ የሚመረቱና የኢትዮጵያ ኩራት የሚሆኑ ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን ምርቶች ማቅረብ ነው” ብለዋል፡፡



Read 1228 times