Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Wednesday, 04 April 2012 07:18

ዘመኑ፤ የእድገት ወይስ የስደት ዘመን?

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ባህል ላይ አንዳች የተለወጠ ነገር፤ ኢኮኖሚው ላይ አንዳች የተጣመመ ነገር አለ

በአንድ አመት፤ ሩብ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ወደ የመን እና ወደ ሳውዲ

የመንግስት አቋም - (በመግለጫ) - ኢኮኖሚው አድጓል፤ ድህነት ቀንሷል

የብዙ ዜጎች አቋም - (በስደት) - የኑሮ ውድነት ብሶበታል፤ ድህነት መሯል

በአይኦኤም እርዳታ በአመት ውስጥ ከየመን የተመለሱት ኢትዮጵያውያን ቁጥር 7 ሺ ነው። ወደ አገራቸው ተመልሰው ለመምጣት መፈለጋቸው አይገርምም። በተለይ ከየመን ወደ ሳውዲ አረቢያ መሸጋገሪያ በሆነችው ሃራድ አካባቢ፤ ስደተኞቹ የሚያዩት እንግልትና ግፍ “አያድርስ” ነው።

ድህነት ያዋርዳል

በየመን በሺ የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ስደተኞች፤ የሚላስ የሚቀመስ ምግብ ፍለጋ፤ መንገድ ለመንገድ የወዳደቁ ነገሮችን ይለቃቅማሉ። በወባና በተቅማጥ በሽታ የሚሰቃዩት ስደተኞች፤ መጠለያ በሌለበት አውላላ በረሃ ላይ ሲተኙ በእባብ ተነድፈው ይሞታሉ። ከዚህ ሁሉ የሚከፋው አደጋ ግን፤ በወሮበላ ቡድኖች የሚፈፀመው የግፍ አይነት ነው - ለወራት ማገትና መደብደብ፤ አይን ማጥፋትና አስገድዶ መድፈር...። የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ተወካይ እንደሚሉት፤ በሃራድ አካባቢ አብዛኞቹ ሴቶች የወሲብ ጥቃት ደርሶባቸዋል።

“ድንበር እናሻግራለን” የሚሉ ደላሎችና ወሮበላ ቡድኖች፤ በየጊዜው ስደተኞችን አግተው እንደሚይዙ የኮሚሽኑ ተወካይ ገልፀው፤ በዚህ አመት ታግተው ከነበሩት 3ሺ ስደተኛ ሴቶች መካከል አብዛኞቹ የወሲብ ጥቃት እንደተፈፀመባቸው ለኢሪን ተናግረዋል። እገታው፤ ለጥቂት ቀናት ወይም ለሳምንታት ብቻ አይደለም። እርቃናቸውን በአነስተኛ ክፍል የታጨቁት ስደተኞች ለበርካታ ወራት በድብደባና በረሃብ ይሰቃያሉ። ብዙዎቹ ሴቶች በተደጋጋሚ ይደፈራሉ።

አጋቾቹ ወረበሎች፤ ከድሆቹ ስደተኞች ገንዘብ ሳያገኙ አይለቋቸውም። አስገድዶ የመድፈር የወሲብ ጥቃትንም የማሰቃያ ዘዴ አድርገውታል ይላሉ - የኮሚሽኑ ተወካይ። ስደተኞች፤ ቤተሰቦቻቸው ዘንድ ስልክ ደውለው ገንዘብ እንዲያስልኩ ይደበደባሉ፤ ቀን ከሌት ይሰቃያሉ። ለስምንት ወራት ያህል የእገታ ስቃይ የበዛባቸው አንዳንድ ስደተኞች፤ እስከ 5ሺ ዶላር የሚደርስ ገንዘብ ከቤተሰቦቻቸው ለማስላክ እንደተገደዱ የተመድ የዜና አውታር ኢሪን ዘግቧል።

በተለያዩ አካባቢዎች፤ በረዥም ግንብ የታጠሩ ቤቶች ለእገታ እንደሚያገለግሉ የጠቀሰው ኢሪን፤ ከእገታ ባመለጠ ስደተኛ ጠቋሚነት የተገኘው ውጤት የአካባቢውን ፖሊሶች እንዳስደነገጠ ገልጿል። ፖሊሶች በጥቆማው መሰረት ሲሄዱ፤ ወሮበሎቹ በቀላሉ እጅ የሚሰጡ አልሆኑም። ፖሊሶች ተታኩሰው ነው ወደ ቤቱ የገቡት። አስደንጋጩ ነገር ይሄ አይደለም። ቤቱ ውስጥ የተገኙት 70 ስደተኞች፤ በድብደባና በረሃብ የተጎሳቆሉ ከመሆናቸውም በተጨማሪ፤ ከውስጥ ልብስ በስተቀር እራቁታቸውን ናቸው። አንዳንዶቹ አይናቸው ጠፍቷል፤ አንዳንዶቹ እጃቸው ተሰብሯል። ከድህነት የመነጨ የሰው ውርደት!

የብዙዎቹ ስደተኞች ህልም፤ ወደ ሳውዲ አረቢያ መሻገር ቢሆንም፤ እንግልትና ግፍ የበዛባቸው የተወሰኑ ስደተኞች ወደ አገራቸው መመለስ ይመኛሉ። ግን፤ መመለሻ ገንዘብ የላቸውም። ብቸኛ ተስፋቸው አለማቀፉ የሚግሬሽ ተቋም አይኦኤም ነው። ከተለያዩ መንግስታትና ድርጅቶች በሚያገኘው ገንዘብ፤ ወደ አገር መመለስ የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን በአውሮፕላን ሲያጓጉዝ የቆየው አይኦኤም፤ ሰሞኑን በገንዘብ እጥረት ሳቢያ የማጓጓዝ ስራውን ለማቋረጥ ተገዷል። ችግሩ ይሄ ብቻ አይደለም።

 

የየመን የስደት ጎርፍ (ከ17ሺ ወደ 100ሺ)

በአመት ውስጥ 7ሺ ገደማ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን በአይኦኤም እርዳታ ከየመን ቢመለሱም፤ በዚሁ ጊዜ በራሳቸው ወጪ ወደ የመን የተጓዙት ስደተኞች ቁጥር ከአስር እጥፍ በላይ ይበልጣል። እስከ ታህሳስ ወር ድረስ ባለው የአንድ አመት ጊዜ፤ ከ75ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን ወደ የመን እንደገቡ የዩኤን የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ገልጿል። የመን፤ በፖለቲካ ቀውስና በግጭት ብትታመስም፤ የጉዞው አደጋና ስቃይ ቢዘገንንም፤ የስደቱ ጎርፍ ጨመረ እንጂ አልቀነሰም።

እንደ ድሮው ቢሆን ኖሮ፤ አስተማማኝ ባልሆኑ ጀልባዎች ታጭቀው፤ የሞት ሞታቸውን አደገኛውን የባህር ጉዞ አቋርጠው፤ ወደ የመን ጠረፎች የሚደርሱት ስደተኞች፤ በአብዛኛው ሶማሊያዊያን ነበሩ። በ2000 ዓ.ም፤ ወደ የመን ከገቡት ሃምሳ ሺ ያህል ስደተኞች መካከል 33ሺዎቹ ሶማሊያውያን ናቸው፤ 17ሺ ያህሉ ደግሞ ኢትዮጵያውያን።

ከአንድ አመት በኋላ ግን፤ ከሶማሊያዊያን ስደተኞች ይልቅ፤ የኢትዮጵያዊያን ቁጥር መብለጥ ጀመረ። በ2002 ዓ.ም ደግሞ፤ የኢትዮጵያውያን ስደተኞች ብዛት ከሶማሊያዊያን መብለጥ ብቻ ሳይሆን፤ ጭራሽ እጥፍ ያህል ሆኗል። በዚያው አመት ከ53ሺ በላይ ስደተኞች የመን እንደደረሱ የሚገልፀው የኮሚሽኑ መረጃ፤ 18ሺዎቹ ሶማሊያዊያን፤ 34ሺ ያህሉ ደግሞ ኢትዮጵያውያን እንደሆኑ ያስረዳል።

በአረብ አገራት የተከሰተው የፖለቲካ ቀውስ፤ የስደተኞችን ጎርፍ ሊገታ ይችላል ወደ ሚል ግምት ሊገፋፋን ይችላል። ከስጋት የተነሳ፤ ብዙ ሰዎች የስደት ሃሳባቸውን ቢለውጡ አይገርምም። በተግባር የታየው ግን ሌላ ነው። አምና በ2003፤ የመን እንደ በርካታዎቹ የአረብ አገራት በፖለቲካ ቀውስና በግጭት ብትታመስም፤ የኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ቁጥር በእጥፍ ጨምሯል። እስከ ዘንድሮው ታህሳስ ወር ባለው የአንድ አመት ጊዜ ውስጥ፤ ከ75ሺ በላይ የኢትዮጵያ ስደተኞች፤ በተለያዩ የባህር ጠረፎች በኩል ወደ የመን ገብተዋል። የሶማሊያ ስደተኞች ደግሞ 27ሺ።

በዚህም አላበቃም። የኮሚሽኑ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ባለፈው የካቲት ወር ብቻ ወደ 10500 የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ወደ የመን ገብተዋል። የካቲት፤ ልዩ ወር ስለሆነ አይደለም። የስደተኞች ብዛት በየአመቱ እየጨመረ ስለመጣ ነው። ካለፈው አመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ማነፃፀር ይቻላል። አምና በየካቲት ወር፤ የየመንን መሬት የረገጡ ኢትዮጵያዊያን 8ሺ ናቸው። በዘንድሮው የካቲት ወር ግን፤ የስደተኞቹ ቁጥር በሰላሳ በመቶ ጨምሯል። የስደት ጉዞው በዚሁ ከቀጠለ፤ በአመት ውስጥ ወደ የመን የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር 100ሺ ገደማ ሊሆን ይችላል።

የምዝገባ ስደትም ጨምሯል (ከ20ሺ ወደ 150ሺ)

የስደተኞችን እንግልትና ስቃይ ለመቀነስ ያስችላል ተብሎ፤ በመንግስት በኩል እየተመዘገበ የሚካሄደው የስደት ጉዞ ከአመት አመት እየጨመረ ነው። በ2001፤ በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ተመዝግበው ወደ ተለያዩ የአረብ አገራት የሄዱ ኢትዮጵያውን፤ ወደ 20 ሺ ገደማ ነበሩ (በግማሽ አመት አስር ሺ መሆኑ ነው)። ያ ቁጥር፤ ዛሬ በስምንት እጥፍ ጨምሯል። ዘንድሮ በስድስት ወራት ውስጥ ብቻ፤ ከ80ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን በሚኒስቴሩ ተመዝግበው ወደ ሁለት የአረብ አገራት ሄደዋል። በዚሁ ከቀጠለ፤ በአመት የስደተኞቹ ቁጥር ከ150ሺ በላይ ይሆናል።

ሌላ ሌላው ሳይቆጠር፤ ወደ የመን እና ወደ ሳውዲ አረቢያ፤ በህጋዊና በህገወጥ መንገድ የሚሰደዱት ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከ250ሺ በላይ ሊሆን ይችላል ማለት ነው። በኬንያ፤ በታንዛኒያና በኡጋንዳ በኩል፤ ወደተለያዩ የደቡብ አፍሪካ አገራት የሚደረገው ስደት ሲጨመርበት ምን ያህል እንደሚሆን መገመት ያስቸግራል። ወደ ሱዳን፤ በዚያም ወደ ግብፅ እና እስራኤል፤ እንዲሁም ወደ ሊቢያና ጣልያን የሚሰደዱትም፤ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ናቸው። ይሄ ሁሉ ሳይቆጠር፤ በአመት ውስጥ፤ ወደ የመንና ሳውዲ አረቢያ ብቻ ሩብ ሚሊዮን የኢትዮጵያ ስደተኞች የሚጎርፉ መሆናቸው ያስደነግጣል። ኢትዮጵያ ውስጥ ምን ያህል አስከፊ ችግር ቢኖር ነው?

የተለወጠ ባህል፤ የተጣመመ ኢኮኖሚ

አደገኛው የስደት ጉዞ፤ እንዲህ የተባባሰበት ምክንያት ምንድነው? “ድንበር እናሻግራለን” የሚሉ ደላሎችና ቡድኖች፤ የተወሰነ ያህል ተፅእኖ ይኖራቸው ይሆናል። ነገር ግን፤ ደላሎች ይሄን ሁሉ ወጣት ማታለል ይችላሉ ብለን ካሰብን የዋህነት ተጠናውቶናል ማለት ነው። አለበለዚያ ደግሞ፤ “የከፋ ችግር የለም” እያልን ራሳችንን ለማታለል እየሞከርን መሆን አለበት።

በጥንታዊ “ባህል”፤ ከቀዬው ከሰፈሩ መራቅ የማይወድ ህዝብ በበዛበት አገር ውስጥ፤ እንዲህ በመቶ ሺ የሚቆጠር ወጣት ወደ ውጭ እንዲጎርፍ የሚያስገድድ ምን መአት ተፈጠረ? የአገሬው ባህል ላይ፤ አዲስ የተፈጠረ ወይም የተለወጠ ነገር መኖር አለበት።

መቶ ሺ ወጣቶች፤ ሰላም የሆነችውን አገር እየለቀቁ፤ ሽብርና ጦርነት ባተራመሳት ሶማሊያ በኩል፤ የፖለቲካ ቀውስና ግጭት ወዳናወጣት የመን ለመጓዝ የሚገደዱት ለምንድነው? ኑሮንና ህይወትን የምንመለከትበት አስተሳሰብ ካልተለወጠ በቀር፤ ሰላም ካለበት አገር እየለቀቁ፤ ግጭትና ጦርነት ወዳለበት አገር እንዴት ስደት ይበረክታል?

“የአገሪቱ ኢኮኖሚ እያደገ ነው፤ ድህነት እየቀነሰ ነው” በሚባልበት ወቅት፤ ምነው የአገራችን ወጣቶች ስደትን መረጡ? የኢኮኖሚው አይነትና የድህነቱ መልክ ላይ አንዳች የተሳሳተ ወይም የተጣመመ ነገር አለ።

አሳሳቢ ጥያቄዎች ናቸው - ፓርቲዎችና መንግስት፤ ዜጎችና ምሁራን ቆም ብለው ሊመረምሯቸው የሚገቡ አሳሳቢ ጥያቄች። እንደሚመስለኝ፤ የአገሬው ባህልና የአስተሳሰብ አዝማሚያ ላይ ከመጣው ለውጥ ጋር፤ የአገሬው የተጣመመ ኢኮኖሚና ድህነት አልጣጣም ማለታቸው፤ ለስደት ጎርፍ ዋና መንስኤ ሆነዋል።

በእርግጥ፤ መሰረታዊው የአገራችን ኋላቀር ባህልና አስተሳሰብ፤ ያን ያህልም አልተለወጠም ማለት ይቻላል። ጥንታዊው የአገራችን ባህል፤ ዛሬም እንደድሮው፤ ለሳይንስ፤ ለግል ማንነት፤ ለግል ብልፅግና፤ ለግል ነፃነት ብዙም ክብር አይሰጥም። ባህላችን፤ ከስረመሰረቱ አልተቀየረም፤ እንደድሮው ነው። ነገር ግን፤ የአገራችን ኋላቀር ባህል፤ ስረመሰረቱንና አስኳሉን ይዞ እንደጥንቱ እየቀጠለ ቢሆንም፤ ዳርዳሩን መቀየሩ አልቀረም። እንዴት በሉ።

 

ወጣ ወጣ ብሎ መሞከር

እንግዲህ፤ አገራችን ውስጥ፤ በሳይንስ ሳይሆን፤ በጭፍን እምነትና በጭፍን ልማድ መነዳት የተለመደ ነው - እንደድሮው። በግል ማንነት ከመቆም ይልቅ፤ በቀዬና በትውልድ ቦታ፤ በብሄር ብሄረሰብ ወይም በጭፍን እምነት የመቧደን አባዜ አልለቀቀንም። ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን ልማድ በጭፍን ተቀብሎ፤ በዚያው ቀዬ መኖር እንጂ፤ ነገሮችን በግል እንደ አዲስ መመርመርና መሞከር፤ ለአገራችን ብርቅ ነው።

ቢሆንም ግን፤ በሳይንስና በግል ማንነት ዙሪያ፤ የአገራችን ባህል ዳርዳሩን እየተለወጠ መጥቷል። በጥንቱ ልማድ የትውልድ ቀዬ ውስጥ “ከወገን ጋር” አብሮ በችጋር ከመኖር ይልቅ፤ የቀዬን ልጆች ተከትሎ መሰደድ እየተበራከተ ነው። በእርግጥ፤ በጭፍን የቀዬን ልጆች ተከትሎ መሰደድ፤ መሰረታዊ የባህል ለውጥ አይደለም። ነገር ግን ከወገን ተነጥሎ፤ ከቀዬ ወጣ ወጣ ብሎ የማየትና የመሞከር አዝማሚያ ተስፋፍቷል። እንዲህ አይነቱ የለውጥ ዳርዳርታ፤ በቀላሉ የሚቆም አይመስለኝም - ከግሎባላይዜሽን ጋር የተያያዘ በመሆኑ። የሞባይል ስልክን ብቻ ማየት ይቻላል። ከጣልያንም ሆነ ከየመን፤ ከደቡብ አፍሪካም ሆነ ከእስራኤል፤ የኢትዮጵያ የገጠር ቀዬ ድረስ መልእክት ለማስተላለፍ፤ እንደድሮ ከባድ አይደለም።

በእርግጥ፤ ከወገን ተነጥሎ ወጣ ወጣ ብሎ የማየትና የመሞከር አዝማሚያ፤ ለብቻው አልተስፋፋም። በግል ብልፅግናና በግል ነፃነት ዙሪያ ካለን ባህል ጋር የተሳሰረ ነው። እነዚህ ነጥቦች ላይስ ምን አይነት ለውጥ አለ?

 

ድህነትን ከመጋራት፤ ኑሮን ማሻሻል

የአገራችን ባህል፤ ለብልፅግናና ለነፃነት ክብር የለውም። የበለፀጉ ሰዎችን ከመመቅኘትና ከመጥላት ጋር፤ ድህነትንና ምናኔን የማድነቅ ወግ፤ አሁንም አልቀረም። ከቤተሰብ ጀምሮ፤ በሰዎች የእርስ በርስ ግንኙነት ውስጥ፤ ከመርገጥና ከመረገጥ ውጭ፤ የመከባበር አማራጭ የማይታይበት ኋላቀር ባህል፤ ዛሬም ከኛው ጋር ነው። “ለአገር ጥቅም፤ ለህዝብ ፍላጎት” በሚል ሰበብ የግል ነፃነትን መጣስ፤ ዛሬም ድረስ የአገራችን የዘወትር አኗኗር እንደሆነም አያከራክርም። የባህላችን ስረመሰረት፤ ከድሮው አልተለወጠም። ነገር ግን፤ ጫፍጫፉን አንዳንድ ለውጦች ብቅ ብቅ ብለዋል።

ለብልፅግና መንፈሳዊ ክብር የመስጠት፤ እንዲሁም “የብልፅግና ዋናው መሰረት ምንድነው?” ብሎ ምላሽ ለማግኘት የመጣጣር ባህል ባይፈጠርም፤ በረሃብ እስኪሞቱ ድረስ እግር አጣጥፎ የመቀመጥ ድንዛዜ እየቀነሰ መጥቷል። እንደ ጥንቱ ድህነትን አሜን ብሎ የመቀበል ስሜት ተሸርሽሯል።

የግሎባላይዜሽ ዘመን አይደል? እንደ ድሮው በወሬ ወሬ ብቻ ሳይሆን፤ በኢንተርኔት፤ በቲቪ ቻናል፤ በሞባይል ጭምር፤ የሰዎችን ኑሮ በቅርበትና በስፋት ማየት እየተቻለ ነው። ሌሎች ሰዎች የበለፀገ ኑሮ እንደሚኖሩ የሚመለከት የአገሬ ሰው፤ እንደ ድሮው በድንዛዜ ባህል ውስጥ የመቆየት ፍላጎቱ ቢቀንስ ምኑ ይገርማል? “ለወገን፤ ለአገር፤ ለህዝብ ጥቅም” በሚል ሰበብ፤ በድህነት ታፍኖ የመኖር ፍቃደኝነቱም ይሳሳል። በተቃራኒው፤ “እንደ ሌላው የቀያችን ሰው”፤ “እንደ ሌላው አለም”፤ ኑሮውን ለማሻሻል ቢያንስ ቢያንስ እግሩን ያንቀሳቅሳል - አማራጭ ካጣም፤ አገሩን፤ ህዝቡንና ወገኑን ጥሎ ይሰደዳል።

 

የተጣመመ ኢኮኖሚ ወደ ስደት

በእርግጥ፤ ከላይ የጠቀስኳቸው የባህል “የዳርዳርታ” ለውጦች፤ የግድ ስደትን ያስከትላሉ ማለት አይደለም። ኑሮን በማሻሻል ላይ ያነጣጠሩ ናቸው፤ ለውጦቹ። እነዚህን ለውጦች፤ በአግባቡ ሊያስተናግድ የሚችል የኢኮኖሚ ሁኔታ በአገራችን ውስጥ ቢኖርና ቢስተካከል ኖሮ፤ ያን ያህልም የስደት ጎርፍ አይፈጠርም ነበር። የአገራችን ኢኮኖሚ ግን ከመስተካከል ይልቅ፤ እየተጣመመ መጥቷል።

የኢኮኖሚ እድገት ተመዝግቧል ይባላል። አዎ፤ ተመዝግቧል። ነገር ግን፤ መንግስት የሚወስደው ድርሻ ከአመት አመት እየጨመረ፤ በዚያው ልክም የሃብት ብክነትና ሙስና እየሰፋ ስለመጣ፤ የብዙ ዜጎች ኑሮ አልተሻሻለም። የጠማማው ኢኮኖሚ አንድ ገፅታ ምን መሰላችሁ? ያ የምታውቁት የኑሮ ውድነት።

በመንግስት የሚፈፀመው፤ ከልክ ያለፈ የገንዘብ ህትመትና ስርጭት፤ ዋነኛው የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ምንጭ ነው። የዋጋ ንረት፤ መነሻውንና ውጤቱን ካየን፤ ታክስና ግብር ከመጨመር ጋር ይመሳሰላል። መንግስት፤ ከዜጎች ሃብት የሚወስድበትና በኢኮኖሚው ውስጥ ድርሻውን የሚያሳድግበት ዘዴ ነው - የዋጋ ንረት።

ይሄውና እንደምታዩት፤ የዋጋ ንረቱና የኑሮ ውድነቱ አልረገበም። ዘንድሮም ልክ እንደአምናው ከጥር ወር ወዲህ፤ የዋጋ ንረት ብሶበታል። ካለፈው አመት ጋር ሲነፃፀር፤ በየካቲት ወር የምግብ ሸቀጦች ዋጋ በ50 በመቶ ገደማ ጨምሯል። አምና 200 ብር ይፈጅብን የነበረ የምግብ ሸቀጥ ዘንድሮ፤ 300 ብር ይፈጅብናል። በሌላ አነጋገር፤ አምና ሶስት ኪሎ በምንገዛበት ገንዘብ፤ ዘንድሮ ሁለት ኪሎ ብቻ እንገዛበታለን። አንዱ ኪሎ የት ሄደ? በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የመንግስት ድርሻ ሆኗል። የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት፤ ከተጨማሪ ታክስ ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ የሚገለፀውም በዚህ ምክንያት ነው።

በእርግጥ፤ መንግስት ይህንን የሚፈፅመው፤ “ለአገር ልማት”፤ “ለኢኮኖሚ እድገት”፤ “ለህዝብ ጥቅም”፤ “ለድህነት ቅነሳ”፤ “ለፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል” በማሰብ እንደሆነ መነገሩ አይቀርም። ነገር ግን፤ በኑሮ ውድነት ዜጎችን የሚቀጣ “የአገር ልማት”፤ እንደ ድሮው “አሜን” ብለው የሚቀበሉ ዜጎችን አያገኝም። ከአፍ ጉርሻ ነጥቆ ለሌላ የሚያጎርስ “የድህነት ቅነሳ”፤ ወይም ዜጎችን በድህነት የሚያቀራርብ “የሃብት ክፍፍል”፤ ...የድሮው ያህል ተቀባይነት የላቸውም። ከዘመኑ “የባህል ለውጥ ዳርዳርታ” ጋር አይጣጣሙም። ታዲያ፤ በኑሮ ውድነት ከመቀጣት፤ ወይም በድህነት እኩል ሆኖ ከመኖር ይልቅ፤ በርካታ ዜጎች በስደት “እድላቸውን” ለመሞኮር ቢጎርፉ ይገርማል?በአጭሩ፤ የነገሮች አለመጣጣም፤ ስደትን አስፋፍቷል። በአንድ በኩል፤ ኑሮን በማሻሻል ላይ ያነጣጠረ “የባህል ለውጥ ዳርዳርታ” አለ። በሌላ በኩል ደግሞ፤ በአለም ደረጃ በኑሮ ውድነት ግንባር ቀደም እየሆነ የመጣ “ጠማማ ኢኮኖሚ” አለ። እነዚህ ሁለቱ፤ አብረው ሊሄዱ የሚችሉ አይደሉም።

 

 

Read 1938 times Last modified on Wednesday, 04 April 2012 07:27

Latest from