Saturday, 06 May 2023 18:26

“ዕዳ የሌለበትን ድህነትና፣ በሽታ የሌለበትን ክሳት የመሰለ ነገር የለም”

Written by 
Rate this item
(7 votes)

አንድ የስፓኒሾች ተረት አለ፡፡
ከዘመናት በፊት አንድ ንጉስ፣ ያለ የሌለ ገንዘቡን አዳዲስ ልብስ በማሰፋት ያጠፋ ነበር፡፡ ወደ አደባባይ አዲስ ልብስ ለብሶ ብቅ እንደማለት የሚያስደስተው ነገር የለም፡፡ አዲስ ልብስ ከመውደዱ የተነሳ “ሌሎች ንጉሶች ወደ ጦር ሜዳ ሲውሉ፣ ፈረስ ጉግስ ሲጫወቱ፣ እሱ ከመልበሻ ክፍል ውስጥ ይገኛል” እየተባለ ይታማ ነበር፡፡  
አንድ ቀን ሁለት ብልጥ ሸማኔዎች ወደ ንጉሱ ከተማ ይመጣሉ፡፡ ምርጥ ልብስ ለመስፋት እንደሚችሉም ይናገራሉ፡፡ በተለይም ደግሞ እነሱ የሚሰሩት ልብስ፤ ሌቦች የሆኑ እና የስራ ብቃት የሌላቸው ሰዎች ሊያዩት የማይችሉት ተዓምረኛ የሆነ ልብስ መሆኑን በኩራት ያስረዳሉ፡፡ የዚህ ተዓምረኛ ልብስ ወሬ ንጉሱ ጆሮ ይደርሳል፡፡ ንጉሱም “እንዲህ ያለ ልብስ ቢኖረኝ እኮ፣ ይታይሃል አይታይህም እያልኩ የትኛው ባለስልጣን ሌባና ለስራው ብቃት የሌለው መሆኑን ለማረጋገጥ እችላለሁ” ሲል ያስብና ሁለቱንም ሸማኔዎች አስጠርቶ  ብዙ ገንዘብ ሰጥቶ፣ “በሉ በልኬ ልብስ ስሩልኝ!” ሲል ያዛቸዋል፡፡
ልብስ ሰፊዎቹም የሸማኔ እቃቸውን ዘርግተው ሲያበቁ እጅግ ውድ የሆነ ሀርና ወርቅ እንዲቀርብላቸው ይጠይቃሉ፡፡ ያሉት ይፈጸምላቸዋል። ያንን ሃርና ወርቅ ይደብቁና እንደሚሸምን ሰው ባዶ እጃቸውን እያንቀሳቀሱ እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ይቆያሉ፡፡
 የስራቸው ሁኔታ የት እንደደረሰ ለማወቅ የፈለገው ንጉስ፣ ወደ ሸማኔዎቹ ሊሄድ ፈለገ። “ድንገት ተዓምረኛው ልብስ አልታይ ካለኝስ?” በሚል ስጋት እራሱን ተጠራጠረና ሁለት ታማኝና ለስራ ቦታቸው ብቃት አላቸው የሚላቸውን ባለስልጣኖቹን “ሂዱ እስቲ አጣሩና ኑ!” ብሎ ይልካቸዋል፡፡ ሁለቱ ባለስልጣኖች ሸማኔዎቹ ክፍል አጠገብ ሲደርሱ፣ “አንተ ግባ! አንተ ግባ!” በመባባል ይጣላሉ፡፡ በመጨረሻ እጣ ያወጣሉ፡፡ እጣ የወጣለት ቀድሞ ይገባል፡፡ ሸማኔዎቹ ባዶ እጃቸውን እያወናጨፉ ስራ ቀጥለዋል፡፡ ባለስልጣኑ ምንም ልብስ አይታየውም፡፡ አይኑ እስኪፈርጥ ከፍቶ ተመለከተ፡፡ ምንም ልብስ የለም፡፡ ሸማኔዎቹም “ጌታዬ እንዴት ያለ ግሩም ቀለም ያለው ምርጥ ልብስ አይታይዎትም? ቀረብ ይበሉና ያስተውሉት?” ሲሉ ይጠይቁታል፡፡ ባለስልጣኑም “አሁን እኮ ይሄ ልብስ አይታየኝም ብል ሌባና ለስራው ብቁ ያልሆነበት ሹመት ላይ የተቀመጠ ሰው ነው ልባል ነው” ሲል ያስብና “እጅግ ድንቅ ልብስ ነው! ይህንኑ ለንጉሱ እነግራቸዋለሁ። በበኩሌ ስራችሁ በጣም አድርጎ አስደስቶኛል!” ሲል ይዋሽና ይወጣል፡፡ ሁለተኛው ባለስልጣንም ልክ እንደ በፊተኛው ባለስልጣን ያለ ሁኔታ ያጋጥመዋል፡፡ ግን እሱም “ሌባና ለስራው ብቃት የሌለው ነው” እባላለሁ ይልና “ግሩም ድንቅ ልብስ ነው!” ብሎ ይመልሳል፡፡
ሁለቱም ባለስልጣኖች ለንጉሱ ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ አይነት ልብስ እየተሰራ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ንጉሱ ይደሰታል፡፡ ሸማኔዎቹ ተጨማሪ ብርና ሃር እንዲሁም ወርቅ ይጠይቃሉ፡፡ ንጉሱ በደስታ ይፈቅዳል፡፡ እንደገናም ሌሎች ባለስልጣኖች ይልካል፡፡ መልሱ የተለመደ ይሆናል፡፡ እንደውም በክብረ በአሉ ወቅት በአደባባይ ለብሶ መታየት እንዳለበት ከባለስልጣኖቹ ምክር ያገኛል፡፡ ቀስ በቀስ ወሬው ወደ ከተማው ህዝብ ተዛመተ፡፡ በየነገዱ በየጎሳው በየቋንቋው ስለልብሱ ተአምረኛነት ተነገረ፡፡ ንጉሱ ገና ልብሱ ሳያልቅ ለሸማኔዎቹ የወርቅ ሜዳልያ ሸለመ፡፡
ሸማኔዎቹ እያነጉ ይሰሩ ጀመር፡፡ ክብረ በአሉ ከመድረሱ በፊት መጨረስ አለብን እያሉ ሲጣደፉ ይታያሉ፡፡ ልብሱ ግን ለማንም አይታይም፡፡ የተለያየ የልብስ ዲዛይን እንደሰፉ ሁሉ ተራ በተራ ባዶ እጃቸውን እያነሱ መስቀያው ላይ ሲሰቅሉ ይታያሉ፡፡ በመጨረሻም “ልብሶቹ ተሰርተው አልቀዋል!” ሲሉ አወጁ፡፡ የክብረ በአሉ ቀን ንጉሱ ወደ ሸማኔዎቹ በአጀብ መጣ፡፡ ሸማኔዎቹም በተራ በተራ ባዶ እጃቸውን ከፍ እያደረጉ፤ “ይሄው ቦላሌው! ይሄው ኮቱ! ይሄው ሸሚዙ! ይሄው ባለወርቅ ዘቦ ካባ! ይሄው የራስ ማሰሪያው! ከሸረሪት ድር የቀለሉ፣ ለሌባና ለስራው ብቃት ለሌለው ሰው የማይታዩ ምርጥ ልብሶች!” አሉና በኩራት ተናገሩ፡፡ የንጉሱ አጃቢዎች ምንም ባይታያቸውም፣ ሌባና ብቃት የለሽ ከምንባል በሚል “በጣም ምርጥ ልብሶች ናቸው!” አሉ፡፡
ሸማኔዎቹ ወደ ንጉስ ዞረው “ይበሉ ወደ መስታወቱ ይምጡና ይለኩዋቸው!” አሉ፡፡ ንጉሱ ልብሶቹን ሁሉ አወለቀና ወደ መስታወቱ ቀረበ፡፡ ሸማኔዎቹ አንድ በአንድ ልብስ የሚያለብሱ መሰሉ፡፡ በመጨረሻ ንጉሱ ወደ መስታወቱ ዞረ፡፡ በዙሪያው የተሰበሰበ ሰው ሁሉ፤ “ንጉስ ሆይ እንዴት አማረብዎ! ላይዎ ላይ የተሰፋ እኮ ነው የሚመስለው! እንዴት ያለ ቀለም፣ እንዴት ያለ ምርጥ ስፌት!” እያለ አድናቆቱን ገለፀ፡፡ “ሰረገላው ቀርቧል ንጉስ ሆይ!” አለ  ባለሟል፡፡
ንጉሱ “ዝግጁ ነኝ!” አለና አንዴ ወደ መስታወቱ ተመለከተ፡፡ መለመላውን ነው፡፡ ግን - እንዴት ልብሱን አይታየኝ ይበል? “አረረረረ! እንዴት አምሮብኛል ጃል!” እያለ ሰረገላው ላይ ወጣ፡፡ አጃቢዎቹ በክብር ተከተሉ፡፡ ወደ ተሰበሰበው ህዝብ ሲቃረብ ንጉሱ እራቁቱን ተነስቶ ቆሞ እጁን እያውለበለበ ለህዝቡ ሰላምታ ይሰጥ ጀመር፡፡ ህዝቡም፤ “ንጉሳችን እንዴት ያለ ድንቅ ልብስ ለብሰዋል! ታይቶ የማይታወቅ፣ በልካቸው የተሰፋ ምርጥ መጎናፀፊያ!” እያለ አጨበጨበ፡፡ ማንም ምንም ልብስ አይታየኝም ለማለት አልደፈረም፡፡ ሌባና ብቃት የለሽ እንዳይባል ነዋ!
በመካከል ግን አንድ ህፃን ልጅ፡-  “እንዴ! ንጉሱ እራቁታቸውን ናቸው!” አለ፡፡
ይሄኔ የልጁ አባት መተንፈሻ በማግኘቱ “የሰማያቱ ያለ! የዚህን የየዋህ ልጅ ድምፅ ሰማችሁልኝ” ብሎ ልጁ ያለውን አጠገቡ ላለው ሰው ይነግረዋል። ያኛውም “ንጉሱ እራቁታቸውን ናቸው አለ እኮ ያ ልጅ!” ሲል አስተጋባ፡፡ ከመቅፅበት “ንጉሱ እራቁታቸውን ናቸው!” ይል ጀመር የተሰበሰበው ህዝብ፡፡
ንጉሱ ደነገጠ፡፡ ሰው የሚለው እውነት መሆኑን አውቋል። ነገር ግን “ክብረ-በአሉ በወጉ መቀጠልና ማለቅ አለበት!” አለ ለራሱ፡፡ ስለዚህ የበለጠ በኩራት ይንጎማለል ጀመር፡፡ ህዝቡ ቀስ በቀስ እያንሾካሸከ እየተመናመነ ወደ ቤቱ ሄደ፡፡ በግርግሩ ማህል ሸማኔዎቹ ሃርና ወርቁን ይዘው ጠፉ።
***
ኢትዮጵያ እውነቱን የሚናገር ህፃን ልጅ ትፈልጋለች፡፡ ያየውን በግልፅ የሚናገር ሰው ትሻለች፡፡ ከልሂቅ እስከ ደቂቅ ያለው ህዝብ ያልነበረው እንደ ነበረ፣ የሌለው እንዳለ አድርጎ የሚያምንበት ሥርአት ከተፈጠረ አገር ከፍተኛ አደጋ ላይ ናት ማለት ነው፡፡ ንጉሱም፣ መኳንንቱም የሌለ መጎናፀፊያ ተላብሰው፤ በተራቆተች አገር ላይ፣ የተራቆቱ ባለስልጣናት፣ የተራቆተ ህዝብ የሚመሩበት የእውር - የድንብር እና፣ የአስመስሎ ማደግ ዘመን ውስጥ ይኖራል ማለት ነው፡፡ ከዚህ ይሰውረን! እርቃኑን ያለውን የሀገር ኢኮኖሚ በሸማኔዎች ተዓምራዊ ልብስ መሸፈን እንደማይቻል በግልፅ እያየን ነው፡፡ ይህን ቀደም ብለው ያዩ፣ የማስጠንቀቂያ ደውል የደወሉ አያሌ እንደነበሩን አይተናል- የሚሰማ ጆሮ ቢያጡም፡፡ “አስደንጋጭ የድህነት አደጋ”፣ “የመበተን አፋፍ” የአንድ ጀምበር እርቃናችን አይደለም፡፡ አገርም በአንድ ምሽት እንደማትገነባ ሁሉ በአንድ ምሽት የማስጠንቀቂያ ደውል አትፈረካከስም፡፡ ሙሰኛ ሁሉ ሌብነቱና የስራ ብቃት ማጣቱ እንዳይታወቅበት “በሀር አሽማት ወገቧን!” ሲላት እንዳልከረመ፣ ሲጨንቀው ደግሞ “አገር ያየህ ና ወዲህ በለኝ!” ማለቱ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው፡፡ በአንፃሩ ነገሩ ሁሉ በመጨረሻ ሰአት “ከፊት አጫውተው፣ ከኋላው ዝረፈው!” ለመሆኑ የሀገራችን የለውጥ ዋዜማ ሰአታት ሁሉ የእርዱን ጥሪ መርዶ ሲነግሩን እንደሰነበቱ አንዘነጋም፡፡ ያለፉት የሀገራችን መሪ “መርከቡ ሲሰጥም አይጦች ከየጉሬያቸው ብቅ ይላሉ” ብለው ነበር ፡፡ ዛሬ የምንሰማው ደግሞ “የሚሰምጥ ሰው ሳሩንም ቅጠሉንም ለመጨበጥ ይፍጨረጨራል” የሚል ነው፡፡ (A drowning man catches a straw ነው ነገሩ) የኢኮኖሚያችን የመጨረሻ እንጥፍጣፊ የድህነታችን ልዩ አዋጅ በሆነበት በአሁን ሰአት፣ ከቶ መመለሻውና ማጣፊያው ያጠረበት የራቁት ጉዞ ይመስላል፡፡ የመበታተንና የድህነት አደጋ ጎላ ብሎ መገለፁ ለሌላ ኢላማ ቢሆንስ ብሎ መጠራጠር ግን መቼም አይቀሬ ነገር ነው፡፡ ስር በሰደደና በብሩህ መንገድ ሳይገለፅ የሰነበተ የብራ-መብረቅ ይመስላልና ለምን አሁን ድንገት ናዳ ወረደ ማለት የአባት ነው፡፡
የፖለቲካ ድርጅቶች እርቃንዋን የቆመችውን አገር ከመቀመቁ ለማውጣት ምን እናድርግ ከማለት ይልቅ የ“ማን ይምራት ማን ይምራት” የሃሳብ አውጫጭኝ ላይ ያተኮሩ ይመስላል፡፡ ይህም ሌላ እርቃን ነው፡፡ የአዲስ ልብስ ሽመናውን የተያያዙ ብልጣ ብልጦችም፣ የማይታይ ተዓምራዊ ልብስ እንሰራለን የሚል ማስታወቂያ እያስነገሩ የሚገበዙ ይመስላል፡፡ ያደረ-አፋሽ የሚመስሉ አዲስ ድግ በአሮጌ ወገብ ላይ ያሰሩ የሚመስሉ ቡድኖችንም የስልጣን ዛር ያገረሸባቸው ይመስላል፡፡ ባለሟሉም፣ ባለስልጣኑም፣ ንጉሱም፣ህዝቡም ፓርቲዎቹም የማይታየውን ልብስ ለመደረብ ከመጣር ይልቅ እርቃናችንን ቀርተናል እና፣ ሌባውን “ሌባ ነህ!” ብለን፣ ብቃት የሌለውን “ብቃት የለህም!” ብለን የተራቆተችውን አገር ፖለቲካዊ ልዩነትን አቻችሎ ለኢኮኖሚ ድቀቷ መፍትሄ መሻት አንገብጋቢ ነው፡፡ ከእንግዲህ ጩኸቴን ቀሙኝ ብሎ መጮህ ሌላ ጩኸት እንጂ ሁነኛ መፍትሄ አያመጣም፡፡
በአንድ ወገን በመዋቅርም ከመዋቅርም ውጪ “የመነኩሲት ምርኩዝ፣ ከላይ ባላ ከታች ዱላ” እንዲሉ ሰራተኛው መከፋቱ፣ በሌላ ወገን “ስለ ሃብታም ይሰበሰቡና በደሃ ላይ ይፈርዳሉ” እንዲሉ፤ የአብዬን ለእምዬ (Blame-shifting ) እየበረከተ እውነተኛው ድህነት ምናችን ጋ እንደሆነ እንዳናይ መሆናችን መባባሱና የወትሮውን ሙሾ ማውረድ መቀጠሉ ለማንም አይበጅም፡፡ የፖለቲካው ደጃፍ ተከርችሞ የኢኮኖሚ መሶብ አይሞላም የምንለውን ያህል፣ ልባችንን በቂም አጥረንም ሰላማዊ የችግር መፍቻ ዘዴ አይገኝም ማለትም ዛሬ ግድ ሆኗል፡፡
በአንፃሩ ደግሞ ለየአቋም ድህነታችን ሰበብ ፍለጋ ደቃቁንም፣ አንኳሩንም ጉዳይ እያነሳን “እንኳንስ መዞሪያ ነጠላ አግኝታ፣ ድሮም ዘዋሪ እግር ነው ያላት” እንደሚባለው፤ ለአቤቱታ ብቻ ብንሰለፍ አገርን የማዳን ሃላፊነትን ከመሸሽ በቀር የረባ እርምጃ አይዋጣልንም፡፡
ጉዳዩ ገሃድ ነው፡፡ የእውቀት ድህነት፣ የጥበብ ድህነት፣ የመቻቻል ድህነት፣ አርቆ የማስተዋል ድህነት፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ የኢኮኖሚ ድህነት አንድ ላይ ተደማምረው የድህነት ጌቶች አድርገውናል፡፡ በሁሉም አቅጣጫ እጅግ አሳሳቢ የድህነት ወለል ላይ ተንጋለን ነው የምንገኘው፡፡ የብዙ ሀገራዊ እዳ ጥርቅም ጫንቃችን ላይ አለ፡፡ ከተንጋለልንበት ወለል “በቀኝ አውለን” ብለን ቀና ለማለት በየአቅጣጫው ያከማቸነውን እዳ እንከፍል ዘንድ ቢያንስ “እዳ የሌለበትን ድህነትና በሽታ የሌለበትን ክሳት የመሰለ ነገር የለም” የሚለውን የወላይታ ተረት እንደ እለት ፀሎት ማስታወስ ይገባናል፡፡

Read 1767 times