Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Saturday, 03 March 2012 14:42

ስብሃት በ”ትኩሳት” የቀረብን ደራሲ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የስብሃት የስነምግባር ሃሳቦች፤ እንደ ኢትዮጵያ ጥንታዊ ናቸው። ስብሃት፤ በሶሻሊዝም ሃሳቦች ያምናል። ግን አብዮተኛ” አይደለም። ጀግኖችን ይወዳል። ግን ጀግንነትን የሚወልዱ ሃሳቦች የሉትም። “ባህላዊ” የስነምግባር ሃሳቦችን ይቀበላል። ግን “ነውር” ይፅፋል።

ስብሃት ገብረእግዚአብሄር፤ እጅግ የሚያስቆጭ ደራሲ እንደሆነ ይሰማኛል። ያን ያህል አቅም የሌለው “ተራ ሰው” ወይም “ቀሽም ደራሲ” በተለያዩ ምክንያቶች ባክኖ ቢቀር ብዙም አያስቆጭም። ስብሃት ግን “ተራ” የሚባል አልነበረም። ዘወትር የማያጋጥም፤ በየቦታው የማይበቅል፤ እንደ ብርቅ ሊቆጠር የሚችል ከፍተኛ የአእምሮ አቅም ነበረው። ለዚህም ነው፤ ስብሃት በትኩሳት መባከኑ፤ እጅግ ይቆጫል የምለው።

በእርግጥ፤ እንዲህ በደፈናው መናገር ትርጉም የለውም። እውነት ከፍተኛ አቅም እንደነበረው የሚያሳይ ማስረጃ አለ? እውነትስ መባከኑን የሚያመለክት ማረጋገጫ አለ? እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ ያስፈልጋል። የስብሃትን ከፍተኛ አቅም የሚመሰክሩ ተናጋሪዎችና ፀሃፊዎች ብዙ ስለሆኑ፤የመጀመሪያውን ጥያቄ ለነሱ ብተወው ይሻላል። የ”መባከኑ” ጥያቄስ? በቅድሚያ የስብሃትንና በዘመኑ የነበሩትን አስተሳሰቦችና ሃሳቦች፤ እንዲሁም እምነቶችና ስሜቶችን ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል። ለዚህም፤ በስፋት የሚታወቁ የአገር መረጃዎችንና “ትኩሳት” የተሰኘውን የስብሃት ድርሰት እያጣቀስኩ ጥያቄውን ወደ መመለስ ለመሻገር እሞክራለሁ።

(“ትኩሳት”፤ ጠቅላላ ድርሰቱ የስብሃት ሃሳብና ስሜት የተገለፀበት ቢሆንም፤ በተለይ የድርሰቱ ዋና ገፀባህርይ፤ የስብሃትን የወቅቱ ዋና ዋና አስተሳሰብና ስሜት በይበልጥ ይገልፃል ብዬ አምናለሁ። ሊያከራክር እንደሚችል ቢገባኝም፤ ለጊዜው በዚሁ አልፌዋለሁ። በእርግጥ፤ ድርሰቱ በደፈናው፤ የስብሃትን አስተሳሰብና ስሜት ይገልፃል የሚለው አባባል፤ ራሱ ስብሃት የሚስማማበት ይመስላል። “ትኩሳት” መፅሃፍ መግቢያ ላይ ስለ ድርሰቱ እንዲህ ብሏል - “በዚያ በትኩሳት እድሜያችን የኖርነውንና ያሰብነውን ሳላሻሽል ‘እንደ ወረደ’ ፃፍኩት”።)

በነገራችን ላይ ትኩሳት የሚለው ቃል፤ የ1960ዎቹ አ.ም የሶሻሊዝም ትኩሳትንም ለመጠቆም ይረዳናል - (የስብሃት መፅሃፍ በአብዛኛው “የወሲብ ትኩሳት” ቢሆንም)። እንደ ዘበት ወደ መነሻዬ ገባሁ። መነሻዬም እነሆ - ከ1960 እስከ 1970 አ.ም የዘለቀው የሶሻሊዝም ትኩሳት፤ ከስብሃት መባከን ጋር የተቆራኘ ጉዳይ ነው። ለነገሩማ፤ ስብሃት ብቻ ሳይሆን፤ ብዙ ኢትዮጵያውያን ባክነውበታል። እንዴት በሉ። አንድ መረጃ ልጥቀስላችሁ።

“የሰው አማካይ አመታዊ ምርት” ሲባል ሰምታችሁ ይሆናል። ጠቅላላ የአገር ምርት በገንዘብ ተሰልቶ፤ ለጠቅላላ ህዝብ ቢካፈል እንደማለት ነው። አንዳንዶች አሳጥረው “ፐር ካፒታ” ብለው የሚጠሩት ይሄው ስሌት፤ በአማካይ ስለ ሰዎች የኑሮ ሁኔታ ያሳያል ተብሎ ይታሰባል። የአለም ባንክ መረጃ እንደሚያሳየው፤ የኢትዮጵያ “ፐር ካፒታ” ማሽቆልቆል የጀመረው በ60ዎቹ አ.ም ነው - ከሶሻሊዝም ትኩሳት ጋር። የኢትዮጵያውያን ኑሮም እንዲሁ እየወረደ ለአመታት ቀጥሏል። ለማንሰራራትም ረዥም ጊዜ ወስዷል።

ኢኮኖሚው ቀስ በቀስ እያንሰራራ፤ በ67 አ.ም ወደ ነበረበት ደረጃ መድረስ የቻለው በ1997 አ.ም ነው። “30 አመት በከንቱ ባከነ” የሚል ትርጉም አይሰጣችሁም? “የአንድ ትውልድ ዘመን ባከነ” ብንለውስ? ለማለት የፈለግኩት፤ የሶሻሊዝም ትኩሳት፤ ከስብሃት ጋር ብቻ ሳይሆን፤ ከብዙ ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ታሪክና ኑሮ ጋር የተሳሰረ ነው። ብዙዎች ለሶሻሊዝም ደስኩረዋል፤ ሰብከዋል፤ ፎክረዋል፤ ረሽነዋል፤ አጨብጭበዋል፤ አስረዋል፤ አሞግሰዋል፤ አሰቃይተዋል... በዚያውም ባክነዋል።

እጅግ ብዙዎች ደግሞ  በሶሻሊዝም ተገድለዋል፤ ታስረዋል፤ ተርበዋል፤ ተሰደዋል፤ ተሰቃይተዋል፤ ንብረት ተወርሰዋል፤ ባክነዋልም። መከራ የደረሰባቸው ሶሻሊዝምን ስለተቃወሙ እንዳይመስላችሁ። “ከራስ ጥቅም በፊት የሌሎችን ጥቅም ማስቀደም፤ ከራስህ በፊት አገርን ማስቀደም፤ ህዝብን ማስቀደም፤ ለፓርቲና ለመሪ ተገዢ መሆን” በማለት መስዋእትን የሚያውጁ ሶሻሊስታዊ የስነምግባርና የፖለቲካ ሃሳቦች አጥፊ ሃሳቦች ቢሆኑም፤ ያን ያህልም ተቃውሞ አልነበረባቸውም። አሁንም ድረስ እነዚህን የመስዋእት መርሆችንና ሃሳቦችን የሚቃወም ብዙ ሰው የለም። ደግሞም፤ የመስዋእት መርህና ሃሳቦች ለአገራችን አዲስ አይደሉም። ከሃይማኖት ጋር ተያይዘው አገራችን ውስጥ ለዘመናት ስር ሰደው የቆዩ ጥንታዊ የስነምግባር ሃሳቦች ናቸው። ሃሳቦቹ፤ የዘመነኛነት ልብስ ደርበው፤ በሶሻሊዝም ቅርፅ ብቅ ሲሉም ብዙ ተቃዋሚ ሃሳብ አልገጠማቸውም።

በድርሰት አለምስ? የመስዋእት መርሆችን አምነውና ተቀብለው፤ የሶሻሊዝምን ትኩሳት ለማራገብና ለማዳመቅ፤ ሶሻሊዝምን ለማሞገስና ለመስበክ የፕሮጋንዳ ድርሰት እየፃፉ የባከኑ ደራሲዎችን መጥቀስ ትችላላችሁ። ስብሃት ግን ከእነዚህ ውስጥ የለበትም። ግን ሶሻሊዝምን ይቃወማል ማለት አይደለም። በጭራሽ አይቃወምም። እንዲያውም እንደ ብዙዎቹ ኢትዮጵያውያን፤ ስብሃትም የሶሻሊዝም “የመስዋእት መርሆችንና ሃሳቦችን” አምኖ ተቀብሏቸዋል። ትንሽ ትንሽ ከማራገብና ከማሞገስም ወደ ኋላ አላለም። ማስረጃ የታለ? ትሉ ይሆናል።

በእርግጥም፤ ስብሃት፤ በተለያዩ ጊዜያት፤ ቼጉቬራን፤ ካስትሮን፤ ማኦንና የመሳሰሉ የሶሻሊዝም አብዮተኞችንና አምባገነኖችን እያሞጋገሰ መፃፉ በቂ ማስረጃ ላይሆን ይችላል። ነገር ግን፤ የሶሻሊዝም አባት ወይም አሳዳጊ የሚባለውን ማርክስ ሲያወድስ፤ በተለይ ደግሞ የማርክስን ሃሳቦች ሲያዳንቅ በተለያዩ ቃለምልልሶች ሰምተናል። ይሄም በቂ ማስረጃ አይሆንም። በትኩሳት ድርሰቱ ውስጥ፤ አድናቆት እየተቸራቸው የተቀረፁ ገፀባህርያትን መመልከት ይሻላል - ባህራምንና ሉልሰገድን።

“የሚወደድና የሚከበር ልጅ ነው። ያስታውቃል” ተብሎ በገፅ 40 የተፃፈለት ሉልሰገድ፤ ለዚህ አድናቆት እንዴት በቃ?  ሉልሰገድ በድርሰቱ ውስጥ ከፍተኛ አድናቆት የተቸረው፤ ከሴት ጓደኛው ጋር በተያያዘ ምክንያት ነው። (እንግዲህ፤ የሉልሰገድ የሴት ጓደኛ አማንዳ ትባላለች። እዚያ ካሉ ሴቶች ሁሉ፤ በመልክና በቁመናዋ አስቀያሚ ነች። በዚያ ላይ፤ ከሉልሰገድ ውጭ ተካ ከሚባለው ጓደኛው ጋር ወሲብ ፈፅማለች - ለነገሩ ከማንም ወንድ ጋር ትተኛለች የተባለላት ነች)። የትኩሳት ተራኪና ዋና ገፀባህርይ እንዲህ በማለት ሉልሰገድን ያደንቃል።

“ይሄ ሉልሰገድ ተራ ሰው አይደለም። ከአማንዳ ጋር ባደረገው ግንኙነት የታየኝ ጠባዩ የሀበሻ ጠባይ አይመስልም። ... አስቀያሚ ሴት መተኛቱስ የሀበሻ ደንብ ነው። ሰው ሁሉ እያየው አቅፏት መዞሩ ግን! ...”

አሁን ይሄ አድናቆት ነው? ትንሽ ያልተለመደ አይነት አድናቆት ሊመስል ይችላል። ግን አስቡት። ሉልሰገድ፤ አማንዳን አይወዳትም። በድርሰቱ መሰረት፤ ሉልሰገድ፤ እንዲሁ ጊዜያዊ ስሜቱን ለማርካት ከአማንዳ ጋር ወሲብ ቢፈፅም አይገርምም። የተለመደ ነው። ግን በየመንገዱ አብሯት ይታያል። አቅፏት ይዞራል። ይሄን ሲያደርግ ደስ አይለውም። ይደብረዋል። ሌሎች አስደሳች ነገሮችን ማከናወን ወይም አዝናኝ ቦታዎችና ሰዎች ጋ መሄድ ቢፈልግም፤ እሷን ባይወዳትም፤ ብትደብረውም፤ የራሱን ደስታ ትቶ ለሷ ስሜት ሲል ይቸገርላታል። የራሱን ደስታ መስዋእት ያደርጋል። ለሌላ ሰው ደስታ ቅድሚያ ይሰጣል። ታዲያ አድናቆቱ እንግዳ ነገር ነው? ጥንታዊ የአበሻ ስብከትና የሶሻሊዝም ዲስኩር አልሆነባችሁም?

“የራስህን ጥቅም መስዋእት ማድረግ፤ የሌሎችን ጥቅም ማስቀደም” የሚለውን የስነምግባር መርህ፤ “አናውቀውም፤ ወይም ያልተለመደ እንግዳ ነገር ነው” ልትሉ አትችሉም። ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ዘመን ያስቆጠረ ጥንታዊ የእምነት መርህ ነው። በዚያ ላይ፤ መስዋእትነት፤ የሶሻሊዝም መርህ ነው። “ከእያንዳንዱ እንደ ችሎታው፤ ለእያንዳንዱ እንደ ችግሩ”  ይባል የለ? የስብሃት ድርሰት ሉልሰገድን እያደነቀ ይቀጥላል።

“... አምራው ቢተኛት ያባት ነው። እየሰለቸችው እወድሻለሁ ማለቱ ግን! ...ልጅቱ አስቀያሚ በመሆኗ አይወዳትምና፤ ተካ ተኛኋት ብሎ ሲነግረው ከተካ ጋር አለመጣላቱስ እሺ። እሷ ራሷ ተካ ተኝቶኛል ብላ ስትናዘዝ፤ ሰበብ አገኘሁ ብሎ እሷን አለማባረሩ ግን! “ ገፅ 45።

በስብሃት ድርሰት ውስጥ፤ ባህራም ለተሰኘው ኢራናዊ ገፀባህሪ የተቸረው አድናቆትም ተመሳሳይ ነው - በመስዋእት መርህ ላይ የተመሰረተ። ባህራም፤ የራሱን ህይወት፤ የራሱን ጥቅምና ደስታ መስዋእት ለማድረግ ተዘጋጅቷል። ለምን ሲባል፤ ለኢራናዊያንና ለኢራን ሲባል። የስብሃት ድርሰት ውስጥ የተገለፁት ከፍተኛ አድናቆቶች፤ “የራስን ጥቅምና ደስታ ለሌሎች ሰዎች መስዋእት ማድረግ አለብህ” በሚለው የመስዋእት መርህ ላይ የተመሰረቱ ናቸው።

“መስዋእት” ሲባል፤ አንዳች ጥቅም ለማግኘት፤ ወይም አንዳች የምትወደውን ስኬት ለመቀዳጀት ታስቦ የሚከፈል ዋጋ እንዳልሆነ ልብ በሉ። ሉልሰገድ አማንዳን ቢወዳትና፤ አንዳንዴ እየደበረው አቅፏት ቢዞር፤ “መስዋእትነት” አይሆንም። የሚወዳትን ልጅ ይዞ መቀጠል ይፈልጋል። አንድ ድርጊት፤ “መስዋእትነት” የሚሆነው፤ ለራስ ጥቅም የማያስገኝና ራስን የሚጎዳ ከሆነ ነው። ጥቅም ለማግኘት ማሰብማ፤ “ሃጥያት” ሆኖ ተኮንኗል፤ “ፀረ ሶሻሊዝም” ተብሎ ተወግዟል። “መስዋእት”፤ በከንቱ የሚከፈል ዋጋ፤ በከንቱ የሚባክን ህይወት ነው።

እንደ ስብሃት ትኩሳት ሁሉ፤ የ1960ዎቹ የሶሻሊዝም ትኩሳትም፤ በዚሁ የመስዋእት መርህ ላይ የተገነባ ከመሆኑም በላይ በተግባርም ታይቷል። በእርግጥ አንዳንዶቸች፤ የመስዋእትነት መርህ ተግባራዊ አልሆነም ብለው ያጉረመርማሉ። ነገር ግን፤ በተግባር የብዙዎች ህይወትና ደም፣ ኑሮና ንብረት፤ ነፃነትና ደስታ በከንቱ ባክኗል። በከንቱ ጠፍቷል (መስዋእት ሆኗል)። ሁሉም ሰው በአንድ ጊዜ መጥፋት ነበረበት ካልተባለ በቀር፤ የደረሰው ጥፋት በቂ አይደለም ካልተባለ በቀር፤ “የመስዋእት መርህ” አጥፊነትና መዘዝ በተግባር ታይቷል። መፈክሩም ጥፋትን ያውጃል። “ደም መፍሰስ አለበት። ብዙ ቆሻሻ የተመረዘ ደም መፍሰስ ይኖርበታል” ገፅ138።

ስብሃት፤ በሃሳብ ደረጃ፤ በጥንታዊውና በሶሻሊስታዊው የመስዋእት መርህ እንደሚያምን በቂ ማስረጃ ያቀረብኩ ይመስለኛል። በእርግጥ፤ ሁልጊዜ በዚህ የጥፋት መርህ ማመንና ሙሉ ለሙሉ በዚህ ክፉ መርህ መመራት አይቻልም። የሚሞክር ካለም፤ ሳይውል ሳያድር ይሞታል፤ ይጠፋል። አገሪቱና ነዋሪዎቿ፤ በጥንታዊውና በሶሻሊስታዊው የመስዋእት መርህ ሙሉ ለሙሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያልጠፉት፤ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ስለማይሆን ነው።

በተመሳሳይ ምልኩ፤ ስብሃት ያንን የመስዋእት መርህ አምኖ ቢቀበልም፤ ሌላ አማራጭ የስነምግባር መርህ ባይኖረውም፤ ሁል ጊዜ ያንን አምኖ መተግበር አይችልም። ነገር ግን ስብሃት፤ በመስዋእት መርህ ጭልጥ ብሎ ያልሰጠመው፤ በዚህ ምክንያት ብቻ አይደለም። በእርግጥ “ትኩሳት”  ድርሰት ውስጥ፤ ሶሻሊዝምን የሚሰብኩና ካፒታሊዝምን የሚያወግዙ ዲስኩሮች ጥቂት አይደሉም። እንደወሲብ ትእይንቶቹ ሁሉ፤ በየቦታው ተዘርተዋል። ከገፅ 120 እስከ ገፅ 146 ድረስ ደግሞ በሰፊው ተለቋል። እንዲያም ሆኖ፤ ስብሃት እንደ አንዳንድ ደራሲዎች፤ ዘው ብሎ አልገባበትም። የፕሮፓጋንዳ ወይም የስብከት ደራሲ አልሆነም። ትኩሳት ድርሰቱ ውስጥም ይህን የሚደግፍ መረጃ እናገኛለን።

“እኔ’ኮ በሪቮሊሽን አላምንም ... አንተኮ ሪቮሊሽን ለማድረግ የምትፈልገው፤ በሰው ልጅ ጥሩነት የፀና እምነት ስላለህ ነው።  ... የሚጨቆነው ተራው ሰው የነሱን (የገዢዎቹን) ስልጣን ቢሰጠው፤ ልክ እነሱ የሚሰሩትን ግፍ ይሰራል።... ጭቆና ሊቀር የማይችል የሰው ልጆች እጣ ነው። ጥያቄው ‘ማንስ ይጨቁን፣ ማንስ ይጨቆን’ ነው እንጂ፤ ‘እንዴት አድርገን ጭቆናን እናጥፋ’ አይደለም። ሰው ከስረ መሰረቱ አስቀያሚ፣ መጥፎ፣ ክፉ ነው። ስለዚህ ለሰው ልጆች ብዬ እንኳን ህይወቴን ልሰዋ ይቅርና የአንድ ቀን እንቅልፌን አልሰጥም” ገፅ 138።

እንግዲህ ተመልከቱ። የመስዋእት መርህን አምኖ ይቀበላል። በዚሁ መርህም ሉልሰገድንና ባህራምን ያደንቃል። ነገር ግን፤ “የመስዋእት መርህ ትክክል ነው” ብሎ ቢያምንም፤ ለሰው ልጆች ብዬ መስዋእት ለመሆን ፍቃደኛ አይደለሁም ይላል። ስብሃት ጭልጥ ብሎ የፕሮፓጋንዳ ወይም የስብከት ደራሲ ለመሆን አለመፍቀዱ ከዚህ ሃሳብ ጋር የተያያዘ ይመስለኛል። በእርግጥ፤ “የሰው ልጅ ከንቱ ነው” የሚለው መጥፎ ሃሳብ ለአገራችን አዲስ አይደለም። “የአዳም ዘር ሁሉ፤ የአዳም ሃጥያትን ወርሷል” በሚለው እምነት አማካኝነት በሰፊው የተንሰራፋና ምእተአመታት ያስቆጠረ ጥንታዊ ሃሳብ ነው። ጥንታዊ የኢትዮጵያ ቅርስ ቢባልም አይበዛበትም - “ሰው ከንቱ” የሚለው  ሃሳብ። የሆነ ሆኖ፤ ስብሃት ጥንታዊውንና ሶሻሊስታዊውን የመስዋእት መርህ በሃሳብ ደረጃ አምኖ እየተቀበለ፤ ግን ደግሞ ወደ ጎን ጣል ጣል ለማድረግ የሞከረው፤ “ሰው ከንቱ” በሚለው ሰበብ ነው።

ከዚህም በተጨማሪ፤ ስብሃት የተቀነጨቡ የጀግንነት ታሪኮችንና የጀግንነት ገጠመኞችን ይወዳል። በጋዜጣ ፅሁፎቹና በድርሰቶቹም ውስጥ እነዚህን የተቀነጫጨቡ ታሪኮችና ገጠመኞችን በየጊዜውና በተደጋጋሚ ፅፏል። የጀግንነት ጥማት፤ ለማንኛውም ሰው በተለይ ደግሞ ለደራሲ፤ እጅግ የተቀደሰ ስሜት ነው። ስብሃት ይህን ቅዱስ ስሜት ተቀብቷል። ነገር ግን፤ የመስዋእት መርህና የጀግንነት ጥማት እርስበርስ አይጣጣሙም። የመስዋእት መርህ፤ ከምስኪንነት ጋር እንጂ፤ ከጀግንነት ታሪክ ጋር አብሮ አይሄድም። ከዚህም የተነሳ፤ ስብሃት የመስዋእት መርህን፤ በከፊል እንጂ ሙሉ ለሙሉ በሃሳብ፣ በስሜትና በተግባር ከራሱ ጋር ለማዋሃድ አልፈቀደም ብዬ አስባለሁ። በሌላኛው ከፊል ደግሞ የጀግንነትና የቅንነት ጥማት ይዟል - ከአጥፊ የመስዋእት መርህ የሚሸሸግበት። እዚህ ላይ ነው ችግሩ።

ተቃራኒ ነገሮችን ተሸክሞ ለመቀጠል መሞከር፤ ውስጥን ይቦረቡራል። በመስዋእት መርህ እያመነ፤ በተቻለ መጠን ከመርሁ ለመሸሽና ለመደበቅ መመኘት ዋጋ የለም። የመስዋእት መርህን በደንብ መርምሮ፤ ክፉ የጥፋት መርህ መሆኑንም ተገንዝቦ፤ ከጀግንነት ህይወት ጋር የሚጣጣምና የጀግንነት ጥማትን የሚያረካ ትክክለኛና ቅዱስ መርህ ለማግኘት መጣር ነበር የሚያዋጣው። የስብሃት ትኩሳት ውስጥ እንደሚታየውም፤ ቅንጫቢ የጀግንነት ታሪኮችንና ገጠመኞችን መተረክ ማምለጫ አይሆንም። “ነውር” የተባሉ አባባሎችን የመናገርና የመፃፍ ጀብደኝነት ይዞ፤ ከሃሳብ ለመሸሽ መሞከር መፍትሄ አይሆንም። “ትርፉ”፤ መባከን ነው። እንዴት? በሌላ ፅሁፍ ልመለስበት።

 

 

Read 6069 times Last modified on Saturday, 03 March 2012 14:55

Latest from