Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Saturday, 28 January 2012 11:16

የኋሊት መንሸራተት ይብቃን

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ኢትዮጵያ፤ “አፈና ከገነነባቸው 50 አገራት አንዷ ነች” - ኢአይዩ

“የጭቆና አገር ለመሆን አፋፍ ላይ ደርሳለች” ሄሪቴጅ ፋውንዴሽን

“ነፃነት በእጅጉ ከተሸረሸረባቸው 5 አገራት አንዷ ነች” ፍሪደም ሃውስ

መንግስት፤ የምንመኘውን ያህል አሟልቶ፤ የዜጎችን ነፃነት ባያከብር እንኳ፤ ቢያንስ ቢያንስ በታጋሽነትና በመቻቻል መንፈስ ትችቶችን ለማስተናገድ ቢጥር ምናለበት? ከተቃዋሚ ፓርቲዎችና ከተቀናቃኝ ፖለቲከኞች የሚሰነዘሩ ወቀሳዎችን ብቻ ሳይሆን፤ የዜጎችን አቤቱታና የምሁራንን ትችት ለመስማት ትእግስት እያጣ መምጣቱ በጣም አሳሳቢ ነው። ከዚህና ከዚያ አንድ ሁለት ትችት ብቅ ብቅ ሲሉ፤ ይበረግጋል፤ ሃላፊዎች ይቆጣሉ። “አመፀኛ” ወይም “ፀረህገመንግስት” ብለው ለመፈረጅ የሚቸኩሉም ጥቂት አይደሉም። ጭራሽ በ”አሸባሪነት” መወንጀልም፤ ቀላል እየሆነ ነው።

ምናልባት፤ ትችቶችን ከስልጣን ተቀናቃኝነት ጋር እያይዘው ስለሚያዩት ይሆን የሚቆጡት? ችግሩ፤ ይሄ ከሆነ ብዙም አያስቸግርም። የስልጣን ተቀናቃኝነት ውስጥ ሊገቡ የማይችሉ አለማቀፍ ተቋማት የሰነዘሯቸውን ትችቶች መሰረት አድርገን መነጋገርና መወያየት እንችላለን። በፖለቲካና በኢኮኖሚ ነፃነት ዙሪያ አለማቀፍ እውቅና ያተረፉ አራት ተቋማት በቅርቡ ያወጧቸው አመታዊ ሪፖርቶችን እንመልከት።

ኢትዮጵያ በዲሞክራሲ ሚዛን

“ዘ ኢኮኖሚስት ኢንተሊጀንስ ዩኒት” በየአመቱ የሚያዘጋጀው የጥናት ሪፖርት፤ Index of Democracy በሚል ርእስ ይታወቃል። ዘንድሮም እንደ ወትሮው 167 አገራትን የሚዳስስ የጥናት ሪፖርቱን አሰራጭቷል። ዋነኛዎቹ መመዘኛዎች አምስት ናቸው - የምርጫ ፍትሃዊነት፤ የመንግስት ብቃት፤ የፖለቲካ ተሳትፎ፤ የፖለቲካ ባህል እና የግል ነፃነት አከባበር። የየአገሩን የፖለቲካ ስርአት በመመዘኛዎቹ እየመረመረ፤ ምን ያህል እንደተራመዱና ምን ያህል ወደኋላ እንደቀሩ በዝርዝር ይገልፃል። እንደየውጤታቸውም በአራት ምድብ ይከፍላቸዋል።

በመጀመሪያው ምድብ ውስጥ የዘረዘራቸውን 25 አገራት፤ “የተሟላ ዲሞክራሲ የሰፈነባቸው አገራት” በማለት ሪፖርቱ ሰይሟቸዋል። ከእነዚህም አንዷ፤ አፍሪካዊቷ ሞሪሼስ ናት። በሁለተኛው ተርታ ውስጥ 78 አገራት ገብተዋል። ከነጉድለቱም ቢሆን፤ በአመዛኙ የዲሞክራሲ ስራአት ለመገንባት ችለዋል የተባሉ አገራት ናቸው። ደቡብ አፍሪካን፣ ማሊን እና ጋናን ጨምሮ 10 ያህል የአፍሪካ አገራት በዚህ ምድብ ውስጥ እናገኛለን። ለዘመናት፤ ከዳር እስከ ዳር በአምባገነንነት መካራዋን ስትበላ የነበረችው አፍሪካ ባለፉት 10 አመታት እጅግ እየተሻሻለች መጥታለች ማለት ይቻላል። በርካታ አገራት፤ ወደ ነፃነት የሚያራምድ የተረጋጋ የፖለቲካ ስርአት እየገነቡ ነው። ኢትዮጵያ ከእነዚህ አገራት መካከል ብትሆን እንዴት ጥሩ ይሆን ነበር!

በሶስተኛ ምድብ የሚመጡት፤ ቅይጥ ስርአት ውስጥ የሚገኙ አገራት ናቸው - የዲሞክራሲና የአፈና ስርአት ያደባለቁ። ከእነዚህ 36 አገራት መካከል፤ ኬንያንና ኡጋንዳን፤ እንዲሁም በእርስበርስ ጦርነት ውስጥ ተዘፍቀው የነበሩ ላይቤሪያና ሴራሊዮንን ጨምሮ 13 የአፍሪካ አገራት ተጠቅሰዋል።

የመጨረሻው ምድብ፤ አፈና ጎልቶ ይታይባቸዋል ተብለው በኢአይዩ ጥናት የተዘረዘሩ አገራት የተዘረዘሩበት ነው። ኢትዮጵያ በ121ኛ ደረጃ፤ ኤርትራ በ154ኛ ደረጃ በዚሁ ምድብ ውስጥ ገብተዋል። Authoritarian regimes ይላቸዋል ሪፖርቱ። 50 ያህል አገራትን የያዘው ይሄው ምድብ፤ ከማዳጋስካርና ከራሺያ ጀምሮ፤ እስከ ሰሜን ኮሪያ ድረስ ይዘልቃል።

የአገሮችን ፖለቲካዊ ስርአት ለመፈተሽ በሚያገለግሉት አምስት መመዘኛዎች፤ በተለይም በ3ቱ፤ የኢትዮጵያ ውጤት እጅግ ዝቅተኛ ነው። በምርጫ ሂደት ፍትሃዊነት፤ ከመጨረሻዎቹ የአለም አገራት አንዷ ሆናለች። በመንግስት ብቃትና በግለሰብ ነፃነት አከባበርም ደረጃዋ ዝቅተኛ ሆኗል። በፖለቲካ ባህልና በፖለቲካ ተሳትፎ፤ ትንሽ ሻል ያለ ውጤት ይታይባታል - መካከለኛ የሚባል።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ስርአት ሲፈተሽ፤ ከ50ዎቹ የአለማችን የአፈና አገራት አንዷ ሆና መመዝገቧ አያሳዝንም? በጣም አሳሳቢው ጉዳይ ግን፤ ከአመት አመት ደረጃዋ እየተባባሰ መምጣቱ ነው። በ2000 አ.ም ከአለም አገራት ውስጥ 105ኛ ደረጃ ነበራት። “ዲሞክራሲና አፈና የተቀየጠባቸው፤ በከፊል ነፃነት የሚታይባቸው” ተብለው ከሚዘረዘሩ አገራት ጋር ነበር የተመደበችው። በ2002 አ.ም የአገሪቱ ደረጃ ወደ 118ኛ አሽቆለቆለ። የአፈና ምድብ ውስጥ ገባች። ዘንድሮ ደግሞ፤ እዚያው የመጨረሻ ምድብ ውስጥ፤ ደረጃዋ ወደ 121ኛ ወረደ። “አገሪቱ ወዴት እያመራች ነው?” ለሚለው ጥያቄ አመታዊዎቹ ሪፖርቶች ምላሽ የሚሰጡ ቢሆንም፤ “መጨረሻዋ ወዴት ነው?” የሚለው ጥያቄ ግን ገና አልለየለትም።

በኢኮኖሚ ነፃነት ስትመዘን

ሄሪቴጅ ፋውንዴሽን የሚያዘጋጀው አመታዊ የጥናት ሪፖርት፤ ለኢትዮጵያ የሚያፅናና አይደለም። በኢኮኖሚ ነፃነት ላይ የሚያተኩረው፤ የሄሪቴጅ ሪፖርት፤ በአስር መመዘኛዎች ላይ የተመሰረተ ነው። የኢንቨስትመንት አፈቃቀድን ጨምሮ፤ አለቅጥ እየሰፋ የመጣው የመንግስት በጀትና የገንዘብ ህትመት መፍትሄ ባያገኝም ካለፈው አመት እንደሚሻል የገለፀው ሄሪቴጅ ፋውንዴሽን፤ በእነዚህ መመዘኛዎች የማንሰራራት ምልክቶች እንዳሉ ገልጿል፤ ነገር ግን የአገሪቱ የኢኮኖሚ ነፃነት ከ2000 እና ከ2001 አ.ም ጋር ሲነፃፀር፤ አሁን ዝቅተኛ ነው ብሏል። ምክንያቱም፤ በቀሪዎቹ ስድስት መመዘኛዎች የተሻሻለ ነገር እንደሌለ አልያም ችግሮች እንደተባባሱ ይገልፃል።

በተለይ የቢዝነስና የንግድ ስራዎች ላይ፤ የዜጎች ነፃነት  እንደተሸረሸረ የሄሪቴጅ ሪፖርት ይጠቅሳል። ኢትዮጵያ፤ በ2011 ሪፖርት ውስጥ፤ ከአለም አገራት ያላት ደረጃ 144ኛ ነው። ከ46 የአፍሪካ አገራት ጋር ስትነፃፀርም ደረጃዋ  ዝቅተኛ ነው - 30ኛ። “በአብዛኛው ነፃነት የለሽ” ከሚባሉት አገራት ጋር የተመደበችው ኢትዮጵያ፤ በዚሁ ምድብ ውስጥ የመጨረሻዋ “ውራ” ነች - “የጭቆና አገራት” ወደሚባሉት ሰላሳ የአለማችን አገራት ለመሻገር አንድ ደረጃ ብቻ ነበር የቀራት።

ወደ ኋላ የምትንሸራተት አገር

የተለያዩ ተቋማት በሚያወጧቸው አመታዊ ሪፖርቶች ላይ፤ “የጭቆና አገራት”፤ “የአፈና አገራት”፤ “ነፃነት የለሽ አገራት” የሚባሉ ምድቦች ውስጥ የማትጠፋ አገር ብትኖር ኤርትራ ነች - ከሰሜን ኮሪያ ጋር። ኢትዮጵያ ወደነዚህ ምድብ ስታመራ ማየት በጣም ያሳዝናል። የፍሪደም ሃውስ አመታዊ የነፃነት ሪፖርት ውስጥ፤ ተጠቃሽ አገር ሆናለች።

የ195 አገራትን የፖለቲካ ስርአት በመመርመር፤ የዜጎች ነፃነት አከባበርን (የፖለቲካና የግል ነፃነት አከባበርን) ይመዝናል - የፍሪደም ሃውስ የጥናት ሪፖርት። መዝኖም በሶስት ምድቦች ይከፍላቸዋል  - “ነፃ”፤ “በከፊል ነፃ” እንዲሁም “ነፃ ያልሆኑ” በሚሉ ምድቦች።

የአለማችን 87 አገራት፤ ከሞላ ጎደል ነፃነት የሚከበርባቸው አገራት እንደሆኑ ከነመመዘኛዎቹ የሚዘረዝረው የፍሪደም ሃውስ ሪፖርት፤ “በከፊል ነፃ” የሚል ምድብ ውስጥ ደግሞ 60 አገራትን ዘርዝሯል። አብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት በዚህ ምድብ ውስጥ የሚካተቱ ናቸው።  ሪፖርቱ የመጨረሻው ምድብ ውስጥ፤ “ነፃ ያልሆኑ የአለማች 48 አገራት” ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ አንዷ ኢትዮጵያ ነች።

የእርስ በርስ ግጭት ሲታመሱ ቆይተው፤ ከቅርብ አመታት ወዲህ የተረጋጉት ሴራሊዮንና ላይበሪያ ሳይቀሩ፤ ደረጃቸውን እያሻሻሉ “በከፊል ነፃ” ወደሚል ምድብ መግባት እየቻሉ፤ ኢትዮጵያ እንዴት ከመሻሻል ይልቅ እየባሰባት “ነፃ ያልሆኑ” ምድብ ውስጥ ገብታ ትቀራለች?

ለነገሩማ፤ ኢትዮጵያኮ ከ10 አመታት በፊት፤ “በከፊል ነፃ” የሚባለው ምድብ ውስጥ ነበረች። መሻሻል ባትችል እንኳ እንዴት እዚያው መቆየት ያቅታታል?  ፍሪደም ሃውስ እንደሚለው፤ ባለፉት አምስት አመታት ውስጥ፤ በከፍተኛ መጠን የዜጎች ነፃነት ከተሸረሸረባቸው አምስት የአለማችን አገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ሆናለች።

እንግዲህ፤ የአሜሪካዎቹ ሄሪቴጅ ፋውንዴሽንና ፍሪደም ሃውስ እንዲሁም የእንግሊዙ “ዘ ኢኮኖሚስት ኢንተሊጀንስ ዩኒት” ያወጧቸውን ሪፖርቶች አይተናል። ሂዩማን ራይትስ ዎች፤ “በኢትዮጵያ አፈና ተባብሷል” በማለት በተደጋጋሚ የሚያወጣቸው መግለጫዎችንና ሪፖርቶችንም መጠቃቀስ ይቻላል። በዊኪሊክስ የተለቀቁ የአሜሪካ ኤምባሲ ሚስጥራዊ ደብዳቤዎችም፤ “የኢትዮጵያ መንግስት ከጊዜ ወደ ጊዜ አፋኝ እየሆነ ነው” የሚሉ ተደጋጋሚ መልእክቶችን ይዘዋል። ፈረንሳይ ውስጥ ወደ ተቋቋመውና በመላው አለም ለፕሬስ ነፃነት ወደ ሚከራከረው “ሪፖርተርስ ሳንፍሮንቴ” እንሸጋገር።

 

ፍርሃት ያጠላባቸው የግል ጋዜጦች

ሪፖርተርስ ሳንፍሮንቴ፤ በቅርቡ በኢትዮጵያ ጉብኝት እንዳካሄደ በመጥቀስ ባወጣው ሪፖርት፤ በግል ጋዜጦች ላይ የፍርሃት ድባብ አጥልቷል ብሏል። የተወሰኑ የግል ጋዜጦች እየታተሙ መሆናቸውን እንደማስረጃ በማቅረብ፤ “ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት ጨርሶ እንዳልጠፋ እናምናለን” ሲሉ የተናገሩት የተቋሙ ሃላፊ፤ ነገር ግን ከጥቂት አመታት ወዲህ የፕሬስ ነፃነት እየጠበበ መምጣቱን ገልፀዋል።

የአዲስ ነገር እና የአውራምባ ጋዜጦች ህትመት መቋረጡን በማስታወስ የተቋሙ ሃሳፊ ሲናገሩ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ መስራት አስጊ የሆነባቸው በርካታ ጋዜጠኞች መሰደዳቸውም፤ በአገሪቱ ውስጥ የፕሬስ ነፃነት እንደተሸረሸረ ያመለክታል ብለዋል። በተለይ ደግሞ፤ ከሁለት አመት በፊት የወጣው የፀረሽብር ህግ፤ የፕሬስ ነፃነትን ለማፈን እየዋለ ነው የሚሉት እኚሁ ሃላፊ፤ በቅርቡ የተፈረደባቸው ሁለት የስዊድን ጋዜጠኞችንና ሰሞኑን ከ10 አመት በላይ እስር የተፈረደባቸው ሁለት ኢትዮጵያዊያን ጋዜጠኞችን በምሳሌነት ጠቅሰዋል። ሌሎች በስደት የሚገኙ 6 ኢትዮጵያዊያን ጋዜጠኞችም፤ በፀረሽብር ህግ ክስ እንደቀረበባቸው ሃላፊው ገልፀው፤ ሃሳብን ከመግለፅ የሚገታ የዝምታና የፍርሃት መንፈስ አንዣብቧል በማለት ለተባበሩት መንግስታት ደብዳቤ ፅፈዋል።

 

የኢትዮጵያ መንግስት፤ ከአለማቀፍ የሰብአዊ መብትና የፕሬስ ነፃነት ተቋማት የሚቀርቡ ሪፖርትቶችንና ትችቶችን አይቀበልም። ለምሳሌ፤ የስዊድናዊያኑን ጋዜጠኖች እስር በመቃወም ትችቶች ሲሰነዘሩበት ወዲያውኑ አጣጥሏቸዋል። “ለነጮችም ለጥቁሮችም አንድ አይነት መመዘኛ መኖር አለበት” የሚል መንፈስ የያዘው የመንግስት ምላሽ፤ “ተቋማቱ  ስለፕሬስ ነፃነት ጩኸታቸውን የሚያሰሙት፤ ነጭ ጋዜጠኞች ስለታሰሩ ነው” የሚል መልእክት ያስተላልፋል።

ነገር ግን፤ ሪፖርተርስ ሳንፍሮንቴ እና ሌሎች አለማቀፍ የፕሬስ ነፃነት ተቋማት፤ ለበርካታ አመታት፤ በተለይ የኢትዮጵያዊያን ጋዜጠኞች እስር ሲባባስ፤ ተመሳሳይ ጩኸት ሲያሰሙ እንደነበር ይታወቃል። የጋዜጠኞች እስር እየቀነሰ በመጣባቸው ወቅቶችም፤ “የኢትዮጵያ የፕሬስ ነፃነት ሁኔታ እየተሻሻለ ነው” በማለት ሪፖርት ማቅረባቸው አይካድም። አለማቀፍ ተቋማት፤ በኢትዮጵያ ላይ የወቀሳና የትችት ሪፖርት ሲያቀርቡ፤ በመንግስት በኩል የሚሰነዘሩ ሌሎች ምላሾችም አሉ። ብዙውን ጊዜ፤ ሪፖርቱን ከማስተባበል ይልቅ፤ ተቋማቱን የሚያጣጥል ምላሽ ገንኖ ይወጣል - “የኢትዮጵያን እድገት ማየት የማይሹ”፤ “የኢትዮጵያን ልማት ሲሰሙ የሚተናነቃቸው”፤ “የቅኝ ግዛት ስሜት የተጠናወታቸው”፤ “በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ አዛዥ ለመሆን የሚቋምጡ”፤ “በስኬታችን ምክንያት የሚጠሉንና የሚጠምዱን የውጭ ሃይሎች” በማለት ያብጠለጥላቸዋል። ሪፖርቶቹ፤ ሁልጊዜ ትክክል ይሆናሉ ባይባልም፤ ተቋማቱን ማንቋሸሽ አሳማኝ ምላሽ አይደለም። ደግሞም፤ አለም ሁሉ ኢትዮጵያን ጠምዶ ይይዛታል ብሎ ማሰብ ስህተት እንደሆነ፤ የመንግስት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ በፅሁፍ ሰፍሯል። በዚያ ላይ፤ “ስኬታችንን ማየት የማይሹ ጠላቶቻችን” ተብለው ዛሬ የተብጠለጠሉት ተቋማት፤ ነገ “ይሄው የኢትዮጵያን እድገት መሰከሩልን” ተብለው እንደ ታማኝ ወዳጅ በማስረጃነት ሲቀርቡ ይታያል።

ለምሳሌ “ዘ ኢኮኖሚስት” በአመታዊ ሪፖርቱ፤ ኢትዮጵያን “በአፈና አገራት” ውስጥ ሲመድባት፤ “ለኢትዮጵያ የማይተኛ ውሸታም ጠላት” እንደሆነ ተቆጥሮ ይወገዛል። ከቀናት በኋላ፤ በሳምታዊው መፅሄቱ “የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በፍጥነት እያደገ ነው” ብሎ ሲዘግብ ደግሞ፤ “እውነታውን የሚመሰክር ሃቀኛ ዘጋቢ” ተብሎ በማስረጃነት ይመረጣል። ትንሽ ቆይቶ ትችት ሲሰነዝር ደግሞ፤ እንደገና “ታሪካዊና ዘላለማዊ ጠላት ነው” ተብሎ ይፈረጃል። እንዲህ አይነቱ የማብጠልጠል ምላሽ፤ ብዙ አያስኬድም። ካስፈለገ፤

በተጨባጭ መረጃ ማስተባበል! ለማስተባበል ከመሯሯጥ ይልቅ ደግሞ፤ ትችቶችን እያስተናገዱ፤ ስህተቶችን ለማረም መዘጋጀትና መትጋት ይሻላል። ባለፉት ጥቂት አመታት በብዙ አቅጣጫ ሲሸረሸር የቆየው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ነፃነት፤ በፍጥነት ሳይታረም እንዲሁ ከቀጠለ፤ ለመንግስትም፣ ለዜጎችም፤ በአጠቃላይ ለአገር አይበጅም።

 

 

 

Read 3644 times Last modified on Saturday, 28 January 2012 11:29

Latest from