Saturday, 20 May 2023 15:03

የቁጫ ህዝብ ዴሞክራሲዊ ፓርቲ ገዢውን ፓርቲ ወቀሰ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 የብልፅግና አመራሮች የም/ቤት አባላትን “ም/ቤቱን ለቃችሁ ውጡ” እያሉ ነው


         ብፅግና ፓርቲ፤ በደቡብ ክልል ህዝብ ም/ቤት፣ የቁጫ ህዝብ ተወካዮች የሆኑ የም/ቤት አባላትን “ከም/ቤት አባልነት አሰርዣችኋለሁ” በማለትና ደብዳቤውን ለሚዲያ በማሰራጨት በቁጫ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አመራሮችና አባላት ላይ የሰብአዊ የመብት ረገጣ እየፈጸመ ነው ሲል ከሰሰ።
ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም በተካሄደው አገራዊና ክልላዊ ምርጫ፣ በቁጫ ምርጫ ክልል የብልፅግና ፓርቲን ጨምሮ ሰባት የፖለቲካ ፓርቲዎች ቢወዳደሩም የቁጫ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቁሕዴፓ) ያቀረባቸው ዕጩዎች በአብላጫ ድምጽ ማሸነፋቸውን ያመለከተው ፓርቲው፤ ውጤቱን ከብልጽግና ፓርቲ ውጭ ያሉ ፓርቲዎች በጸጋ መቀበላቸውን ይገልፃል።
በተቃራኒው ብልፅግና ፓርቲ በምርጫ በመሸነፉ ምክንያት አኩርፎ በርካታ የምርጫ ሥነ-ምግባር ጥሰቶችን በመፈጸም መራጭ ህዝቡንና በየደረጃው ያሉ የቁህዴፓ አባላትን በማሰር፣ በመደብደብና በገንዘብ በመቅጣት በሃይል ከፓርቲው እንዲወጡ አስገድዷል ብሏል- ፓርቲው። የቁጫ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ቦሌ በሚገኘው የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት ቢሮ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ የቁሕዴፓ አመራርና አባላት በብልፅግና ፓርቲ እየደረሰባቸው ነው ያለውን ሰብአዊና ዲሞክራሲዊ መብት ረገጣ በዝርዝር ገልጿል።
በምርጫው መሸነፉን ተከትሎ፣ የቁጫን የህዝብን ቀልብ መሳብ ያልቻውና የህዝብን ድጋፍ ይሁንታ ያላገኘው የብልፅግና ፓርቲ፣ ከህግ አግባብ ውጭ የቁህዴፓ አመራርና የደቡብ ክልል ሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የቁጫ ህዝብ ተወካዮች የሆኑ ሦስት የም/ቤት አባላትን “ከምክር ቤት አባልነት አሰርዣለሁ” የሚል ደብዳቤ በተለያዩ ሚዲያዎች ማሰራጨቱን የጠቆመው ቁህዴፓ፤ ይህም ሳይበቃው በቁጫ ምርጫ ክልል በሁሉም መዋቅሮች “የቁህዴፓ ተወካዮች ከም/ቤቱ ተባርረዋል” በማለት የደስታ መርሃ ግብር በማሰናዳት ተወካዮቹን በመረጠው ህዝብና  በፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች ዘንድ ቁጣና ግጭት እንዲፈጠር የተለያዩ ቀስቃሽ ድርጊቶችን በመፈጸም ላይ ይገኛል” ብሏል- በመግለጫው።
“የደቡብ ክልል ም/ቤት፤ አንድ አባል ከም/ቤት አባልነት ሊወጣ የሚችልበት የህግ አሰራና ሂደትን በሚጣረስ መልኩ “የቁጫ ህዝብ ተወካዮች ከክልል ም/ቤት አባልነት ተሰርዛችኋል” በማለት ያሰራጨው ደብዳቤ፣ የምርጫ ህግና ሥርዓት ዋጋ እንዲያጣ ብሎም በሃገራችን የተጀመረው ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና መድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንዲገባ የሚገፋፉ ኢ- ህገመንግስታዊ ድርጊት ነው።” ሲል ኮንኗል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ተባባሪ ፕ/ር ገነነ ገደቡ በቁጫ ሰላምበር የግድያ ሙከራ ሲደረግባቸው ም/ቤቱ ምንም አለማለቱ ጥሩ መልዕክት የሚያስተላልፍ አይደለም ለምክርቤቱም ክብር የሚመጥን አይደለም ሲል ፓርቲው አማርሯል።“ይህ አድራጎት በሰላማዊ ትግል መስመር ብዙ ጫናዎችን አልፎ ይወክለኛል ያላቸውን ተወካዮቹን ለውክልና ያበቃውን ህዝብ በእጅጉ መናቅና ከህገመንግስቱ ድንጋጌዎች ጋር በእጅጉ የሚቃረን እንዲሁም በአገራችን የዲሞክራሲ ስርዓት ዕድገትን ለማምጣት የምናካሂደውን ጥረት የሚያጨናግፍ ነው” ብሏል- ፓርቲው።
በሌላ በኩል በደቡብ ክልል በጋሞ ዞንና በቁጫ ሦስቱም መዋቅሮች የብልፅግና ፓርቲ ገና ሊካሄድ የታቀደውንና በብዙዎች ዘንድ ተስፋ የተጣለበትን የሃገራዊ ምክክር ሂደትን ዋጋ የሚያሳጣ የሴራ ድራማ ላይም መትጋቱን ቁህዴፓ ይገልፃል።
በዚህም መሰረተ ብልፅግና “ሚያዚያ 28 እና 29 ቀን 2015 ዓ.ም በአርባ ምንጭ በቁጫ ሰላምበር ከተሞች  “የቁጫ ህዝብ የእርቀ ሰላም ኮንፍረንስ” ማካሄዱን የጠቀሰው ቁህዴፓ፣ የቁጫ ህዝብ ህጋዊ ተወካይ  ሆን ተብሎ ባልተጋበዘበት ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ማንም ባልተሳተፈበት፤ የምክክር ተግባራትን እንዲያከናውን ሥልጣን የተሰጠው የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን በማያውቀው መልኩ፣ የገዛ ራሱን ካድሬዎች ሰብስቦ መላውን መራጭ ህዝብ በአስነዋሪ ሁኔታ በሚያንኳስሱ መፈክሮች የተሞላ ጉባኤ ማድጉን በመግለጫው አመልክቷል።
“ገዢው ፓርቲ ብቻውን ተሰብስቦ ራሱ አጥፊ፣ ራሱ አስታራቂ፣ ራሱ ከራሱ ጋር ታራቂ የሆነበትንና የቁጫ ህዝብንና በቁጫ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ሃይሎችን ያላማከለ “ድራማ” መሰራቱ ሳያንስ፤ ጉባኤውን “የህዝብ ሃሳብ የተንጸባረቀበት ነው” በሚል ለፌደራል መንግሥት ባለስልጣናት ሪፖርት  ማድረጉ ከባድ የማጭበርበር ተግባር ነው ሲል ወቅሷል- ፓርቲው። ከዚህ አንፃር የሚመለከታቸው የፌደራል መንግስት አካላት ተደርጓል የተባለውን የእርቀ ሰላም ሂደት ምን ይመስል እንደነበር  በገለልተኛነት እንዲያጣሩም ጥሪ አቅርቧል።
እነዚህን መሰል ኢ-ሰብአዊና ህገ-መንግሥታዊ ተግባራት በጋሞ ዞን ባሉና ተፎካካሪ ፓርቲዎች የህዝብ ይሁንታ ባገኙባቸው የቁጫና የዛይሴ ምርጫ ክልሎች በገዢው ፓርቲ ትውልድ ይቅር የማይሉት በደሎች እየተፈጸሙ ናቸው ያለው ቁጫ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፤ በእነዚህ አካባቢዎች ገዢው ፓርቲ ሰላማዊ ትግልን ወደ ጎን የመተውን አካሄድ ትቶ፣ ለማናቸው የህዝብ ጥያቄዎች ጆሮ እንዲሰጥ እንዲሁም፣ የታችኛው የመንግስት ባለስልጣናትን ገደብ ያጣ አምባገነንነትና ሌብነት እንዲያስቆም እንጠይቃለን ብሏል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ማንም እየተነሳ የምክር ቤት አባላትን “የምክር ቤት መታወቂያ ካርዳችሁን ተመላሽ አድርጋችሁ ም/ቤቱን ለቃችሁ ሂዱ” እያሉ ኢ-ህገመንግሥታዊ ብይን እንዳይሰጡ መንግስት የማያዳግም እርምጃ ፓርቲው፤ የብሄር ማንነትና የራስ አስተዳደር የህዝብ  ጥያቄዎችም በህገ-መንግስቱ መሰረት አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጣቸውና በመላ አገሪቱ እውነተኛ ፍትህን ማረጋገጥ እንዲቻል ጥሪውን አቅርቧል።

Read 849 times