Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 21 April 2012 15:49

የመጠጥ ውድድር በኢቲቪ?

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ባለፈው ሳምንት እሁድ፤ ከሃዋሳ በኢቲቪ የቀረበው የአመት በአል መዝናኛ ጣፋጭ ነበር። በምሳ ሰአት የተሰራጨው መዝናኛ፤ ከድምፅ ጥራትና ከቅንብሩ ጀምሮ፤ በብዙ ነገሩ ተዋጥቶለታል ማለት ይቻላል ... መጨረሻው ላይ ተበላሸ እንጂ። በአንድ ትንፋሽ  ቢራውን ቀድሞ የጨለጠ ይሸለማል ተብሎ ሆይሆይታ ሲፈጠር፤ አይኔን ማመን አልቻልኩም። የማስታወቂያ ሆይሆይታውን የሚመሩና የሚያዳምቁ የኢቲቪ ጋዜጠኞች መሆናቸው ነው የገረመኝ። በጭራሽ ከጋዜጠኛ የማይጠበቅ ነገር ነዋ።

በነገራችን ላይ፤ በዚህ ግርድፍ ማስታወቂያ ቅር የተሰኘሁት፤ ኋላቀርነትን እንደሚያመልኩ ወገኞች ለመሆን ስላሰብኩ አይደለም። ከሶሻሊዝም አባዜ መላቀቅ እንዳቃታቸው ቀሽም “አብዮተኞች”፤ የማስታወቂያ ጥላቻ የለብኝም። እንዲያውም ማስታወቂያን ጨምሮ ሌሎች “የማርኬቲንግ” ስራዎችን በጣም አከብራለሁ። የስልጣኔ ውጤት ነው። የመዝናኛ ዝግጅቱ፤ “መጨረሻ ላይ ተበላሸ” ያልኩትም፤ የቢራ ምርቶችን ዝቅ አርጌ በማየት አይደለም። ሰዎች በየስራ መስካቸው በሚያካሂዱት ጥረትና በምርታቸው መኩራት እንደሚገባቸው አውቃለሁ። የቢራ ምርትም እንደዚያው ነው።

“...ፋብሪካው የሁላችንም ነው፤ ቢራውን እየጠጣችሁ የምታጠናክሩትና ለአገር ኢኮኖሚ አስተዋፅኦ የምታደርጉት እናንተ ናችሁ ...” እየተባለ በፕሮግራሙ ጣልቃ ሲነገር ሰምታችሁ ይሆናል። ጥሩ፤ ቢራ አምራቹ ተቋም እንዲህ ብሎ ቢናገር መብቱ ነው። ምናልባት በዚህ አባባል የማይስማሙ ሊኖሩ ይችላሉ።  አለመስማማት መብታቸው ነው። ለሌላ የስራና የምርት መስክ ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጡ ከሆነም መብታቸው ነው።

ነገር ግን፤ የምርታማነት ፋይዳ፤ አንዳች ድብቅ ሚስጥር አይደለም። በቃ፤ ሰው የሚወደውንና የሚስማማውን ነገር እንዲያገኝ ማድረግ ነው - ምርታማነት። ይሄው ነው ቅዱስ ተግባር፤ ይሄው ነው እድገት። እናም እንደሌላው የምርት ተቋም ሁሉ፤ የቢራ አምራች ተቋማት በምርታቸው ቢኮሩ፤ ምርታቸውን ለማስተዋወቅ ቢጥሩ፤ ከደንበኞችም መልካም ምላሽ ቢጠብቁ ተገቢ ነው።

ምን ይሄ ብቻ፤ በቢራ አምራች ተቋም ስፖንሰር አድራጊነት የመዝናኛውን ዝግጅት ለማየት በመቻሌም፤  ለተቋሙ ምስጋና ማቅረብ ይገባኛል - ቅሬታዬን ከማስረዳቴ በፊት። ተቋሙ፤ ራሱንና ምርቶቹን ለማስተዋወቅ በሚያደርገው ጥረት፤ እኔን የሚያስደስት መዝናኛ መፍጠሩ የሚያስመሰግን ተግባር ነው። ደግሞም ከላይ እንደገለፅኩት፤ ከየአይነቱ የቀረበው የሙዚቃ ድግስ የተዋጣለት ነበር። ከነባር ጣፋጭ ዜማዎች እስከ አዳዲስ የጎረምሳ ዘፈኖች ድረስ፤ ከአገርኛ ሙዚቃ እስከ ታዋቂ የእንግሊዝኛ ዘፈኖች ድረስ... የመዝናኛ ፕሮግራሙ፤ አብዛኛውን ሰው ለመማረክ በሚያስችል መንገድ ተቀናብሯል። እኔ በበኩሌ እንግሊዝኛ ዘፈን ያቀረበችውን ድምፃዊት አድንቄያለሁ። የድምፅና የአዘፋፈን ብቃት ብቻ ሳይሆን፤ የመድረክ አቀራረቧም፤ ከልብ የሚፈነቅል ይመስላል።

ብዙውን ጊዜ፤ በኢቲቪ የሚሰራጩ የመድረክ ሙዚቃዎች ላይ ጎልቶ የሚታየው የድምፅ ችግር፤ በዚሁ የአዋሳ የመዝናኛ ፕሮግራም ላይ አለመታዩም ያስደስታል። የድምፅ መሳሪያዎችን የማሰናዳትና የድምፅ ጥራት የማረጋገጥ ሃላፊነት የወሰደው ድርጅት ሊመሰገን ይገባዋል። ብቻ ምናለፋችሁ? በጥቅሉ ሲታይ፤ የመዝናኛ ዝግጅቱ ግሩም ነበር።  ዘ የመድረክ ሙዚቃ በጥራት መቅረቡም ያስደስታል። ምናልባት፤ “የክብር እንግዳ” ባያበዙና፤ ወጣቶችንም በርከት አድርገው ወደ መዝናኛው ፕሮግራም ቢጋብዙ ኖሮ፤ ይበልጥ ደማቅ በሆነ ነበር። እጃቸውን አጣምረውና ተኮሳትረው መድረኩን የሚመለከቱ “የክብር እንግዶች”፤ የመዝናኛውን መንፈስ ያቀዘቅዙታል።

ከዚህ ውጭ፤ በአዝናኙ ፕሮግራም የተደሰተ ሰው ሁሉ፤ አዘጋጆቹንና ስፖንሰሩን ቢያመሰግን፤ ምስጋናው ለራሱም ጭምር ይሆናል። “ስፖንሰሮች’ኮ፤ ለራሳቸው ጥቅም ብለው እንጂ፤ ለኛ አስበው አይደለም” በማለት ለማጣጣል የሚሞክሩ ሰዎች እንደሚኖሩ እገምታለሁ። ተሳስተዋል። ጥሩ ነገር የሚያቀርብልንን ሰው ለማመስገን፤ የግድ ተጎድቶ እስክናየው ድረስ የምንጠብቅ ከሆነ፤ አንድም ሞኝነት ነው፤ አልያም ክፋት ነው።

ጎበዝ አስተማሪንና ሃኪምን፤ ታታሪ ግንበኛንና ሾፌርን የምናመሰግነው፤ ለኛ ሲሉ ራሳቸውን ስለሚጎዱ ነው? ለራሳቸው ኑሮና ሙያ ብለው በሚያከናውኑት ስራ አማካኝነት፤ ጥሩ ነገር ሲያቀርብሉን ነው ማመስገን ያለብን። የስፖንሰሮች ጉዳይ፣ ከዚህ  የተለየ አይደለም። የቢራ ፋብሪካውም፤ የአመት በአል መዝናኛ በማቅረብ፤ ምርቱን ለማስተዋወቅ መሞከሩ ተገቢ ነው።

ለነገሩ፤ በቢራ አምራቾች ዘንድ፤ የገበያ ፉክክር እየጨመረ አይደል? ገና ብዙ ይጠብቃቸዋል እንጂ። ለቢራ አምራቾች፤ መጪው ጊዜ የብርቱ ውድድርና የከባድ ፉክክር ጊዜ ነው።  ታዲያ ምኑ ይጠየቃል! በመዝናኛም ሆነ በሌላ መንገድ፣ የሰዎችን ትኩረት በመሳብ ራሳቸውንና ምርቶቻቸውን ለማስተዋወቅ መጣራቸው መልካም ነው። እንዲያውም፤ “ገበያ አጣን፤ ገበያ ጠፋ” ብለው ለሚያማርሩ  አላዋቂዎች ወይም መላ ለሚፈልጉ ጀማሪ አምራቾች ጥሩ ትምህርት ሊሆን ይችላል። የቢራ አምራች ተቋማት የሚያካሂዱት የማርኬቲንግ ጥረት፤ ለብዙዎች አርአያ መሆን የለባቸውም? ቅሬታዬም ከዚህ ይጀምራል።

አርአያና ማስተማሪያ ሊሆኑ በሚችሉ ተቋማት ውስጥ፤ የጎሉ ስህተቶችን ማየት ያሳዝናል። ይበልጥ የሚያሳዝነው ግን፤ የኢቲቪ ስህተት ነው።

 

ጋዜጠኝነትና ማስታወቂያ ተደበላለቀ

እስቲ አስቡት። የኢቲቪ የመዝናኛ ፕሮግራም አዘጋጆች፤ ይህን “ቢራ ጠጡ”፤ በዚህ “ቢራ ተደሰቱ” የሚል ማስታወቂያ ከመድረክ ማስተጋባታቸው ትርጉሙ ምንድነው? ጋዜጠኞች፤ በሚዛናዊነት የሚዘግቡ እንዲሁም ትክክለኛነቱ ለሚያምኑበት ነገር ምስክርነት የሚሰጡ ወይም አቋማቸውን አይደሉም እንዴ?  የኢቲቪ ጋዜጠኞች፤ “ይህን ቢራ ጠጡ፤ በዚህ ቢራ ተደሰቱ” እያሉ ሲናገሩ የሰማናቸው...፤ መቼም የዜና ዘገባ ማቅረባቸው አይደለም። የሚያምኑበትን ሃሳብና አቋማቸውን እየገለፁ ናቸው እንዳንል ደግሞ፤ “ይህን ወይም ያንን ቢራ ጠጡ” የሚል አቋም እንደማለት ይሆንብናል። እና ታዲያ፤ የንግግራቸው ትርጉም ምንድነው?

ጋዜጠኞቹ የተናገሩት ነገር፤ የንግድ ማስታወቂያ ቢሆንም፤ በጋዜጠኞች አፍ የተነገረ ስለሆነ ብቻ፤ “የዜና ዘገባ” ወይም “የአቋም መግለጫ” ካባ ይላበሳል። በጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥ ደግሞ፤ አንደኛው ነገር የሌላ ነገር ካባ እንዲደርብ ማድረግ ትልቅ የሙያ ስህተት ነው። ማስታወቂያዎች መሰራጨት ያለባቸው፤ የማስታወቂያ ባህርይ ተላብሰው መሆን አለበት። አንድ የማስታወቂያ ስራ፤ በማንኛውም ሰበብ፤ “የዜና” ካባ ወይም “የአቋም” ካባ እንዲደርብ የሚፈቅድ ሰው፤ የጋዜጠኝነትን ሙያ ጥሷል። ለዚህም ነው፤ የሚዲያ ተቋማት ከፍተኛ ጥንቃቄ ሲያደርጉ የሚታዩት።

ማስታወቂያ ከዜና ጋር ወይም ማስታወቂያ ከአቋም ጋር እንዳይምታታ ለመከላከል፤ የእንግሊዙ ቢቢሲ እና የአሜሪካው ኒውዮርክ ታይምስ፤ እጅግ ጠንቃቃ አሰራሮችን እንደሚከተሉ በምሳሌነት ማየት ይቻላል። ከእነዚህ የጥንቃቄ አሰራሮች መካከል አንዱን ብቻ ልጥቀስ። ለሚዲያ ተቋማቱ በጋዜጠኝነት የሚሰሩ ሰዎች፤ የማስታወቂያ ስራ ውስጥ ከመሳተፍ እንደሚቆጠቡ ቃል ይገባሉ። ይህም ብቻ አይደለም። በተለያዩ መድረኮችና ስብሰባዎች ላይ ንግግር ሲያደርጉም መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል - የሚናገሩት ነገር፤ የሚዲያ ተቋሙን የሚወክል የአቋም መግለጫ እንዳይመስል። በዚህም ምክንያት፤ በንግድ ፉክክር ውስጥ በአድልዎ አንዱን ኩባንያ የሚጠቅም፤ አልያም በፖለቲካ ፉክክር ውስጥ በአድልዎ አንዱን ፓርቲ የሚጠቅም ንግግር አያደርጉም - የቢቢሲና የኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጠኞች። የትኛውም የሚዲያ ተቋምና ማንኛውም ጋዜጠኛ፤ ይህንን የሙያ ስነምግባር በመከተል መስራት ይጠበቅባቸዋል። ባለፈው ሳምንት በተሰራጨው የመዝናኛ ፕሮግራም ላይ ግን፤ ማስታወቂያና ጋዜጠኝነት ተደበላልቀዋል።

 

የ”መጨለጥ” ውድድር

በአንጋፋውና በብቸኛው ብሄራዊ የቲቪ ጣቢያ፤ “በአንድ ትንፋሽ ቢራ የመጨለጥ ውድድር” ሲካሄድ አይታችኋል? ለዚያውም፤ ህፃን አዋቂው እንዲያየው እሁድ ቀን በሚተላለፍ የአመት በአል መዝናኛ ዝግጅት ላይ ነው፤ ይህንን የተመለከትነው።  በአንድ ትንፋሽ ቢራውን በፍጥነት የመጨለጥ ውድድር፤ በተለይ ለህፃናት ምን አይነት መልእክት እንደሚያስተላልፍ ይታያችሁ?

የመጠጥ ውድድር ይቅርና፤ በፍጥነት ምግብ የመብላት ውድድርም የሚያስደስት አይመስለኝም። የመስገብገብና የማግበስበስ፤ የመሻማትና የመዝረክረክ ስሜት ነዋ ጎልቶ የሚታይበት። ሰዎች፤ በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው፤ የምግብ አቀራረብ አሳምረው በእርጋታ የሚመገቡት አለምክንያት ነው? ጉንጫቸው እስኪወጠር ድረስ እያግበሰበሱ የመጉረስ ችሎታ አጥሯቸው አይደለም። በስርአት መመገብ የሚያስፈልገውኮ፤ ለሰው ልጅ ክብር ሲባል ነው - ለራስ ክብር ሲባል።

አውሬዎች እየተሻሙ ቢያግበሰብሱ አይገርምም። ምግብ አያመርቱም፤ አያዘጋጁም። ሰው ግን ያመርታል፤ የራሱ ምርት ስለሆነም የትም አይሄድበትም። አይስገበገብም። የራሱ ምርት ስለሆነ ክብርና ኩራት ይሰማዋል። ስለዚህ አቀራረቡን አሳምሮ ተረጋግቶ ይበላል። የመጠጥም ተመሳሳይ ነው። ታዲያ፤ በአንድ ትንፋሽ ፈጥኖ የመጨለጥ ውድድር ለምን ያስፈልጋል? ምናልባት፤ “ሽሚያና መስገብገብ በማያስፈልገው ምግብ ላይ፤ ሽሚያ ማየት ያስቃል ብትሉ”፤ እሺ ይሁን። ሽሚያው መጠጥ ላይ ሲሆንስ? በፍጥነትና በአንድ ትንፋሽ ቢራውን የጨለጠ ይሸለማል እየተባለ ከመድረክ ሲታወጅስ? አንዳች ተፈላጊ የብቃት አይነት አይመስልም? ለህፃናት ማለቴ ነው።

በአንድ ትንፋሽ ቢራውን ቀድሞ የጨለጠ፤ ሽልማት እንደሚያገኝ በሆይሆይታ እየተዳመቀ የሚታወጀው፤ ዘወትር በምናውቃቸው የመዝናኛ ፕሮግራም ጋዜጠኞች ሲሆንስ? “ሶስት ተወዳዳሪዎች ይፈለጋሉ፤ ሽልማት አለው” ... ጋዜጠኞቹ ናቸው እንዲህ እያሉ ግብዣውን የሚያስተጋቡት።

በእርግጥ፤ የቢራ አምራቹ ተቋም ተወካይ፤ ወዲያውኑ የማስተካከያ ሃሳብ ለጋዜጠኞቹ ተናግሯል። በውድድሩ መሳተፍ የሚችሉት፤ ከ18 አመት እድሜ በላይ የሆናቸው ሰዎች ብቻ ናቸው በማለት ተወካዩ ተናግረዋል። ጥሩ ነው፤ ለዚህም ምስጋና ይድረሳቸው። ነገር ግን፤ ውድድሩን ለማየትና ለመዝናናትም የእድሜ ገደብ እንደሚያስፈልገው፤ ተጨማሪ የማስተካከያ ሃሳብ የሚያቀርብ ሰው አልተገኘም። ቢያንስ ቢያንስ፤ ከ14 አመት በታች የሆናቸው ልጆች፤ የመዝናኛ ፕሮግራሙን እንዲመለከቱ አይመከርም ብሎ ማስጠንቀቅ አይቻልም ነበር? ሌላ ቀላል መፍትሄም አለ። ውድድሩ እዚያው መድረክ ለተገኙ ሰዎች ቢከናወን እንኳ፤ በቲቪ የሚሰራጨው በቀጥታ ስላልሆነ፤ “ኤዲት” አድርጎ ማስቀረት ይቻል ነበር።

 

 

 

 

 

 

Read 2270 times Last modified on Saturday, 21 April 2012 15:51