Saturday, 06 May 2023 17:52

እናት ባንክ “ለእናቴ” የተሰኘ አገር አቀፍ የፅሁፍ ውድድር አዘጋጀ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

እናት ባንክ ማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል የሚሳተፍበትና ዳጎስ ያለ ሽልማት የሚያስገኝ “ለእናቴ” የተሰኘ የፅሁፍ ውድድር ማዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡ ባንኩ ይህን ያስታወቀው ሀሙስ የካቲት 26 ቀን 2015 ዓ.ም ረፋድ ላይ በሀያት ሬጀንሲ ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡ በውድድሩ መሳተፍ የሚፈልግ ማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል ስለ እናቱ የሚሰማውን ስሜት በA4 መጠን ወረቀት ከ3 ገፅ ባልበለጠና ባላነስ ፅፎ መወዳደር ይችላል ተብሏል፡፡
በፅሁፍ ሁሉም ሰው ለእናቱ ያለውን ፍቅር፣ ክብር፣ አክብሮትና ውለታ ግጥም ባልሆነ ነገር ግን በወግ፣ በደብዳቤ ቅርፅ የሚገልፅበትና ለእናቴ የሚልበት መልካም አጋጣሚ እንደሚሆን የባንኩ የማርኬቲንግ ፕሮሞሽንን የደንበኛ አገልግሎት ዳይሬክተር ወ/ሮ አክሊል ግርማ ተናግረዋ፡፡የመወዳደሪያ መስፈርቱና የውድድሩ ዳኝነት በቋንቋና በፅሁፍ ተግባቦት ሰፊ ልምድ ባላቸው ከፍተኛ ባለሙያዎች የተዘጋጀና የሚከናወን እንደሆነም ሀላፊዋ ጨምረው ገልፀዋል፡፡ የፎክሎር ባለሙያና መምህር ገዛኸኝ ፀጋው (ዶ/ር) እና ደራሲና ጋዜጠኛ ቴዎሮስ ተ/አረጋይ በአማካሪነት የሚሳተፉበት ይሄው “ለእናቴ” የተሰኘ የፅሁፍ ውድድር፤ ለጊዜው በአገሪቱ የስራ ቋንቋ በአማርኛ የተዘጋጀ ሲሆን፣ ተወዳዳሪዎች 50 በመቶ የቅርፅ ጉዳዮች፣ 50 በመቶ ደግሞ የይዘት ጉዮች በድምሩ 100 ነጥብ እንዲይዙ ተደርገው መዘጋጀታቸውም  ታውቋል፡፡
ተወዳዳሪዎች ለውድድር የሚያቀርቡት ፅሁፍ ከዚህ ቀደም በሌሎች የህትመት እና ኤሌክትሮኒክስ የመገናኛ ብዙሃን ላይ ያልቀረቡ ወጥ እና አዲስ መሆን ያለበት ሲሆን ፅሁፍ ግልጽና ተነባቢ እንዲሆን በኮምፒዩር ተተይቦ በ12 ፎንት የፊደላት መጠንና በ1.5 የህዳግ መስመር መቅረብ እንዳለበትም ተብራርቷል፡፡ በተጨማሪም ተወዳዳሪዎች ስማቸውንና አድራሻቸውን ለውድድር በሚያቀርቡት ወረቀት ላይ መፃፍ እንደሌለባቸው የተገለጸ ሲሆን  ፅሁፉን አሸገው የሚያቀርቡበት ፓስታ ላይ ብቻ መፃፍ እንዳለባቸው ታውቋል የማስረከቢያ ጊዜው ከሚያዚያ 26 ቀን እስከ ግንቦት 23 ቀን 2015 ዓ.ም እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ተወዳዳሪዎች የመወዳደሪያ ጽሁፋቸውን በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ የእናት ባንክ ቅርንጫፍ በአካል ሄደው ማስገባት ይጠበቅባቸዋል የተባለ ሲሆን በሁሉም አካባቢ እናት ባንክ ተደራሽ ባለመሆኑ Lenate @ enatbankssc.comየኢሜል አድራሻን በአማራጭነት መጠቀም ይቻላል ተብሏል፡፡ በውድድሩ ከ1-3 የወጡ አሸናፊዎች ዳጎስ ያለ የገንዘብ ሽልማትና የእውቅና የምስክር ወረቀት የሚበረከትላቸው ሲሆን አሸናፊዎች የሚሸለሙትን የገንዘብ መጠን የባንኩ ሃላፊዎች ከመግለፅ ተቆጥበዋል፡፡ አሸናፊ ፅሁፎችን ባንኩ ለተለያየ ጉዳይ ሊጠቀምባቸው ይችላል የተባለ ሲሆን ውድድሩ ማንኛውም እናቱን የሚወድ ሀሳቡን የሚገልፅበት እንጂ ፕሮፌሽናል የስነ ፅሁፍ ወድድር አለመሆኑን የፕሮጀክቱ አማካሪዎች በአፅንኦት ገልፀዋል፡፡
“ለእናቴ” የተሰኘው ይሄው ውድድር በየዓመቱ አይነቱን እየቀያየረ የባንኩ አንድ መለያ ሆኖ እንደሚቀጥልም ታውቋል፡፡ እናት ባንክ ማህበረሰቡ ከሚወዳደርበት በተጨማሪ የባንኩ ሰራተኞች ብቻ የሚወዳደሩበት መርሃ ግብርም እንደሚኖረው ተብራርቷል፡፡ እናት ባንክ በአሁኑ ወቅት ከብር ሁለት ቢሊዮን በላይ የተከፈለ ካፒታል ባለቤት ሲሆን ከ60 በመቶው በላይ ድርሻ የሴቶች መሆኑንና በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች 137 ቅርንጫፎችን ከፍቶ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት እየሰጠ ስለመሆኑ ያብራሩት የባንኩ ሃላፊዎች፤ ባንኩ በተለይም ለሀገራችን ባለውለታ እንቁ ሴቶች በስማቸው ቅርንጫፍ እየከፈተ ስራውን መቀጠሉ ልዩ ያደርገዋል ተብሏል፡፡


Read 1805 times