Saturday, 03 June 2023 20:02

የጓሮ ማህበረሰብ 3ኛ ዓመት ዛሬ በባዛርና በኤግዚቢሽን ይከበራል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  በኮቪድ19 ወረርሽኝ ወቅት ከተጀመሩቀዳሚ ንቅናቄዎች አንዱ የሆነውና ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣው “የጓሮ ማህበረሰብ” (Home Gardening Community) የተመሰረተበትን 3ኛ ዓመት ዛሬ ግንቦት 26 ቀን 2015 ዓ.ም ከረፋዱ 4፡00 ጀምሮ በፈንድቃ የባህል ማእከል በባዛርና ኤግዚቢሽን እንደሚከበር ተገለፀ፡፡ በጥንዶቹ ጋዜጠኛ ትእግስት ታደለና ስለሺ ባየህ የተመሰረተው “የጓሮ ማህበረሰብ”፤ ሰው ባለችው ጥቂት ክፍት ቦታ ላይ የጓሮ አትክልቶችንና ቅመማ ቅመሞችን ቢያመርትና ቢመገብ ወጪውን ሁለትም ኦርጋኒክ  የሆኑ ምግቦችን በመመገብ ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን ከማዳበር አንፃር ያለውን ፋይዳ በፊስቡክ ገፅ ለማስታወቅ “የጓሮ ማህበረሰብ” የተሰኘ የፌስቡክ ገፅ መክፈታቸውን ከመስራቾቹ አንዱ የሆነው አቶ ስለሺ ባየህ ተናግሯል፡፡
በዚህ የፌስቡክ ገፅ ላይ ለየ ሀገራችን ቅመማ ቅመሞችና ዝርያዎች ስላላቸው ጥቅምና ለመሰል ጉዳዮች እየተፃፈና የጓሮ ማህበረሰብ አባላት መረጃ እየተለዋወጡ ከቆየ በኋላ ይህ እሳቤ እያደገ መጥቶ ዛሬ ላይ ከ30 ሺህ በላይ ተከታዮችን ማፍራት መቻሉንም አቶ ስለሺ ለአዲስ አድማስ ገልጿል፡፡
ይህንኑ ስራ ህጋዊ ሰውነት ባለው ተቋም ለማከናወን “ጓሮ ሚዲያ ኤቨንትስና ፕሮሞሽን” የተሰኘ ተቋም በማቋቋም በርካታ ፋይዳ ያላቸውን ስራዎች እያከናወኑ እንደሚገኙ የተናገረው መስራቹ፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት አትክልቶችና ቅመማ ቅመሞች የሚለዋወጡበት፣ ስለጓሮ ጠቀሜታ ውይይትና ተሞክሮ የሚካፈሉበት የጓሮ ማህበረሰብ ባዛርና ኤግዚቢሽን ሲዘጋጅ መቆየቱ የተገለጸ ሲሆን፤ ዛሬም 3ኛ ዓመቱን በደመቀ ባዛርና ኤግዚቢሽን እንደሚያከብር አቶ ስለሺ ተናግሯል።
በባዛር ኤግዚቢሽኑ ላይ ኦርጋኒክ ማር አምራቾችና ከተፈጥሮ ዕፅዋት የውበት መጠበቂያ ምርት አምራች ኩባንያዎች በርዕስ ጉዳዮ ዚሪያ ውይይት ይካሄዳል ተብሏል። በዕለቱም ምሁራን፣ ከጤና፣ አካባቢ ጥበቃ፣ ከተፈጥሮና ኦርጋኒክ ምግቦች አንጻርና ከተለያዩ ጉዳዮች አኳያ ንግግር የሚያደርጉ ሲሆን ተፈጥሮን በመንከባከብ ለተተኪ ትውልድ ያቆዩ ጀግኖች የሚመሰገኑበት መርሃ ግብርም እንደሚኖር አቶ ስለሺ ባየህ ገልፀዋል።

Read 807 times