Saturday, 12 August 2023 00:00

“ብላ ያለው ተጋግሮ ይጠብቀዋል ተሸከም ያለው ታስሮ ይጠብቀዋል”

Written by 
Rate this item
(3 votes)

በአንድ መንደር የሚኖር አንድ ድመት ያለው ሰው አለ፡፡ ድመቱ በመንደሩ እየተዘዋወረ በርካታ የድመት ወዳጆችና ውሽሞች አፈራ፡፡ አንድ ቀን አንዷ ድመት ዘንድ፣ ሌላ ቀን ሌላ ድመት ዘንድ እየተዘዋወረ ሲወሰልት ከረመ፡፡ በውጤቱም የመንደሩ ድመቶች ሁሉ አረገዙ፡፡ አያሌ ተፈለፈሉ። የሰፈሩ ሰው ሁሉ በድመቶች ብዛት ተጨናነቀ፤ መረረውና እድሩ ተሰበሰበ፡፡ ይሄንኑ ምሬቱን ተወያየ። በመካያው የአገር ሽማግሌዎች ተመርጠው ወደ ባለድመቱ ሄዱና እንዲህ አሉ፡-
“ጌታዬ፣ መቼም አንተ አስበህ ለተንኮል ያደረግኸው አይመስለንም፡፡ ሆኖም ችግሩ መፈጠሩ አልቀረም”
ሰውዬውም እንዲህ ለምድር ለሰማይ የከበዱ ሰዎች ላይ ምን ችግር ፈጠርኩባቸው በሚል ተሽቆጥቁጦ፤
“ምን ጥፋት አገኛችሁብኝ ጌቶቼ?” ሲል ጠየቀ፡፡
የሽማግሌዎቹ ተወካይም፡-
“አየህ ያንተ ድመት በሰፈሩ አንዲትም የቀረችው ድመት የለች፡፡ የድመት ማቲ ተፈለፈለ ተፈለፈለና በዚህ ምክንያት መንደሩ ሁሉ በድመት ተወረረ፡፡ አሁን ድመትህን ታስርልን ዘንድ ልንጠይቅህ ነው የመጣነው፡፡”
ሰውዬው፡-
“ታዲያ ምን ችግር አለ? እኔ እንደሚሆን አደርጋለሁዋ!” አለ፡፡ አመስግነውት ይለያያሉ፡፡
ባለድመቱ ሲያወጣ ሲያወርድ ይቆይና በመጨረሻ ውሳኔ ላይ ይደርሳል፡፡
ከጊዜ በኋላ በመንደሩ አንድ አደገኛ የእንስሳት ወረርሽኝ ይገባል፡፡ የሰፈሩ ትናንሽ ድመቶች በሙሉ ይረፈረፋሉ፡፡
ጭንቅ መጣ- ምክንያቱም አይጥ ደግሞ በተራው መንደሩን ወረረው፡፡ ሳሎን ከጓዳ የአይጥ መናኸሪያ ሆነ፡፡ የአገሩ ሽማግሌዎች እንደገና ወደ ባለ ድመቱ ይመጣሉ፡፡
ባለድመቱ፡- “አሁን ደግሞ ምን ተፈጠረ አባቶቼ?”
የሽማግሌዎቹ ተወካይም፡- “አንድ ችግር ገጠመን ወዳጄ፡፡ ያ የአንተ ድመት ከቤቱ መውጣት ካቆመ በኋላ አይጥ አላስቀምጥ አለን፡፡ አንድ ጊዜ ደግመህ ብትቸገርልንና ድመቱን ብትለቀው?”
ባለ ድመቱ፡- “አባቶቼ ያንንማ ለማድረግ ከእንግዲህ አልችልም፡፡”
የሽማግሌዎቹ ተወካይ፡- “ለምን ወዳጄ?”
ባለ ድመቱ፡- “ለአንዴም ለሁሌም እንዳያስቸግራችሁ ብዬ አኮላሸሁት!”
ሁሉም ጭንቅላታቸውን ያዙ፡፡ አዝነው መንገዳቸውን ሲቀጥሉ፣ ባለድመቱ ተጣራና አንድ ተስፋ ሰጣቸው፡-
“ጌቶቼ ሆኖም ድመቴ ስራ አልፈታም፡፡ ሊያግዛችሁ ይችላል”
ቆም ብለው፡- “በምን መንገድ ይረዳናል?”
ባለ ድመቱ፡- “የአማካሪነት አገልግሎት ስራ ጀምሯል- Consultant ሆኗል!!!”
***
የአማካሪው ዓይነት በበዛ ቁጥር ማ በጤና፣ ማ ተስፋ በቆረጠና በተኮላሸ አቋም እንደሚያማክር ለመለየት ያስቸግራል፡፡ አማካሪው ከግራ ከቀኝ መሯሯጡ ሲበዛ ማ “የመጣው ይምጣ!” በሚል እንደሚያቅድ፣ ማ በአቦ-ሰጡኝ እንደሚመራ፣ ማ አለቃውን የሚያስደስት መፈክር ማስገር እንደሚሻ፣ ማ እንደበቀቀን ከላይ የተነገረውን ብቻ በመደጋገም አዋቂ ለመምሰል እንደሚፍረመረም አበጥሮ ለማየት እጅግ ያዳግታል፡፡ በመንደር በሰፈሩ አንድ ሽለ-ሙቅ አጥቂ (fertile) ድመት ብቻ መኖሩንና የተፈለፈሉ ድመቶች እንደ አሸን መፍላት አሳሳቢ ሁኔታ መፍጠሩ፤ የትኩረቱን አቅጣጫ ሁሉ ከአይጦች መምጣት አንፃር እንዳይታይ አደረገው፡፡ ሁኔታው የአገር የቀዬውን አይን ማወሩ የሚገርመውን ያህል፣ የባለድመቱ ድመቱን የማኮላሸት ፈጣን እርምጃ ይብስ አስደንጋጭነቱን ያጎላዋል፡፡ ያ ሳይበቃ የመንደሩ ሰዎች፤ አይጦች መፈልፈል ሲጀምሩ፣ “እኛ እንዴት አይጦቹን ልናስወግድ እንችላለን?” የሚለውን  ጥያቄ አላነሱም፡፡ የተለመደውን የድመቱን ጌታ እንደ መፍትሄ በማሰብ ወደሱዉ ያመሩት ሽማግሌዎች ብቸኛው መልስ አለመኖሩን ሲረዱ፣ የደረሰባቸው የሀሞት መፍሰስም፤ የማሳቁን ያህል፣ የድመቱ የአማካሪነት አገልግሎት ደግሞ ከተፍ አለ፡፡ “ባላጋባ ማጫፈር ያቅተኛል ወይ?” ዓይነት ተሳትፎ መሆኑ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ የሀገራችንን የችግር መፍትሔ አሰጣጥ፣ የዕቅድ አወጣጥ፣ ድቀት አፈረጃጀትና አፈታት (Crisis management) ምን እንደሚመስል፣ ሌሎችንም ሁናቴዎች የሚያመላክት ሁኔታ ነው፡፡ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ምስቅልቅል ሂደቶች እንደተለመደው በሹም-ሽር (appoint-demote) ፈጣን እርምጃ እንዳንገላገለው “ወተት ያጠጧት ውሻ፣ ቅቤ ሳትቀቡኝ አልሄድም ትላለች” እንዲሉ፤ የውስጥ አዋቂነትና ጠላት የማብዛት ስጋት መንገዶችን ሁሉ እያቆላለፉ መራመጃ ያሳጡ ይመስላሉ፡፡ ምንም እንኳ የምሩ ሰዓት አይቀሬ ቢሆንም፣ ጊዜያዊ መረጋጋትን (temporary stability) የሚሰጡ ሁኔታዎችን በማሰላሰል “አንገብጋቢ አይደለም” ብሎ እንደማለፍ ያለ አደገኛ መፍትሄ የለም፡፡ ዛሬ የሚፈጠርን ችግር ነገ እናስብበታለን ብለን አንዘልቀውም፡፡ ጉድጓዱን ሳይደፍኑ አይጢቱን የማሳደድ ዓይነት ብልሀት ሙስናን እንደማያስወግድ ሁሉ፤ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መሰረተ-ጉዳዮች ውስጥ ያሉ ጉድጓዶችን በቀና ልቡና ሳይደፍኑ መረጋጋት፣ መቻቻል፣ በራስ መተማመን በዋዛ የሚገኙ ነገሮች አይሆኑም፡፡ ከሁሉም ቀዳሚው አርቆ ማስተዋል ነው፡፡ የቤት ስራን ለመስራት የምንተጋውን ያህል፣ ኃላፊነትን ለመወጣት ሌት-ተቀን እንፍጨረጨራለን የምንለውን ያህል፣ አርቆ አስተዋይነትን በተገቢው መጠን መያዝ ይኖርብናል፡፡ ከዚህ ወይም ከዚያ እርምጃ ሀገር ምን ትጠቀማለች ማለትን ግንዛቤ ውስጥ ልናስገባ ያሻናል፡፡ ከምሁራንና ከረዥም ዕድሜ የልምድ ባለቤቶች የሚገኘውን ዕውቀት እንዴት በአግባቡ ለሀገር በሚበጅ ፈርጁ መጠቀም ይገባል ብሎ በብልህ ልቡና ማሰብ ይገባል፡፡
የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች የመፏከቻና የመሻኮቻ መድረክ መፍጠር ሳይሆን፣ ያልተሄደበትን መንገድ እንዴት እናግኘው የማለትን ብልሀት መሻት ያስፈልጋል፡፡ በአሉታዊ-መነሻ ሳይሆን በአዎንታዊ-መነሻ ላይ ቆሜና የሀገሪቱን መዳን አስቀድሜ፣ እንዴት ልጓዝ? ብሎ የማሰብ ሆደ-ሰፊነት እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ የተመቻቸ ሁኔታ አይፈጠርልኝም ብሎ የተስፋ-ቆራጭ መንገድ ከማሰብ የግድ መንገዱን መፍጠር አለብኝ ብሎ ቆርጦ መነሳት፤ ህዝብን ወደ በለጠ አዘቅት ከመምራት፣ አገርንም ይበልጥ ወደ ተወሳሰበ አደጋ ከመግፋት የሚገታ ብስለት ይሆናል፡፡ “የሞኝ ጀርባ ሲመታ የአስተዋይ ጀርባ ያመዋል” ይሏልና፤ ከህመማችን ተነስተን፤ የአተያያችን አቅጣጫ ቀናና አዎንታዊ መሆን እንደሚገባው አበክሮ ማስተዋል ነው፡፡
የሀገራችንን ሁኔታ “አንዴ ካመጣው ምን ይደረግ” በሚል ህሊና ለማለፍ አዳጋች ነው፡፡
“አይጣል ይሏል እንጂ ከጣለ ምን ይሏል
ከመቀነት ወጥቶ ብር ይኮበልላል”
ብለን ያላሳብ ለመተኛት የሚቻል ቢሆን መታደል ነበር፡፡ ሆኖም በተጨባጭ አካልንም አዕምሮንም የሚኮሰኩስ ሳንካ በየቢሮው፣ በየበሩ፣ በየማጀቱ ይጎረብጣልና ዐይንን መግለጥ ወይም ማፍጠጥ ብቸኛ አማራጭ ይሆንብናል፡፡ ለማንኛውም ተኝቶ ማደር አለመቻሉን ነው የምናጤነው፡፡
ስለ ተግባራዊ ዲሞክራሲያዊነት፣ ስለ እውነተኛ ፍትሀዊነት፣ ስለ ልባዊ መልካም አስተዳደርና ዕብለት-አልባ ስለሆነ የሀገር ዕድገት የምናወራ ከሆነ፤
“ብላ ያለው ተጋግሮ ይጠብቀዋል
ተሸከም ያለው ታስሮ ይጠብቀዋል”
ለሚል ዓይነት አሰራርና ተጨባጩን ሂደት እድል ለሚያስመስል ወገናዊ አካሄድ፣ ከቶም ቦታ ልንሰጠው አይገባም፡፡

Read 1134 times