- የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የፌደራል መንግስት ጣልቃ እንዲገባ በይፋ ጠይቀዋል
- የሚኒስትሮች ም/ቤት በክልሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ ወስኗል
- የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ጎንደርና ላሊበላ የሚያደርገዉን በረራ አቋርጧል
- እንግሊዝና ስፔን ዜጎቻቸው ወደ አማራ ክልል እንዳይጓዙ አስጠንቅቀዋል
ለወራት በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች ሲካሄድ የነበረው ተቃውሞና የታጣቂዎች ግጭት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ ተነግሯል። የቀውሱ አካባቢም እየሰፋ በመሄድ በርካታ ቦታዎችን አዳርሷል።
ለሁለት አመታት በትግራይ ታጣቂ ሃይሎች የተከፈተውን ጦርነት ሲያስተናግድ የከረመው ክልሉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በታጣቂዎችና በፀጥታ ኃይሎች መካከል በተቀሰቀሰው ግጭት ሳቢያ የክልሉ ነዋሪዎች ለከፍተኛ ስጋት የተጋለጡ ሲሆን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ፣ የፌደራል መንግሥቱ ጣልቃ እንዲገባ በይፋ ጠይቀዋል።
በክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ ተፈርሞ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጻፈው ደብዳቤ፣ በክልሉ ያለውን የፀጥታ መደፍረስ በመደበኛ የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቆጣጠር አዳጋች በመሆኑ የፌደራል መንግሥቱ ጣልቃ እንዲገባ ተጠይቋል።
“በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቋቋም የማይቻል ሁኔታን ስለማሳወቅ” በሚል ከአማራ ክልል መንግሥት፣ ለፌደራሉ መንግሥት ሐምሌ 27 ቀን 2015 ዓ.ም በተጻፈው ደብዳቤ ላይ ክልሉ ከባድ ችግር እንደገጠመው ተጠቅሷል።
በዚህም ምክንያት “የፌደራል መንግሥት አስፈላጊውን የሕግ ማዕቀፍ እንዲተገብር”፣ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ ማቅረቡ በደብዳቤው ተገልጿል። በክልሉ ያለው የፀጥታ መደፍረስ በክልሉ ከፍተኛ ሰብአዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እያስከተለ መሆኑን የጠቀሰው የክልሉ መንግሥት፣ የፌደራል መንግሥቱ በአገሪቱ ሕገ መንግሥት መሠረት አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል።
በሌላ በኩል፤ የሚንስትሮች ም/ቤት በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ ውሳ አሳልፏል።
በክልሉ ባለው የጸጥታ ችግር መባባስ ምክንያት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ክልሉ የሚያደርጋቸውን በረራዎች ለመሰረዝ ተገዷል። አየር መንገዱ ከትናንት ጀምሮ ወደ ጎንደር፣ ላሊበላና ኮምቦልቻ የሚያደርጋቸውን በረራዎች መሰረዙን ለማወቅ ተችሏል።
የፈረንሳዩ የዜና ወኪል አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ፣ ታጣቂዎች የላሊበላ አውሮፕላን ማረፊያን በቁጥጥራቸው ስር ማድረጋቸውን ዘግቧል። የኢትዮጵያ አየር መንገድም ወደ ጎንደርና ላሊበላ በረራ አቋርጫለሁ ማለቱን ዘገባው ጨምሮ ጠቅሷል።
በተጨማሪም በጎንደር ከተማ ካለፈው ረቡዕ ጀምሮ በመንግሥት የጸጥታ አካላትና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተደረገ ባለው ውጊያ ምክንያት ከሐሙስ ጀምሮ ወደ ጎንደር የሚደረግ የአየር በረራ ተቋርጧል። ወደ ላሊበላ በቀን ሁለት ጊዜ ከሚደረጉ በረራዎች የመጀመሪያው ማክሰኞ ሐምሌ 25 ቀን 2015 ዓ.ም ጠዋት ላይ የተደረገ ሲሆን፤ “ተጨማሪ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ላሊበላ አየር ማረፊያ ሊገቡ ነው” የሚል ወሬ የሰሙ የፋኖ ታጣቂዎች ወደ ሥፍራው አቅንተው ጥበቃ ላይ ከነበሩ የፌዴራል ፖሊስ አባላት ጋር የተኩስ ልውውጥ ማድረጋቸውን እማኞች ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል። ይህን ተከትሎም ከቀኑ 6 ሰዓት ከ50 ላይ ላሊበላ ኤርፖርት ማረፍ የነበረበት ተሣፋሪዎችን የጫነው ሁለተኛው የመንገደኞች አውሮፕላን ካለው የጸጥታ ስጋት አንጻር ሳያርፍ ተመልሷል።
በክልሉ እየተካሔደ በሚገኘው ግጭት ምክንያት፣ እንግሊዝና ስፔን፣ ለዜጎቻቸው የጉዞ ማስጠንቀቂያ ሲወጡ ሲሆን፣ የእንግሊዙ የውጭ ጉዳይ ቢሮ፣ “የዐማራ ሚሊሻ ፋኖ፣ የላሊበላን አየር ማረፊያ ተቆጣጥሯል፤” ሲል አስታውቋል።
ከእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ጋራ ተመሳሳይ የጉዞ ማስጠንቀቂያ ያወጣው፣ በአዲስ አበባ የሚገኘው የስፔን ኤምባሲ፣ በላሊበላ የሚገኙ የስፔን ዜጎች፣ ኤምባሲውን እንዲያነጋግሩ አሣስቧል።
የኢፌዲሪ መከላከያ ሰራዊት ሰሞኑን በሰጠው መግለጫ፤ በፋኖ ስም እየተንቀሳቀሱ የሃገር ሰላም ለማወክ በሚሰሩ አካላት ላይ እርምጃ እወስዳለሁ ብሏል።
የሰራዊቱ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሩ ኮሎኔል ጌትነት አዳነ በሰጡት መግለጫ ላይ እንዳመለከቱ፤ ከሰሞኑ በጎንደር የሰሜን ምዕራብ ዕዝን ዓመታዊ አፈጻጸም ለመገምገም ወደ ስፍራው እያቀኑ በነበሩ የሰራዊቱ አባላት ላይ ከጩሂት 2 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሲደርሱ ተኩስ ተከፍቶባቸዋል ብለዋል ።
የሰራዊቱ አባላት በመመለስ ላይ ሳሉም በቆላድባ አካባቢ በተመሳሳይ ተኩስ እንደተከፈተባቸው ገልጸው፤ “ሃሳብ ሲነጥፍ ነፍጥ አንግቤ እዋጋለሁ” የሚል አካል ላይ ሰራዊቱ የሚወስደውን እርምጃ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ኮሎኔል ጌትነት በዚሁ መግለጫቸው፤ ጉልበተኛና መሳሪያ ታጥቆ እንቅፋት እሆናለሁ ያለው አካል ላይ የሃይል እርምጃ ይወስዳል ብለዋል። ከዚሁ ጋር አያይዘውም መከላከያ ላይ ነፍጥ ከሚያነሱ በተጨማሪ ሚዲያን ጨምሮ ሌሎች ግንባሮችን ይመራሉ ያሏቸው ወገኖች ላይም እርምጃ በመውሰድ ተቋማቸው አገራዊ ጸጥታን የማስከበር ኃላፊነቱን እንደሚወጣ አስገንዝበዋል፡፡
Published in
ዜና