Saturday, 12 August 2023 20:45

በአማራ ለተከሰተው ግጭት ሰላማዊ መፍትሔ እንዲፈለግለት 9 የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማት አሳሰቡ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች  የተቀሰቀሰውንና በርካታ  ሠላማዊ ዜጎችን ለህልፈት ዳርጓል የተባለው ግጭት  በእጅጉ እንዳሳሰባቸው የገለፁ የሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማት፤ ግጭቱን   ለመፍታት በሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎች የተጀመሩ የሰላም ጥረቶችና ስምምነቶች በክልሉም እንዲተገበሩ ጠየቁ። የክልሉን ሠላም ለማስጠበቅ በተጣለው  የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ  አፈጻጸም ወቅት የመንግስት የጸጥታ አካላት ያልተመጣጠነ ኃይል እንዳይጠቀሙና  ብሔርን መሠረት ያደረጉ  ጥቃቶችና  የጅምላ እስሮች እንዳይፈጸሙም ተቋማቱ አሳስበዋል።
በክልሉ  ከወራት በፊት የተቀሰቀሰውና ሰሞኑን ተባብሶ የቀጠለው ግጭት ለንጹሃን ዜጎች ህልፈት ምክንያት መሆኑን ያመለከቱት ተቋማቱ፣ ግጭቱን ለማስቆም የሚወሰዱ እርምጃዎች የብዙሃንን ደህንነት፣ የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶችእና ነጻነቶች አደጋ ላይ የማይጥሉ  መሆን  እንደሚኖርባቸው ገልጸዋል።  
በአማራ ክልል በተፈጠረው ግጭት ስጋት እንደገባቸው የገለጹትና ግጭቱ በሰላማዊ መንገድ መፈታት የሚችልበት መንገድ እንዲፈለግ ያሣሰቡት ዘጠኙ ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማት፤ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ህብረት፣  የመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ)፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል፣ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር፣ የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት፣ የኢትዮጵያ ሴቶችና ሕፃናት ማህበራት ህብረት፣ የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች፣ አዲስ ፓወር ሀውስ  እና ሴታዊት ንቅናቄ   የተሰኙት   ድርጅቶች ናቸው።
በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፉና ስር እየሰደዱ መሆኑን የጠቆሙት ተቋማቱ የመንግስት የጸጥታ አካላት  የሕዝብን ሰላም እና ደኅንነት ለማስጠበቅ እንዲሁም ሕግና ሥርዓትን ለማስከበር ያለመ እንደሆነ የተነገረለትን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚያስፈጽሙበት ወቅት ያልተመጣጠነ ኃይል ከመጠቀም እንዲታቀቡ፣  የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈጸም የሚወጡ መመሪያዎችና ደንቦች፤ ለዜጎች ተደራሽ በሆኑ አማራጮች በተከታታይ እንዲደርሱ ጠይቀዋል። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈጻጸም ሂደት ውስጥ  ብሔርን መሠረት ያደረጉ ማግለሎችና ጥቃቶች እንዳይስፋፉና የጅምላ እስሮች  እንዳይከናወኑም  ጥሪ አቅርበዋል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባለፈው አርብ የደነገገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ፤ በአማራ ክልል ከተፈጠረው የጸጥታ መደፍረስ ጋር “ግንኙነት ያላቸው፣ ጉዳዮችን የሚያባብሱ፣ ስምሪት የሚሰጡ” የተባሉ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋል እንደተጀመረ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ማስታወቁ ይታወሳል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚያስፈጽመውን ጠቅላይ መምሪያ ዕዝን  በዋና ሰብሳቢነት የሚመሩት አቶ ተመስገን ጥሩነህ ባለፈው  እሁድ በሰጡት መግለጫም፤ በቀጣይ ቀናት የሚወሰዱ እርምጃዎች እንደሚኖሩ ጠቁመዋል።
በሌሎች የአገሪቱ ክልሎች በተከሰቱ ግጭቶች የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች፣ ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችና ሌሎችም ጉዳቶች በክልሉ እንዳይፈጸሙ ከፍተኛ የመከላከል ስራዎች እንዲያከናወኑና የተጠያቂነት ስርዓት እንዲዘረጋ የጠየቁት ተቋማቱ፤ ግጭቱ በተከሰተባቸው የአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞችና አጎራባች አካባቢዎች ለሚገኙ ተፈናቃዮች ሰብአዊ እርዳታዎች በአግባቡ እንዲደርሱ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲደረግ  ጥሪ አስተላልፈዋል።
በአማራ ክልል የተከሰተው ግጭት መንስኤዎችና ዘላቂ መፍትሔው፤ በሚመለከታቸው አካላት ተለይቶ መቅረብ እንዳለበት በመግለጫቸው ያመለከቱት የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማቱ የሀገር ሽማግሌዎች የሲቪል ማህበራት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የእምነት ተቋማትና  መገናኛ ብዙሃን  ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ   የበኩላቸውን ግፊት ማድረግ  እንዳለባቸው አመልክተዋል። በሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎች የተጀመሩ የሰላም ጥረቶችና ስምምነቶች፤ በአማራ ክልል በሚንቀሳቀሱ ወገኖችና በፌዴራሉና በክልሉ መንግሥታት መካከል የሚተገበርበት ዕድል እንዲፈጠርም ጥሪ አቅርበዋል።

Read 1297 times