Saturday, 20 May 2023 20:12

ሦስት የልጆች መጻሕፍት በብሬይል ተዘጋጁ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 ነገ በአብርሆት ቤተ መጻሕፍት ይመረቃሉ


         በልጆች መፃሕፍት ደራሲነቷ በምትታወቀው ሳምራዊት አርአያመድህን መርሻ የተዘጋጁ ሦስት የአማርኛ የብሬይል የልጆች መፃሕፍት በነገው እለት በአብርሆት ቤተ-መፃህፍት ከጠዋቱ 3፡30 እስከ 5፡00  እንደሚመረቁ ተገለፀ፡፡
ከዚህ ቀደም 14 የልጆች መፃሕፍትን ያሳተመችው  ደራሲ ሳምራዊት፤ አሁን ደግሞ ከዚህ በፊት ያሳተመችውን ሁለት መፃህፍት (ቡጉሊ ትንሿ ፍየል) እና (ዲባዲና ውሻው ዶቢ) እንዲሁም አንድ አዲስ መፅሐፍ (ባተሌዋ ባጃጅ) የተሰኙት ማየት ለተሳናቸው ልጆች በብሬይል መዘጋጀታቸውን ገልጻለች፡፡
በነገው እለት በሚከናወነው የምርቃት ሥነስርዓት ላይ ማየት የተሳናቸው ልጆችና ሌሎች ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር የሚሳተፉበት  የንባብ  ዝግጅት የተሰናዳ ሲሆን ደራሲዋ  በብሬይል የተዘጋጁትን መጻሕፍት ማየት ለተሳናቸው ልጆችና ለቤተመጻሕፍት በነጻ እንደምታድል ተናግራለች፡፡
“ይህንን ለማድረግ ለረጅም ጊዜ እያሰብኩ ነበር.፤ከዚያም ሁለቱን መጻሕፍት  አዘጋጀሁና ለአንዲት ጓደኛዬ  እቅዴን ስነግራት ይህንን አላማ መደገፍ እንደምትፈልግ  ነግራኝ በእሷ ድጋፍ  ሦስተኛ  መጽሐፍ መጨመር ቻልኩ።” ብላለች፤ደራሲ ሳምራዊት፡፡
“የሚቀጥለው ግቤ ሁሉንም መጻሕፍቶቼን ወደ ብሬይል መለወጥና እነሱን የሚመስሉ ገፀ-ባህሪያት ያሉባቸው መጻሕፍት ማዘጋጀት  ነው”  የምትለው ደራሲዋ፤ “በዚህ አጋጣሚ ጓደኛዬን ትህትና አየለን ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡” ትላለች፡፡
መጻሕፍቱን  ማየት ለተሳናቸው ልጆች  የሚፈልጉ ወይም ይህንን ፕሮጀክት የመደገፍ ፍላጎት ያላቸው ደራሲዋን  በፌስቡክ ገጿ በኩል ማግኘት ይችላሉ፡፡  
 https://www.facebook.com/KidsbooksEthiopia
https://twitter.com/samraraya



Read 1449 times