Saturday, 12 August 2023 20:43

አሜሪካና እንግሊዝን ጨምሮ 5 አገራት በኢትዮጵያ የሰላማዊ ሰዎች ሞትና ጥቃት ያሳስበናል አሉ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የተመድ የሰብአዊ መብት ኮሚሽንም፣ በአማራ ክልል እየተባባሰ የመጣው ግጭት በጽኑ አሳስቦናል ብሏል
- የአውሮፓ ህብረት ልዑክ 19 አገራት ኤምባሲዎችም በጋራ መግለጫቸው በአማራ ክልል በተቀሰቀሰው ሁከት የዜጎች ሞትና አለመረጋጋት እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል


በኢትዮጵያ በተለይም በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ የተከሰቱት ግጭቶች እንዳሳሰባቸው እንግሊዝና አሜሪካን ጨምሮ 5 አገራት በጋራ ባወጡት መግለጫ አስታወቁ። አገራቱ በዚሁ መግለጫቸው፤ አለም አቀፉ ማህበረሰብ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ዘላቂ ሰላም የሚደረገውን ጥረት መደገፉን እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።
አሜሪካ፣ ዩናይትድኪንግደም፣ አውስትራሊያ፣ ጃፓንና ኒውዚላንድ ትናንት በጋራ ባወጡት መግለጫቸው፤ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች የተቀሰቀሰው ግጭት ለሰላማዊ ሰዎች ሞትና ለአካባቢው አለመረጋጋት ምክንያት ሆኗል ብለዋል።
የኢትዮጵያውያንን ዘላቂ የተረጋ አገር የመፍጠር ግብን እንደሚደግፉ የገለጹት አምስቱ አገራት፤ ሁሉም ወገኖች ንፁሃን ዜጎችን እንዲጠብቁና ሰብአዊ መብትን እንዲያከብሩ ጠይቀዋል። አገራቱ ሁሉም ወገኖች ግጭቶችን  በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በጋራ እንዲሰሩ ጥሪ ባቀረቡበት በዚሁ የጋራ መግለጫቸው፤ እንዳመለከቱት አለም አቀፉ ማህበረሰብ ለኢትዮጵያውያን ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የሚደረገውን ጥረት መደገፉን እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።
መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ከተማ ያደረጉ የአስራ ዘጠኝ አገራት ኤምባሲዎችና በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት ልዑክ በበኩላቸው፤ ሁሉም ተፋላሚ ወገኖች ንፁሃን ዜጎችን ከጥቃትና ከጉት እንዲጠብቁ አሳስበዋል።
በአማራ ክልል የተቀሰቀሰው ሁከትና የንፁሃን ዜጎች ሞት እጅጉን አሳስቦኛል ያለው በኢትዮጵያ የህብረቱ ልዑክና መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የአስራ ዘጠኝ አገራት ኤምባሲዎች የጋራ መግለጫ፤ የውጪ አገር ዜጎች ከግጭቱ አካባቢ ለቀው እንዲወጡና ደህንነቱ ወደተጠበቀበት ስፍራ እንዲሄዱ እንዲፈቀድም ጠይቀዋል።
ከአውሮፓ ህብረት ልዑክ ጋር በጋራ መግለጫቸውን ያወጡት የፈረንሳይ፣ የጀርመን፣ ሲውድን፣ አውስትሪያ፣ ቤልጂየም፣ ፊንላንድ፣ ዴንማርክ፣ ቼክ ሪፐብክ፣ ጣሊያን፣ አየርላንድ፣ ስፔን፣ ሮማኒያ፣ ፖላንድ፣ ስሎቬኒያ፣ ማልታ፣ ኔዘርላንድስ፣ ሉክሰምበርግና ሃጋሪ ኤምባሲዎች ናቸው።
በተያያዘ ዜና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ከትናንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ በአማራ ክልል እየተባባሰ የመጣው ሁኔታ ግጭት በእጅጉ  አሳስቦኛል ብሏል።

Read 1013 times