Saturday, 20 May 2023 15:13

የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች በክልሉ ጉዳይ ላይ እየመከሩ ነው

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(4 votes)

  ክልሉን መሪ በማሳጣትና የህዝቡን ሰላም በመናድ የሚመጣ ውጤት የለም
            
     ባለፉት ወራት በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ሲናጥ የከረመው የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች በክልሉ ጉዳይ ላይ እየመከሩ መሆኑ ተገለፀ፡፡ የክልሉ ርዕስ መስተዳደር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ፣ በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር እንደገለፁት፤ የአማራ ህዝብ ጥያቄዎቹን እንደገና በአግባቡ ሊያጤንና ሊፈትሽ ይገባል ብለዋል፡፡ ህዝቡ ነባርና ያልተመለሱ ጥያቄዎች  እንዳሉት ያስታወሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የህዝቡ ጥያቄዎች ምላሽ የሚያገኙበት መውጫ መንገድ ማስቀመጥ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
የክልሉ ነባር ጥያቄዎች ተብለው በርዕሰ መስተዳድሩ የተገለጹት ጉዳዮች፤ የማንነትና ወሰን ጥያቄ፣ የህገመንግስት ማሻሻያና የብሔሩ ተወላጆች በማናቸውም የአገሪቱ ክልሎች የመኖር መብት መከበር የሚሉት መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡
ገዢው ፓርቲ ብልፅግና የህዝቡን ጥያቄ በመመለስ ሂደት ላይ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ፤ በክልሉ ህዝብና በመሪ ድርጅቱ መካከል አለመተማመን እንዲጎለብት የሚሰሩ ፅንፈኛ ኃይሎች መኖራቸውንም ተናግረዋል፡፡
በአማራ ክልል ውስጥ የአመራሮች መገደል መደጋገሙን የተናገሩት ዶ/ር ይልቃል፤ “ክልሉን መሪ በማሳጣትና የህዝቡን ሰላም በመናድ የሚመጣ ዉጤት አይኖርም፤ አመራሮችን በመግደል የክልሉን ችግር መፍታት አይቻልም ብለዋል፡፡ የክልሉ ገዥ ፓርቲ አማራ ብልጽግና የህዝቡን ጥያቄዎች እንዲመለሱ ለማድረግና የአማራን ህዝብ ጥቅሞች ለማስከበር በሚጥርበት ወቅት እንቅፋት አጋጥሞታል ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ “ባለቤታቸው ያልታወቁ” ባሏቸው አድማና አመፆች ሳቢያ አመራሩ ለጥያቄዎቹ አስፈላጊው ግብና  ስልት እንዳይኖረው ተደርጓል ብለዋል፡፡
ከትናንት በስቲያ በባህርዳር ከተማ የተጀመረውና በአማራ ህዝብ ጥያቄዎች ላይ ትኩረቱን ያደረገው ጉባኤው በማጠናቀቂያውም በርዕሰ ጉዳዮቹ ላይ መክሮ ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

Read 2300 times