Monday, 07 November 2011 12:18

“የኮተቤ ኮሌጅ ልዕልና” ወይስ “የአስተዳደር ድርቅና”? ምዝገባ የተከለከሉ ተማሪዎች - አቤቱታ ለማሰማት የደጅ ጥናት ጉዞ

Written by  ዘመን
Rate this item
(0 votes)

ነገሩ እንዲህ ነው፤ በ2004 የትምህርት ዘመን የዲፕሎማና የዲግሪ መርሀ ግብር፤ የምዝገባ ቀን ጥቅምት 4 እና 5 መሆኑን፤ ኮሌጁ በማስታወቂያ አስነግሯል - ለሁለተኛና ለሶስተኛ አመት ተማሪዎች፡፡ ብዙዎችም በእነዚሁ ቀናት ተመዝግበዋል፡፡ አንድ ቀን ያለፈባቸውና ያልተመዘገቡ ተማሪዎችስ? በየትኛውም አገር፤ በየትኛውም የትምህርት ተቋም፤ መደበኛው የምዝገባ ጊዜ ለሁሉም ተማሪዎች እኩል አመቺ ሊሆን አይችልም። ያለነው ደግሞ፤ በሶስተኛው አለም ነው፤ በኢትዮጵያ። ለዚህም ነው፤ የመረጃና የትራንስፖርት አገልግሎት በተስፋፋባቸው ሃብታም አገራት ውስጥ የሚገኙ አለማቀፍ ዩኒቨርሲቲዎች ጭምር፤ መጠባበቂያ የምዝገባ ጊዜ የሚያዘጋጁት። ችግሮች በበዙባት አገራችንም፤ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች ተመሳሳይ የምዝገባ አሰራር እንደሚከተሉ ይታወቃል።

በተለያዩ ችግሮች ሳቢያ በመደበኛ የምዝገባ ቀን መድረስ ለማይችሉ ተማሪዎች፤ ከመጠነኛ ቅጣት ጋር ተጨማሪ የመመዝገቢያ ጊዜ ይሰጣቸዋል - ከ2 እስከ 5 ቀን፡፡ በህመም ወይም ከአቅም በላይ በሆነ ሌላ ችግር፤ በጊዜ ያልተመዘገበ ተማሪ ከመጣም፤ አትመዘገብም አይባልም - ለተወሰኑ ቀናት። በከፍተኛ ችግር ሳቢያ እንደዘገየ የሚያረጋግጥ ማስረጃ ለማቅረብ የቢሮክራሲ ፈተናዎችን መጋፈጥ ባይቀርለትም የተወሰነ ተጨማሪ የምዝገባ እድል ያገኛል። 
እንኳን የትራንስፖርትና የመረጃ አቅርቦት ባልተስፋፋባት አገራችን ይቅርና፤ በበለፀጉት አገራትም፤ እንዲህ አይነት አሰራር የተለመደ ነው። በተለይ፤ በአገር ውስጥና በውጭ፤ ለበርካታ አመታት የተማሩ የኮሌጅ አስተዳዳሪዎች፤ ይህን አሰራር ከማንም የበለጠ ሊያውቁት ይችላሉ። ታዲያ፤ ይህንን እውነታ ላለማየት አይኑን የሚጨፍን የኮሌጅ አስተዳደር እዚሁ አገራችን ውስጥ ብታዩ አይገርምም? አንድ ቀን ያለፈበት ተማሪ እንዳይመዘገብ በዘፈቀደ የሚወስን አስተዳደር ቢያጋጥማችሁስ? ካጋጠማችሁ፤ ኮተቤ ግቢ ውስጥ ገብታችኋል ማለት ነው።
በመደበኛ የመመዝገቢያ ቀናት ጥቅምት 4 እና 5 መድረስ ያልቻሉና አንድ ቀን ያለፈባቸው ተማሪዎች ቢኖሩ ይገርማል? በትክክለኛው አሰራር መሰረት መጠነኛ ቅጣት በመክፈል ለመመዝገብ ጥቅምት 7 ቀን ከመጡት ተማሪዎች አንዱ ነኝ። እንቅፋት ይገጥመናል ብለን አላሰብንም፤ ከቅጣት ጋር የሚካሄድ ተጨማሪ ምዝገባ የተለመደ ነው። መመዝገብ አትችሉም ስንባል፤ ለጊዜው ማመን አልቻልንም። በቃ፤ ጥቂት ሃላፊዎች በሚያውቁት ወይም በማያውቁት ምክንያት ምዝገባው ተዘግቷል፡፡
መጀመሪያ የሄድነው ወደየዲፓርትመንታችን ሃላፊዎች ነው። በየፊናችን አነጋገርናቸው - የመጀመሪያ አቤቱታ እንጂ የመጨረሻ እንዳልሆነ አላወቅንም። የዲፓርትመንት ሃላፊዎች ምላሽ ተመሳሳይ ነው - ወደ አካዳሚክ ዲን ሄዳችሁ አነጋግሩ የሚል። በየፊናችን ያገኘነው ምላሽ ተመሳሳይ ስለሆነ፤ ሁላችንም የአካዳሚክ ዲን ቢሮ አካባቢ ተገናኘን። ተጠራርተን ባንመጣም ችግራችን አሰባስቦን ኮሪደሩን ለአቤቱታ ወረርነው - ቢሮው ለብዙዎቻችን አስፈሪ ነው። ሃላፊውንም ከመፍራት የተነሳ “የቢሮው ንጉስ”፤ “የቢሮው አንበሳ” የሚሉ አሉ።
ቢሮውን አየነው። ለአይን የማይስብና ሳጥን የመሰለ ቢሮ፤ ያን ያህልም አስፈሪ ነው ለማለት አይቻልም። ሃላፊውስ? ሆኖም፤ ይህንና ያንን አውጥተን አውርደን አይደለም የመጣነው። አትመዘገቡም በመባላችን ነው፤ ለአቤቱታ መምጣታችን፡፡ የሃላፊው ምላሽ አንጀት የሚያቆስል ሆነብን እንጂ። በቃ አትመዘገቡም፤ የምትመዘገቡበት ምንም እድል የላችሁም... አነጋገራቸው ደግሞ ይብሳል።
መቼም፤ አለመመዝገባችን ለሃላፊው አስደሳችና ትልቅ ስኬት ሊሆንላቸው አይችልም። ግን ጭካኔ ስናይ፤ ... ለማስረዳት ከመሞከር ይልቅ በጭካኔ ላይ ስርአት የሌለው ሁኔታ ሲደባለቅበት ግራ የሚያጋባ ሆነብን። ትንሽ ቆይተው ደግሞ፤ ከእንግዲህ ምዝገባ እንደማይኖር የሚገልፅ ማስታወቂያ በፀሀፊያቸው አማካኝነት ተለጠፈ፡፡
እንግዲህ ምን ይደረጋል? ተቀባይነት ያላገኘውን ማመልከቻ ይዘን፤ እንደገና አቤቱታችንን ሰምቶ መፍትሄ የሚሰጥ የበላይ አካል እናገኝ እንደሆነ ለማየት ሄድን - ወደ ኮሌጁ ዋና ዲን ቢሮ። ተመስጌን ነው። ቢያንስ ቢያንስ የዋናው ዲን ፀሀፊ፤ የምታመናጭቅና የምትገላመጥ አይደለችም። እንደ አንዳንድ ፀሀፊዎች በየአጋጣሚው ስልጣኗን ለማሳየት አልሞከረችም፡፡ ዋናውን ዲን ማነጋገር እንደምንፈልግ ስንገልፅላት፤ በእርጋታ ሰማች። ዋናው ዲን አሁን ቢሮ ባይኖሩም፤ ሲመጡ ማናገር እንደምንችል ነገረችን፡፡ ቅንነቷን አመስግነን ጠበቅን።
ብዙም ሳይቆይ መጡ። ያለምንም ውጣ ውረድ እንድንገባ ተነገረን፡፡ ህንፃው የድሮ ነው፤ በሩም የጥንታዊነት ምልክት ለማንፀባረቅ የቆመ ይመስላል። ቢሮውም ማራኪ እንደማይሆን መገመት ይቻላል - የተሳሳተ ግምት ይሆናል እንጂ። የቢሮው ሞገስ ቢዘረዘር ለብቻው አምድ ይፈልገዋል፡፡ ግን የቢሮ ግርማ ሞገስ የመዘርዘር ፍላጎት ለጊዜው የለኝም። ብቻ... ሀላፊው ጋር ለመድረስ፤ ለድንጉጥ ሰው ሰአታት፤ ለደፋሩም ደቂቃዎች ይፈጅበታል በሚል ግነት እንለፈው።
ዋናው ዲን አቶ ሣህሉ ክፍሉን ከሚመጥን ፈገግታ ጋር ምን ልርዳችሁ አሉን። ማመልከቻችንን ሰጥተን አነበቡት። ችግራችንን ተናገርን ሰሙን። ችግራቸው ታይቶ ይመዝገቡ የሚል ፅሁፍ ማመልከቻችን ላይ በማስፈር ፈረሙበት። ማመልከቻችንን መሩልን በማለት ተደሰትን፡፡ ከእንባ ጋር ሲታገሉ የነበሩ አንዳንድ ተማሪዎችም ተፅናንተው ፊታቸው ላይ ፈገግታ መታየት ጀምሯል፡፡ ዋናው ዲን፤ የመማር ፍላጎታችንን ያዩልን፤ ሳያንገላቱ ችግራችንን የተረዱልን ለምን ይሆን? በዚያ ቦታ ለምን እንደተቀመጡና ምን እንደሚሰሩ የሚያውቁ ስለሆኑ ብቻ ነው፡፡
ምን ያደርጋል? ዋናው ዲን፤ ከኮተቤ ኮሌጅ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለመሄድ የመልቀቂያ ደብዳቤ አስገብተው ስለቆዩ፤ የመጨረሻው ሰአት ላይ ነው የደረስነው። “ችግራቸው ታይቶ ይመዝገቡ” በሚል በዋናው ዲን የተመራው ደብዳቤ በአየር ላይ ቀረ፡፡
ለማንኛውም የዋናው ዲን ቢሮ ከመግቢያው ጀምሮ፤ ለኛ ለደነገጥንና ለተጨነቅን መከታ የሆነ ቢሮ እንደነበረ አይተን ከማመስገናችን፤ ወዲያው እንዳጣነው ልቦናችን አውቆታል፡፡ እንግዲህ ከዚህ በኋላ እጣ ፋንታችን በኮሌጁ የሪጅስትራል ክፍል ሀላፊና የአካዳሚክ ም/ዲን ተወካይ በሆኑት በአቶ ዘለቀ በየራ እጅ ላይ ብቻ ወደቀ - የግቢው ፈላጭ ቆራጭ እንደሆኑ በሚታመንባቸው ሰው እጅ ማለት ነው፡፡
ብዙ ስልጣን ስለያዙም ሊሆን ይችላል፤ የአንድም ተማሪ ችግር የመስማትና የመረዳት ፍላጎት አላሳዩም፡፡ “ምዝገባ የለም፤ የለም፤ ብያለሁ፤ ብያለሁ” የሚል አይነት ምላሽ የገነነብን፤ የኮሌጁን “ልእልና” ለማስከበር ከሆነ ያሳዝናል። ዘመናዊነት የጎደለው የፋርስንና የሜዶንን ህግ የመሰለ ድርቅና... በጭራሽ በጭራሽ፤ ትውልድን እቀርፃለሁ ከሚል የመምህራን ኮሌጅ አይጠበቅም፡፡
በየትኛውም ተቋማዊ ስራ ውስጥ፤ የጊዜ ሰሌዳ መኖር እንዳለበት ማንም አይክድም። በዘፈቀደና በሃላፊዎች ስሜት የሚደነቀር የጊዜ ሰሌዳ ሳይሆን፤ ተጨባጭ እውነታዎችን ያገናዘበ፤ በህግና ስርአት የሚመራ የጊዜ ሰሌዳ ማለቴ ነው። ለምሳሌ ያህል፤ የመረጃ ልውውጥና የትራንስፖርት አገልግሎት ቅልጥፍናን ማገናዘብ፤ በሰዎች የእለት ተእለት ህይወት ውስጥ ዘወትር የማይጠፉ እንደ ህመምና ሃዘን የመሳሰሉ ክስተቶችንም ከግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል።
በዚህ ስልጡን መንገድ የሚዘጋጁ የምዝገባ የጊዜ ሰሌዳዎች፤ ከመደበኛ የምዝገባ ቀናት በተጨማሪ፤ ከመጠነኛ ቅጣት ጋር መጠባበቂያ የምዝገባ ቀናትን እንዲያካትቱ ይደረጋል። ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ለሚያጋጥማቸው ደግሞ፤ ችግራቸው በማስረጃ ከተረጋገጠ፤ በተወሰነ ደረጃ ተጨማሪ እድል እንዲያገኙ ይደረጋል - በህግና ስርአት በሚመራ ስልጡን የጊዜ ሰሌዳ።
መቼም ያለነው ኮሌጅ ውስጥ ነው - የእውቀት፣ የለውጥ፣ የስልጣኔ፣ የተስፋ ጭላንጭል የሚታይበት። የእውቀትና የስልጣኔ አርአያ እንዲሆነን የሚጠበቅበት አካል፤ ድርቅና በሚመስል የዘፈቀደ አሰራር፤ ያንን ጭላንጭል ለማጥፋት ሲጣደፍ አያሳዝንም?
ለመሆኑ በኮሌጁ ለመደመጥ እድል ያላገኙ፣ በፍርደ ገምድል የኮሌጁ “ባለስልጣናት” አንድ አመት ከዕድሜያቸው ላይ የተነሳባቸው ተማሪዎች ታሪክ ምን ይመስላል፡፡
ከሰሜን ሸዋ ወረጃርሶ ወረዳ ለስራና ለትምህርት የመጣው የ26 አመቱ ወጣት፤ እናትና አባቱ አቅመ ደካማ አርሶ አደር ሲሆኑ ለቤተሰቡ የመጀመርያ ልጅ ነው፡፡ የ12ኛ ክፍል ማትሪክ ፈተናን በጎኃጽዮን ከተማ ወስዶ፣ በ2002 በኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ገብቶ በዲግሪ ፕሮግራም ለ2 አመት ሲማር ቆይቷል፡፡ ትምህርት ብቻ ግን አይደለም፤ ሥራም እየሰራ ነበር፡፡ ያውም ትከሻው እስኪገነጠል እግሩ እስኪነቃ የዕንቁላል ቅርጫት ተሸክሞ ከሱቅ ሱቅ፣ ከሰፈር ሰፈር እየተንከራተተ እንቁላል አከፋፍሎና ቸርችሮ ነው ትምህርቱን የዘለቀው፡፡ ሆኖም ውስጡን አጠንክሮ ተስፋውን አፀድይቶ ልመረቅ አንድ አመት ቀረኝ ሲል አንድ አመት እንዲጨምር ተፈረደበት፡ ወላጆቹን አይዞአችሁ፤ ደርሼላችኋለሁ ሲል ተስፋቸውን የሚያጨልም ችግር ገጠመው፡፡ ወጣቱ የኮሌጁ ተማሪ በኮሌጅ የትምህርት ቆይታው ሁሉ ከ3 ነጥብ በላይ ውጤት ባለቤት ነበር፡፡ ይሄ ወጣት ካሳለፈው የመከራና የችግር ዓመታት አኳያ አንድ ዓመት መጨመሩ የ12 ዓመታት ያህል ቢርቅበት ይገርማልን?፡፡ሌላኛው ወጣት የትምህርትና የለውጥ ናፋቂ ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ሲሆን በሽመና ስራ በሚያገኛት ገቢ የቤት ኪራይ፣ የልጆች ትምህርት ቤት፣ ቀለብ፣ ትራንስፖርት ሸፍኖ በኮሌጁ ውስጥ የሚማር ነበር፡፡
አንድ ልጨምር ከ9 አመት በፊት ወደ አዲስ አበባ ለስራ የመጣው የ27 አመቱ ወጣት ዛሬ የሁለተኛ አመት የኮሌጁ ተማሪ ነው በአዲስ አበባ ኑሮ በ230 ብር አንዲት ክፍል ተከራይቶ ታናሽ ወንድሙን በዛው በኮተቤ ኮሌጅ እያስተማረ ይገኛል፡፡ ይህ ወጣት የሚተዳደረው በቀን ስራ ሲሆን በቀን 25 ብር እየተከፈለው ቢውልም በወር ውስጥ ስራ የሚገኘው በአማካኝ ከ12 ቀን በላይ አይሆንም፡፡ በዚህ አስጨናቂ የኑሮ ትግል ውስጥ የሚማረው ወጣት እስካሁን ያለው አጠቃላይ ውጤት 3.7 ነው፡፡ ፆሙን ውሎ ፆሙን ቢያድርም በትምህርቱ ጉዳይ ቀልድ አያውቅም ነበር፡፡ ዘንድሮ ግን በትምህርቱ የመጨረሻ አመት መጀመሪያ ላይ በወጣው የምዝገባ ሰሌዳ ወቅት በጠና ታመመ፡ጥቂት በህክምና ቢረዳም ሙሉ ለሙሉ አልተሻለውም፡ ገመምተኛው ወጣት ከዳቦና ከህክምናው ቀናንሶ የቋጠራትን ይዞ ወደ እውቀት ምንጭ ኮሌጁ መጣ፤ አይዞህ፣ በርታ የሚሉ የመፅናኛ ቃላትን ጠብቆ አልመጣም፤ መመዝገቢያውን ከነቅጣቱ ከፍሎ ሊመለስ እንጂ፡፡ እድሜ ለቁርጠኛው የኮሌጃችን አመራር፣ ምዝገባ አልተቻለም፡፡ መፍትሄ እናገኝባቸዋለን ያልናቸውን በሮች በየተራ ማንኳኳት አላቋረጥንም። ወደ ት/ቢሮ ሄደናል፡፡ ለኛ ጉዳይ እጅግ ቅርብ የሆኑት የት/ቢሮ ምክትል ሀላፊ፤ ማመልከቻችንን እንኳ ለማንበብ ጊዜ አልነበራቸውም። በቁማችን አንድ ደቂቃ ሰሙን፤ አንድ ደቂቃ አወሩልን። በቃ... ምንም ሊረዱን እንደማይችሉ ነገሩን። ለሳቸው በጣም ቀላል መልስ ነበር፡፡ ተማሪዎቹ ፍትህ ተጓድሎባቸዋል? የእነዚህ ሰዎች ህይወት አላግባብ ተደናቅፏል? ይሄ ለሃላፊው አላሳሰባቸውም። ምን ይሆን የሚያሳስባቸው? የትምህርት ሽፋኑ እየተስፋፋ ነው በማለት የሚሰጡት መግለጫ?.........
ቀጥለን የሄድነው ራዲዮ ፋና ነበር - አቤቱታችንን ለማሰማት። የኮተቤ አዲስ አስተዳደር ምላሽ ምን ይሆን? ጥያቄ ቀረበለት። መረጃ ያላቸው ተማሪዎችን እየተቀበልን ነው አለ የኮሌጁ አስተዳደር - ለሚቀጥሉት ሁለት ቀናትም እንቀበላለን በማለት፡፡ ከዚህ ቀደም መረጃ ይዘን ለበርካታ ቀናት በኮሌጁ ቢሮዎች ደጅ ስንጠና ሰንብተናል - ተቀባይነት ባናገኝም። አሁንም “እንቀበላለን” ብለዋል። እነዚያን መረጃዎች ይዘን፤ ለአቤቱታ ስንኳትን ወደሰነበትንበት የኮሌጁ ግቢ፤ ለደጅ ጥናት ስንመላለስበት ወደነበረው ቢሮ ደረስን። ለወትሮ ከቢሮ ውጭ የሚያዋሩን ሀላፊ፤ የዛሬ አቀባበላቸው ተቀይሮብናል። ምንም እንዳልተፈጠረና ምንም እንዳልተንገላታን፤ “በአዲስ መልክ” ምክንያታዊ አቀባበል ማግኘታችን፤ በአዲስ ሰብአዊነት ጭምር መስተናገዳችን አስገርሞናል። ዋናው ነገር፤ ሁላችንም መመዝገብ መቻላችን ነው፡ ግን፤ ይህ ሁሉ ውጣ ውረድና እንግልት ለምን አስፈለገ? ለምን ይሆን፤ ብዙዎቹ የሀገራችን ሰዎች (የተማሩትም፤ ያልተማሩትም)፤ ለሰው የሚሰጡት ግምት እንዲህ ያሽቆለቆለው? ቅንነት በጠፋባቸውና መልካም አስተዳደር ባልሰፈነባቸው ተቋማት መንገላታት የለት እንጀራችን የሆነውም እኮ በዚሁ ምክንያት ነው፤ ሃላፊዎች ለሰው በሚሰጡት ግምት ማሽቆልቆል የተነሳ ማለት ነው፡፡ የምሁራን መፍለቂያ የሆኑ ትላልቅ የትምህርት ተቋማት ውስጥ፤ ችግሩ በጣም የገነነ መሆኑ ደግሞ ይበልጥ ያሳስባል፡፡

 

Read 1893 times Last modified on Monday, 07 November 2011 12:22