Monday, 07 November 2011 12:29

መኳንንቱን ያጨናነቃቸው ምንድን ነው?

Written by  በክሪስ ሄጅስ
Rate this item
(0 votes)

ክሪስ ሄጅስ የTruthdig.com ቋሚ አምደኛ ነው፡፡ ሄጅስ የሀርቫርድ ዲቪኒቲ ስኩል ምሩቅ ሲሆን ሃያ ዓመታት ገደማ የኒውዮርክ የውጭ ዜና ተላላኪ ሆኖ የሰራ ፀሀፊ ነው፡፡ በቅርቡ ከፍ ሲል በተጠቀሰው ድረ ገፅ ‘Why the elites are in trouble’ በሚል ርዕስ የኒውዮርክ ከተማ የተቃውሞ ሰልፍ ትዕይንትን የሚያሳይ ዘገባ አቅርቦ አስነብቦናል፡፡ ይህንኑ ፅሁፍ አብዱልመሊክ ሁሴን ወደ አማርኛ መልሶ እንደሚከተለው አቅርቦታል፡፡ኬትቹፕ በቁመት አጠር ያለች የ22 ዓመት ወጣት ስትሆን የቺካጎ ከተማ ነዋሪ ነች፡፡ የሚዘናፈል ቀይ ፀጉር አላት፡፡ ደማቅ ቀይ ፍሬም ያለው መነፅርም አድርጋለች፡ መስከረም 10 2004 ከቺካጎ ተጉዛ ኒውዮርክ ከተማ በሚገኘው ዙኮቲ ፓርክ ደረሰች፡፡

ድንኳን ይዛለች፡፡ ተሽከርካሪ የልብስ ሻንጣ ትጎትታለች፡ 40 ዶላር የሚያወጣ ምግብ ሰንቃለች፡፡ ስሊፒንግ ባግ፤ የሆዋርድ ዚን “የአሜሪካ ህዝቦች ታሪክ”ን ስዕላዊ መግለጫ ይዛለች፡፡ ከቺካጎ ስትነሳ የመሄጃ እንጂ የመመለሻ ትኬት አልቆረጠችም፡፡ ኒውዮርክ ገብታ የምትሰራው ሥራ ምን እንደሆነም አታውቀውም፡፡ “ዎል ስትሪትን ተቆጣጠር” የሚል መፈክር ያለውን ሰላማዊ ሰልፍ በተቀላቀለች በመጀመሪያው ዕለት ከሰዓት በኋላ ከእርሷ ጋር በፓርኩ ከፈሰሱት ሰዎች መሃከል የምታውቀው አንድ ሰው አልነበረም፡፡ ወደ ኒውዮርክ ለመሄድ ያሰበችው “የጎዳና ጓዶች” (Adbusters) የተሰኘ አንድ የካናዳ መፅሄት ካነበበች በኋላ ነው፡፡ ይኸው መፅሄት “የተቆጣጠር ጥሪ” አስተላልፎ ነበር፡፡ ኬትቹፕ ወደ ዚኮቲ ፓርክ “የጎዳና ጓዶች” (Adbusters) ስትቀላቀል፤ በተለየ እንድትታይ የሚያደርግ ነገር እንዳልነበራትም ትናገራለች፡፡ 
በፓርኩ ዙሪያ ባሉ ጥላ ቢስ ሰማይ ጠቀስ ፎቆች ውስጥ ያሉት፤ በገንዘብ እና በሰው ነፍስ እንደ አሻንጉሊት የሚጫወቱት፤ የፖለቲካውን መደብ የጠፈጠፉት፤ ሚዲያውን የሠሩት፤ የፍትህ ሥርዓቱን እንደ ውሻ ያዝ የሚሉት፤ የትርፍ ስነ-ምህዳሩን ያዛቡት፤ በቁማር እና በትርፍ ትንበያ የአሜሪካን ግምጃ ቤት ያራቆቱት የፋይናንስ ጌቶች፤ ከህንፃቸው በታች የምትገኘውን ኬትቹፕን ወይም ዘባተሎ የሆኑ የሰላማዊ ሰልፍ ነጋዴዎችን ብዙም ልብ አላሏቸውም፡፡ እነኝህ የፋይናንስ መኳንቶች፤ ከእነርሱ አጥር ውጪ ያለውን ሰው ሁሉ ለዓይን የማይሞላ ጥላ ቢስ አድርገው ይቆጥሩታል፡፡ ስለዚህ በአስተናጋጅነት እየሰራች የወርሃዊ እዳዎቿን ለመክፈል አሳር የምትበላ አንዲት አርቲስት፤ በነኝህ ኃያላን ዓይን እንዴት ትሙላ? እርሷም ሆነች በዙኮቲ ፓርክ የሚተራመሱት ሰዎች መኳንንቱን ምን ሊያደርጓቸው ይችላሉ? እነኝህ ደካሞች በጠንካሮቹ ላይ ምን የሚፈጥሩት አደጋ ይኖራል? ገንዘብን የሚያመልኩ እነኝህ ሰዎች፤ ከጥቂት ቀናት በፊት ለኒውዮርክ ሲቲ ፖሊስ ፋውንዴሽን 4.6 ሚሊዮን ዶላር እንደ ሰጠው ጄፒሞርጋን ቼዝ የሚያምኑት የገንዘብ ኮሮጇቸውን ነው፡፡ ገንዘባቸው፤ የማያቋርጥ ኃይልን እና ደህንነትን ሊገዛላቸው ይችላል፡፡ በገበያ ጣኦታት ፊት ተንበርክከውና በራሳቸው ታላቅነት ታውረው፤ ለሰዎች ስቃይ ቆዳቸውን አደንድነው፤ ለከት በሌለው ስግብግብነት እና ከልካይ በሌለው ጌትነት ክፉኛ ያበጡት እነዚህ ቅምጥል ጌቶች እና መኳንንቶች፤ ዛሬ ግብዝነት የሚያመጣውን ጦስ ሊማሩ ተደግሶላቸዋል፡፡
መኳንቱ እና የሚዲያ አፈ ቀላጤዎቻቸው፤ ከሦስት ሳምንታት በኋላም ኬትቹፕ እና መሰሎቿ ምን እንደሚፈልጉ ለማወቅ ተቸግረዋል፡፡ ጥያቄያቸው እንቆቅልሽ ሆኖባቸዋል፡፡ እስኪ የጥያቄያቸው ዝርዝር የታለ? ለምን የሚፈልጉትን ነገር ግልፅ አድርገው አያቀርቡልንም? አጀንዳቸውን አፍታተው ለማቅረብ የተቸገሩት ለምንድን ነው? እያሉ ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ አሁንም ግራ እንደ ተጋቡ ናቸው፡፡ ሆኖም የኬትቹፕ እና መሰሎቿ ጥያቄ እና ግብ በጣም በጣም ግልፅ ነው፡፡ ፍላጎታቸው በአንድ ቃል ተብራርቶ ሊቀርብ ይችላል - የተቃውሞ ድምፃቸውን የሚያሰሙት እነዚህ ሰዎች በስርዓቱ ውስጥ ሆነው ለመስራት ወይም ለመኖር የሚፈልጉ አይደሉም፡፡ ወደ ዙኩቲ ፓርክ የመጡትም ኮንግረሱ የምርጫ ሥርዓት ማሻሻያ እንዲያደርግ ለመማፀን አይደለም፡፡ የምርጫ ፖለቲካ ቧልታይ ተውኔት መሆኑን አሳምረው አውቀውታል፡፡ ይልቅስ ድምፃቸውን ለማሰማት እና ያላቸውን ስልጣን ለመጠቀም የሚያስችል ሌላ መንገድ መኖሩን ተረድተው የመጡ ናቸው፡፡ በፖለቲካ ስርዓቱ ወይም በሁለቱ ዋና ዋና የፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ እምነት የላቸውም፡፡ ሊኖራቸውም አይችልም፡፡ ሚዲያው የነርሱን ድምፅ አጉልቶ እንደማያሰማላቸው ተገንዝበዋል፡፡ ስለዚህ የራሳቸውን ሚዲያ ፈጥረዋል፡፡ ኢኮኖሚው የኦሊጋርኮቹን እንጂ የእነርሱን ጥቅም እንደማያስጠብቅም አውቀዋል፡ስለዚህ የራሳቸውን ጋሪዮሻዊ ስርዓት ፈጥረዋል፡ይህም እንቅስቃሴ ሃገራችንን ወደ ኋላ የሚወስድ እንቅስቃሴ ነው፡፡
የስልጣን መኳንንቶቹ ሊረዱት ያልቻሉት ግብ እና አላማ ይሄ ነው፡፡ እነርሱ በእኛ ህይወት እና ኑሮ ላይ ባለስልጣን የማይሆኑበትን ጊዜ ማሰብ አይችሉም፡፡ መኳንንቱ፤ ግሎባላይዜሽን እና ልጓም የለሹ ካፒታሊዝም ለዘላለም የፀና የተፈጥሮ ህግ እና መቼም ሊለወጥ የማይችል ዘላለማዊ ሥርዓተ ሂደት ነው ብለው ያምናሉ፡፡ እኛም ይሄንኑ እንድናምን ይሻሉ፡፡ ሆኖም መኳንንቱ ፍጹም ያልተረዱት አንድ ነገር አለ፡፡ በኮርፖሬሽን እጅ የወደቀ መንግስት እስካልጠፋ ድረስ አመፁ መግቻ እንደማያገኝ አልተረዱም፡፡ ይህ አመፅ፤ በደሃው፣ በሰራተኛ ክፍል፣ በአረጋውያን፣ በህሙማን፣ በህፃናት፤ እንዲሁም በኢምፔሪያሊስታዊ ጦርነቶቻችን ውስጥ ገብተው በሚታረዱት እና በጨለማ ጎሬዎቻችን በግርፊያ በሚሰቃዩት ወገኖች ላይ የሚደርሰው ኮርፖሬታዊ ግፍ እና በደል እስካልቆመ ድረስ የሚቀጥል ነው፡፡ የሃራጅ ሽያጭ እና የባንክ የውርስ እርምጃ እስካልተገታ ድረስ የሚያቆም አመፅ አይደለም፡፡ አመፁ፤ ወጣት ተማሪዎች ትምህርት ለማግኘት ዕዳ ውስጥ የሚገቡበት ሁኔታ እና ቤተሰቦች የህክምና ዕዳቸውን ለመክፈል ጥሪታቸውን አሟጠው ለኪሳራ የሚዳረጉበት ሁኔታ እስካልቆመ ድረስ የሚቀጥል ነው፡፡ ይህ አመፅ፤ ትላልቅ ኮርፖሬሽኖች በስነ ምህዳሩ ላይ የሚያደርሱት ውድመት እስካልቆመ እና የእርስ በእርስ ግንኙነታችን እና ከምንኖርባት ፕላኔት ጋር ያለን የግንኙነት ስርዓት በመሰረታዊ መልክ እስካልተለወጠ ድረስ የሚቆም አመፅ አይደለም፡፡ መኳንቶቹ እና ዕድሜውን ሊያራዝሙለት የሚፈልጉት ያፈጀው፣ የከሰረው፣ የበሰበሰው የኮርፖሬት ስልጣን ስርዓት ጭንቀት ውስጥ የገቡት ለዚህም ነው፡፡ የእነዚህ ሰዎች ጥያቄ ምንድን ነው? እያሉ ከመጠየቅ ያልወጡት ለዚህ ነው፡፡ እየሆነ ያለውን ነገር በውል አልተረዱትም፡፡ እነርሱ እውር፣ ድዳ እና ደንቆሮ ሆነዋል፡፡ “ዓለም አሁን በያዘችው ጐዳና መጓዝና ህልውናዋን አስጠብቃ መቀጠል አትችልም” አለች፤ ኬትቹፕ፡፡ “ይህ ሃሳብ ስግብግብ እና ዕውር ሃሳብ ነው፡፡ የሚያዛልቅም አይደለም፡፡ ዛሬ በዓለም ዙሪያ ያሉ ህዝቦች፤ በእኛ እጅ በከንቱ እየተሰቃዩ ይገኛሉ፡፡”
ዎልስትሪትን ተቆጣጠር የሚለው እንቅስቃሴ፤ በትርፍ ስሌት የሚንቀሳቀሰውን የኮርፖሬት ካፒታሊዝም መዋቅርን የሚያኮላሽ አማራጭ ማህበረሰባዊ አደረጃጀትን ፈጥሯል፡፡ ፖሊስ በኒውዮርክ ከተማ የተፈጠረውን ካምፕ ዛሬ ማታ ቢዘጋው፤ የስልጣን መኳንቶቹን ከኪሳራ አይታደጋቸውም፡ ምክንያቱም የእንቅስቃሴው ራዕይ እና መዋቅር ተቃዋሚ ሰልፈኞቹ የነፃነት ፒያሳ የሚል አዲስ ስያሜ በሰጡት፤ በዚያ ፓርክ ባለፉ ባገደሙ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ህሊና ላይ ታትሞ ቀርቷል፡፡ የተቆጣጠር እንቅስቃሴ የሰጠን ታላቅ ቱሩፋት፤ የሚደርስብንን ጥቃት የመከላከል ሥልት እና ሥርዓትን ነው፡፡ ይህም ስልት እና ሥርዓት በሃገሪቱ ወደሚገኙ ሌሎች ፓርኮች እና ከተሞች ተሸጋግሯል፡፡
“ወደ ፓርኩ ገባን” አለች ኬትቹፕ፤ ስለመጀመሪያው ቀን ሁኔታ ስትናገር፡፡ “ለተወሰነ ጊዜ ዝም ብሎ ትርምስ ነበር፡፡ በጣም በርካታ ሰው አለ፡ለመነጋገር ማይክራፎን ይጠቀሙ ነበር፡፡ ማንም ማንንም የማይሰማበት የጨረባ ተስካር ሆነ፡ ከዚያም አንዱ ከመሀከላችን ተነስቶ ክብ - ክብ ሰርተን ምን መደረግ እንዳለበት እና የምንፈልገውም ነገር ምን እንደሆነ ሃሳብ እንለዋወጥ አለ፡፡ እንደ ተባለው አደረግን፡፡ ለእያንዳንዱ ክብ፤ አንድ ሃሳብ መዝጋቢ ተሰየመ፡፡ እነኛ የተወሰዱት ማስታወሻዎች አሁን የት እንዳሉ አላውቅም፡፡ በተያዘው ማስታወሻ መሠረት የተፈጠረ ውጤት ላይኖር ይችላል፡፡ ግን ጥሩ መነሻ ነበር፡፡ በአንድ ጊዜ አንድ ሰው ብቻ ሃሳቡን የሚገልፅበት ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ አንድ፤ የምናደርገው ነገር ሊፈጥረው የሚችለው ለውጥ ብዙ አይታየኝም፡ ብዙም ተስፋ የለኝም የሚል ሰው ገጥሞኝ ነበር፡፡ እኔም ለዚህ ሰው የሰጠሁት ምላሽ፤ ተስፋ ሊኖረንማ ይገባል፡፡ የሆነ ነገር ተፈፅሞ ወይም ተሳክቶ እምናገኝ ከሆነ ይህ የሚሆነው እዚህ ባለነው በኛ ነው አልኩት፡ ደግሞም፤ የተለያዩ ሰዎች ቀዳሚ ትኩረት ሊደረግ ይገባል የሚሉት የተለያየ ነገር ነው፡፡ አንዳንዶች ጥያቄያችን በአንድ ሃሳብ ዙሪያ የሚያጠነጥን መሆን አለበት ይላሉ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ የኤ.አይ.ጂ ሥራ አስኪያጆች ለፍርድ መቅረብ አለባቸው የሚል ሀሳብ ያራምዳሉ፡፡ እንደውም እኛን ለመቀላቀል ከስፔን የመጣች አንዲት ሴት፤ እዚህ የመጣሁት በስፔን የፈፀምነው ስህተት እዚህ እንዳይደገም እናንተን ለማገዝ ነው ብላናለች፡፡ የሚነሳው ሃሳብ ብዙ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ከኛ ጋር የተቀላቀሉት በግል በደረሰባቸው መከራ እና ስቃይ ወይም በዓለም ላይ ሲፈፀም በሚያዩት መከራ ተገፋፍተው ነው፡፡”
“ክብ ሰርተን ተወያየን፡፡ የክብ ውይይቱ ሲበተን ሀሞቴ ፈሰሰ፡፡ ምክንያቱም የሚነሳው ነገር መያዣ መጨበጫ የሌለው ሆኖ ተሰማኝ” አለች ኬትቹፕ፡፡ “ከጎኔ ሆኖ የሚያበረታታኝ ሰው አልነበረም፡፡ ስለዚህ፤ ሁኔታው ትንሽ ተስፋ አስቆራጭ ነበር፡፡ ምን ሊፈጠር እንደሚችልም አላውቅም ነበር፡፡”
“ባለፉት ጥቂት ወራት በኒውዮርክ ከተማ በተካሄዱ ጠቅላላ ጉባኤዎች፤ በርካታ ሰዎች ሲሳተፉ ቆይተዋል” አለች፡፡ “ከነኝህ ሰዎች መካከል አንደኛዋ ብሩኬ ትባላለች፡፡ ብሩኬ የማህበራዊ ስነ-ምህዳር የጥናት ፕሮፌሰር ናት፡፡ ስልጠናም ሰጥታናለች፡፡ እርሷ እና ሌሎች በርካታ ሰዎች፤ ተማሪዎች፣ መምህራን በዚሁ ሥልጠና የተሳተፉ ሰዎች ነበሩ”.፡፡ እነኚህ ሰዎች የጠቅላላ ጉባኤው ስብሰባ አዘጋጆች ሆነዋል፡፡”
“ፖሊሶቹ ማይክራፎን እንዳንጠቀም መከልከላቸው አስቂኝ ነበር፡፡ እነርሱ ይሄን ያደረጉት ሥራችንን አስቸጋሪ ለማድረግ ነበር፡፡ ግን በመጨረሻ ድምፃችንን የሚያጎላ ሁኔታ ፈጠርን፡፡ ድምፁ ከማጉሊያው በበለጠ በአካባቢያችን ያሉ ሰዎችን የሚያበሳጭ ሳይሆን አይቀርም” አለች፡፡ “እኔ ከኋላ ነበርኩ፡፡ ስለዚህ የሚነገረውን ነገር መስማት አልቻልኩም፡፡ ክብ ሰርተን እንደ ቆምን በተለያየ ቦታ ቆሜ ለማዳመጥ ሞከርኩ፡፡ በኋላ አጫጭር አረፍተ ነገር የሚናገረውን ሰውዬ አየሁት፡፡ ሌሎች ሰዎች የሱን ቃል በመድገም ያስተጋባሉ፡፡ ይህ ሃሳብ የማን እንደሆነ አላውቅም፡ ሆኖም ይህ ብልሃት ከመጀመሪያው ዕለት ምሽት ጀምሮ የተጠቀምንበት ነው፡፡ የመጀመሪያው ጠቅላላ ጉባኤ፤ ትንሽ መዘበራረቅ የታየበት ነበር፡፡ ምክንያቱም፤ ሰዎች ጉባዔው ለምን እንደሚካሄድ ምንም ሀሳብ አልነበራቸውም፡፡ “ጠቅላላ ጉባኤ ማካሄድ ምን ይሰራል?” ይሉ ነበር፡፡
“በመጀመሪያ ጉባዔው ጥያቄዎቻችን ምን እንደሆኑ ለመለየት ታስቦ የተፈጠረ መድረክ ነው፡፡ የኮርፖሬቶች ህጋዊ ሰውነት እንዲያከትም ማድረግ የሚለው ሀሳብ በብዙዎች ተቀባይነት ያገኘና ተደጋግሞ የተነሳ ሀሳብ ነበር፡፡” በመጨረሻ፤ በቃ በቡድን በቡድን እንከፋፈል ተባለ፡፡
“ብዙ ሰዎች ከምሽቱ አራት ሰዓት ላይ ፖሊስ ከፓርኩ ያባርረናል የሚል ሥጋት ነበራቸው፡፡ አሳሳቢ የነበረው ጉዳይ ይኽ ነበር፡፡ ለቁጥር የሚያታክቱ ፖሊሶች ነበሩ፡፡ በማንም ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት የማያደርሱ ተቃዋሚ ሰልፈኞችን መሰለል እና መጠበቅ ከተማይቱን ለከፍተኛ ወጪ እየዳረጋት ነው ብለው ሲያወሩ ሰማሁ፡፡ በሰዎች ማይክራፎንነት የምንሰራው ማንኛውም ሥራ ከማንም የተሰወረ ጉዳይ አይደለም፡፡ ከሰው ጋር ተቀላቅለው የገቡ ነጭ ለባሽ ፖሊሶች መኖራቸውን እናውቃለን፡፡ ከእነሱ አንዱን ትናንት ማታ አነጋገርኩት፡፡ ዪእዚህ ምን ትሰራላችሁ? እኛ ሁሉንም ነገር በይፋ ነው የምናከናውነው፡፡ እኛ ከማንም የሚደበቅ ምስጢር የለንም ብዬ አልኩት፡፡
“ማነው መሪው?” የሚል ጥያቄ የሚያነሱት ከመሀላችን የገቡ ነጭ ለባሾች ብቻ ናቸው“ አለች ኬትቹፕ፡፡ “አለ አንዳች ጥርጥር፤ መሪዎቻችን ማን እንደሆኑ ቢያውቁ ለቃቅመው ይወስዷቸው ነበር፡፡ ግን ችግሩ እኛ ምንም መሪ የለንም፡፡ መሪ ተብሎ የተሰየመ ሰው ባለመኖሩ ምንም ማድረግ አልቻሉም፡፡
“በህክምና ቡድን ውስጥ የምትሰራ አንዲት ሴት አለች፡፡ አንዱ ነጭ ለባሽ፤ ሪፖርተር መስሎ ወዲያ-ወዲህ ይላል፡፡ እናም መጀመሪያ ያቀረበው ጥያቄ “መሪው ማነው?” የሚል ነበር፡፡ እርሷም፤ “መሪዋ እኔ ነኝ” አለችው፡፡ እርሱም ለጠቀና “ነው እንዴ፤ እሺ ያንቺ የሥራ ድርሻ ወይም ኃላፊነት ምንድን ነው?” ሲል ጠየቃት፡፡ “እኔ በሁሉም ነገር ላይ ኃላፊነት አለኝ” አለችው፡፡ እርሱም፤ “በእውነት? የሥራ ኃላፊነት መጠሪያሽ ምንድን ነው?” አላት፡፡ እርሷም “እግዚአብሄር” አለችው፡፡
“እና ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ተኩል ሆነ፡፡ ሰዎች ፖሊስ ከካምፓችን ያስወጣናል በሚል ተጨንቀዋል” አለች፤ በመጀመሪያው ዕለት የነበረውን ሁኔታ መለስ ብላ እያስታወሰች፡፡ “ልክ ሦስት ሰዓት ተኩል ላይ ሁሉም ሰው በየተደለደለበት ቡድን ሄደ፡፡ እኔ ያልተጠበቀ ሁኔታ ሲገጥም ዕቅድ በሚነድፈው ቡድን ውስጥ ገባሁ፡፡ የመኝታ ቡድን፤ ሰዎች የሚተኙበትን ካርቶን ፈልጎ የሚያመጣ ነው፡፡ ያልተጠበቀ ሁኔታ ቡድን ደግሞ ፖሊስ ከፓርኩ የሚያስወጣን ከሆነ ምን ማድረግ እንደሚገባን ውሳኔ ያሳልፋል፡፡ ይኸ ቡድን ያሳለፈው ትልቅ ውሳኔ ፖሊስ ዛሬ ማታ ከፓርኩ የሚያስወጣን ከሆነ ጠዋት አራት ሰዓት ላይ ተመልሰን እዚሁ ፓርክ እንገናኝ የሚል ነው፡፡ የአርት እና ባህል ቡድንም አለ፡፡ በፓርኩ ከአንድ ሌሊት በላይ እንደምንቆይ አስበናል፡፡ የምግብ ቡድንም ነበር፡፡ እነርሱ ምግብ ከየትም ብለው ለማምጣት ተዘጋጅተዋል፡፡ የቀጥተኛ ተግባር ኮሚቴ (direct action committee) የሚባልም አለ፡፡ ይህ ቡድን በቦታው አላስፈላጊ የሆነ ድርጊት፤ ማለትም ተሰልፎ ጉዞ እንደማድረግ ያለ ድርጊትን የሚያስተባብር ነው፡፡ የደህንነት ቡድንም አለ፡፡ ይህ ቡድን ከፖሊስ የሚቃጣን ጥቃት ለመከላከል የሚሰራ ነው፡፡ በእኛ ላይ ጥቃት ይሰነዝራሉ ብለን የምናስበው ፖሊሶችን ብቻ ነው፡፡ የደህንነት ቡድን አባላት በየተራ እየተንቀሳቀሱ ሰውን ያነቃሉ፡፡ ሰዎች እንዳይተኙ ያደርጋሉ፡፡ የሥራ ቡድኖች ደግሞ የሎጀስቲክ ውሳኔ ያደርጋሉ፡፡ ጠቅላላ ጉባዔውም ከፍተኛ የፖሊሲ ውሳኔዎችን ያደርጋል፡፡
“የሥራ ቡድኖች የራሳቸውን ውሳኔ አደረጉ” አለች ኬትቹፕ፡፡ “ለምሳሌ አንድ ሰው ላፕቶፑን ለሥራ አበረከተ፡ እኔ ቃለ ጉባዔ ያዥ ስለ ነበርኩ በየቦታው እየዞርኩ፤ “ላፕቶፕ የያዘና የሚያውሰኝ ሰው አለ?” እያልኩ ጠየኩ፡፡ የሚዲያ ቡድን ላፕቶፑን ከኔ ተቀበለና በኢንተርኔት ኮሚቴ ስም በእኔ እጅ እንዲቆይ መልሶ ሰጠኝ፡፡ እንድጠቀምበት፡፡ ኮምፒውተሩ የኔ አይደለም፡፡ እኔ ወደ ችካጎ ስመለስ ይዤው አልሄድም፡፡ አሁን እንኳን ያ ኮምፒውተር የት እንዳለ አላውቅም፡፡ የሆነ ሰው እየተጠቀመበት ነው፡፡ እናም ሰዎች ኮምፒውተሩ ለእኔ እንደ ተሰጠ ሲሰሙ ተናደዱ፡፡ ስለዚህ አንዱ የኢንተርኔት ኮሚቴ አባል ከቡድኑ ፊት ለፊት ቆሞ፤ “ይኽ የኮሚቴው ውሳኔ ነው፡፡ በእርሷ ኃላፊነት እንዲጠበቅ አድርገን ነው” ብሎ ለቡድኑ ነገራቸው፡፡ ግን ኮምፒውተሩ በእርሷ እጅ ይሁን አይሁን ብሎ ጠቅላላው አባል እንዲወስን አላደረገም፡፡ ምክንያቱም ኮሚቴዎች እነርሱን በሚመለከት ጉዳይ የመወሰን ሙሉ ሥልጣን አላቸው፡፡ አንዳንድ ሰዎች የተለየ ሀሳብ ይኖራቸው ይሆናል፡፡ ለጊዜው እንዲህ ያሉ ጉዳዮች የሚወሰኑት በዚህ ዓይነት ነው፡፡ ወደፊት የተለየ አሰራር እንከተል ይሆናል፡፡
“በሚቀጥለው ቀን የሥራ ቡድኖች አንደ አሸን ፈሉ፡ አዲስ መጤዎችን እንኳን ደህና መጣችሁ የሚለው “የእንኳን ደህና መጣችሁ” ቡድን ከሚዲያ ሥራ ቡድን ጋር ተቀላቀለ፡፡ የፅዳት ቡድን -አንዳንድ የዚህ ቡድን አባላት ተሽከርካሪ ጫማ አድርገው፣ መጥረጊያ ይዘው ፓርኩን ይዞራሉ? በህግ ባለሙያዎች የተደራጀ የህግ ቡድን፣ የሁነት ቡድን፣ የትምህርት ቡድን፣ የህክምና ቡድን፣ የአሳላጭ ቡድን፣ -የጠቅላላ ጉባዔ አዲስ አስተናባሪዎችን የሚያሰለጥን፣ የህዝብ ግንኙነት ቡድን አለ፡፡ የአገናኝ ቡድንም አለ፡፡ የአገናኝ ቡድን ተመሳሳይ ተግባር ያላቸውን ቡድኖችን የሚያገናኝ ነው፡፡ ከህዝብ ጋርም የአገናኝ መኮንንነት ሚና አለው፡፡ የኢንተርኔትና የቴክኖሎጂ ብድን አለ፡፡ በአካባቢው ያለው የበርገር ኪንግ ኩባንያ ሰላማዊ ሰልፈኞቹ በድርጅቱ ንብረት እንዳይጠቀሙ ከከለከለ በኋላ፤ ገላ ለመታጠብ የምንጠቀመው የማክዶናልድን ሻወር ነው፡፡
“ከዚህ ሌላ ትናንሽ የቢጤ ቡድኖችም (caucuses) አሉ፡፡ እነዚህ በማህበራዊ አቋምና በሌሎች ጉዳዮች መነሻ የሚፈጠሩ ቡድኖች ናቸው፡፡ የቢጤ ቡድን፤ ለቡድኑ አባላት የማይመቿቸው ሰዎች በማይገኙበት መድረክ ለእነሱ አንገብጋቢ የሆኑ ጉዳዮችን በማንሳት የሚወያዩበት መድረክ ነው፡፡ እናም ትልቁ ስብስብ ለቢጤ ቡድኖች የሚያስቀይም ነገር ከሰራ ያን ተግባር ያስቆሙታል፡፡ የተወሰኑ ቡድኖችን ስሜት የሚነኩ አነጋገሮች ወይም ምልክቶች በፍጥነት እንዲወገዱ ያደርጋል፡፡
“የዚህ ተቃውሞ ሰልፍ ልብ የሚባለው የጠቅላላ ጉባዔ ስብስብ በቀን ሁለት ጊዜ ጧት እና ማታ ይደረጋል፡ የጉባዔው ስብሰባ ብዙውን ጊዜ ሁለት ሰዓት የሚፈጅ ነው፡፡ ጉባዔው ሥራውን የሚጀምረው ክለሳ የሚጠይቁ ጉዳዮችን በመመርመር ነው፡፡ ሁሉም ሰው ጉባዔው እንዴት እንደሚሰራ ያውቃል፡፡ መናገር የፈለገ እጅ ያወጣል፡፡ መዝጋቢው መናገር የሚፈልገውን ሰው ስም ወይም ሌላ መለያ ይመዘግባል፡፡ እጃቸውን የሚያወጡት በብዛት ነጮች ናቸው፡፡ ስለዚህ ነጭ ያልሆነ ሰው ትኩረት ይሰጠዋል፡፡ ጉባዔው በነጮች ሀሳብ እንዳይዋጥ ለማድረግ ነው፡
“አንድ ሰው ሲናገር ሌላው ተቀብሎ ያስተጋባል፡ተሰብሳቢው ለንግግሩ ያለውን ስሜት በምልክት ይገልፃል፡ ሙሉ ስምምነት፣ ከፊል ስምምነት እና ተቃውሞ በጣት እንቅስቃሴ ይገለፃል፡፡
“አንድ ሰው መናገር የሚችለው ስሙ ሲጠራ ብቻ ነው፡፡ ሆኖም ይህ ህግ ብዙ ጊዜ ይጣሳል፡፡ ትልቅ ሥራ ያላቸው የጉባዔው አስተባባሪዎች ናቸው፡ለዚህ ሥራ ትልቅ ትኩረት እንሰጣለን፡ዘረኛ ንግግሮች ወይም ምልክቶች አይፈለጉም፡፡ ካሉም በፍጥነት ይታረማሉ፡፡ ከአስተባባሪዎቹ አንዱ ተናጋሪዎችን የሚመዘግብ ነው፡፡ ሌላው ሰዓት ተቆጣጣሪ ነው፡፡ ሌላው የቫይብ ኃላፊ ነው፡፡ የቫይብ ኃላፊ፤ ሁሉም ሰው ጥሩ ስሜት ላይ መሆኑን ይከታተላል፡ የማንም ሰው ድምፅ አለመታፈኑን ይቆጣጠራል፡ የሆነ የሚረብሽ ሰው ከታየም፤ የቫይብ ኃላፊ ተገቢውን ያደርጋል፡፡
“እኛ ሁሉም ሰው ቅሬታ እንዳይሰማው ለማድረግ እየሞከርን ነው፡፡ ከሁሉም በላይ እንደ ዋና ህግ የያዝነው ሰላማዊ ሰልፈኞቹ ከፖሊስ ጋር ኃይል እና ብጥብጥ ውስጥ እንዳይገቡ ማድረግን ነው፡፡ ፖሊሶቹ ምንም ያህል የጭካኔ ተግባር ቢፈፅሙም ወደ ሁከት አለመግባትን ዋና መመሪያችን አድርገናል፡፡ “እንደምገምተው ፖሊሶቹ እነኛን ሴቶች በጥፊ የመቷቸው በዙሪያቸው ያሉ ወንዶችና ሴቶች ወደ አመፅ እንዲገቡ ለማድረግ ነው” አለች ኬትቹፕ፡፡ “እነሱ ብጥብጥ ይፈልጋሉ፡፡
አመፅ ቢነሳ ደስታቸው ነው፡፡ ነገር ግን ካሜራ የያዘን እና በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞውን የሚገልፅ ህዝብን ምን ያድርጉት?” በማለት ንግግሯን አጠቃለለች፡፡ ለኬትቹፕ ስሊፒንግ ባግ እንደሚመጣላት ነገርኳት፡ አየሩ መቀዝቀዝ ጀመሯል፡፡ ስሊፒንግ ባግ ያስፈልጋታል፡፡ በድንግዝግዙ ብርሃን ውስጥ ኬትቹፕን ተለይቻት የብሮድዌይ ጎዳናን ይዤ ቁልቁል ወረድኩ፡፡ ፖሊሶቹ የሰሩትን አጥር፣ ሞተር ሳይክል ላይ የተቀመጡ የፖሊስ መኮንኖችን፣ ግጥግጥ ብለው የተደረደሩ የፖሊስ መኪናዎችን፣ ወደ ፋይናንስ ተቋማቱ የሚወስደውን መንገድ ዘግተው የቆሙቱን እና ፓርኩን የከበቡትን ፓትሮሎች አልፌ ሄድኩ፡እነኝህ የባንክ ባለቤቶች ከምን ጋር እየተጋፉ እንደሆነ ያወቁት አልመሰለኝም፡

 

Read 1924 times Last modified on Monday, 07 November 2011 12:41