Saturday, 27 May 2023 17:49

ወደ መክሊት ሽሽት፤ ‹‹ራስ››

Written by  -ዮናስ ታምሩ ገብሬ-
Rate this item
(1 Vote)

”--ደራሲ በትረካ ዐውድ ውስጥ፣ ወይም በሚቀርጸው ገጸ-ባሕርይ አስገዳጅነት ያልነበሩና አዳዲስ ተረቶችን፣ ምሳሌዎችን፣ አፈ-ታሪክን የመፍጠር ዕድሉ ሰፊ ነው። ‹‹ራስ›› በርካታ አፈ-ታሪኮች፣ ተረትና ምሳሌዎች፣ ሥነ- ቃል እና ምሳሌያዊ አነጋገሮች የተፈጠሩበት ልብ-ወለድ ነው።--”
        
            መነሻ - ‹‹ራስ›› የደራሲ ፍሬ ዘር ሥራ ነው፤ በ275 ገጽ ዕድሜው በነጠላ ውጤት የተቋጨ ልብ-ወለድ ሲሆን፣ በዋና ገጸ-ባሕርይው (በራስ) ተራዳኢነት እየታገዘ ጭብጡን ተርኳል። ‹‹ራስ›› ለምርጫችንና ለመክሊታችን ቁብ የማይሰጠውን የትምህርት ሥርዐት በወጉ የሚያስቃኝ ድርሰት ነው ብዬ አምናለሁ። በድርሰቱ ውስጥ ‹‹ራስ›› የተባለ ብላቴና በአንገሽጋሹ የትምህርት ሥርዐት ምክንያት አልጋው ቀጋ ይሆንበታል፤ እክፍል ተገኝቶ ትምህርት ከሚከታተል በደዌ ተሰቅዞ የአልጋ ቁራኛ ቢሆን ይመርጣል። ታዲያ ይኼ ብላቴና ያልተጠራበት ድግስ እንደሚቀላውጥ ሰው ውርክብ ውስጥ ይዘፈቃል። ቆሞ መሄድ ሳይችል ብዙ ቁምነገር ይጠበቅበታል፤ ውጤታማ ሊሆን ባለመቻሉ ወደ አያቶቹ ቀዬ ይከተታል - ወደ ገጠር። እዚያ ዛፍ ተካይ ሆነ፤ በትምህርቱ ቢወቀስም መንደሩንና ሀገሩን ታደጋቸው። ‹‹ራስ›› ከተነባቢነት በተረፈ በርከት ያሉ ረድኤቶችን ጀባ የሚለን ድርሰት ነው የሚል እምነት አለኝ። እንሆኝ…
     ሽፋን እና ርእስ - የመጻሕፍ ሽፋኑ ሙሉ በሙሉ ዋናውን ገጸ-ባሕርይ ‹‹ራስ››ን የመግለጽ ሙከራ ነው። ሽፋኑ እንደምንመለከተው የገጸ-ባሕርይውን ሥራ/ተግባር በከፊል ይወክላል ብዬ አምናለሁ። ብሎም ስዕሉ ከድርሰት ሐሳቡ ጋር የማይቃረንና ግልጽ የሆነ መሆኑ ዕሙን ነው። በግሌ እንደ አለመስማማት የማነሳው ሐሳብ ቢኖር፣ የመጻሕፉን ርእስ የሚወክል ስዕል ተስሎ ሳለ ሥሙ አብስትራክት መሆን መቃጣቱን ነው፤ ለዚህም ‹ራ›ን መመልከት ይቻላል፤ የሰው ፊት የመሰለ ድብቅ ስሜት በርእሱ የመጀመሪያ ፊደል ላይ መካተቱ ድረታ ይመስለኛል።
     የገጸ-ባሕርይ አሳሳል - የሀገሬ ሰው ‹‹ሥምን መልአክ ያወጣል›› የሚላት ብሒል አለችው። በድኅረ-ዘመናዊ ሥነ-ጽሑፍ ሥም ግለሰብን፣ ቦታን፣ ድርጊትን… ወዘተ. ይወክላል። የድርሰት ጭብጥና የገጸ-ባሕርይ አሳሳል የጠለቀ ቁርኝት አላቸው። በድርሰት ለተቀረጸ ገጸ-ባሕርይ ሥራውንና ሥሙን የሚሸት የሥራ ድርሻ መስጠት የተለመደ ነው። የሥራ ድርሻን መሠረት አድርገን የምንሰይመው ሥም ተውላጠ-ሥም በመባል ይጠራል። ድርሰቱ ከቀጥተኛ ሥም ይልቅ ተውላጠ-ሥምን መሠረት በማድረግ ገጸ-ባሕርያትን ሠይሟል፤ ገጸ-ባሕሪያቱም በልካቸው የተሰፋላቸውን ሥራ ሲከውኑ እናስተውላለን። ለአብነት ‹‹ራስ›› የተባለ ማቲ በንጡልነት የራሱን የስኬት ዓለም ሲኖር አስተውለናል።
    ሥነ-ውበት/Aesthetic - በድርሰቱ የተካተቱ ውበታም ቃላት፣ ሐረጋትና ገለጻዎችን እንጥቀስ፡- ‹‹ያስኳላ ጠንቋይ›› (ገጽ 9)፣ ‹‹የንብ እናት ሆንኩ›› (ገጽ 29)፤ ‹‹ላስራ አምስት ደቂቃ እረፍት ሁለት ሰዓት ሙሉ መጓጓት የየለት ተግባሬ ነው›› (ገጽ 1)፣ ‹‹ዓይኑ ተሸነቆረ›› ገጽ 32)፤ ‹‹የቤት ሥራ ሲል ላዬ ላይ ቤት የተሰራብኝ ያህል ትንፋሽ ያጥረኛል›› (ገጽ 2)፣ ‹‹በውርርድ ተሸንፌ ያበሳጨሁት እኔ ሌላው ብስጭቱ ነኝ›› (ገጽ 40) እና ሌሎች በውበታቸው ልብን የሚያሞቁ ትረካዎችን መጥቀስ ይቻላል። በተጠቀሱ መዘርዝሮች አጽንኦት መስጠት ያሻው ጉዳይ እንዳለ መመልከት እንችላለን። የዓረፍተ-ነገር አጀማመር የሥነ-ውበት አንድ አካል ነው፤ የመጀመሪያ ዓረፍተ-ነገር ሰዓቢ፣ ግልጽ፣ እንዲሁም የተነባቢነትንና የአንባቢን ትኩረት የሚስብ መሆን እንዳለበት ይታመናል። ገጽ 1፡- ‹‹ትምህርት አልወድም።›› ብሎ ይጀምራል። ይኼ የሚያሳየው ደራሲው የመጻሕፉን ጽንሰ-ሐሳብ በመጀመሪያዋ ዓረፍተ-ነገር ለመወከል ሲል በተደጋጋሚ እንደከለሰ/እንደሠረዘ ነው።
     ቁስ አካላዊ መሣሪያዎች/Mechanical Devices - ቁስ አካላዊ መሣሪያዎች በኢታሊክስ የተጻፉ ዓረፍተ-ነገሮች፣ የተሠመረባቸው ሐረጋት፣ በቃለ-አጋኖ የሚያልቁ ገለጻዎችንና ሌላንም ያካትታል። የዚህ ቴክኒክ ጠቀሜታ በትረካ ወቅት የሚስተዋሉ የአቅጣጫ፣ የሂደትና የጊዜ መለዋወጦች እና የገጸ-ባሕርይውን ትኩረትና አጽንኦት መጠቆም ነው፤ በታሪኩ ውስጥ ምን እየሆነ እንደሆነ አመላካች ናቸው። ለማሳያ፡- ‹‹ኧረ በታባ!››፤ ‹‹እንደ ፈራሁት!›› (ገጽ 85)፤ ‹‹ዝም!›› (ገጽ 85)፤ ‹‹በታባ!›› (ገጽ 191)፣ ‹‹በሞትኩት!›› (ገጽ 177)፣ ‹‹በታባ ሞት!››፣ ‹‹ኧረ ምንድነው በታባ!›› ገጽ 265) እና በርካታ በኢታሊክስ የሰፈሩ ዓረፍተ-ነገሮችን መጥቀስ ይቻላል።
     የቃላት መረጣ እና ምጣኔ - በድኅረ-ዘመናዊ ሥነ-ጽሑፍ ደራሲ መረን ነክቶ የሥነ-ጽሑፍ ሐሳቡን ማካለብ የለበትም፤ በቋንቋ አጠቃቀም ረገድ የድርሰቱ ዋና ገጸ-ባሕርይ ልጅ ስለሆነ ቀላል አማርኛን በመጠቀም በእያንዳንዱ ክስተት መሀል ብቅ እያለ ግብረ-መልስን ሰጥቷል የሚል እምነት አለኝ። ብሎም፣ ደራሲው ለዋናው ገጸ-ባሕርይ ግዝፈትን ለመስጠት በማለም ከአድራጊ ወደ ተደራጊ (active voice) የመተረክ ቴክኒክን ተጠቅሟል።
ደራሲ በቋንቋ አጠቃቀሙ እና በብዕር አጣጣሉ ቁጥብ መሆን እንዳለበት ይነገራል። በንባብ ወቅት የሚከተል መታከትን፣ የሐሳብ መሸራረፍን፣ የፍሰት መወለካከፍን ለመቅረፍ ሲባል የድርሰት ሐሳብ በተንዠረገገ ቋንቋ ባይገለጽ መልካም እንደሆነ ስምምነት አለ። ‹‹ራስ›› በተመጠኑ ቃላቶች፣ በውስን ሐረጋት እና በአጫጭር ዓረፍተ-ነገሮች የመተረክ አባዜ ይታይበታል። ምሳሌ እንጥቀስ፡- ‹‹በገላጣ ስፍራ እየተራመድኩ እግሬ ይማታብኛል፣ ንፋስ ያደናቅፈኛል፣ የማውቀው መልሱ ይጠፋኛል፣ ስሜ ራሱ ይዘነጋኛል›› (ገጽ 11)፣ ‹‹ሰርቶ ማሳየት አይቸግረው፣ ለማስረዳት ቃል አያጥረው›› (ገጽ 139)፣ ‹‹በምንም አትደሰትም፣ ማንንም አትቀየምም፣ በምንም አትናደድም›› (ገጽ 158)፣ ‹‹ከውስጥ ስጠብቃት ከውጭ ተከሰተች። አብርታለች! ደሞ ደብተር ይዛለች›› (ገጽ 219)። ከላይ በምሳሌ የጠቀስኳቸውና ሌሎች ቃላት፣ ሐረጋትና ዓረፍተ-ነገሮች ቁልቁል ቢደረደሩ ግጥማዊ ለዛ እንደሚኖራቸው አልጠራጠርም።          
   የአፈ-ታሪክ እና የምሳሌያዊ አነጋገር ፈጠራ - ደራሲ በትረካ ዐውድ ውስጥ፣ ወይም በሚቀርጸው ገጸ-ባሕርይ አስገዳጅነት ያልነበሩና አዳዲስ ተረቶችን፣ ምሳሌዎችን፣ አፈ-ታሪክን የመፍጠር ዕድሉ ሰፊ ነው። ‹‹ራስ›› በርካታ አፈ-ታሪኮች፣ ተረትና ምሳሌዎች፣ ሥነ-ቃል እና ምሳሌያዊ አነጋገሮች የተፈጠሩበት ልብ-ወለድ ነው። ነባሩን በአዲስ በመተካት (deconstruction) ደራሲ ፍሬ ዘር በትረካ ዐውዶቹ እንዲሁም በገጸ-ባሕርይው ጠባይ ምክንያት የተለያዩ ሥነ-ቃሎችን፣ ተረቶችንና አፈ-ታሪክን ፈጥሯል፤ ማሳያ እንጥቀስ፡-
‹‹ባንድ ድንጋይ ሁለት ጊዜ ተፈነከትኩ›› (ገጽ 4)፣ ‹‹ከተማ - ከሌሎች ተፋፍጎ ማደር›› (204)፣ ‹‹ወማ - ወንድማለም›› (ገጽ 34)፤ እንዲሁም በገጽ 21፣ 35፣ 39፣ 43፣ 53፣ 127፣ 252 (ሥነ-ቃል)… ወዘተ. የተካተቱ ሐሳቦችን መጥቀስ ይቻላል። ከላይ የጠቀስኳቸው ማሳያዎች የዋናውን ገጸ-ባሕርይ መገለጫዎች የሚወክሉ ናቸው የሚል እምነት አለኝ።       
     ዘይቤአዊነት - ፍሬ ዘር ድንቅ የሆነ ተምሳሌት ይቀምማል። በSimulation/ፍጹም ተቃራኒ የሆኑ ሁለት ሐሳቦችን በማገናኘት ጉዳዩ ትኩረት እንዲስብ ያደርጋል። ዘይቤዎቹ በአብዛኛው አነጻጻሪ ሲሆኑ ዋናው ገጸ-ባሕርይ ቋንቋን በመጠቀም ፍትሐዊነትን፣ እውነታን፣ የሐቅ መዛባትን፣ የነገሮች አለመገጣጠምን፣ ግነትን… ይመረምራል። ደግሞ ዘይቤዎቹ ሙድ ዓይነት ትረካ መምሰላቸው ነው።
ምሳሌ፡- ‹‹እንዲያውም ጎበዝና ሰነፍ ተማሪዎችን የሚያመሳስለን አንድ ነገር ሁለታችንም ትምህርት አለመውደዳችን እንደሆነ ደርሼበታለሁ›› (ገጽ 1)፤ ‹‹እሱ ሙስሊም አይደለም። ግን የነቢዩ ሞሐመድ ልደት ከከድር ይልቅ ያሳስበዋል›› (ገጽ 2)፤ ‹‹ኮሶ በመድኀኒት ይሽራል። አውግቸው ግን ማርከሻ የለውም›› (ገጽ 12)፤ ‹‹የመምህር አውግቸውን ፊት ከማይ የሚመጣው እንቁጣጣሽ ልብስ ሳይገዛልኝ ቢቀር ይሻለኛል›› (ገጽ 12)፤ ‹‹ራሱ ክላሽ ታጥቆ ሲያበቃ ግን እናባዬን ሊቀማ መሞከሩ ጅል መሰለኝ›› (ገጽ 37)፣ ‹‹ጎሊያድን ያለወንጭፍ የምገጥምበት ሰዓት አሁን መጣ›› (ገጽ 70)፣ ‹‹አምስተኛ ክፍል ትምህርቶቹ በዙ። እኔም አበሳዬ በዛ›› (ገጽ 161)፣ ‹‹አባዬ ሲያወራ ያዲሳባው ቤተመንግስት ሦስት አጥር ነው ያለው ይላል። የእኔ ሦስት አጥር እህቴ ናት›› (ገጽ 169) እና ሌሎችም።     
    ኑረታዊነት/Existentialism - ይኼ ነጥብ በትረካ ውስጥ ቦግ-ሕልም የሚል አንድ ቴክኒክ ነው፤ ኤግዚስቴንዣሊስም የኑረታዊነት ወ የፍጥሐዊነት መብሰክስክ ነው፤ Existentialists explore questions related to the meaning, purpose, and value of human existence. Common concepts in existentialist thought include existential crisis, dread, and anxiety in the face of an absurd world, as well as authenticity, courage, and virtue…እንዲል ደራሲው በትረካ ዐውድ እና በገጸ-ባሕርይ ሥሜት እየተመራ የተለያዩ ኑረታዊ፣ ፍትሐዊ፣ ፍልስፍናዊ ጥያቄዎችን ያነሳል። ለምሳሌ ገጽ 73፣ 81፣ 138፣ 140፣ 142፣ 144፣ 145፣ 201፣ 250-251 የተነሱ ሐሳቦችን መመልከት እንችላለን።  
 ምልክት/Symbolism - ምልክት የድርሰት ማኅበረሰብን ባሕል፣ ሃይማኖት፣ ቋንቋ፣ ወግ ይወክላል። እውነት የሚመነጨው ከምልክትና ከማኅበረሰብ ፎክሎር እንደሆነ ይታመናል። አብነት እንጥቀስ፡- የዛፍና የደብር፣ የእረኛና የሥም ቁርኝት፤ የገጠሩን ውበት፣ እንዲሁም የተፈጥሮአዊ ውበትና የጥበብን ተጋምዶ፣ ንባብና ማኅበረሰብ (አንባቢ ራሱን የሳተ ተደርጎ እንደሚታይ)፣ ዛፍ መትከል?... ወዘተ. እንደምልክትነት ተካትተዋል።   
ከራስ ጋር ንግግር/Interior Monologue - ዋናው ገጸ-ባሕሪይ በተለያዩ ስሜቶች መካከል በመቸንከር ጊዜውን/ሁኔታውን የሚመጥኑ ጥያቄዎችን ለእራሱ ያቀርባል፤ ምላሹንም ራሱ ይሰጣል። ከራስ ጋር ንግግር። ‹‹ፋሲካ ግን መቼ ነው? ሩቅ ነው መሰል›› (ገጽ 165)፣ ‹‹ከክፍሉ ተማሪ እኔ ብቻ ሁለት ጊዜ ተገረፍኩ። ምን ስላደረግሁ? ስለመለስኩ›› (ገጽ 189) እና የመሳሰሉትን።     
     ሴራ - (ሀ)፣ የድርሰቱ ዋና ገጸ-ባሕርይ ያለመክሊቱ የሚከታተለው ትምህርት የእግር እሳት ይሆንበታል። (ለ)፣ በቤትም በት/ቤትም ስንፍናውን እየተናገሩ የባሰ እንዲያንገሸግሸው ያደርጉታል። (ሐ)፣ የሥነ-ልቡናዋ መምህርት በት/ቤት ተገኝታ ስለመክሊትና ፍላጎት ብሎም እንዴት ስኬታማ መሆን እንደሚቻል ታወያያቸዋለች። ይኼኔ ‹‹ራስ›› በጣም ይንገሸገሻል፤ ጥልቅ ሕልምም ያልማል። (መ)፣ ሰበብ ፈልጎ ትምህርቱን ጥሎ አያቶቹ ዘንድ ይኮበልላል። (ሠ)፣ ሌጣ መሬት ላይ ዛፍ ተክሎ መንደሩንና አገሩን ይታደጋል። (ረ)፣ የከንቲባው ገዳይ በቁጥጥር ሥር ይውላል። ከሞላ ጎደል ሴራው የምስራቻዊ ድምዳሜ (surprise ending) ዓይነት መልክ አለው።        ‹‹ራስ›› እና ስንፍና ሽሽት/A travelling character - ‹‹ራስ›› ከጅምሩ ተንገሽጋሽ ማቲ ነው። አለፍላጎቱ ተማሪ ቤት ተዱሎ ፍዳውን የሚበላ ዓይነት፤ በጉያው ያሉ ግለሰቦች በነገር እየጎነታተሉ፣ ስንፍናውን ብቻ እየደረቱ ያስመርሩት ጀመር። ቢጥር፣ ቢግር ስኬት ጀርባዋን ሰጠቺው። ቢያስር፣ ቢሠራ የትምህርት ፍላጎቱ ነጠፈ። በቤትም በት/ቤትም ተነቀፈ። ስኬትን፣ ራስን ፍለጋ አያቶቹ ጋር ሄደ፤ ተጓዘ። ከአጀብ ተነጥሎ የሚመጥነውን ዓለም ኖረ። ራስን ፍለጋ!
በአጠቃላይ ‹‹ራስ›› እንደ ጣኦስ መልከ ብዙ ቴክኒኮችን ያጨቀ ድርሰት ነው። ከላይ የተገለጹት እና ሌሎች ብዙ ‹ቦግ› ብለው ወዲያው ‹እልም› ያሉ የትረካ ቴክኒኮችን አጭቃለች፤ ደራሲው በቀጣይ ቁስ አካላዊ መሣሪያዎችን፣ እንግዳ ክስተትን፣ ከራስ ጋር ንግግርን፣ የምልክት ፈጠራን እና ሌሎች ቴክኒኮችን በይበልጥ ያዳብራቸዋል ብዬ አምናለሁ።

Read 658 times