Sunday, 17 September 2023 21:19

አልተርፍም ከራሴ

Written by  ድረስ ጋሹ
Rate this item
(3 votes)

ከሩቅ ሰው መስሎ የቆመውን ኹሉ ስቀርበው ድንጋይ ሆኖ አገኘዋለሁ። መቅረብ አደጋ ነው እለዋለሁ እራሴን። ባልና ሚስቶች የሚፋቱት ስለተጋቡ አይደለ? እኮ! ያልተጋባ ፍቺ... ያልተቀራረበ መራራቅን መቼ ያውቀዋል። ከሩቅ የሚያምርን በሩቁ የመያዝ ጥበብ አልለመድኩም። ጽጌሬዳዋን ከመቁረጥ መቆጠብ ደስታን ቢሰጥም፤ አፍንጫዬ ፋታ አይሰጥም። ሊያሸት ይሻና በእጄ በኩል ያስቀጥፋታል፤ በዛው ለዓይኔ ውበቷን ያጎድልበታል።
እጄ የጠቀለለውን ስጎርስ _ስደናቀፍ። ዓይኔ ያየውን ስከተል_ ስወላከፍ። እግሬ የረገጠውን ሳምን_ ስከሽፍ ዘመን አለፈኝ።
ባለአንድ ፈረሱን ሰውዬ። ፈረሱ የጠፋችበትን። ስለ ማጣቱ  አገር ሲገረም እሱ «ለበጎ ነው» ማለቱን። ጊዜ ጠብቃ ሦስት ሆና መምጣቷን። በዚህም ደስታ መብዛቱን። ቀጥሎም  ልጁ በፈረሶች ሲያርስ ተረግጦ እግሩን መሰበሩን። አጽናናን ብለው መጥተው ቁስሉን እየነኩ ሊያባብሱበት ሲሞክሩ፤ «ለበጎ ነውን» የሙጥኝ ማለቱን። እንዳለውም በወቅቱ ጦርነት ተከስቶ የእሱ ልጅ ከጦር ምልመላ መትረፉን፣ ከጓደኛዬ ያልተሟላ ተረት ውስጥ  አስባለኹ።
ምናልባት ደስታ ያለችው ከመከራ ወንዝ ማዶ ነው። እወድቅ ይሆናል አልፎ አልፎ፤ ግን መውደቄ መቃኛዬ ቢሆንስ?_ወደፊት ለመግፋት ወደ ኋላ እንደ መንደርደር፤ ስወድቅም እንደተቆረጠ ዛፍ ዥው ሳይሆን፤ እንደ ድንጋይ ከብለል ማለቱን እመርጣለሁ። የቀረብኩት እንደሚጥለኝ አስቤ ነው። ቢጥለኝም በወደቅኩበት የሚፈ˙ራ እሾህን መሆን አይቸግረኝም።
ብር በእጅህ ይዘህ ታውቃለህ? አዎ! ምን ላድርግበት ብለህ  ብዙ ሐሳቦችን ታስባለህ ...ይኼን ባደርግ ያን ባደርግ ትላለህ፤ በመጨረሻም ለአንተ ይበጀውን ታደርጋለህ። እኔ የአንተ አምሳል ነኝ። ሐሳቤ ፈርጀ ብዙ ጥያቄዬ ግን አንድ «እኔ ማን ነኝ?» ብቻ ነው።
አልተርፍም ከራሴ (አንተን እሸሻለኹ፤ ከራሴ ግን ማምለጤን እንጃ)። ወደ አንተ የምመድረው ጣት የለኝም። ጣቶቼ ሁሉ ሸቀኔን በማራገፍ ላይ ተጠምደዋል። ሸክላነቱ ሲገርመኝ ታጥቦ አይጠራ ገላ መያዜን ጊዜ ገልጦታል። ውኃ ቢፈራውም ገላዬን፤ ውኃን ራሱን መኾን ያምረኛል። የቆሸሸው እንዲፀዳ፣ የጎደፈው እንዲያምርበት ውሃን...ውሃን ብሆን እላለኹ። ጠረን፣ መልኬንና ሽታዬን አውቀው «ነው» ባይሉኝ ‘ወዳለኹ። የወደድኩትን መሆንን ግን እፈራለኹ። ውሃ ቅርጽ የሚኖረው በገባበት ዕቃ ነው። ኒኬል ውስጥ ሲገባ ኒኬል ቅርጽ፣ ባልዲ ውስጥ ሲገባም ባልዲ ቅርጽ አለው። በየተቀጠርኩበት፣ በየገባሁበት ኹሉ አቋሜ እንደ እሥሥት መቀያየሩን እፈራለኹ።
መፍራት ጥሩ ነው (ጎበጥ ሲሉ ለቼቼ የሚያመቻች፣ ጎንበስ ሲሉ የሚደፍቅ ባይበዛ)።
ለዓይን የሚጠገንነውን ግንብ፣ ሊረግጡት የሚያስፈራውን እሾህ፣ ሊሻገሩት ያልሞከሩትን ወንዝ ፍርሃት ያስችላል። ደንግጠህ ታውቃለህ? ካርታ እየተጫወትክ ፖሊስ ደርሶ አሯሩጦህ ያውቃል? ጠላ ቤት ገብተህ በብርጭቆ ላለመፈንከት የሮጥከው ትዝ ይልሃል? ስትፈራ ያልዘለልከው አጥር አለ? እኮ! ፍርሃት ውስጥ የመሸገ ኃይል አለ።
ስትፈራው የነበረውን ልጅ ለድብድብ ጋብዘኸው ታውቃለህ? ጉሩምቦውን አንቀህ የያዝከው፤ ብትለቀው አፈር እንደሚያስግጠህ ስለምታውቅ መሆኑ መች ጠፋኝ። የፍርሃት አያያዝ ምንጩ ከየት ነው? ፍርሃትን ምሽግ ያደረግክ ኃይል ሆይ ተገለጥ። ነጻነት ግብግቧ ከፍርሃት ጋር ነው። መልኳም ኹለት ዓይነት ነው። አንዷ ነጻ ሆኖ ለመቆየት የምትፈራ ፍርሃትን ታሳያለች፤ ሌላዋ የምትፈልገውን ነጻነት ለማግኘት ፍርሃትን ስትታገል ትውላለች። ልብ ይበጀውን ይመርጣል።
አባቷ ነይ ብሎ በሞተር ሳይክሉ ይዟት ሲከንፍ አየሁት_ሮዛን። ጀርባውን እንቅ አርጋ ስትይዘው እንደፈራች ገብቶኛል። ምናልባትም ፍርሃት ደህንነቷን ማቆያ ሆኗታል። እልፍ ስል ዱርዬዎች ገጥመዋል። ከመሐላቸው አንዱ ሲሸሽ አየሁት። መሸሽ እንዲሁ አካሉ እንዳይጎድል አግዞታል። እልፍ ስል ተሳዳቢ አባት አላፊ አግዳሚውን ሲያጥረገርግ አየሁ። ምናልባትም መናገርን ፈርተው አንገታቸውን ደፍተው ያለፉት ወጣቶች የሰውዬውን ኃጢያት ቀንሰዋል። እልፍ ስል እናቱ፣ እህቱ እየተደፈሩ እያየ ዝም ያለ ወጣት አየሁ። በዚህ አዘንኩ። ተበቀል አልለው_ አይባል፤ ግደል አልለው_ አይባል። ለውሳኔ የቸገረ ስሜትን ያኔ አወቅኳት።
ፈርጀ ብዙ ሐሳብ ፤ለነጠላ ጥያቄ።
ኢየሱስ ምድር ላይ ያን ያህል ለማስተማር የደከመ ብዙ ዓላማ ኖሮት ነው አልልም። ዓላማው አንዲት ናት። እሷም ፍቅር። በፍቅር በኩል ኹሉም እንዳለ አምናለሁ። ወደ እግር ዝቅ ቢል ትኅትናን፣ ጴጥሮስን ቢቀበል አለማራቅን፣ ይሁዳን ቢያቅፍ ባላንጋራ መውደድን፣ ሲሰቀል ቢያቃስት ይቅርታን ...በየእርምጃው የተከላቸው በሙሉ በፍቅር ማዕቀፍ ውስጥ ናቸው።
አብዝቼ የምጨነቀው አቅልዬ ለመኖር ነው። በል ሲለኝ እግሬን አነሳለሁ ወደ ጠላ ቤት። ገብቼ ከመቀመጤ እሳት የላሰው አስተናጋጅ መርቲ ያስጨብጠኛል። ዓይኔ ከገፈታው ላይ ያፈጣል። እኮ! ቀላል ነገሮች ከፍ ይላሉ። ወደ አፌ ለግቼ ሳብ ሳደርግ ወደ ጉሮሮዬ እንዳይገባ ምላሴንና ከንፈሬን አስተባብሬ ገፈታ አስቀራለሁ፤እተፋለሁም። ወትሮም ቀላል ነገር ከላይ መታየት፤ ቀን ሲያዝበትም ተተፍቶ መውደቅ ግብሩ ነው።
አልተርፍምኮ ከራሴ።
ነገሬ ሁሉ የአጓት ጥጋብ ነው። አለኝ ብዬ ሳልጨርስ የለኝም ይሉት ቃል ይመጣል። ደስታዬ እንደ እሥሥት መልክ ይፈራረቃል። ደስታን ፈጽሞ ከዓለሙ አልጠብቅም። ከራሴ ተጸንሶ፣ ተወልዶ፣ አድጎ ማየትን እሻለሁ። ወደ አንተ የምቀስረው ጣት ምናልባት ጥሩ ነገር ላመላክትህ እንጂ ልጠነቁልህ እንደማይሆን እረዳለኹ። ሳልደርሰብህ አትደንግጥ፤ ውሎዬ ከጥላዬ ጋር ነው። ገመናዬን ብታውቀው ባጤ፣ መጥፎ ታሪኬን ቢመሰክር ግድግዳዬ እንጂ ሌላ አይሆንም። እንዴት ነው ሰው መውደድና ሰው መራቅ አብረው የሚመጡ አንዳትል እኔን እየኝ።
በሚወዱኝ ተጠምጄ የሚጠሉኝን ላይ አልቻልኩም። መንገድ አገናኝቶናል አውቃለሁ። ታዲያ የገጠር ሙሽሮች አይደለንምና ለክብር አንደባደብም። ገጠርን ያንኳሰስኩት መሰለህ?_በፍጹም። ሰርገኞች ሙሽራ ይዘው ሲኼዱ  መንገድ ላይ ሌላ ሙሽራ ቢያገኙ ለክብር ይገጥማሉ። ይደባደባሉ። ከራሴ አልተርፍም እመነኝ።
ክብር ፍርሃትን አዝሎ ይዞራል።
የአንዱ ሙሽራ ሰርገኛ መንገድ ቢለቅ ምን ይሆናል?_ምንም። ተሸነፉ ላለመባል ግን ዱላ ሲማዘዝ ምን ይሰማሃል?_ያው ክብር ማጣትን በመፍራት ያለውን መዘዝ ይሆናል። ክብሩ ይቅርብኝ ስል ፍርሃቴን ድል እንደነሳሁ እንድትረዳኝ እሻለሁ።
ጥላዬን ሳይቀር እጠረጥራለሁ። አንተን ግን ከቦታ መርጬ ሰፊ ቦታ፣ አልፎም ቀመር ከሌላት ልቤ ላይ አደላደልኩህ። መደላደል ጥሩ እንዳልሆነ ያወቅኩት ከጓሯችን አዛባ ላይ የበቀለው ቃጭማ ተፈንግሎ ያየሁ ቀን ነው። ድሎት ማንን ጠቀመ?_ማንንም። ባሻ ሳጥናኤል አለቃ ተደርጎ ቢሾም አምላክ ነኝ አለ፤ ይገፋውን እጅ ያዳበረ ቃሉ ነበር። አዳም ገነት ውስጥ ተንፈላሰህ ኑር ቢሉት ዐይኑን ወደ አይሆነው አዞረ፤ ሞትንም ወደራሱ ጠራ። መደላደል ለአንተም እንደነሱ ነው። ትለብሰው ቢሰጡህ፣ ትከናነበው ያምርሃል። አምሮት ጥሩ አይደለም ብዬ እንዴት እመክርሃለሁ?
የጠሉት ይወርሳል፤ የፈሩት ይደርሳል።
 ፍርሃትን ቢፈሩት ከመድረስ ላይቀር፣ ቢሸሹ ከመጠጋት ላይመለጥ ምን ተሻለኝ? ወደ ኋላዬ ተጉዤ ያጠራቀምኳቸውን እርምጃዎች ፊትለፊት ለመጣ ሰጥቶ መኼድ እንዴትስ ይሆንልኛል?
ሄድኩለታ ቤቱ ድረስ።
ውጣ አልኩት በሩ ላይ ቆሜ። ተንደርድሮ ሲመጣ ሮዛ የአባቷን ወገብ እንዳነቀችው አነቅኩት። ፈሪ ከያዘ አይለቅምና አጠበቅኩበት። ለደቂቃዎች ታግለን ጣልኩት። ሆዱ ላይ ተቀምጬ፣ በግራ እጄ በሸሚዙ አንቄ ይዤ በቀኝ እጄ መነረት ያዝኩ። አፌ የድረሱልኝ ጥሪ ማሰማቱን ሰዎች ሲደርሱ አወቅኩ።
«አንተ በላይ ሆነህ እየደበደብከው መጮህህ ለምን ነው?» አለኝ ሽማግሌው።
«የአሁን ግልብጥ ነኝ» አልኩታ፤ እንደዛ ተረተኛ።
ገላጋይ ያለው ጠብ ደስ ይላል። አውላላ ሜዳ ላይ መግጠም ለመላላጥ ነው። ገደል ዳር፣ ውሃ ዳር፣ እሳት ዳር መግጠም ተያይዞ ለማለቅ ነው። ፍርሃት እንዲሁ ለዚህ ከበጀች ለልባችሁ አስተዋውቋት።
ጸቡ ረገብ ሲል ማሰብ ጀመርኩ። ከእርሱ ጋር ያጋጠመኝ መቅረቤ አይደል? ውሃ ሊያጠጣ አዝሎ በወሰደው እባብ እንደተነደፈው አህያ፣ ጭድ ሲጥል በበሬ እንደሚወጋው ገበሬ እንድሆን ማን ፈረደብኝ?_ አላውቅም።
ጎትተው ያስገቡትን ጎትተው ሊያስወጡት ይከብዳል። ጎተራ ቀዳ የገባች አይጥ በገባችበት  ቀደዳ ተመልሳ መውጣት አትችልም። በልታ ስለምትወፍር ሰፊ ቀዳዳ ትፈልጋለች። ወዳጅነትም ሲጀምሩትና ሲጨርሱት እንዲህ ነው። በቡና የጀመሩት መወዳጀት ቢላ አማዝዞ፣ ነፍስ አጠፋፍቶ ይቋጫል።
ሲያልቅ አያምር ትላለች_ሮዛ።
ፍርሃትን መሳሪያ አድርጌ ራሴን ከመጥፋት እሱንም ከማጥፋት ታድጌው ቆየሁ። ፈርቼ ክብሬን አሳነስኩ፤ ደፍሮ ክብሩን አጸና። እኔም ደፍሬ ለክብሬ ብሰለፍ የከረረ ይበጠስ ነበር። እንዲሁ አንዱ ሲነገር የሚሰማ ሌላ ሰፊ ጆሮ፣ አንዱ ሲጠላ የሚወድ ሌላ ጥሩ ልብ ያሻናል።
እነሳና አስባለኹ ሁሉንም _ከራሴ እንደማልተርፍ በተለይ።
ያገናኘችን ቀጭን መንገድ ግራ ቀኝ ገደል ናትና፣ ያስተዋወቀችን ሕይወት ኖረ ሞተ ናትና፣ ከጥልም ፍሬ ከጸብም ፍሬ አይታፈስና የማርያም ጣቴን እንካ። ለምን ዓይንህ ደም ጎረሰ? ስለምን እርቅን ፈራህ? እንቅር ወይ እንደቀረን?
«ኧረ ፈሪ ፈሪ ኧረ ፈሪ ብልጡ
ሲሸሽ የሚያይበት ዓይን አለው በቂጡ»
ለአንተ ይብላኝ ነፍሴን በእጅህ ለመደፍጠጥ ለቋመጥከው። አዎ! ለአንተ ይብላኝ የመሸናነፍ ትርጉም ላልገባህ። እኔ በልጅነቴ እንደሳልኩት ጭራቅ ጀርባዬ ኹሉ ዓይን ነው። ገፍተህ ብትመጣ ገፍቼ እሸሻለሁ። ይኼንም ከአቅም ማነስ ሳይሆን በድፍረት የመጣ ክብርን ስለመናቅ አድርገህ ቁጠረው።
«ጀግናና ብርሌ ሳይቆይ ይሰበራል
ፈሪ ተራራ ነው ዘላለም ይኖራል »
ሐቅ አለው አዝማሪ። ዘላለም መኖር የምችል ይመስለኛል። በአንተ እጅ ብጠፋ እንኳ በሚወዱኝ ሰዎች ልብ ውስጥ እኖራለሁ። ለዓይንህ ባንስም ለሰዎች  ሐሳብ ሙሉ የምሆን ይመስለኛል።
 ደም የጎረሰ ዓይኑን ይዞ ጠበቀኝ። ጠብን በፈረቃ ማድረግ የፈለገ ይመስላል። የተወጠረ ደረቱ፣ የተነፋፋ ባቱ ጎልያድን አስመስሎታል። የይቅርታ ደብዳቤዎቼን አንብቦ እንደተናደደ ቅልጭብ አድርጎ አስረዳኝ።
«ሰው ይቅር ሲሉት ይናደዳል እንዴ?» አልኩት
«ገጥመን ይለይልናል የምን መልፈስፈስ!» ብሎ ተከመረብኝ። አበራየሁት። ፍርሃት ውስጥ ኃይል መሽጓል።
Read 367 times