Sunday, 03 September 2023 21:27

ጫማ አዳሹ!

Written by  ድረስ ጋሹ
Rate this item
(4 votes)

«አልሆን ያለህ ጊዜ መጉላትና መግዘፍ
ከትልቆች መሐል አንዱን መርጠህ ዝለፍ»
በገጣሚው ኑረዲን ኢሳ ትጻፍ እንጅ ንብረትነቷ ለዳንኤል ናት። የነገር ጥሙን የሚቆርጠው ወደ ጫማ አዳሹ መሥሪያ ቦታ ኼዶ ሃሜት በማውራት ነው ። ገና ከሩቅ ፀጉሩን መፍተል፣ የከንፈሩን ጫፍ ደረቅ ቆዳዎች በጥርሶቹ መቀንጠብ ይጀምራል። ለአጨዳ እንደሚተ˙ባ ማጭድ ምላሱ እንዲሁ ትሆናለች።የተዋጠች ቅቤ አትቀረውም ይሉታል፤ ሰዎች፡፡ እሱም እንኳን የተዋጠውን ሊዋጥ የታሰበውን ቀድሞ እንደሚያውቅ ያምናል።
ጫማ አዳሹ ማሩ ይኼን ሰው ይወደዋል። ከአንዳንድ መዥገር ሰዎች እርሱ ፲ እጥፍ  ይሻለኛል ይላል ደጋግሞ። ዳንኤል ድምፁን አጥፍቶ ወደ እርሱ ቢመጣ እንኳ  በጠረኑ ያውቀዋል። ሲቀናው የአስካለችን ጠጅ ቀማምሶ፣ እሳት ልሶ ..እሳት ለብሶ ይከሰታል።
«አገር» ይላል ገና ሲጀምር።
«ማገር» ይለዋል ማሩ ።
«አምድ ብታጣ» ይለዋል መልሶ፡፡
«ይጠብቃት ብዙ ጣጣ» ይለዋል ማሩ ።
ይግባባሉ አይገልጸውም። ዳንኤል መጥቶ ይቀመጥባት ቦታ አለችው። አላፊ አግዳሚውን፣ ወጪ ወራጁን እየቃኘ የወሬ ርእስ ይፈበርካል። ዳሌዋ ገዘፍ ያለች ሴት ካለፈች፤የሰማኸኝ በለውን «ኧረ ምኑን ሰጠሽ»፤ያልተመጣጠኑ ባል እና ሚስቶችን ካየ፣  የንዋይ ደበበን «ወዶ የገባ ሰው»ን፣ በዱርዬዎች የምትፈፀም ግፍ ከታየችውም፣ «ጃ ያስተሰርያል» እያለ ያንጎራጉራል። ማሩ ከአቀረቀረበት ቀና ሳይል ለዳንኤል ምን እንደታየው በዘፈን ምርጫዎቹ ይረዳል። ትንሽ ከመከናወቱ ሲረጋጋ፣ ወደ ነፍሱ ሲመለስ «ይቺ አገር ወዴት እየኼደች ነው?» ብሎ ይጠይቃል። ማሩ ይኼኔ ይስቃል።
“አትሳቅ፤ አዎ! ይቺ አገር ወዴት እየኼደች ነው?»
«ሲጋራ ስትለኩስ የሚወጣው የላይተር እሳት ብርሃኑ ወዴት አቅጣጫ ያርፋል?»
«ምኑን አውቀዋለኹ። የጠየቅኩህን ብቻ መልስልኝ አቶ ማሩ »
«ይኼ ነው ወዳ˙ይሉት አቅጣጫ »
ትንሽ ዝምታ በመሐላቸው ትንከላወስ ጀመር። የዳንኤል አፍ ቢሰፋ በቂጡ ይተነፍሳልና ሳይቆይ ርእስ አገኘ። ማሩ አቀርቅሮ የሚሠራበትን የጫማ መስፊያ፣ የሚቆርጥበትን ምላጭ፣ ክሩን፣ ሶሉን በተመስጥኦ አየ። ስማ ማሩ  ጫማ አዳሽነት ቅኔ ነው። አንድም ለድንግል መንገድ መረማመጃ፣ ሌላም አልማዙ ለተበላው መንገድ መንፏቀቂያነት ይበጃል_ጫማ። እሾህ ˙ረግጦ የሚሰብር ሶል የሰጠሃቸው ለታ በተለይ ትመሰገናለህ። ሳልነግርህ ደግሞ ...መውጊያና መቁረጫህ እንደነገሌ ብዙ ሲያገለግሉህ እያየሁ ነው።
«እህሳ!... መውጋት እና መቁረጥን እንጀራዬ አርጎብኝ »
«አይ!..አይ የእንጀራ ነገር...»
«ወንድማለም የእሷማ ነገር ... ያጋፋል ድንበር» (ማሩ ተከዘ)።
ቅዳሜ ዕለት ነበር። ዳንኤል ክንፍ አብቅሎ ወደ ጫማ አዳሹ ሥራ ቦታ ኼደ _መውጋት መቁረጥን ሊያይ። ጠጅ አልጠጣና ወሬ ጠፋው። ያለወትሮው ድንጋይ ላይ ነበር የተቀመጠ፤ማሩ «ድንጋይ ላይ  ድንጋይ  ተቀምጧል» ሲለው ነቃ እንጅ።
«ለመሆኑ ጫማ ማደስ ሰላም ይሰጥሃል?» (ዝም ላለማለት ጠየቀ)
ማሩ፣ የከንፈሩን ታችኛ ክንፍ በታችና ላይ ጥርሱ ነከሰ።
«ጫማ ማደስ ለእኔ የተከበረ ሙያ ነው።ያው...መንገዱ ከፍቷል መሰል ጫማዎች ቶሎ ቶሎ እየተጎዱ ወደ እኔ መምጣት ይዘዋል...»
«አዎ! መንገዱማ ከፍቷል። ግን...»
«ግን ምን?»
«አረማመዳቸው ቢሆንስ ችግሩ?»
«መጠርጠሩስ። እግር እንደ ጫማ አይታደስ እንጅ ተራማጁን ወግቼም ቆርጬም ልክ ባገባሁት...»
«ባትለውማ ከመውጋትና ከመቁረጥ የዘለለ ታሪክ ሊኖር..» (ዳንኤል በንዴት ተግለብልቦ ተነሳ፤ ብሎም ማሩን ገላምጦ ኼደ)
ዳንኤል ካለዛሬ ተና’ዶ አያውቅም። ይህ እንግዳ ጸባዩ ያስደነገጠው ማሩ፣ ያሰፋውን ጫማ አንከፍርሮ ተቀመጠ። ትልልቆችን መዝለፍ ላይ የተሰማራችው የዳንኤል ምላስ መገራቷ ገረመው። የምላስ ወለምታ በቅቤ አይታሽና ወደ ስራው ተዘናበለ። ጉልበቱ ላይ ያነጠፋትን ጨርቅ፣ ከሷ በላይ የተቀመጠችዋን ጫማ፣ ከጫማው ላይ የተሰካውን መስፊያ፣ በጫማዋ ቀዳዳዎች ገባ ወጣ የሚሉትን ክሮች፣ መደላድል ሆነው የተሸጎጡ ሶሎች፣ ይጠብቅ ዘንድ ማሰሪያውን ሳይቀር አይቶ አንዳች ኃይል አፉን ለነገር ተባለት።
መንገድ ከሌለ፤ ጫማ ያስፈልጋል?
ብሎ ከራሱ ጋር መሟገት ሲጀምር፣ አንዲት ቆንጆ ሴት ጫማ በፌስታል ቋጥራ አመጣችለት። በእጇ አጨማድዳ የየዘችውን ብር ሲያይ፣ ውስጣዊ አመጹን ረሳው። ሞላ ፈላ ስሜቱም አላሳናዝርህ አለው። ሲፈራ ሲቸር ተቀብሎ «ምን ልስፋልሽ ?» አላት። ፈገግ ብላ «ሥውር አርገው » ብላው ኼደች።
ሥውር ስፌት
በደም ሥሩ የሚራወጡ የደነገጡ ደሞች በዙበት።ሥውር ስፌትን ሲሰፋው ቢኖርም ትርጉም የሰጠው አሁን ነው። ሁሉም በጊዜው ዋጋ አለው።ስለ ህመም መደበቅ ትንሽም ቢሆን በራለት።«ሥውር አርገው ትበለኝ? እኔስ ህመሜን በሥውር መያዜ አይገርምም? ይኼ ክር በላይ ቢሰፋ እንደማያምረው እኔም ብሶቴን ብናገር እጠላ፤ እነቀፍን?
(ሞት ይቅር ይላሉ ሞት ቢቀር አልወድም
አፈሩም ድንጋዩም ከሰው ፊት አይከብድም)
--ያለ ገጣሚው ከሰው ፊት ለመሸሽ አይደል? ታዲያ ሥውር ህመምን የመረጥነው፣ ከሰው ፊት ለመሸሸ ነው ለካ...እያለ ሰፍቶ ጨረሰ።
ጥላ የለሹ ዳንኤል መጣ።
አንተ ማሩ «ያቺ ምኞት ማንን ወለደች በል?»
«ትዕቢትን»
«ትዕቢት ...ያቺ ብርሌ ቅርጿ ...ያቺ ሆድ እንጅ ጭንቅላት አልባዋ»
«እህሳ!»
የድሮ ቀናቸው ተመለሰች። ይቅርታ ሳይባባሉ መታረቅ እንዴት ነው የሚያምረው። ዘመኑ እያቆረፈደው ከመጣው ክቡር ቃል አንዱ ይቅርታ ነው። ይቅርታ ጸጸትን ካላዘለ፤ ምኑ ቂምን አስጣለ? በዓይን ጥቅሻ ተግባብቶ ...የተፈጠረውን ረስቶ፣ ከባህር ለጣሉት ወዳጅ፣ ይቅርታ ቃሉን ሸሽገው በልብ ቢቀርቡት እንኳ...ይሆነው እንደ ታንኳ። «በጓደኝነት መሐከል ይቅርታ እና ምሥጋና ምንም ናቸው» ይላል ዳዊት። የዳንኤል ረጅም ምላስ እንደ አህያ ብልት ይተረተር፤ ይሰበሰባል። ከሆነች ቀን፣ ከሆነች ሰከንድ ወዲህ እየሆነ ያለው ሌላ ቢሆንም፣ ዳንኤል ያ ሃሜተኛው ነው። ለየሌሊቶች ስም ይሰጣቸዋል። ይኼ የእንደዚህ ፣ይኼ የእንደዚህ_ምላሱ ሲተረተር። የተናገረውን ወደ ሌላ ያላክካል _ምላሱ ሲሰበሰብ።
«እውነት አንተ ከአናብስት መንጋጋ ሞልቅቆ ያተረፈውን ዳንኤል በግብር ትመስለዋለህ?” (ማሩ ነገር ተኮሰ)
«ማሩ ነው ትጠራበት፤ መምረሩን አንዴት ቻልክበት?»
«ሰራህልኝ!... ተወው ጫማዬን ባድስ ይጠቅመኛል»
«ያው... የታደሰለት ሰውም ሌላ ይመኛል»
«ይመኛ ...ምን ተዳዬ»
«አንተም ልትል ነው «ሙዳዬ...ሙዳዬ?»
«እና ከማን አንሳለሁ?»
«እል ነበር እኔም ቂል ሳለሁ።»
ኹለተኛ ኩርፊያ። ዳንኤል የልቡን ተናግሮ ግን ተቀይሞ ተነሳ። ቅያሜአችን ከአፋችን ...ከቃላችን ሆኗል። የማንም በትር ሳይነካው እጃችን ላይ ለምጽ እናገኛለን፤ ምናልባት ጥርሳችንን እንጠርጥር።
የመጨረሻው መጀመሪያ
የዳንኤል ጫማ ተገነጠለ። ከፍቅር ይልቅ ችግር ያቀራርባል። ኮሮና ሲገባ የተረዳዳው ሰው አሁን የጎሪጥ ነው የሚተያይ። ችግር ያለዝባል፣ይሞርዳልም። ዳንኤል ግራ ገባው። ከማሩ ውጭ ጥሩ ጫማ አዳሽ አያውቅም። ሲፈራ ሲቸር የኩርፊያ በሩን ገንጥሎ፣በእርቅ መንጦላዕት ተጠቅልሎ ኼደ። ማሩ ግንባሩን አጠፈ። መቼም ከዚች ኹለት በኹለት ክፍሉ አላጣውም ብለህ ትፈነጭብኛለህ አይደል? የሚል መሰለው። እንደምንም ተጠግቶ በእጁ የያዘውን የአንድ እግር ጫማ፣ አድስ ብሎ ሰጠው። ቀና ብሎ አይቶ ተቀበለው።
«ሥውር ስፋው እሺ»(በተማጻኝ ድምጽ)
«ገመናህን ላሳይ አይቻለኝም አታስብ፤ሰው ግን በሥውር ተለክፏልሳ..»
  ዳንኤል ደስ ብሎት መላ አካሉ ሳቀ። ጉዞውን ለሌላ እግር ትቶ መለሰ አለ። እንደለመደው ...
«ከአገር » አለው
«ሆድ ይሰፋል»
« እሱ ˙ሚሆነው ሲኖር ቤት»
«ልብም ሲለምድ ሥውር ስፌት»
 ተቃቀፉ።

Read 384 times