Saturday, 22 July 2023 12:42

እያንዳንዱ ሰው ለእራሱ የሚሰጠው ህክምና...

Written by  ሀይማኖት ግርማይ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

   በዓለም የጤና ድርጅት መረጃ መሰረት በዓለምአቀፍ ደረጃ ከ5 ሰዎች ውስጥ አንድ ሰው የህክምና አገልግሎት ለማግኘት ወይም የህክምና ባለሙያዎች አገልግሎት ለመስጠት በሚቸገሩበት ሁኔታ ውስጥ ይገኛል። እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጉ የህክምና ባለሙያዎች እጥረት እንዳለ ይገመታል። ይህ እጥረት በይበልጥ የሚስተዋለው በመካከለኛ እና ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት ውስጥ ነው። ስለሆነም ከህክምና ባለሙያ ጋር በጋራ በመሆን እንዲሁም የባለሙያዎችን ምክር በተከተለ መልኩ ታካሚዎች በግላቸው (ለእራሳቸው) የህክምና አገልግሎት እንዲሰጡ ይበረታታል።
በእንግሊዘኛ ሰልፍ ኬር (Selfcare) በመባል የሚጠራው እራስን መንከባከብ ወይም እራስአገዝ የህክምና አገልግሎት በዓለምአቀፍ ደረጃ ከሰኔ 17 እስከ ሀምሌ 17 ይከበራል። በዓለም የጤና ድርጅት መረጃ መሰረት ለአንድ ወር ያህል ክብረበዓሉ ሲከበር ከዚህ ቀደም ሰዎች እራስን በመንከባከብ ያገኙትን ጥቅም ታሳቢ በማድረግ (እውቅና በመስጠት)፣ ስለ ህክምናው ለሌሎች በማስተዋወቅ እና ተግባራዊ በማድረግ ነው።
እራስን የመንከባከብ (Selfcare) ፕሮጀክት ዋና አስተባባሪ የሆኑት የፅንስ እና የማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት ዶ/ር (ተባባሪ ፕሮፌሰር) ደረጄ ንጉሴ “ሰልፍ ኬር (Selfcare) ማለት እራስን መንከባከብ እንደማለት ነው” ብለዋል። በሽታን በመከላከል እንዲሁም ከህክምና ባለሙያ ጋር በመሆን ለእራስ ህክምና በመስጠት ተግባራዊ የሚደረግ ነው።
የእራስ አገዝ የህክምና አገልግሎት ወይም እራስን መንከባከብ (Selfcare) መመሪያን (Guideline) አስመልክቶ ሰኔ 13 ቀን 2015 ዓ.ም በጤና ሚንስቴር እና በኢትዮጵያ የፅንስ እና የማህፀን ሀኪሞች ማህበር አማካኝነት የውይይት መድረክ አዘጋጅቶ ነበር። በመርሀግሩ ላይ የተገኙት የጤና ጥበቃ ሚንስቴር የእናቶች እና ህፃናት ጤና ዳይሮክቴሬት ዳይሬክተር ዶ/ር መሰረት ዘላለም እንደተናገሩት ለእራስ የሚሰጥ የህክምና አገልግሎት በኢትዮጵያዊያን ዘንድ የተለመደ ነው። ማለትም በባህላዊ መንገድ ሲተገበር ቆይቷል። “ባህላዊ ህክምና የዘመናዊ ህክምና መነሻ ነው” ብለዋል ዶ/ር መሰረት ዘላለም። አክለውም በባህላዊ መንገድ ሲተገበር የቆየውን ለእራስ የሚሰጥ የህክምና አገልግሎት በማሳደግ ዘመናዊ ህክምናን በዘመናዊ መንገድ እንዲሰጥ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
“ከዚህ ቀደም በተሳለጠ መንገድ አይኑር እንጂ እናቶች በነፍሰጡር ወቅት ማቅለሽለሽ ሲኖር ቀለል ያለ ከሆነ ኮምጣጣ ነገር በመጠቀም ችግሩን ለመቀነስ ይሞክሩ ነበር” ያሉት በጤና ሚንስቴር እናቶች እና ህፃናት፤ አፍላወጣቶች የጤና አገልግሎት ስራ አስፈፃሚ የእናቶች ጤና ፕሮግራም ዴስክ ሀላፊ የሆኑት ሲስተር ዘምዘም ማህመድ ናቸው። እንደ ባለሙያዋ ንግግር ለእራስ ህክምና መስጠት የሚቻለው በ2 መንገድ ነው። ይህም ከህክምና ባለሙያ እገዛ ጋር (በጋራ) እና ከህክምና ባለሙያ ውጪ (ለብቻ) ለእራስ የህክምና አገልግሎት መስጠት ነው። ባለሙያዋ አክለውም ሰዎች ሌላ ሰው ከሚሰጣቸው የህክምና አገልግሎት በተሻለ እራሳቸውን ማከም እንደሚችሉ ተናግረዋል። ከህክምና ባለሙያ ውጪ አገልግሎቱ የሚሰጠው ቀለል ላለ ችግር ሲሆን ችግሩ (ህመም) ከፍ ሲል ግን የህክምና ባለሙያ ማማከር ያስፈልጋል። ሲስተር ዘምዘም እንደተናገሩት እ.ኤአ በ2016 በተደረገ ጥናት መሰረት 49.8 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች በገጠር አከባቢ የሚኖሩ እና ያልተማሩ ናቸው።
የፅንስ እና የማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት ዶ/ር ደረጄ ንጉሴ አገልግሎቱን የማስተዋወቅ (Advocacy) ስራ ሲሰራ ትኩረት ከሚደረግባቸው ጉዳዮች መካከል የተጠቃሚዎችን የትምህርት ደረጃ ታሳቢ በማድረግ በሚረዱት ቋንቋ ተደራሽ ማድረግ መሆኑን ተናግረዋል። “ለአብዛኛው ሰው ተደራሽ በሆነ ሀገራዊ ቋንቋ የማዘጋጀት እሳቤ አለ” ብለዋል ዶ/ር ደረጄ ንጉሴ። እንደ የህክምና ባለሙያው ንግግር መምሪያው ተግባራዊ የሚደረገው ከጤና ሚንስተር ጋር በጋራ መሆን ሲሆን ፕሮጀክቱ የ5 ዓመት እርዝማኔ ይኖረዋል። ለእራስ የሚሰጥ የህክምና አገልግሎት በፅንሰሀሳብ ደረጃ አዲስ አለመሆኑን ዶ/ር ደረጄ ጠቅሰዋል። ስለሆነም ይህ አገልግሎት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም እንዲሁም ወደ የህክምና ተቋም ለመሄድ አመቺ ባልሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ለሚገኙ ታካሚዎች ተደራሽ ለማድረግ ታሳቢ ያደረገ ነው። ከዚህ በተጨማሪም የህክምና ተቋማት እና የህክምና ባለሙያዎች ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ ታካሚዎች ለእራሳቸው ጤና ተሳታፊ እንዲሆኑ ያደርጋል።
የኢትዮጵያ የፅንስ እና የማህፀን ሀኪሞች ማህበር ይህ አገልግሎት ተግባራዊ ሆኖ በስነተዋልዶ ጤና ዙሪያ ሴቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሙያዊ ድጋፍ ያደርጋል። እንዲሁም በገንዘብ ድጋፍ የሚያደርገው ዓለምአቀፍ የእራስ እንክብካቤ ቡድን ነው። ሁለቱ ተቋማት ከጤና ሚንስቴር እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመሆን ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚሰሩ ዶ/ር ደረጄ ተናግረዋል።
በእራስ በሚሰጥ የህክምና አገልግሎት ላይ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የስነተዋልዶ ጤና የህክምና አገልግሎቶች;
የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት
የአመጋገብ ስርአት; በቅድመ እርግዝና ወቅት የተስተካከለ የአመጋገብ ስርአት እንዲኖር እገዛ ያደርጋል።
በቤት ውስጥ የሚደረግ የእርግዝና ምርመራ
በእርግዝና ወቅት የሚያጋጥም የደም ማነስ; ቢኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2016 በተደረገ ጥናት ነፍሰ ጡር እና ጡት የሚያጠቡ እናቶች 29በመቶ የደም ማነስ ችግር እንዳለባቸው ተረጋግጧል። ስለሆነም የአመጋገብ ሁኔታን በማስተካከል ችግሩን ለመቀነስ ይረዳል።
በእርግዝና ወቅት የስኳር እና የደም ግፊት ምርመራ
የወለዱ እናቶች ከህክምና ተቋም ውጪ(በቤት ውስጥ) ለእራሳቸው ማድረግ ስለሚገባቸው እንክብካቤ
የህፃናት አያያዝ; ህፃናት የተለያዩ በሽታዎች ሲያጋጥማቸው እንዲሁም እንክብካቤ ለማድረግ እናቶች (ማህበረሰብ) ከህክምና ባለሙያዎች በሚገኝ ምክር መሰረት በእራስ መተግበር እንዲችሉ ያደርጋል።  
የኤች አይ ቪ ምርመራ በእራስ (ከህክምና ተቋም ውጪ) ማድረግ
በስነተዋልዶ ጤና ዙሪያ ለእራስ የሚሰጠውን የህክምና አገልግሎት ተጠቃሚ የሚሆኑት ሁሉም ሴቶች ናቸው። ነገር ግን በይበልጥ ተጠቃሚ የሚሆኑት በመውለጃ የእድሜ ክልል ውስጥ (ከ15 እስከ 49 ዓመት) የሚገኙ ሴቶች መሆናቸውን ዶ/ር ደረጄ ንጉሴ ተናግረዋል። እንደ ሲስተር ዘምዘም ንግግር ተገልጋዮች (ታካሚዎች) የህክምና አገልግሎት ለእራሳቸው እንዲሰጡ በሚደረግበት ወቅት ለራሳቸው ጤና ተሳትፎ በማድረጋቸው የተለያዩ ጥቅሞችን ያገኛሉ። ይህም ለእራሳቸው ጉዳይ እራሳቸው እንዲወስኑ በማድረግ፣ በእውቀት፣ አገልግሎቱን በቀላሉ እንዲያገኙ በማድረግ እና አላስፈላጊ ምልልስን በመቀነስ የሚያግዝ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ለህክምና ባለሙያዎች ጥቅም ይሰጣል። በጤና ተቋማት በጥቃቅን ችግሮች የሚኖርን መጨናነቅ በመቀነስ የአገልግሎቱን ተደራሽነት ይጨምራል።
የፅንስ እና የማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት ዶ/ር ደረጄ ንጉሴ እንደተናገሩት ለእራስ የሚሰጥ እንክብካቤ (Selfcare ) ከህክምና ተቋም እና ከህክምና ባለሙያዎች ጋር በጋራ ወይም ከባለሙያዎች በተገኘ ምክር አማካኝነት የሚከወን እንጂ ከህክምና ባለሙያ እውቅና ውጪ የሚተገበር አለመሆኑን ማስተዋል ያስፈልጋል። አገልግሎቱ ወደ የህክምና ተቋም ባለመሄድ ወይም ባለሙያ ባለመፈለግ የሚተገበር ሳይሆን ወደ ህክምና ተቋም ያለውን ምልልስ በመቀነስ የሚደረግ ነው። “ከህክምና ተቋም ጋር በጥምረት የሚሰራ እንጂ ሙሉበሙሉ ከህክምና ተቋም ጋር ያለውን አገልግሎት የሚያስቀር አይደለም” በማለት ዶ/ር ደረጄ ንጉሴ ተናግረዋል።


Read 370 times