Saturday, 05 August 2023 12:21

ኦልግሪን አግሮ ኢንዱስትሪ ላቀረበው ክስና አቤቱታ የጋሞ ዞን የወረዳ አመራሮች የሰጡት ምላሽ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

”ባለሃብቱ የአካባቢውን ገጽታ ማጠልሸቱ ተገቢነት የለውም”

በቅድሚያ ስምዎትንና የሥራ ሃላፊነትዎን ይንገሩን?
አቶ ታምራት ጎአ እባላለሁ፡፡ አሁን ላይ የገረሴ  ዙሪያ ወረዳ ገቢዎች ፅ/ቤት ሃላፊ ነኝ፤ የቀድሞው የንግድ ፅ/ቤት ሃላፊ ማለት ነው፡፡
በሥራ ሃላፊነትዎ ስለ ኦልግሪን አግሮ ኢንዱስትሪ የሚያውቁትን ያካፍሉን?
ኦልግሪን በኮሻሌ አካባቢ በጊዜው በተወሰነ ደረጃ እያለማ ነበር፡፡ እኔ በዚያን ጊዜ የማውቀው ከሰራተኞች የተቆረጠ የስራ ግብርና የእርሻና መሬት መጠቀሚያ ግብር እንዳልተከፈለና በየጊዜው ከወረዳው ጋር  ጭቅጭቅ እንደነበረ ነው፡፡
ምን ያህል ነው በወቅቱ ያልተከፈለው የግብር መጠን?
በጊዜው  ብዙ ነበር፤ ከ2013 በፊት የሰራተኛ የስራ ግብር ወደ 593 ሚሊዮን ብር ገደማ አለመከፈሉን አውቃለሁ። በወቅቱ  በዚህ ጉዳይ ከፍተኛ ፍ/ቤት ድረስ ከስሰናል፡፡ ባለሃብቱ ሲገኝ ንብረትም ካለው ንብረቱ ተይዞ እንዲከፍል ተብሎ ነበር የተወሰነው፡፡ እስካሁን የክስ ንብረት አጥተን ነው የተውነው፡፡ ግን  ባለሃብቱ ለወረዳው መገበር ወይም መክፈል ያለበት እዳ እንዳለ አውቃለሁ።
ይሄን ሁሉ ገንዘብ እናንተ ለምንድነው በጊዜው ያልጠየቃችሁት?
በየጊዜው  ይጠየቃል፤ ይከፈላል ይባላል፤ ቀጠሮ ይሰጣል፡፡ ይሄ እኮ ሌላ የሥራ ትርፍ ግብር አይደለም፤ በባለሃብቱ  ሥር  ያሉ ሰራተኞች መክፈል ያለባቸው የሥራ ግብር ነው። ከኢንቨስተሩ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም። ባለሃብቱ በታማኝነትና በአደራ ያንን ቆርጦ ለመንግሥት ማስገባት ሲገባው ለግል ጥቅሙ እያዋለው በወቅቱ ማስገባት አልቻለም። በጊዜው ሲጠየቅም መልካም ምላሽ የማግኘት እድሉ በጣም ጠባብ ነው የነበረው።
ይሄ የአንድ ዓመት ወይም የሁለት ዓመት ብቻ ዕዳ አይደለም። አንድ ባለሃብት ይሄን ያህል ዕዳ እስኪጠራቀምበት ድረስ እንዴት ዝም ተባለ? ወይስ ማስጠንቀቂያ ሰጥታችኋል?
በየጊዜው ማስጠንቀቂያ ይሰጣል፤ ተወካይ አለው፤ በተወካዩ በኩል እንዲደርሰው ብዙ ጥረት ተደርጓል፡፡ በእርግጥ ኢንቨስተሩ ብዙ ጊዜ በአካባቢው አይገኝም፡፡ “እሩቅ ነው፣ ሌላ ቦታ ነው፣ ውጭ ነው፣ አዲስ አበባ ነው“ ሲባል ነው የከረመው። ከ2013 በፊት ያለው ከ2.2 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆን እዳ ነው፡፡ እኛ እንደ ገቢዎች ንብረት ለመያዝ ሞክረናል፤ አንድ መኪና ተይዞ እዚህ ታስሮ መጨረሻ ላይ ፍ/ቤት ከስሰን ነበር፡፡ ነገር ግን ከልማት ባንክና ከሌሎች ግለሰቦች ከንብረቱ ያላነሰ ብድር ስላለበት ይሄንን ሸጣችሁ መውሰድ አትችሉም ሲባል፣ ከንብረቱም ከገንዘቡም ሳንሆን ቀረን፡፡
አሁን ለመንግሥት መግባት የነበረበትን ገቢ ማነው የሚሸፍነው?
ባለሃብቱ እንግዲህ መጀመሪያ ላይ 2ሺ ሄክታር መሬት ነው የወሰደው፡፡ ከዚያ ቀጥሎ ወደ 2013 ላይ 1ሺ 500 ሄክታር ነው የሆነው። ይሄን እስከሚያለማ ወይም ልማት ባንኩ መሬቱን ለሌላ ሰው አሳልፎ ሲሰጥ የኛንም እዳ ታሳቢ አድርጎ ለኛም የሚከፍልበት ህግ ስለሚያዝ እሱን እየጠበቅን ነው።
ባለሃብቱ  ስንት ሄክታር ላይ ነበር ያለሙት?
ወደ 300 ሄክታር ነበር ለጊዜው ያለማው፤ የወሰደው ወደ 2ሺ ሄክታር መሬት ነው፡፡
ምን ምን ነበር የለማበት?
 ሙዝና ሌሎች ሰብሎችም ነበሩ፡፡
ሌሎች ሰብሎች ምንድን ናቸው?
ሰሊጥም አምርቷል፤ በቆሎና የተለያዩ ነገሮች ነበሩ በጊዜው።
ባለሃብቱ ከወረዳ እስከ ዞን ድረስ ያሉ አመራሮች ተጽዕኖ አድርገውብኛል የሚል ክስ አቅርበዋል---
እኔ  በእርግጥ ወደ ገቢዎች የመጣሁት ከ2014 ዓ.ም ወዲህ ነው፡፡ ነገር ግን የተለየ ተፅዕኖ በባለሃብቱ ላይ አልተደረገም፡፡ እንግዲህ ከ1996 ጀምሮ  ይሄን መሬት ተረክቦ እያለማ ነው ያለውና ተፅዕኖ ቢኖር እስከ ዛሬ እንዴት ይኖራል?! አንዳንዴ ሰው ሲሸነፍ መሸነፉን ላለመቀበል አካባቢው ላይ የሚፈጥረው ያልተገባ ገፅታ ጥሩ አይደለም። ባለሃብቱ ከፈለገ ነገም ተመልሶ መጥቶ ሊያለማ ይችላል፡፡ ግን ትክክል ያልሆነ ነገር ማውራቱና የአካባቢውን ገጽታ ማጠልሸቱ ተገቢነት የለውም። ስለዚህ ባለሃብቱ ላይ የተለየ ተፅዕኖም ሆነ ጫና አላደርግንም፡፡ ቁጭ ብለን እንነጋገር፤ እዳውንም ጊዜ ሰጥተን መውሰድ እንችላለን ለማለትም እኮ ሰውየውን በአካል እንኳን ማግኘት አልቻልንም። የእሱ ተወካይም ነበር፤ በኋላ ተወካዩንም ማግኘት አልቻልንም። በበቃኝ እኮ ነው ወጥቶ የሄደው፡፡ ሜዳውም ሜዳ የሆነው፣ ሙዙም ሌላውም ውሀ የሚያጠጣው አጥቶ ነው በራሱ ጊዜ የጠፋው እንጂ ወረዳው  በጣም ብዙ ታግሶታል፡፡  ይሄን ያህል እዳ ማንም ግለሰብ ላይ ቢኖርበት፣ ግለሰብ ያሳድራል እንዴ!? ወረዳው መልማት የሚችል በጣም ሰፊ መሬት አለን፣ በቂ ውሃም አለን፤ ተጨማሪ ኢንቨስተሮች ያስፈልጉናል ብሎ በጣም ተሸክሞታል፡፡ ነገር ግን  ዛሬ ላይ ባለሃብቱ የአካባቢውን ገጽታ በሚያጠፋ መልኩ መምጣቱ ብዙም ተቀባይነት የለውም።
ባለሃብቱ ያቀረቡት ክስ ሁሉ ትክክል አይደለም ነው የሚሉት?
ትክክል አይደለም፡፡ ይሄን ያህል ያልተከፈለ ዕዳ እኮ ችለን ባለሃብቱ እስኪመጣ እየጠበቅን ነው። የተለያዩ መኪናዎች፣ ጋሪዎች፣ የተለያዩ ንብረቶች እያሉ፤ ይሄ ቋሚ ንብረት ስለሆነ ቢመጣ ሊያለማው ስለሚችል፣ ሲመጣ እንነጋገራለን ብለን እየጠበቅን ነው ያለነው። እስካሁን መሬቱ ባዶ ሜዳ ጨፈቃ ለብሶ ነው ያለው፤ እና ልዩ ተፅዕኖ አሳድረን የፈጠርነው ነገር የለም፡፡ አሁንም ቢሆን በወረዳችን ሰፊ መሬት አለን፤ ውሃም አለን፤ አየር ንብረቱም በጣም የተሻለ ነው። እርሻ ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ማዕድናትም አሉ። የድንጋይ ከሰል ጭምር ያለበት ወረዳ ነው፤ ገና እየተጠና ነው፤ ይረጋገጣል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ወርቅና ቢያንስ ከ15 በላይ ማዕድናት ያሉበት ወረዳ ነው፤ ምንም ያልተነካ ጥሬ የተፈጥሮ ሃብት ያለበት አካባቢ  ነው፡፡ ከዚህ አንጻር  የትኛውንም ጉዳይ በሰላማዊ መንገድ  መነጋገር እንችላለን።
በመጨረሻ የሚያክሉት ነገር ካለ--?
እንግዲህ ባለሃብቱ እስከ 2015 አጋማሽ ድረስ ወደ 2.2 ሚሊዮን ብር እዳ አለበት፡፡ በዚህ የተነሳ ወረዳችን ዛሬ ላይ ደሞዝ መክፈል አልቻለም፤ በጣም ከፍተኛ ችግር ውስጥ ነው ያለነው፡፡
ግለሰቡ እዚህ አገር ላይ እዚህ ወረዳ ላይ የቆየ ሰው ነው፤ ያለማ ሰው ነው፤ ብዙ ሃብት ያገኘ ሰው ነው፤ ይሄንን ታሳቢ አድርጎ እዳውን  የሚከፍልበት መንገድ ቢፈጥር ጥሩ ነው፡፡ ከአሰራር ጋር ተያይዞ የተለየ ነገር ካለ ከእኛ ጋር መነጋገር ይቻላል። ነገር ግን 2.2 ሚሊዮን ብር እዳ ያለበት ግለሰብ መሆኑን፣ ለህዝባችን ልማት እንድንሰራ እኛንም እንዲረዳን ጥሪ ማስተላለፍ እፈልጋለሁ።

,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,---------------------------------------------------------

”ባለሃብቱ ተጽዕኖ ቢደረግበት ኖሮ ይሄን  ያህል ጊዜ አይቆይም ነበር”

በመጀመሪያ ስምዎትንና የሥራ ሃላፊነትዎን ይንገሩን?
ካሣሁን ዋሲሁን እባላለሁ፤ በገረሴ ወረዳ ምክትል ከንቲባና የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ ነኝ።
እስቲ ስለ ወረዳው በጥቂቱ ያስተዋውቁን?
ወረዳው ከአዲስ አበባ 560 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ሦስቱንም የአየር ንብረቶች ያካተተ አካባቢ ነው። ቆላማ፣ ወይን አደጋና ደጋ የአየር ንብረት ማለት ነው፡፡ በቆላው አካባቢ ጤፍ፣ ሰሊጥ፣ ሙዝ፣ በቆሎ፣ ማሽላ ሲበቅልበት፤ በደጋውና ወይን አደጋው ደግሞ ባቄላ፣ አተር፣ ስንዴ፣ ገብስና ማሾ  የመሳሰሉት ይበቅሉበታል፡፡
እርስዎ በቀደመው ጊዜ ያለዎት ሃላፊነት  ምን ነበር?
ከ2010 ዓ.ም በፊት ቦንካ ወረዳ ተብሎ ነው የሚታወቀው፡፡ ከዛ በኋላ ነው እንግዲህ ገረሴ ዙሪያ ወረዳ ተብሎ የተዋቀረው።  ከ2010 -2013 ዓ.ም ድረስ በአመራርነት ሰርቻለሁ፡፡
በወቅቱ በአካባቢው ላይ  ምን ያህል ኢንቨስተሮች  ነበሩ?
በወቅቱ በአካባቢው ላይ አንድ በግብርና ዘርፍ ላይ የተሰማራ ባለሀብት ብቻ ነው የነበረው፡፡ ኦልግሪን አግሮ ኢንዱስትሪ ኃ.የተ.የግል ማህበር ይባላል፡፡
ኦልግሪን ብቻ  ነው  የነበረው?
አዎ፤ እሱ ብቻ ነበር።
መቼ ነው እዚህ አካባቢ ኢንቨስት ማድረግ የጀመረው?
ወቅቱን በትክክል ባላውቀውም፣ እኔ ወደ አመራርነት ከመጣሁበት ከ2010-2013 ዓ.ም ባለው ጊዜ  ነበር።
እሱ ብቻ ለምንድን ነው የነበረው? በቂ መሬት የለም ወይስ ፍላጎቱ ያላቸው ሌሎች ባለሃብቶች አልነበሩም ወይስ የእናንተ የማስተዋወቅ (ፕሮሞሽን) ችግር ነው?
የኛ ችግር አልነበረም፤ ሌሎች ባለሃብቶች በመጥፋታቸውም አይደለም፤ በወቅቱ ባለው  ሁኔታ መሬቱን ተቀብሎ የነበረው ኦልግሪን በመሆኑ ነው፡፡
ተጨማሪ መሬቶችን ለሌሎች ባለሃብቶች ለምን ምቹ አላደረጋችሁም?
ይሄ ባለሃብት በሰዓቱ የነበረውን መሬት ተቆጣጥሮት ነበር፡፡ ሰፊ መሬት የነበረን እዚያ አካባቢ ነው፡፡ ከነበረን መሬት ወደ 2ሺ ካሬ የሚሆነው በባለሃብቱ ስም ነው  የነበረው። ለኢንቨስትመንት አመቺና ውሃም በአቅራቢያው የሚገኝ፣ የመሬቱ አቀማመጥ (አግሮኮሎጂው)ለእርሻ የሚያመች  እሱ የያዘው መሬት አካባቢ ነው፡፡
ከባለሃብቱ ጋር ያላችሁ ግንኙነትና  ቀረቤታ እንዴት ነበር?
ከእኛ ጋር በግል ችግር አልነበረብንም።  እንደ መንግስት ደግሞ  ባለሃብቱ ከእርሱ የሚጠበቅበትን ግዴታ ባለመወጣት የተነሳ ብዙ ግጭቶች ነበሩ። የእርሻና የመሬት መጠቀሚያ ግብር በወቅቱ ያለመክፈል ሁኔታ በእጅጉ ይስተዋል  ነበር። ለምሳሌ ከ2007-2009 ዓ.ም ድረስ የገቢዎች ጽ/ቤት ሃላፊ ነበርኩ። በዚያን ጊዜ የንብረት መያዝ፣ ማስጠንቀቂያ የመስጠት---እስከ መደባደብ የደረስንበት ሂደቶች ነበሩ። በተደጋጋሚ ለግብር የንብረት መያዣ ሰጥተን ነበር። በአጋጣሚ እርሱን ስላላገኘነው የክልልና የዞን አመራሮችን ይዞ በዚህ ሲያልፍ የንብረት መያዣ ስንሰጠው አልቀበልም የሚል እሰጣ ገባ ውስጥ የገባንበት ሂደት ተፈጠረ፡፡
እርምጃ አልወሰዳችሁም?
አልወሰድንም። በደራሼ ሲመለስ በዞን ተይዞ ታስሮ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ዕዳውን አልከፈለም፡፡ ከዚያም ለውጡ መጣ፡፡ ግን ችግሩ በዚያው ነው የቀጠለው፡፡
ባለሃብቱ፤ በወቅቱ የነበሩት አመራሮች እርስዎን ጨምሮ ከፍተኛ ጫና አድርገውብኛል፤ ከፍተኛ በደል ተፈጽሞብኛል፤ ጥቂት ባለሃብቶች ለጥቂት የወረዳው ባለሥልጣናት ሙስና በመስጠት በጣም ከፍተኛ ጫና አድርሰውብኛል፡፡ በዚህ የተነሳ ለ500 ሚሊዮን ብር ኪሳራ ተዳርጌአለሁ ብለዋል፡፡ እርስዎ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ይላሉ?
እንግዲህ በሰዓቱ ሌላ ባለሀብት አልነበረም፤ እሱ ብቻ ነው የነበረው። እሱ ብቻ ሆኖ ከሌላ ባለሃብት ጋር ተሞዳሙደን በእሱ ላይ ጫና የምናደርስበት ሁኔታ እንደሌለ ማወቅ አለባችሁ። ባለሃብቱ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ ነው መሬቱን የያዘው፤ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ምንም ሳያመርት፣ ለህብረተሰቡ ለአርሶ አደሩ ምንም መሰረተ ልማት ሳይገነባ ነው የቆየው። ይህን ንብረት መያዣ እያደረገ ከየባንኩ እየተበደረ  ነው የቆየው። ተጽእኖ ቢደረግበት ኖሮ ይሄን ያህል ጊዜ አይቆይም ነበር።
በተጨማሪም ባለሃብቱ በብሔሬ፣ በማንነቴ የተነሳ ከፍተኛ ተፅዕኖ ተደርጎብኛል ብለዋል፡፡ በዚህ ቅሬታስ ላይ ምላሽዎ ምንድን ነው?
በብሄር ላይ ተንተርሰን ተጽዕኖ ያደረግነው ነገር የለም፤ ሊኖርም አይችልም፤ ህገ-መንግስታችንም ይሄን አይፈቅድም። ይሄ ደግሞ ቢኖርም በሰዓቱ በህግ መብቱን ሊያስከብር ይችላል። እኔ በነበርኩበት ወቅት  ያለብህን እዳ ክፈል ተብሎ ከመጠየቅ ያለፈ ብሄር ተኮር ጥቃት አልተደረገበትም።
ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ስጋት ለገባቸው ሌሎች ባለሃብቶች ምን መልዕክት ያስተላልፋሉ?
ብዙ ከሌላ ቦታ የመጡ ሰዎች አሉ፤ ኑና አካባቢያችንን አልሙ ነው የምለው። ለዚህ ደግሞ ዋስትናችሁ ህገ-መንግስቱ ነው እንጂ ግለሰብ አይደለም፤ ስለዚህ አትፍሩ የሚል መልዕክት ነው የማስተላልፈው።


Read 835 times