የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ትላንት ምሽት በአማራ ክልል ያለውን አሳሳቢ የጸጥታ ሁኔታ በተመለከተ ባወጣው መግለጫ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅትም ሰብአዊ መብቶች ሊከበሩና ለሰላማዊ ውይይት ቅድሚያ ሊሰጥ እንደሚገባ አሳስቧል፤ ኮሚሽኑ ከሚያዝያወር 2015 ዓ.ም ጀምሮ እየተባባሰ የመጣውን የአማራ ክልል የትጥቅ ግጭትና የጸጥታ ችግር እንዲሁም በሰብአዊ መብቶች ላይ ያስከተለውን ተጽዕኖ ሲከታተል መቆየቱንና ይህንኑም አስመልክቶ በነዋሪዎችና በአካባቢው ላይ ያደረሰውንና የሚያደርሰውን ጉዳት ከግምት ውስጥ በማስገባት፤ ለሰላም አማራጮች ቅድሚያ እንዲሰጥ፣ ሲቪልሰዎች ለተጨማሪ ጉዳት እንዳይዳረጉ ጥንቃቄ እንዲደረግ ማሳሰቡ የሚታወስ ነው። ሆኖም የጸጥታ ሁኔታው ከመሻሻል ይልቅ ከሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ እየተባባሰ በመምጣቱ ብዙ የክልሉ አካባቢዎች በግጭት ውስጥ መሆናቸውን፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ሲቪል ሰዎች ላይ ጥቃት መፈጸሙንና ሲቪል ሰዎችና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን፣ የትራንስፖርትና ሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎቶች መቋረጣቸውን፣ በቅርቡም የኢንተርኔት አገልግሎት በብዙ የክልሉ አካባቢዎች መቋረጡን፣ ነዋሪዎች በነጻነት ለመንቀሳቀስና ሥራቸውን ለመከወን መቸገራቸውን እንዲሁም የእንቅስቃሴ ገደቦች በአንዳንድ አካባቢዎች መጣላቸውን ለመገንዘብ መቻሉን ኮሚሽኑ ጠቁሟል።
ግጭቱ ከሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች በግጭትና በተለያዩም ክንያቶች የተፈናቀሉ፣ እንዲሁም ከጎረቤት ሀገራት ግጭት በመሸሽ የተሰደዱ በክልሉ የሚገኙ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችንም (ስደተኞች፣ ጥገኝነት ጠያቂዎች እንዲሁም ፍልሰተኞች) ለከፍተኛ ችግር የሚዳርግ ነው ብሏል- ኢሰመኮ።
ኮሚሽኑ ከሚመለከታቸው የክልሉና የፌዴራል መንግሥት አካላት ጋር መነጋገርን ጨምሮ፣ በክልሉ እያከናወነ ያለውን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል፣ እንዲሁም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅትም በአዋጅ ቁጥር 210/1992 (በአዋጅ ቁጥር 1224/2012 እንደተሻሻለው) አንቀጽ 6(12) መሠረት፣ በተሰጠው ተግባርና ኃላፊነት እንደሚቀጥል አስታውሷል።
ሁሉም ወገኖች ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ለሰላም አማራጮች ቅድሚያ እንዲሰጡ፣ ግጭቱን ከሚያባብሱ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ፣ የክልሉን ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ በመንግሥት የሚወሰዱ እርምጃዎች በማናቸውም ሁኔታ ቢሆን ነዋሪዎችን ለበለጠ ጉዳትና ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት እንዳይዳርጉ ተገቢው ጥንቃቄ እንዲደረግ ኮሚሽኑ አሳስቧል። በተጨማሪም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም ያወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 6/2015 በሕገ-መንግሥቱና ኢትዮጵያ ተቀብላ ባጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ዕውቅና ያገኙሰብአዊ መብቶችንና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርሖችን በተለይም የጥብቅ አስፈላጊነት፣ በማናቸውም ሁኔታ የማይገደቡ መብቶችን የመጠበቅ፣ የተመጣጣኝነትና ከመድልዎ ነጻ መሆን መርሖችን ባከበረ መልኩ እንዲተገበር ኢሰመኮ ትላንት ምሽት ባወጣው መግለጫ አሳስቧል።
Saturday, 05 August 2023 11:44
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም ሰብአዊ መብቶች ሊከበሩና ለሰላማዊ ውይይት ቅድሚያ ሊሰጥ እንደሚገባ ኢሰመኮ አሳሰበ
Written by Administrator
Published in
ዜና