Saturday, 03 June 2023 13:14

ኢትዮ ቴሌኮም ከአ.አ ዩኒቨርሲቲ ጋር የዲጂታል አገልግሎቶች ለማቅረብ የሚያስችል ስትራቴጂያዊ የአጋርነት ስምምነት አደረገ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

     ኢትዮ ቴሌኮም  ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር የኮኔክቲቪቲና ዲጂታል አገልግሎቶች ለማቅረብ የሚያስችል ስትራቴጂያዊ የአጋርነት ስምምነት ከትላንት በስቲያ  አድርጓል፡፡
  ስምምነቱ፤ 18 ካምፓሶችን ከፍተኛ ፍጥነት ባለው የኢንተርኔት አገልግሎት ማገናኘት፣ ስማርት ክፍሎችን መገንባት፣ የተለያዩ የዲጂታል አገልግሎቶችን ማቅረብ፣ ከፍተኛ ባንድዊድዝ ያለው የብሮድባንድ ኢንተርኔት አገልግሎት አቅርቦት ከ24 ሰዓት ክትትልና የጥገና ዋስትና ጋር የሚያካትት ነው ተብሏል፡፡ ይህም ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ዲቫይሶችና ተርሚናሎችን በረጅም ጊዜ ክፍያ ለማቅረብ፣ የእውቀት ሽግግርና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ እንዲሁም የምርምርና ፈጠራ ስራዎችን የሚያግዙ ቴክኖሎጂዎችንና የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን ለማከናወን የሚያስችል እንደሚሆን ተጠቁሟል፡፡ በተጨማሪም፤ የቴሌብር የዲጂታል የክፍያ ሥርዓትን በመጠቀም ነባር ወይም አዲስ ተመዝጋቢ ተማሪዎች የምዝገባ፣ የፈተና፣ የማመልከቻ፣ የሰነድ ማረጋገጫ፣ የትምህርት ክፍያዎች፣ የትምህርት ማስረጃዎች፣ የአልሙኒና መሰል የአገልግሎት ክፍያዎችን ካሉበት ሆነው በመፈጸም አገልግሎት ለማግኘት የሚያባክኑትን ጊዜና ገንዘብ ለመቆጠብ እንዲሁም ዩኒቨርሲቲው የአገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን፣ የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠትና አስተዳደራዊ ወጪዎች ለመቀነስ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ኩባንያው አመልክቷል፡፡
 በሌላ በኩል፤ኢትዮ ቴሌኮም  ከዚህ ቀደም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር፣ በቴሌኮሙኒኬሽን ኔትወርክ ኢንጂነሪንግና የቴሌኮሙኒኬሽን ኢንፎርሜሽን ሲስተም የሙያ መስኮች የጋራ ካሪኩለም በመቅረጽ፣ በድህረ-ምረቃ ፕሮግራም፣ ባለፉት ሦስት ተከታታይ ዙሮች፣ 152 የኩባንያው ባለሙያዎች በመስኩ ሰልጥነው በመመረቅ  ወደ ሥራ ገበታቸው ተመልሰው የተሻለ ሙያዊ አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን፣ በ2023 የትምህርት ዘመንም ለ4ኛ ጊዜ 53 ተማሪዎችን በቴሌኮሙኒኬሽን ኔትወርክ ኢንጂነሪንግና ኢንፎርሜሽን ሲስተም የትምህርት ዘርፎች ተቀብሎ ለማስተማር የሚያስችል ስምምነት ተደርጓል፡፡
ኩባንያው፤ ከአዲስ አባባ ዩኒቨርስቲ ጋር በርካታ ስትራቴጂያዊ ስራዎችን በአጋርነት በመከወን ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ በቀጣይም  የዩኒቨርሲቲውን የአሰራር ስርዓት ለማዘመንና የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት የሚያደርገውን የቴክኖሎጂና መሰል ድጋፎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡

Read 620 times