Sunday, 27 August 2023 19:46

ተዋጊ ህሊና

Written by  ድረስ ጋሹ
Rate this item
(2 votes)

በቅጠሎቹ ከፀሐይ የከለላት፣ ግንዱ አልጋ ሆኖ ያስተኛት ያ የጽድ ዛፍ ተቆረጠ። ጽድ መቁረጥ እንደማሳደጉ አይከብድም። ያው መናድ መካብን አይመስለውም፤ አያክለውምም።
ቻይኒስ ባምቡን የማያውቅ የለም። የበዙ ዓመታትን ሥር በመስደድ ይገፋል፤ ከአምስት ወይም ስድስት ዓመት በኋላ በፍጥነት ከመሬት በላይ ይምዘገዘጋል። በግምት ከ30-90 ሳ.ሜ (ከ12 እስከ 35 ኢንች) ያድጋል_በቀን። አንዳንዱ ስሜት እንዲህ ውስጥ ለውስጥ ለማደግ ረጅም ጊዜ ይወስድና ሲወለድ በፍጥነት ይቀጣጠላል፤ ይኼን ይፈሯል።
የዛች ሴት እንባ ወደ ውስጥ መፍሰስ ጀምሯል። እንባዋ አፍንጫዋን ታ’ኮ ቢመጣ ታብስበት እጅ የላትም። ምናልባትም ያበላችው ሰው ዱሽ እንዳደረጋት ይገመታል። በመሆኑም በአጎረስኩ እጄን ተነከስኩ ብትል ያምርባታል።
ዘጠኝ ልጆች ያሳደገች እናት ናት።
ማርገዝን ያህል ኃላፊነት፤ ምጥን ያህል ጭንቅ አይታለች።
ብዙ ነገሮች ተነጥቀውን ይሰጡናል። እኛም አናውቅ እንደሰታለን። ሳይሞት በፊት የመጀመሪያ ልጇን ካድሬዎች አሰሩት፤ ክፉኛ አዘነች። መልሰው ሲፈቱት ግን አዲስ ደስታ ተወለደ። ይኸው ነው አዲስ ነገር መስጠት የተሳነው ያለን ነጥቆ መልሶ በማቀበል ደስታን ሊሰጥ ይጥራል። ታሪኳ በካድሬ አያልቅም። ደስታዋን የነጠቋት ሰዎች ደስታ ሊሰጧት ይከቧታል። ምናልባትም ከሰረቋት ደስታ ቆንጥረው እንጅ አዲስ እንዳይደል ግልጽ ነው።
ከዘጠኙ የተረፈው ልጇ በግጥም የታጀበ ደብዳቤ ጻፈላት።
“ምናልኩሽ እናቴ...
በትልቅ እንስራ ወተት የሰጠሽኝ
የት ላይ ተቀምጦ ይገፋው ብለሽኝ።”
ደብዳቤውን ሰው ገልጦ አነበበላት። ሰምታ ዝም አለች። ኃዘን ሰቅዞ ይዞ አላላውስ እንዳላት ለመገመት አይከብድም። ስምንቱ ልጆቿ ይኼን ቅሬታ ከትበው ለእናታቸው ሳይልኩ የአሞራ ቀለብ ሆነዋል። ጥሩ ግጥም እንደሚያደምጥ፣ ሜድቴሽን ውስጥ እንዳለ፣ ከዓለም እንደተራራቀ ሰው ሆነች። ዓይኗ ፍጥጥ፣ ግንባሯ ሽብሽብ፣ ከንፈሯ ዛል ብሏል። የለበሰችው ጎዳ ቀሚስ ተዝረክርኳል።
“እንዳልዋጋ ቀንድ የለኝ
 እግዜር ጎዳ አድርጎኝ”
ማለቱ አይቀርም ቢጠይቁት ቀሚሷን። ከሥሯ እንደተመዘዘች ዕጽ፣ ውኃ እንደጠማት ተክል ሆናለች። አፍንጫዋን አማክለው ለመውረድ የሚሽቀዳደሙ እንባዎች በደም ሥሮቿ ገብተዋል። አቤት ዝምታዋ መክበዱ። በቀኝ በኩል ለይምሰል  ከምትፈስ የእንባ ዘለላ አንዲት ዝንብ ጥሟን ትቆርጣለች። ይኸው ነው፣ ከኀዘኗ ደስታ ይቀዳል።
“ሆድ ይፍጀው”  
ዝምታዋን ገርስሶ የመጣ ክቡድ ንግግር ነው።
ላየው ኅልቆ ቢሱን ጉዞ፣ ለታዘበው ወዠባሙን ቀን የኀዘኗን ቅጥ ይረዳል። አንገቷን አቀርቅራ፣ ዱሽ እጆቿን አንከፍርራ ኀዘኗን ትፈትላለች። በእንዝርት ወገብ ላይ የሚዞረው ጥጥ ለአቅመ ልቃቂት ሲበቃ ይወጣል፤ የእሷ ኀዘን ለአቅመ-መውጣት አልደረሰም።
ኀዘን ሲበዛ ቃል ያንሳል።
ኀዘን ሲበዛ መናገር አያቀለውም።
ዝም...ጸጥጥ...እልም ወደ ውስጧ። እንባዎቿ ከደሞቿ እኩል በሰውነቷ ይሮጣሉ። መሬት ስትንቀጠቀጥ በውስጧ እንደሚደንሰው ዌቭ ፣ እንባዎቿ ለድርጊቶቿ አባሪ ይሆናሉ።
በልጅነቷ መጻሕፍትን አገላብጣለች። አልወለድም ምርጫዋ ነው። ምርጫዋን እንዳልኖረች ሲሰማት ሌላ ህመም። የአቤ ጉበኛ ስሜት ይጋባባታል። መወለድ ትርጉሙ ከስቃይ ጋር ጋብቻ መፈጸም እንደሆነ ታምናለች። ከእናት ማህጸን ከሰፊው ዓለም ...ወደ ጠባቧ ዓለም የመቀላቀልን አባዜ አጥብቃ መቃወም ያምራታል።
የዓለምን ጣዕም ለልጆቿ ልታቀምስ...ለአቅመ አዳም ለአቅመ ሔዋን ልታደርስ ...ዘጠኝ ተንበረከከች፤ ዘጠኝ ህመም ወለደች።
ዱሽ እጇን ተንተርሳ ተኝታ ታልማለች። አንገቷ በዶማ ቢላ ሲታረድ ባነነች። መከረዋን ስለት እንዲያቀለው ትሻለች፤ ዳሩ ቀን ቀንን ሲወልድ ኅዘኗ ይራባ ያዘ። ለመሆኑ እንደኀዘን የሚራባ አለ? ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሏት የተባለው ሰው ነው ወይስ ኀዘን?
ይቺ ሴት ቅዳሜ’ለት ገበያ ወጣች። ፀሐይም ተከተለቻት። ሃምሌ ይዟት አርፍዶ ሲለቃት እስሯ የተፈታላት እንቦሳ መሰለች_ፀሐይ። ፍንድቅ ...ፍንድቅድቅ ብላ አላፊ አግዳሚውን ዓይን ታስመልስ ጀመር።
ገበያው የሚጀምረው በዶሮ ነው። ዓይኗ ወደ ቀይ ዶሮ፤ ወደ ባለድርብ ኮከናሙ ተወረወረ። የቤቴ አምላክ ይኼን ይወዳል ያለች አስመስሏታል ፊቷ።
“ስንት ነው?” (ዋጋ ጠየቀች ቀርባ)
“ውሰጂ...ይኸው ኮከኑ ...ይኸው ክብደቱ ...ውሰጂ ...ውሰጂ” (አዋከባት)
ቶሎ “ዋጋ” ባለመጥራቱ ሰበብ ተወችው። ለልጆቿ ጫማ ልትገዛ ወደ ሱቅ ስትኼድ አንበሳ ጫማ ይቀናት ነበር። የጫማዎች ዋጋ ቅድሚያ ተለጥፎ ስታየው ሐሴት ታደርጋለች። ሰው አቅሙን አውቆ ይገዛል ነው ብሂሏ። የሰውም ዋጋ ተመን፣ የመኖር መብቱ የተጠበቀ ነው የሚለውን የሚያስቀድምላት ትሻለች። ለሥጋ ...ዋጋ፤ ለነፍስም ...ዋጋ።
እንቁላሉ በቀኝ በኩል እንደ ዲብ ተከምሯል። ዓይኗ ክፉኛ ተንቀዋለለ፥አእምሮዋ በአይወጣው የሐሳብ ዳገት ዛለ። በረጅም የራስ ፀጉሯ መሐል ትንሽ ነፍሳት ትሯሯጥበት ጀመር። ያንን እንኳ አክካ ለማንሳት ጣት አጠራት። ሰው ትልቅ ነገር ሲያጣ “ጣቴን ተቆረጥኩ” የሚለው በምክንያት ነው ለካ። የጣት ነገር ...
ልቧ ከእንቁላሉ አልራቀም።
ቀድሞ የተፈጠረው እንቁላል ነው ወይስ ዶሮ? የተለመደ ጥያቄ።
ዶሮ ቀድሞ ተፈጠረ፤ እንቁላልም ከዶሮ መጣ።
ወይስ?
እንቁላል ቀድሞ ተፈጥሮ፤ ዶሮ ከእንቁላል ተፈጠፈጠ። ነገሩ በቁስሏ እንጨት ስለሚሰድ ችላ አለችው።
አእምሮዋ ሐሳቧን ያደራጅ ጀመር። እንቁላል ..ከቅርፊት እስከ አስኳል። ከውጭ የሰበሩት እንደሁ ሕይወት ያጣል። ስብራቱ ከውስጥ ከሆነ ግን ጫጩት ያወጣል...ሕይወትም ከዕድገት ትተጫጫለች (If an egg is broken by outside force, life ends. if broken by inside force, life begins. great things always begin from inside). ለዚህም የውስጤ ኀዘን ፈንቅሎኝ ሊወጣ ይገባል ስትል ወሰነች። በደቂቃዎች ልዩነት ራሷን ቤቷ ውስጥ አገኘች።
አእምሮዋ ታጥቋል። መድፍ፣ ታንክ፣ ዲሽቃ፣ ብሬል፣ ከዛም ከዛም በላይ። የእጇን ባዶነት ያየ፣ ያውም ዱሽ መሆኗን አውቆ የሚንቃት ቢኖር ዋጋ ይከፍላል።
ካድሬው በሯን አንኳኳ። የለመደውን መብል መጠጥ ትሰጠው ዘንድ በፊቱ ተማጸናት_ወይ ፍንክች።
ዋናውን በር በእግሯ ገፍትራ ዘጋች። ህሊናዋ የጦርነት ቀጣና ሆኗል። መሣሪያ የያዘን በመሣሪያ ይታገሉታል፤ አእምሮው የታጠቀን ግን ምን ያደርጉታል? ምንም። ቤቱ ለብቻዋ የቀረበት ምክንያት፣ የልጆቿ አልጋ ባዶውን መዋል ማደር የጀመረበትን ሰበብ አመነዠከች።
ከቤቷ ጠባብ ክፍል ገብታ መስታዎት ፊት ቆመች። ፊቷ ላይ የተወሳሰበ ድር ስታይ አቀረቀረች። በዚህ ቅጽበት የለበሰችው ቀሚስ ያነሳቸውን አቧራዎች አየች።
አቧራዎች ተጋፍተው ይመጣሉ። በየልብሱ መንጠላጠል፣ በየአገኙት ዘሎ መግባት ይወዳሉ። ውኃ ያጠራቸው ዘንድ፤ እጅ ይቀንሳቸው ዘንድ ኃይል አለው።ታዲያ ውኃውም ካለ እጅ አይቀዳ፣ እጅም ካለጣት አይሆን ሆነባት(ለእሷ እንጂ ለዮሴፍና ለወርቁ ማሞ ተችሏል)።
የደብዳቤው ሰሞን የሆነው ሆነ። የስምንቱን ልጆቿን ኀዘን ማስተጋቢያዋ ዘጠንኛው ሆኗል። ለግሞ የቆየው እንባዋ፣ በ“እርሱ ሰጠ እርሱ ነሳ” ስሌት የቆየ አእምሮዋ፣ በቀሪው ልጇ ሊጨክን አልቻለም። አትገፋውን ተራራ፣ አትጥለውን ታጋይ እንደተሰጠች አምና በሐሳብ ትዋጋ ያዘች።
ጣሊያን በመጣች ጊዜ በንብ ያሯሯጡ እናቶችን መላ፣ የጣይቱን ብልህነት አዋሕዳ የሐሳብ ውጊያዋን ግፋ አለች። አላለመደችውም እንጂ ዱሽ እጇ ብዙ መስራት ይችል ነበር። ለእርሷ የቀናት በአእምሮዋ መዋጋት ነው፤ እሱንም እንዲህ ጀመረች።
አሐዱ:
ስብሰባ ጠሯት ቀበሌ። አካለ ጎደሎ ብለው ሊረዷት መሆኑ ሲገባት ረጅም ሳቋን ሳቀች።
 “ለምን ሳቅሽ?” ቢሏት
“እጄን ትታችሁ ሸጋ ጥርሴን እንድታዩልኝ ፈልጌ” ሆነ መልሷ።
ክልኤቱ:
እንደ ሠራተኛ የምታገለግላት ታንጉት ናት። ብዙ ጊዜ ሰዎች እየመጡ ሊያጠፏት እንደሚዝቱ ምሣ ሰዓቷ ላይ ነገረቻት።
“ምን አሉሽ ለመሆኑ?”
“እናቷ ጉያ ብትገባም አታመልጠን ነው የሚሉት”
“አካሌማ መች ራቃቸው፤አእምሮዬ እንጂ” ብላ ተነሳች።
ሠለስቱ
ሁለተኛው ስብሰባ በወረዳቸው ተቀጠረ። በዕለቱ ሰብሳቢው  በበቅሎ መሐንነት አስታኮ ተቃዋሚዎቹን ኩም ሲያደርግ ሰማች። ነፋስ እንደነካት ቅጠል ኧፈፍ ብላ ተነሳች።
“ለመሆኑ ስድብን ከሚያፈራ አፍ የሌሎች መሐንነት አይሻልም?” አለችው በድፍረት። ጉርምርምታም ሆነ።
መንገዷን ጀመረች እንጂ አልቆመችም። በየኼደችበት ትተኩሰው ቀለሃ አላት። ከልቧ የሚወጡ የመልስ ምቶች ወደ ኋላ ያሳስባሉ። እሷን ትጥቅ ሊያስፈታ የሚችል አካል የለም። ቢገርፏት ማቁሰል፣ ቢመቷት መጉዳት፣ ቢያስሯት ልፋት እንጂ ሐሳቧ ሊቀየር አይችልም።
የሸፈተን ሰው ያድ˙ኑታል።
የሸፈተን ልብ ምን ያደርጉታል?_ምንም።
ስለተቆረጠው ጽድ፣ ሊያድግ ዓመታትን ሊጠፋ ሰዓታትን ስለወሰደው ታስባለች። ምሶሶ ለሆነው፣ ጎጆዋን ቀጥ አድርጎ ስላኖረው ትብሰለሰላለች። ህሊናዋ ለውጊያ ሰልቷል፤ የኼደችው መንገድ ወደ ኋላዋ ቀርቷል። እንደ ጓያ ነቃይ የፊት የፊቷን ልትነቅል፤ አእምሮዋ ላይዝል የተነሳች ትመስላለች_ምንትዋብ።

Read 441 times