Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Friday, 06 January 2012 10:17

ጉዞ ወደ ጉራጌ አገር

Written by 
Rate this item
(0 votes)

እንዴት ከረማችሁልኝ? ያኔ የአንዳንድ ሸቀጦች እጥረት በተፈጠረባት ወቅት እኛ ሰፈር ዘይት በስፕሬይ መልክ መጥቶ ነበር፡፡ አሁን ግን ተመስገን ነው፡፡ በዘይት ሻወር አልወሰድንም እንጂ … ምን ቀረ? ፅሁፍ አልሞላ እንዳለው አምደኛ ሰላምታ ሳላበዛ ሰተት ብዬ ወደ ቁም ነገሬ ልዝለቅ፡፡ ዛሬ ወደተዋበው የጉራጌ ክልል ጉዞ እናደርጋለን፡፡ ፍላፃዎቻችንም በእጆቻችን እንዳሉ ናቸው፡፡ እንዳስፈላጊነቱ መወርወራችንን አንዘነጋም፡፡ ከዚህ በፊት ከኔ ቀድመው ብዙ ጊዜ ሄደው ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ እሱ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ የጉራጌ አካባቢ በኔ መነፅር ይህን ትመስላለች፡፡ ጉዞአችን የተሳካ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለም፡፡ ከየት እንጀምር? ከአውቶቡስ ተራ፡፡ ወያላው ላንቃው እስኪሰነጠቅ “አገና - አገና” እያለ ይጠራል፡፡ ወደዚያው መሆኔን ስገልፅለት በወያላ ትህትና እቅፍ ድግፍ አድርጐ አስገባኝ፡፡

እንዲህ ባለ ሁኔታ የቀሩትን ሰዎች አሰባስቦ ጉዞአችንን “ሀ” ብለን ጀመርነው፡፡ መኪናችን ጭፍጭፍ አይሱዙ ነው፡፡ ማለቴ ቅጥቅጥ አይሱዙ፡፡ሹፌርዬ ሲነዳ መስሚያ የለውም፡፡ ገና ከአዲስ አበባ ሳንወጣ በየሰው መሀል እጥፍ፣ እጥፍ እያለ ሲያሽከረክር ለተመለከተው፤ ሰለሜ ሰለሜ በመኪና ተጀመረ እንዴ ያሰኛል፡፡ ኧረ እንዳይጀመር!!ወዳጄ አንድ የቤት ስራ ልስጥዎትና ታክሲዎችን ልብ ብለው ይመልከቷቸው፡፡ በርግጥም ሰለሜ ሰለሜ በመኪና ተጀምሯል ይላሉ፡፡ በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ታክሲ ከሕዝብ ማመላለሻነት ባሻገር፣ እንደማህበረሰብ ድረ-ገፅነት እንደሚያገለግል አላውቅም እንዳይሉኝ! እስቲ ዝም ብለው ቀለሙን ይመልከቱትና “ከፌስ ቡክ” ጋር ያመሳክሩ፡፡ አሁንም ግልፅ ካልሆነለዎት ታክሲዎቻችን እንደማህበረሰብ ድረ-ገፅነት የሚል ፅሁፍ በቅርቡ ይጠብቁ፡፡ እዚያው እንገናኝ፡፡ ወደ ዋናው ስቱዲዮ እንመለስና ጉዞዋችንን እንቀጥል፡፡ ከአዲስ አበባ ወጥተናል፡፡ ከተማ ከተማ የሚሸቱ ነገሮችን ጥለን ወደፊት ወደ ገጠሩ እየሸመጠጥን ነው፡፡ መኪናውን “ኦሽ” የሚልልን በማጣታችን ከሾፌሩ ጋር ሳንወድ በግዳችን ተስማምተናል፡፡ በወልቂጤና በአዲስ አበባ መካከል ያሉት ጥቃቅንና አነስተኛ ከተሞች ከዚህ እንደሚከተሉት ናቸው፡፡ አለም ገና፣ ሰበታ፣ ተፍኪ፣ አዋሽ በሉ፣ ተጂ፣ አስጐሪ … አስጐሪ ለምን እንደተባለ ላጫውትዎት፡፡ በጊዜው አንዲት ጠላ ነጋዴ ነበረች አሉ፡፡ ያኔ ታዲያ እንደ አሁኑ ከማስታወቂያቸው ብዛት የተነሳ ሰውን ትክት የሚያደርጉም ሆነ ብቁ የሚባሉ የማስታወቂያ ሰራተኞች አልነበሩም፡፡ (ክፍት የስራ ማስታወቂያ ወዳለፈው ዘመን መሻገር ከቻሉ ሄደው የማስታወቂያ ሰራተኛ ቢሆኑ ያበላዎታል) ከዚህ የተነሳ ማስታወቂያዋን የምትሰራው “አስጐሪ” (እዚህ ግቢ) እያለች ነበር፡፡ በኦሮምኛ ቋንቋ ማለት ነው፡፡ አዋሽ ቡኒ፣ ቱሎ ቦሎ … ቱሉ ቦሎም ስሟን ያገኘችው በአካባቢው ካለ ተፈጥሯዊ ገፅታ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ቱሉ ማለት ጋራ ሲሆን ቦሎ ማለት ጉድጓድ እንደማለት ነው፡፡  እነዚህን ጥቃቅንና አነስተኛ ከተሞች መንግስት ባስቀመጠው የትራንፎርሜሽን የእድገት እቅድ ተጠቅመው አድገውና ተመንድገው ወደፊት አገር አቀፍ የከተሞችን ቀን እንደሚያዘጋጁ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ በዚህ አጋጣሚ መቀሌ እንኳን ደስ አለሽ!! ወልቂጤ ላይ ምን የመሰለ የጉራጌ ክትፎ አጣጥመን፤ ወደ ግራ ታጠፍንና ዋቢ የተባለውን ወንዝ ተሻግረን ጉዟችንን በፒስታ መንገድ ላይ ተያያዝነው፡፡ አንድ ሀያ ሰላሳ ኪሎ ሜትር ከተጓዝን በኋላ በአፍሪካ በመንገድ ግንባታ አንደኛ የሆነው መንግስታችን ኢህአዴግ እያሰራው ያለው መንገድ ላይ ደረስን፡፡ የላይኛውን አረፍተ ነገር በቅንፍ ማድረግን በመርሳቴ ይቅርታ ያድርጉልኝ፡፡ መንገዱም በመንግስት በተበጀተ 600 ሚሊዮን ብር እንደሚገነባ ኮራ ብለው አጫወቱን፡፡ መንግስታችን ሺ አመት እንዲነግስልን ፀሎታችንን አድርሰን ስንነቃ አገና ከተማ ደርሰን ነበር፡፡ የምሄድበትን መንደር አለማወቄ ብዙም ስጋት አልፈጠረብኝም፡፡ ቢበዛ ሰው መጠየቅ ነው፡፡ የት አገር ነው አሉ ሰዎች የማያውቁትን ነገር መጠየቅ ያሳፍራቸዋል አሉ፡፡ እኛ አገር ብቻ እንዳይሆን፡፡ ወዲያው መንገድ ሊያውቅ ይችላል ብዬ የገመትኩትን ጠና ያለ ሰው የቦታውን ስም ጠቅሼ ጠየኩት፡፡ ሰኞ ህዳር 11 ቀን 2004 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ ተጠያቂም በማያሻማ ሁኔታ መንገዱን ከጠቆመኝ በኋላ በሰላም እንድደርስ መርቆ ጉንጭ በሚያወልቅ የጉራጊኛ አሳሳም ስሞ ተሰናበተኝ፡፡ በወፎች ዝማሬና በዛፎች ሽውሽውታ ታጅቤ ጉዞዬን ተያያዝኩት፡፡ የአካባቢው ፀጥታ እጅግ በጣም ያስፈራል፡፡ ፀጥ ረጭ ከማለቱ የተነሳ አንዲት የደረቀች ቅጠል እንኳ ከወገኖቿ ተለይታ ወደ መሬት ስትወድቅ የሚያሸብር ስሜት ይፈጥራል፡፡ ከመርካቶ ግርግርና ትርምስ ጩኸትና ግፊያ ወጥተው እንደዚህ ወዳለ ፀጥታ ውስጥ ሰርገው ሲገቡ ወደ ኤደን ገነት አካባቢ የተጠጉ ሊመስልዎት ይችላል፡፡  ይህን አጋጣሚ ተጠቅሜ ጫማዬን እንዳመሰግን ይፈቀድልኝ፡፡ ያንን ቁልቁለትና አቀበት፣ ወጣ ገባውን፣ ድንጋያማውን የመሬት አቀማመጥ ቁንጥጥ አድርጋ በመያዝ ወድቄ እንዳልሰበር ትልቁን አስተዋፅኦ አበርክታለች፡፡ በተለይ መንግስታችን ባስገነባቸው መንገዶች ላይ መሄድ የለመደ በእንዲህ አይነቱ መንገድ መጓዝ ሊያስቸግረው ይችላል፡፡ እግር ኳስ ተጫዋቾችና ራጮች ብቻ ናቸው እንዴ ሲያሸንፉ ጫማቸውን የሚስሙት ብዬ ጫማዬን ለመሳም ቃጥቶኝ ነበር፡፡  ጥቂት እንደተጓዝኩኝ መንገዱ ግራ እንደመጋባት ሲያደርገኝ የሚጠየቅ ሰው ፍለጋ ማነፍነፍ ጀመርኩኝ፡፡ ብዙም ሳይቆም ሁለት አዛውንቶች ሰጋር ሰጋር የሚባሉ አይነት በቅሎዎች ይዘው በቅርብ ርቀት ከፊት ለፊቴ ተመለከትኳቸው፡፡ ፈጠን ብዬ ደረስኩባቸውና ጥያቄዬን ሰነዘርኩላቸዉ፡፡ “ደህና ዋላችሁ?” አልኩኝ፡፡ ያለኝን ትህትና ሁሉ አሟጥጬ በመጠቀም፡፡ እነርሱም ቢሆን እንግዳ መሆኔ አልጠፋቸውም ነበርና አፀፋውን መለሱልኝ፡፡ ቦታ ጠፍቶብኝ እንዲረዱኝ መፈለጌን ስገልፅላቸዉ፡፡ አንድ ሽማግሌ ቆፍጠን ብለው፣ “የምትፈልገውን ቦታ ለማወቅ የሚጠየቀው ሰውዬ ይኸውና” ሲሉኝ በአነጋገር ለዛቸው እየተማረኩ፣ “ወደ ዋድሮ” መሄድ እንደምፈልግ አጫወትኳቸው፡፡  አንዲት የሽማግሌ እርምጃ ጠጋ ብለው፣ “ዋድሮ ማን ቤት ነው መሄድ የፈለከው?” በማለት  በጥያቄ አፋጠጡኝ፡፡ እኔም የሞተው አያቴን ስም ተናገርኩኝ፡፡ አትኩሮታቸውን ሳይቀንሱ ለዚህ ሰውዬ ምኑ እንደሆንኩ ጠየቁኝ፡፡ ምንነቴንም አስረዳሁ፡፡ ሰውዬውም የአያቴ ወንድም ልጅ ወይም ያባቴ ያጐት ልጅ ሆነው ቁጭ፡፡ እንደገና ሳብ አድርገው፣ “አንተማ ደምህ ከደሜ፣ አጥንትህ ከአጥንቴ ነው” በማለት ቅድም በነገርኳችሁ የአሳሳም ዘዴ አንደኛውን ጉንጬን አላሉት፡፡ በመቀጠልም በቅሎዋቸው ላይ እንድቀመጥ ጋበዙኝ፡፡ እሳቸውን የሚያክል ሰውዬ እያሉ እንደማልቀመጥ እስኪገባቸው ድረስ አስረዳኋቸው፡፡ እሳቸው ኮርቻው ላይ ተቀመጡ፡፡ እኔንም ከኋላ እንድቀመጥ አስገደዱኝ፡፡ በእግሬ ልከተልም ብላቸውም አልተስማሙም፡፡ በመጨረሻም የሳቸውን ትዕዛዝ በማክበር በበቅሎዋ የኋላ ወንበር ላይ እንደምንም ብዬ ተቀመጥኩ፡፡ በቅሎ ላይ ስሳፈር የመጀመሪያዬ መሆኔን ልብ ይበሉልኝ፡፡ የበቅሎዋ የኋላ ወንበር በጣም ይቆረቁራል፡፡ አሁን ደግም የቂጤን ዋንጫ የሚያወልቅ ነገር ተገኘ፡፡ የእንስሳት መብት ተሟጋቾች በቦታው አለመኖራቸው በጀን እንጂ በአንዲት በቅሎ ላይ ለሁለት መሳፈር  ሊያስጠይቅ ይችላል ብዬ ፈርቼ ነበር፡፡ የገረመኝ ነገር ቢኖር ሰዎቹ በቅሎ ሲመጣ ጉዞዋቸውን ገታ በማድረግ በቅሎውን ሲያሳልፉ ስመለከት በጣም ሲያስገርመኝ ቆየ፡፡ እኛ አዲሳበባዊያንም እንደዚህ ያለ የመንገድ አጠቃቀም ስርአት ቢኖረን ብዬ የሞኝ ምኞት ተመኘሁ፡፡

 

 

 

Read 2986 times Last modified on Friday, 06 January 2012 10:21