Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 17 March 2012 09:15

ኢህአዴግ፤ “አንድም፤ ሁለትም” ነው

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

አንድም “አብዮታዊ ልሁን” ይላል፤ ሁለትም “ዲሞክራሲያዊ ልሁን” ይላል።

አብዮታዊው - ተቃዋሚዎችን ያስፈራራል፤ የሊዝ ህግ ያውጃል፤ “አንድ ለአምስት” ያደራጃል።

ዲሞክራሲያዊው ለተቃዋሚ ብር ያካፍላል፤ መሬት ለኢንቨስተር ይሰጣል፤ ማህበራት ነፃ ይሁኑ ይላል

የኢህአዴግ ነገር እንቆቅልሽ እየሆነ ለብዙዎች አስቸጋሪ የሚሆነው፤ ለካ አለምክንያት አይደለም። ግራ ስትሉት ወደ ቀኝ፤ እንደገና ቀኝ ስትሉት ግራ እየሆነ አንዳንዴ ቂም፤ ቁጣና እስር ያበዛል። ሌላ ጊዜ ደግሞ፤ እርጋታ፤ ይቅር ባይነትና ቻይነት ይላበሳል። አንዳንዴ፤ የኢትዮጵያ ተስፋ ኢህአዴግ ብቻ ነው፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን እንዳያንሰራሩ እናደርጋቸዋለን፤ እሽሩሩ አንላቸውም ብሎ ይፎክራል። ሌላ ጊዜ ደግሞ፤ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ ያስፈልጋል፤ ተቃዋሚዎች የገንዘብ እጥረት ካለባቸው ሊጠይቁን ይችላሉ ብሎ ይጋብዛል። ለፖለቲካው እንቆቅልሽ ፍቺ ሊሆን የሚችል መልስ ያገኘሁ ይመስለኛል። ለዚያውም ከራሱ ከኢህአዴግ ውስጥ፤ ነው ምላሹን የምናገኘው - (እከተለዋለሁ ከሚለው የ”አብዮታዊ ዲሞክራሲ” አስተሳሰብ ውስጥ)።

 

 

እስቲ በየጊዜው የምትሰሟቸውን የኢህአዴግ አቋሞች አሰላስሉ። አንዳንዴ፤ የግል ቢዝነስ ዋነኛ የእድገት ሞተር ነው በማለት፤ ለኢንቨስትመንትና ለቢዝነስ ማነቆ የሆኑ የተንዛዙ የቢሮክራሲ እንቅፋቶችን ለማስወገድ ዘመቻ ይጀምራል። ሌላ ጊዜ ደግሞ፤ የግል ቢዝነሶች ዋነኛ እንቅፋት ስለሆኑብኝ እቆነጥጣቸዋለሁ በማለት፤ አዳዲስ የቢሮክራሲ መሰናክሎችንና ቁጥጥሮችን በዘመቻ ይተክላል።

ኢህአዴግ፤ የውጭ አገራትን በተመለከተም እያሰለሰ ተቃራኒ አስተያየቶችን ይሰነዝራል። አንዳንዴ፤ አሜሪካንና አውሮፓን በጠላትነት እየፈረጀ፤ አምባገነኖችና ኢምፔርያሊስቶች መሆናቸውን በመግለፅ የውንጀላ መአት ያወርድባቸዋል። ሌላ ጊዜ ደግሞ፤ የዳበረና ምርጥ የዲሞክራሲ ስርአት የሰፈነባቸው እንደሆኑ በመጥቀስ ያሞግሳቸዋል። ምናለፋችሁ! ኢህአዴግ፤ በየጊዜው ከአንድ አቋም ወደ ተቃራኒው፤ ከአንድ አቅጣጫ ወደ ሌላ አቅጣጫ ይንደረደራል። ለጊዜያዊ “ጥቅም” ተብሎ የሚፈጠር የዥዋዥዌ ጨዋታ እንዳይመስላችሁ!

 

ጊዜያዊ የዥዋዥዌ ጨዋታ

በእርግጥ እንደ ብዙዎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሁሉ፤ ኢህአዴግም እንደ አመቺነቱ ጊዜያዊ የፖለቲካ ዥዋዥዌ መጫወቱ አይካድም። ለምሳሌ፤ “ሰብአዊ መብት ትጥሳለህ” የሚል ወቀሳ ከአሜሪካና ከአውሮፓ ሲሰነዘርበት፤ ኢህአዴግ በቁጣ ይገነፍላል - “የማላውቃችሁ መሰላችሁ? ሰብአዊ መብትን የምትረግጡ ወራሪዎችና አምባገነኖች ናችሁ” ብሎ ያወግዛቸዋል። ግን ብዙም ሳይቆይ ሲያሞግሳቸው ትሰማላችሁ። የፓርቲዎች ምዝገባ ህግ ወይም የፀረ ሽብር ህግ አዘጋጅቶ ትችት ሲቀርብበት፤ ምን አይነት ምላሽ እንደሰጠ ታስታውሱ ይሆናል። “ህጎቹን እኛ አልፈጠርናቸውም። የዳበረ ምርጥ የዲሞክራሲ ስርአት ከሰፈነባቸው ከአሜሪካና ከአውሮፓ አገሮች የተኮረጁ ናቸው” በማለት ይከራከራል።

ይሄን ስናይ፤ ኢህአዴግ ለጊዜው እንደማምለጫ የሚያገለግል የፖለቲካ ዥዋዥዌ ይጫወታል ልንል እንችላለን። የዥዋዥዌ ጨዋታው፤ በኢህአዴግ ላይ ብቻ ሳይሆን በብዙዎቹ የአገራችን ፓርቲዎች ላይ ዘወትር የሚታይ አሳሳቢ ችግር እንደሆነ አምናለሁ። ነገር ግን፤ ኢህአዴግን ጨምሮ የአገራችን ፓርቲዎች ችግር ከዚህ ይብሳል። የፓርቲዎች የአቋም ዥዋዥዌ፤ ጊዜያዊ የማምለጫ ጨዋታ ብቻ አይደለም። ተፈጥሯቸው ነው። እያንዳንዱ ፓርቲ፤ በውስጡ በርካታ ተቃራኒ አስተሳሰቦችን ይዞ ለመራመድ ስለሚሞክር፤ በየጊዜው የእርምጃው አቅጣጫ ይለዋወጣል፤  በየጊዜው አቋሙ ይቀያየራል። የኢህአዴግም እንደዚያው ነው። ለዛሬ፤ ለማሳያ ያህል፤ ከላይ እንደጀመርኩት በኢህአዴግ እንቆቅልሽ ዙሪያ ባተኩር አይሻልም?

 

ነባር የዥዋዥዌ ተፈጥሮ

እንቆቅልሽ እየሆነ የሚያስቸግረን የኢህአዴግ የፖለቲካ ዥዋዥዌ፤ በአብዛኛው ጊዜያዊ ጨዋታ ሳይሆን፤ ከራሱ ከኢህአዴግ ተፈጥሮ የሚመነጭ ነባር ባህርይ ነው። ኢህአዴግ በተፈጥሮው፤ “አንድም፤ ሁለትም ነው” ማለት ይቻላል። አንድም “አብዮታዊ” ልሁን ይላል፤ ሁለትም “ዲሞክራሲያዊ” ልሁን ይላል። አንደኛውንና ገናናውን “አብዮታዊ ኢህአዴግ”፤ ሌላኛውንና አናሳውን “ዲሞክራሲያዊ ኢህአዴግ” ብለን ልንሰይማቸው እንችላለን። ይህንን መንታ ማንነት፤ በሁሉም የኢህአዴግ አስተሳሰቦች ውስጥ ታገኙታላችሁ።

ለምሳሌ የኢኮኖሚ አስተሳሰቦቹን ተመልከቱ። አንድም፤ “ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል” እያለ የሚሰብክ ሶሻሊስት ነው። ሁለትም፤ “ያፀደቅኩት ህገመንግስት ነጭ ካፒታሊዝምን ያሰፍናል” እያለ የሚናገር ነው። በፓለቲካውስ? አንድም፤ “የቡድን መብት፤ የብሄር ብሄረሰብ መብት፤ የብዙሃን መብት” እያለ ህዝባዊነትን (ሶሻሊዝምን) ይደሰኩራል። ሁለትም፤ “የግለሰብ መብት የህገመንግስታዊ ስርአታችን አንድ ምሶሶ ነው” በማለት ይናገራል።

አንዳንዴ “አብዮታዊው ኢህአዴግ” ይነሳበታል፤ እናም ወደ ግራ አቅጣጫ ይንደረደራል። ሌላ ጊዜ ደግሞ፤ ሰከን ብሎ “ዲሞክራሲያዊው ኢህአዴግ” ይባንናል፤ ያኔ ወደ ቀኝ አቅጣጫ ይንፏቀቃል። በእርግጥ እንዲህ በተቃርኖ ተወጥሮ እስከ ወዲያኛው መዝለቅ አይችልም። ፈጠነም ዘገየም፤ ወደ አንዱ አቅጣጫ እያመዘነ መሄዱ የማይቀር ነው (በተቃርኖ ተወጥሮ መፍረስ ወይም መፈንዳት ካልፈለገ በቀር)። ከሁለቱ ተቃራኒ አቅጣጫዎች (ከሁለቱ ተቃራኒ ማንነቶች) መካከል አንዱ እስኪያሸንፍ ድረስ ግን፤ ተቃራኒዎቹ ማንነቶች እየተፈራረቁ በዥዋዥዌ አገሪቱን ይዞ በአዙሪት መሾሩ ይቀጥላል።

አብዮታዊው ኢህአዴግና ዲሞክራሲያዊው ኢህአዴግ፤ ምን ያህል ተቃራኒ አቋሞችን እንደሚይዙ ለማየት፤ የተለያዩ ርእሰ ጉዳዮችን በማንሳት እንመልከት። በቢዝነስና በመንግስት ጣልቃ ገብነት ላይ፤ በኪራይ ሰብሳቢና በጥገኛ፤ በተቃዋሚ ፓርቲና በሚዲያ ክርክር ላይ፤ በህገመንግስትና በአገራዊ መግባባት ላይ፤ “ሁለቱ ኢህአዴጎች” በአቋም ይለያያሉ። ሌላው ይቅርና በዲሞክራሲና በአብዮት ላይ ያላቸው አቋምም ለየቅል ነው። አንዳንዶቹን ለመመልከት እንሞክር።

 

የምርጫ ተሳትፎና፤ የፓርቲዎች ክርክር

“አብዮታዊው ኢህአዴግ”፤ የኛ ዲሞክራሲና የፖለቲካ ምርጫ ከአሜሪካ ይበልጣል ይላል - የመራጮች ተሳትፎ በኢትዮጵያ ከፍተኛ መሆኑን በመጥቀስ። በአሜሪካ፤ መምረጥ ከሚችለው ህዝብ መካከል ከ60 በመቶ በታች ያህሉ በምርጫ ይሳተፋል። በኢትዮጵያ ግን ከ85 በመቶ በላይ ድምፅ በመስጠት ይሳተፋል በማለት ያብራራል - አብዮታዊው ኢህአዴግ። ኮሙኒስቶች የሚያዘወትሩት አባባል መሆኑን ልብ በሉ። የአንድ ፓርቲ አገዛዝና፤ እንደ ሳዳም ሁሴን የመሳሰሉ አምባገነኖች በነገሱባቸው አገራት ውስጥ፤ ከ90 በመቶ በላይ ህዝብ በምርጫ ይሳተፍ እንደነበረ ግን አይወራም።

በአሜሪካ እንደሚታየው፤ በቀጥታ የሚተላለፍ የፓርቲዎችና የፖለቲከኞች ክርክር አስፈላጊ እንዳልሆነ የሚገልፀው “አብዮታዊው ኢህአዴግ”፤ በቀጥታ ስርጭት የህዝብ ጥያቄች ጎልተው አይወጡም በማለት ያጣጥለዋል። የፖርቲዎች ክርክር በሚዲያ ከመሰራጨቱ በፊት “ኤዲት” ሲደረግ፤ የህዝብ ጥያቄዎች ጎልተው ይወጣሉ በማለትም ይከራከራል።

“ዲሞክራሲያዊው ኢህአዴግ” በበኩሉ፤ የአሜሪካ ዲሞክራሲ እጅግ የዳበረ እንደሆነና ኢትዮጵያም ቀስ በቀስ ዲሞክራሲን በመገንባት እንደምታዳብር ይገልፃል። በቀጥታ የሚሰራጭ የፓርቲዎችና የፖለቲከኞች ክርክር፤ በአሜሪካ እንደሚታየው ከጠንካራ የዲሞክራሲ ባህል ጋር የተሳሰረ እንደሆነና ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው በአድናቆት ይናገራል - “ዲሞክራሲያዊው ኢህአዴግ”። በኢትዮጵያ ግን የዲሞክራሲ ባህል ስላልዳበረ፤ በቀጥታ የሚሰራጭ የፓርቲዎች ክርክር፤ እንደ 97ቱ ምርጫ ስሜታዊነትንና ግጭትን ይፈጥራል የሚለው “ዲሞክራሲያዊው ኢህአዴግ”፤ ቀስ በቀስ ዲሞክራሲያዊ ባህል ማዳበር አለብን ይላል።

 

የፖለቲካ አማራጮችና አገራዊ መግባባት

አብዮታዊው ኢህአዴግ፤ “የአሜሪካ ዲሞክራሲ፤ የኮካ እና የፔፕሲ አማራጮች የሚቀርቡበት የይስሙላ ዲሞክራሲ ነው ይላል። ዋና ዋናዎቹ የአሜሪካ ፓርቲዎች የኒዮሊበራል አቋም አራማጆች (አፍቃሬ ካፒታሊዝም) እንደሆኑ በመግለፅ አብዮታዊው ኢህአዴግ ትችቱን ሲያቀርብ፤ በአሜሪካ የፖለቲካ ምርጫ ውስጥ የሶሻሊዝምና የኮሙኒዝም አማራጮች ጎልተው አለመታየታቸው የዲሞክራሲ እጦትን ያመለክታል ሲል ያናንቀዋል።

ለመሆኑ፤ ኮሙኒስት ፓርቲው ዘንድሮ በምርጫ ቢያሸንፍ፤ ህገመንግስቱን አፍርሶ የግለሰብ መብቶችን በመጣስ ንብረት ሊወርስ ነው? በሚቀጥለው ምርጫ ሪፐብሊካን ፓርቲ ሲያሸንፍ ደግሞ ህገመንግስቱን እንደገና አውጆ ንብረት ይመልሳል? ለነገሩ ህገመንግስቱ አንዴ በኮሙኒስት ፓርቲ ከፈረሰ፤ ከዚያ በኋላ ምርጫ የሚባልም አይኖርም። ኮሙኒዝም ከሰፈነማ ችግር የለም - “ለአብዮታዊው ኢህአዴግ”።

“ዲሞክራሲያዊው ኢህአዴግ” ብቅ ሲል ደግሞ፤ ይህን የሚያፈርስ ሌላ ሃሳብ ይናገራል። ጤናማ ፖለቲካ ባለበት አገር ውስጥ ሙሉ ለሙሉ የግለሰብ መብትን የሚፃረሩ አማራጮች ጎልተው አይወጡም የሚለው “ዲሞክራሲያዊው ኢህአዴግ”፤ ዋና ዋናዎቹ ፓርቲዎችና አማራጮች በመሰረታዊ መብቶችና ሃሳቦች ላይ የሚስማሙ ይሆናሉ በማለት ያስረዳል። ለምሳሌም፤ የአሜሪካዎቹ ዋና ዋና ፓርቲዎች (ሪፐብሊካንና ዲሞክራት ፓርቲዎች) ይጠቀሳሉ። በእርግፅ ሌሎች ፓርቲዎችም አሉ፤ የሚከለክላቸው የለም - ኮሙኒስት ፓርቲም ሳይቀር መንቀሳቀስ ይችላል። ግን፤ ብዙ ሰው ስለማይደግፋቸው በፉክክር ጎልተው አይወጡም። በሌላ አነጋገር፤ የዳበረ የዲሞክራሲ ባህል ባላቸው አገራት ውስጥ፤ የለስላሳ መጠጥና የመርዝ አማራጮች በፉክክር ጎልተው አይወጡም። የተለያዩ የለስላሳ መጠጥ አይነቶች ናቸው የሚፎካከሩት (ፔፕሲና ኮካ እንደማለት)። በአጭሩ፤ የሰከነ ጤናማ ፖለቲካ እንዲኖር፤ በመሰረታዊ መብቶች ላይ አገራዊ መግባባት ያስፈልጋል ይላል “ዲሞክራሲያዊው ኢህአዴግ”።

ለአብዮታዊው ኢህአዴግ፤ “አገራዊ መግባባት” ማለት፤ ሁሉም ፓርቲዎችና ዜጎች፤  በሁሉም ጉዳዮችና ውሳኔዎች ላይ፤ ኢህአዴግን እንዲከተሉና እንዲደግፉ ማድረግ ማለት ነው። በትምህርት ቤትና በሚዲያ፤ በመንግስትና በፓርቲ መዋቅር ሁሉ የኢህአዴግ ሃሳቦችን በመስበክ፤ በፕሮፖጋንዳ ዘመቻ ሌሎች ሃሳቦችን በመድፈቅ፤ ኢህአዴግን የሚቃረን ሃሳብ ጎልቶ እንዳይወጣ በማፈን፤ “አገራዊ መግባባት” ይመጣል ብሎ ያስባል።

መሰረታዊ ሃሳቦች ላይ ብቻ ሳይሆን እያንዳንዷ ፖሊሲና ውሳኔ ላይ፤ ሁሉም ዜጎች ሆ ብለው በድጋፍ እንዲጮሁ ይፈልጋል - “አብዮታዊው ኢህአዴግ”። “የዋጋ ቁጥጥር ጠቃሚ ነው” የሚል ፖሊሲ ሲያመጣ፤ ህዝቡ በእልልታ መደገፍ አለበት። “የዋጋ ቁጥጥር ጠቃሚ አይደለም” የሚል ፖሊሲ ሲያመጣም፤ ህዝቡ እልልታውን መቀጠል ይኖርበታል። “ሙስናን መቆጣጠር ችለናል” ሲል... መደገፍ፤ “ሙስና አሳሳቢ ሆኗል” ሲባልም ህዝቡ ድጋፉን መግለፅ ይጠበቅበታል። “ቢፒአር ስኬታማ ሆኗል” ሲባልም ሆነ፤ “ቢፒአር ዝርፊያን እንጂ ስኬትን አላስገኘም” ሲባል፤ ሁሉም ዜጋ ማጨብጨብ አለበት። ለአብዮታዊው ኢህአዴግ፤ አገራዊ መግባባት ማለት እንዲህ ነው። በቃ፤ የ”አገራዊ መግባባት” ይዘት፤ ለከት የለውም። በመሰረታዊ ሃሳቦች ላይ ብቻ ሳይሆን፤ በየጊዜው በሚለዋወጡ ውሳኔዎች፤ ፖሊሲዎችና አንቀፆች ላይ፤ ዜጎች “ተግባብተው” ድጋፍ መግለፅ ይኖርባቸዋል -  “ህዝባዊ ንቅናቄ” ይባል የለ? ይሄ እንግዲህ፤ ይዘቱ ነው። ዘዴውስ? “አገራዊ መግባባት” ለመፍጠር... ያው ዘዴዎቹ የታወቁ ናቸው - የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ፤ የኢኮኖሚ ጫና፤ የፖለቲካ አፈና... ወዘተ።

“ለዲሞክራሲያዊው ኢህአዴግ” ግን፤ አገራዊ መግባባት ማለት፤ በዝርዝር ውሳኔዎችና አንቀፆች ላይ ሳይሆን፤ በተወሰኑ መሰረታዊ ሃሳቦች ላይ ብቻ የሚያተኩር ነው። ለምሳሌ የስልጡን ፖለቲካ ዋነኛ መሰረታዊ ሃሳቦች ሶስት ናቸው - የግለሰብ መብት መከበር፤ የነፃ ገበያ መስፋፋት እና የህግ የበላይነት መስፈን። የዲሞክራሲ ዋነኛ መሰረተ ሃሳቦች ሶስቱ እንደሆኑ፤ በ1993 አም. በኢህአዴግ የታተመ የተሃድሶ መፅሃፍ ውስጥ በግልፅና በዝርዝር ተፅፏል። ያንን ፅሁፍ ስታነብቡ፤ ከ”ዲሞክራሲያዊው ኢህአዴግ” ተቆንጥሮ መፅሃፉ ውስጥ የገባ ፅሁፍ ነው ልትሉ ትችላላችሁ። ለዲሞክራሲያዊው ኢህአዴግ፤ “የአገራዊ መግባባት” ይዘት፤ በእነዚህ መሰረታዊ ሃሳቦች ዙሪያ የሚያጠነጥን ነው።

ሁሉም ሰው በመሰረታዊዎቹ ሃሳቦች መስማማት አለበት ማለት አይደለም። በመሰረታዊ ነጥቦች ዙሪያ፤ አብዛኛው ምሁርና ዜጋ ተቀራራቢና ተመሳሳይ አቋም ወይም ዝንባሌ ከያዘ፤ መሰረታዊዎቹ ሃሳቦች የበላይነት ተቀዳጅተዋል፤ በመሰረታዊዎቹ ሃሳቦች ላይ አገራዊ መግባባት ተፈጥሯል  ማለት ነው ይላል ዲሞክራሲያዊው ኢህአዴግ። የአገራዊ መግባባት ይዘት፤ በመሰረታዊ ሃሳቦች ዙሪያ የተገደበ ከሆነ፤ አገራዊ መግባባት ለመፍጠር የሚገለግል ዘዴስ ምን አይነት ነው? በመማማርና በውይይት፤ በክርክርና በፉክክር መሰረታዊዎቹን ሃሳቦች ማስተዋወቅ፤ ማብራራት፤ ትክክለኛነታቸውን ማሳየትና አብዛኛውን ሰው ማግባባት ነው ዋናው ዘዴ። ዘዴው፤ ከይዘቱ ይመነጫል። “የግለሰብ ነፃነት መከበር አለበት” የሚለው መሰረታዊ ሃሳብ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ማድረግ የሚቻለው፤ ለግለሰብ ነፃነት መከበር አስተዋፅኦ ባለው የሃሳብና የውይይት ነፃነት አማካኝነት ነው።

 

ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ህገመንግስት

ለ”አብዮታዊው ኢህአዴግ”፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ፀረህገመንግስት ፓርቲዎች ናቸው። ፀረህገመንግስት ማለት፤ ኢህአዴግን የሚተች ወይም የሚቃወም ማለት ነው። የህገመንግስት አንቀፆች ላይ ቅሬታ ያለውና ለማሻሻል የሚፈልግ ሰው ሁሉ ፀረህገመንግስት ተብሎ ይፈረጃል። ተቃዋሚ ፓርቲዎች ህገመንግስቱን ተጠቅመው ስልጣን መያዝና ህገመንግስቱን መለወጥ ይፈልጋሉ በማለት ያወግዛቸዋል - “አብዮታዊው ኢህአዴግ”።

“ዲሞክራሲያዊው ኢህአዴግ” በበኩሉ፤ ህገመንግስቱንም ሆነ ኢህአዴግን መቃወም ወንጀል ነው እንደማይል ይናገራል። ማንኛውም ዜጋና ፓርቲ፤ ህገመንግስቱን በሃይል እስካልጣሰ ድረስ፤ ህገመንግስቱን መቃወምና ለማሻሻል መጣር ወይም ኢህአዴግን መቃወምና በምርጫ ለማሸነፍ መትጋት መብቱ ነው የሚለው “ዲሞክራሲያዊው ኢህአዴግ”፤ በጠመንጃና በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን ለመያዝ የሚሞክሩ ወገኖች ፀረህገመንግስት ናቸው ይላል። ከዚህ ውጭ፤ ስርአት በተከተለ መንገድ ህገመንግስቱን ማሻሻልና አንቀፆችን መለወጥማ እኔም እፈልገዋለሁ ይላል - “ዲሞክራሲያዊው ኢህአዴግ”።

 

ኪራይ ሰብሳቢና ልማታዊ፤ ጥገኛና ትርፋማ

አብዮታዊው ኢህአዴግ፤ “በመንግስት ግዙፍ ጣልቃ ገብነት አማካኝነት ካልሆነ በስተቀር ልማት አይመጣም” ይላል። የግል ቢዝነስና የግል ኢንቨስትመንት አላማ ትርፍ ላይ ያነጣጠረ ስለሆነ ልማት ላይ አያተኩሩም የሚለው አብዮታዊው ኢህአዴግ፤ ነጋዴዎችን ኪራይ ሰብሳቢ ይላቸዋል። ለአብዮታዊው ኢህአዴግ፤ ኪራይ ሰብሳቢ ማለት፤ ድሮ “በዝባዥ፤ ቡርዧ” ከሚባለው ጋር ተመሳሳይ ነው። ባለ ፋብሪካዎች፤ በዝባዥ ቡርዧ ተብለው ይወገዙ አልነበር? አሁን ደግሞ ኪራይ ሰብሳቢ ይባላሉ።

በኢንቨስትመንት አማካኝነት ትርፍ ማግኘት፤ ያለ ስራ ገንዘብ እንደማግኘት ሆኖ ይታየዋል ለ”አብዮታዊው ኢህአዴግ”። ...ህንፃ ከገነባ በኋላ ቁጭ ብሎ ሳይሰራ ኪራይ መሰብሰብ፤ ...ባንክ ከፍቶ ዝም ብሎ ወለድ መሰብሰብ፤ ...ፋብሪካ ከፍቶ፤ እንዲሁ አንዲት ብሎን ሳያጠብቅ ዝም ብሎ ትርፍ መሰብሰብ፤ ...አንዴ ድርሰት አሳትሞ፤ የሙዚቃ አልበም ወይም ፊልም ሰርቶ፤ “ኮፒ ራይት” እያለ ለአመታት ትርፍ መሰብሰብ ... ይሄ ሁሉ “ለአብዮታዊው ኢህአዴግ” ኪራይ ሰብሳቢነት ነው። እናም፤ በመንግስት ጣልቃ ገብነት፤ ኪራይ ሰብሳቢነትን አጠፋለሁ፤ ልማታዊ ሰራዊትን እፈጥራለሁ ይላል። ለዚህም፤ መንግስት ትልልቅ ኮርፖሬሽኖችን በማቋቋም የቢዝነስ ስራ ውስጥ መግባት አለበት፤ እንዲህ አይነቱ “የመንግስት ጣልቃ ገብነት” ሁሌም ያስፈልጋል፤ እናም የሁልጊዜ ግቡ ነው - “ለአብዮታዊው ኢህአዴግ”። የግል ቢዝነስ ግን፤ መሳሪያ ነው። ለመንግስት ጣልቃ ገብነት የሚያስፈልግ በቂ ታክስና ግብር የሚገኘው ከየት ነው? ከግል ቢዝነስ። የግል ቢዝነስ ማለት የምትታለብ ላም ማለት ነው።

ይህን የሚቃረን ደህና አስተሳሰብ የምንሰማው፤ “ዲሞክራሲያዊው ኢህአዴግ” ከእንቅልፉ የባነነ ጊዜ ነው። ቢዝነስ ውስጥ የመንግስት ጣልቃ ገብነት ሲስፋፋ፤ ሙስናና የሃብት ብክነት አብሮ ይንሰራፋል እያለ ሲፅፍና ሲያስነብብ የነበረው “ዲሞክራሲያዊው ኢህአዴግ”፤ በነፃ ገበያ ስርአት ውስጥ ምርታማ ሰዎች በአትራፊነት እየበለፀጉ አገርንም ያሳድጋሉ በማለት ያስረዳል። መንግስት፤ ኢኮኖሚና ቢዝነስ ውስጥ ጣልቃ ሲገባ ግን፤ ምርታማ ሰዎች አትራፊ አይሆኑም። ምርታማ ያልሆኑ ሰዎች ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር በሚፈጥሩት የአድልዎና የሙስና መረብ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ያገኛሉ፤ በጥረታቸው ሳይሆን የመንግስትን ስልጣን መከታ በማድረግ ይበለፅጋሉ፤ የመንግስት ጥገኛ ናቸው ሲልም ዲሞክራሲያዊው ኢህአዴግ ትንታኔ ያቀርባል።

እንዲህ ለማብራራት ሲሞክር የሚታየው “ዲሞክራሲያዊው ኢህአዴግ”፤ ቢዝነስ ውስጥ መንግስት ጣልቃ ሲገባ ጥገኝነትና ኪራይ ሰብሳቢነት ይስፋፋል በማለት የነፃ ገበያ ስርአት እንደሚያስፈልግ ይገልፃል። ለዲሞክራሲያዊው ኢህአዴግ፤ ምርታማነትና ትርፋማነት መልካም ተግባር ነው። ኪራይ ሰብሳቢ አያስብልም። ያለ መንግስት ጣልቃ ገብነት በአለም ገበያ ተወዳዳሪና አትራፊ መሆን የሚችሉ ቢነዝነሶች መፈጠር አለባቸው የሚለው ዲሞክራሲያዊው ኢህአዴግ፤ የግል ቢዝነስ ዋነኛ የኢኮኖሚ እድገት ሞተር ስለሆነ እንደዋነኛ ግብ መቆጠር እንዳለበት ያመለክታል። በእርግጥ የመንግስት ጣልቃ ገብነትን፤ በአንዴ ማስወገድ ስለማይቻል ቀስ በቀስ የሚወገድ ጊዜያዊ መሳሪያ እንደሆነ የሚገልፀው “ዲሞክራሲያዊው ኢህአዴግ”፤ የግል ቢዝነስ ግን ዘላቂ ግብ እንደሆነ ይናገራል።

አብዮት እና ዲሞክራሲ

ሁለቱ ኢህአዴጎች፤ “አብዮት” እና “ዲሞክራሲ” በሚሉት ቃላት ሳይቀር አቋማቸው ይለያያል። ለአብዮታዊው ኢህአዴግ፤ ከመነሻው “ዲሞክራሲ” ማለት፤ ወደ ሶሻሊዝም መሸጋገሪያ ድልድይ ማለት ነው - ህዝቡን ለሶሻሊዝም ለማዘጋጀት የሚያገለግል መሳሪያ። የአብዮታዊው ኢህአዴግ አላማ፤ እንዲሁ ዲሞክራሲን አስፍኖ መቀመጥ አይደለም።

ዲሞክራሲን እየጠበቁና እያሳደጉ መቀጠል አይደለም። ዲሞክራሲው አብዮተኛ መሆን አለበት ይላል - አብዮታዊው ኢህአዴግ። በሌላ አነጋገር፤ “ዲሞክራሲ የስር ነቀል ለውጥ መሳሪያ መሆን አለበት - ወደ ሶሻሊዝም ለመሸጋገር”። ዲሞክራሲያዊው ኢህአዴግ ግን፤ ዲሞክራሲ ራሱን የቻለ ግብ እንደሆነ ሲናገር ይደመጣል።

የግል ነፃነት፤ ነፃ ገበያና የህግ የበላይነት የሰፈነበት ስርአት (ማለትም የዲሞክራሲ ስርአት) መገንባት፤ የመጨረሻ ግብ ነው። “አብዮት” ማለት ደግሞ፤ ለዲሞክራሲ ግንባታ የሚያገለግል መሳሪያ ነው። ከኋላቀር ባህልና አስተሳሰብ ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ለመሸጋገር ስር ነቀል ለውጥ ማካሄድ ያስፈልጋል። አብዮት ማለት ወደ ዲሞክራሲ የሚያሸጋግር ስር ነቀል ለውጥ ማለት እንደሆነ “ዲሞክራሲያዊው ኢህአዴግ” ይናገራል።

 

 

 

Read 4299 times Last modified on Saturday, 17 March 2012 09:21