Saturday, 03 June 2023 19:37

ፖለቲካው አልተቻለም

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)

 ፖለቲካ፣ በብዙ ውጣ ውረድ ቆስቁሰው ያቀጣጥሉታል። ከነደደ በኋላ ግን፣ ማጣፊያው ያጥራል።
ዓይቱንና ልኩን ባናውቅበት ነው። በእርግጥ ብናውቅበት እንኳ፣ ዓይነቱ ተለይቶና ጠርቶ፣ ተመጥኖና ተለክቶ፣ ስራው ተጠናቅቆ ለምርቃት እንደግሳለን ማለት አይደለም። ጊዜ ይፈጃል። ግን ዓይነቱንና ልኩን ካወቅንበት፣ የወደፊት ራዕይ ይሆናል። የእለት ተእለት ጉዟችንን ለማቃናት ያገለግለናል። ካላወቅንበት ነው ችግሩ።
ቅሬታ ለማቅረብና ሰሚ ለማግኘት አስበን ፖለቲካውን ስናስጮኸው፣… እሺ፣… አፉን ይፈታ። ታፍኖ የነበረ አንደበት የውስጡን ይተነፍሳል። አዲስ አየርም ያገኛል። መልካም ነው። በማግስቱ ግን፣ ድምፁ ተቀይሯል። ወደ ሁካታ ተለውጧል። ሰሚ ለማግኘት የከፈትነው አንደበት፣ ለከት ሳያገኝ ሰሚዎችን የሚያባርር ጆሮ የሚያደነቁር ጫጫታ ይሆናል። እልልታና ዋይታ እስኪምታታብን ድረስ ውጥንቅጡ በጠፋበት የጩኸት ጎርፍና ውሽንፍር፣ አገር ይደበላለቃል። የቀለጠ የስካር መንደር ይሆናል።
በደል ለማስቀረት ወይም መፍትሔ ለማግኘት የሚጠቅም መስሎን፣ ረግቶ የተኘውን ፖለቲካ እንወዘውዘዋለን። ከድንዛዜ የቀሰቀስነውና ያነቃነቅነው ፖለቲካ ግን፣ በደመነፍስ እየተደናበረ፣ ያለ ልጓም እየጋለበ፣ እየተላተመና እያጋጨ፣ አገሩን ያተራምሰዋል።
ፖለቲካ አስቸጋሪ ነው። እንተወው ብለን ስንርቀው፣ እሱ አይተወንም። ታዲያ፣ ወደ ተራራ ብንሸሽ፣ እዚያው አኮራምቶ የሚያሰቃይ በረዶ፣ ቁልቁል ዋሻ ውስጥ ብንሸሸግ የተስፋ ምልክቶችን ሁሉ የሚያጠፋ መቃብር ሲሆንብን፣ ምን እናድርግ? እሳት መጫር እንጀምራለን።
ቅዝቃዜው አጥንት ድረስ ሲጠዘጥዘን፣ ድንግዝግዝ ብዥታው ሲያስጨነቀን፣ ቆፈኑና ድቅድቅ ጨለማው ሲያስፈራን፣ የነፍስ ሙቀትና የብርሃን ጭላንጭል ቢናፍቀን ይፈረድብናል እንዴ? ጨለማው ውስጥ በዳበሳ፣ በውርጭ እየተንቀጠቀጥን እንለኩሰዋለን። ግን ምን ዋጋ አለው? ለጊዜው ቦግ ይላል። ሙቀቱም ድምቀቱም ደስ ይላል። ነገር ግን፣…
የጫርነውና ያራገብነው የፖለቲካ እሳት፣ ያንንም ያንንም እያነካካ፣ ግራ ቀኝ እየተፈናጠረ፣ አገሬውን ለማጥፋት መጣደፍ ይጀምራል። በዋዛ አይበርድለትም። እፍ ብንለው በቀላሉ አይታዘዝልንም።
የእልፍ አእላፍ ሰዎች ሕይወት ረግፎ፣ የሚሊዮኖች ኑሮ ከተነቃቀለና ከጨለመ በኋላ፣ ቀሪዎቹ ለትንሽ ይተርፋሉ።
በየአቅጣጫው እየተግለበለበ አገሬውን አቃጥሎ ሲያበቃ፣ እንደምንም ይበርድለታል። ይዳፈናል። “እፎይ!” ያስብላል። ግን ለጊዜው ነው። በሁለት ዓመት ጦርነት አንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን መሞታቸውን ስትሰሙ፣… እልቂቱ ለማመን አይከብድም? ይዘገንናል።
በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲህ አይነት የጦርነት እልቂት፣ ባለፉት 70 ዓመታት በዓለም ታይቶ ይታወቃል እንዴ? በድንጋጤ ቆም ብለን፣ በጥንቃቄ ለማሰብ፣ “ምን ሆነን ነው?” ብለን ራሳችንን ለመታዘብና ለመመርመር የጸጥታ ጊዜ ብንፈጥር፣ ከዚህም ጋር ፖለቲካው ሰክኖ ቢረጋጋ አይገርምም ነበር።
የዛሬው ዘመን ግን፣ የመስከን ጊዜ የለውም። የአምና የካቻምና እሳቶች ገና መብረድ ሲጀምሩ፣ ከግራና ከቀኝ ሌሎች እሳቶች ይለኮሳሉ።
ለነገሩ፣ አንዴ ረመጥ፣ ሌላ ጊዜ ረግረግ እየሆነ ያስቸገረን የአገሪቱ ፖለቲካ፣ ሰክኖ እንዲረጋጋ ብንፈቅድለት እንኳ፣ ልኩንና ዓይነቱን ለማስተካከል አንሞክርም። የሰለለና ረግቶ የተኛ፣ ቆፈናም ወይም ሽባ ፖለቲካ ይሆንብናል።
ቢቆሰቁሱት ያጣድፋል፤ ቢያረጋጉት ያሰለቻል። ለነገሩ፣ ዛሬ በኢንተርኔትና በሞባይል ዘመን፣ ፖለቲካው ገና መስከን ወይም መረጋጋት ሲጀምር ነው ቅሬታ የሚፈጠረው።“ፖለቲካው ደነዘዘ፤ ጆሮው ተደፈነ። ዓይኑ ተጋረደ። አንቀላፍቶ ቀረ”… የሚሉ ጥቂት ድምፆች ይመጣሉ። ሁሌም ይኖራሉ።
በእርግጥ፣ ለጊዜው ብዙ ሰሚ አያገኙም። ለአፍታም ቢሆን አገሩ ፀጥ ረጭ ይላል። አለምክንያት አይደለም። በፖለቲካ ሰበብ የተፈጠሩት ጥፋቶች፣ ትርምሶች፣ እልቂቶችና ውድመቶች፣… ለህሊና ይከብዳሉ። እረፍት የሚነሱ ስጋቶችና ግርግሮች፣ ኑሮን የሚያናጉ የጥቃት ዘመቻዎችና ስደቶች፣… ከብዙ ሰው አእምሮ ለመደብዘዝ ትንሽ ጊዜ ይወስዳሉ። እናም፣…
ፖለቲካ ላይ ሲያሰፈስፍ ሲክለፈለፍ የነበረ ስሜት ይሸማቀቃል። የፖለቲካ መርዘኛ ድምፆችን ለመስማት በጉጉት ጆሮውን ደቅኖ፣ የመጠፋፋት ግጥሚያዎችን ለማየት በናፍቆት ዓይኑን አፍጥጦ የሚውል ሰው፣ ለጊዜውም ቢሆን ቁጥሩ ይቀንሳል። የፖለቲካ ወሬ አላፊ አግዳሚ ወሬ፣ አሰልቺ የቸከ የቃላት ኳኳታ ይሆንበታል። የማነቃቂያ (የሞቲቬሽን) ዲስኩር ይበራከታል። ፖለቲካው ቢቀዘቅዝ ቢረጋ ድምፁ ጠፍቶ ፀጥ ረጭ ቢል ይሻላል?
እንዲያም ሆኖ፣ የተዳፈነውን ፖለቲካ፣ ውሎ ሳያድር እንደገና ለመለኮስ የሚመኝና ተግቶ የሚቆሰቁስ አይጠፋም። ወዲያውኑ ተቀጣጥሎ አይንቀለቀልም። ሚሊዮኖች በፖለቲካ ቆስለዋልና። ቢሆንም ግን፣ ፖለቲካው ዝም ብሎ አይቀርም። ቢያንስ ቢያንስ፣ በግማሽ ልብ መንጎዳጎድ ማጉረምረም አያቅተውም። በጭብጨባ የታጀቡ የስብሰባ “ድስኩሮች” እና “የጥቂት ብሶተኞች እሮሮ” እየመሰለ ይመጣል። በዚሁ አይቆምም።
ያው፣… “ሕይወት ትግል ነው፣ ኑሮ ፈተና ነው” ይባል የለ! አስከፊዎቹ የፖለቲካ አደጋዎችና ዘግናኝ ጥፋቶች ከሰው አእምሮ ከደበዘዙ በኋላ፣ መደበኛ የኑሮ ቅሬታዎች እጅግ ገዝፈውና በዝተው መታየታቸው መች ይቀራል? የኑሮ ቅሬታ ደግሞ፣ የፖለቲካ ነዳጅ ነው።
ከጥቂት ብሶተኞች በተጨማሪ፣ ሌሎች አጃቢና አዳማቂ ድምፆች እየበረከቱ፣ ለአፍታ ደንዝዞ የነበረው ፖለቲካ ይሟሟቃል። “የብዙ ሰዎች የቅሬታ መተንፈሻ” ይሆናል።
አንዳንዶችም ወሬና ጨዋታ ፈልገው፣ ሌሎች ደግሞ ለተሳትፎ ያህል ወደ ፖለቲካው ውካታ ይቀላቀላሉ።
ጨዋታ አዋቂዎችና የጨዋታ እድምተኞች፣… ብሶትና ቅሬታ እየደረደሩ በእልህ አይንተከተኩም። የፖለቲካ ጭቅጭቅ አያረካቸውም። ንትርኩና ንዴቱ አይመስጣቸውም። ይልቅስ፣ ፖለቲካው መዝናኛቸውና መጫወቻቸው ነው። ሰፊ የማላገጫ ሜዳ መስሎ ይታያቸዋል።
ደግሞም መጫወቻ ይሆንላቸዋል። ታዲያ፣ ለጊዜው ነው - (ተመልሶ እስኪጫወትባቸው ድረስ)። መዝናኛ ሆኖ አይዘልቅማ።
እየመረረ እየከረረ ይመጣል። ጨዋታ አዋቂዎችና እድምተኞች እንደልብ ሲዝናኑበት፣… ለካ ፖለቲካው ሳያስቡትና ሳይታወቃቸው፣ ከስራቸው አምልጦ ሄዷል። መጫወቻና ማላገጫ ያደረጉት ፖለቲካ፣… ለካ፣ መልኩ ተገልጦ፣ አስፈሪ አውሬ መስሏል። በሰፈርና በቢሮ፣ የሁሉም ሰው ወሬ፣ የፖለቲካ ወሬ ሆኗል። የአዳሜ የእለት ውሎና አዳር፣… በፖለቲካ ተጥለቅልቆ፣ እንደማዕበል ሲናወጥ ያገኙታል።
የሰው ኑሮ፣ የፖለቲካ አዳማቂና መጫወቻ፣ የሰው ሕይወትም ፖለቲካውን የሚያሟሙቅ ማገዶ ከሆነ በኋላ፣ ምን መላ አለው! መግቻ አይገኝለትም። መመለሻም የለውም። ያኔ፣ በቀላሉ የማይገላገሉት የአገር ህመም፣ የዜጎች መከራ ይሆናል - ፖለቲካ።
ፖለቲካ በተፈጥሮው ክፉ አውሬ ስለሆነ አይደለም። ይመስላል። አንዴ ከቀሰቀሱት በኋላ፣ እንደ አውሬ ይሆንብናልና። ግን ስለማናውቅበት ነው።
ሕይወትንና ኑሮን፣ ቤትና ንብረትን ከአጥር ውጭ ሆኖ የሚጠብቅ ዘበኛ ሲሆን ነው ፖለቲካ የሚያምርበት።
ጓዳ ድረስ ገብቶ በሕይወታችንና በኑሯችን ላይ እየነገሰ ጊዜ ግን፣ ዘበኛ ሳይሆን ዘራፊ፣ አጥር ጠባቂ ሳይሆን አጥር የሚሰብር አውሬ ይሆንብናል። ዓይነቱንና ልኩን ስላላቅንበት ነው የሚያጠፋን።


Read 997 times