በወርሃዊ ክፍያዎች ወይንም በየትምህርት ተርሙ በሚደረጉ ክፍያዎች ላይ ከፍተኛ ጭማሪ አደረጉ ከተባሉ ት/ቤቶች መካከል አንዳንዶቹ ጭማሪው የተደረገው ከወቅቱ የዋጋ ንረት ጋር በተያያዘ በመምህራን ደሞዝና በልዩ ልዩ ወጪዎች ላይ የሚደረገው ክፍያ በመጨመሩ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ቅሬታቸውን ካቀረቡ ወላጆች መካከል አብዛኛዎቹ የልጆቻቸውን የትምህርት ቤት ክፍያ መክፈል የማይችሉበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ተናግረዋል፡፡ መንግስት አንዳንድ ት/ቤቶች እያደረጉ ያሉትን አግባብነት የሌለው ጭማሪ ተቆጣጥሮ ት/ቤቶቹ ወደ ህጋዊ መስመር እንዲገቡ ማድረግ ያልቻለበት ምክንያት አልገባንም ብለዋል - ወላጆች፡፡ ልጆቻቸውን ባለፈው ሰኔ ወር እንዳስመዘገቡ የነገሩን አንድ ወላጅ፤ አሁን በመስከረም ወር ልጆቻቸውን ወደ ት/ቤት ሲልኩ 50 በመቶ ጭማሪ መደረጉ እንደተገለፀላቸው ተናግረዋል፡፡ የአዲስ አበባ ት/ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሃይለ ስላሴ ፍስሃ ጉዳዩን አስመልክቶ ላቀረብንላቸው ጥያቄ በሰጡን ምላሽ፤ ት/ቢሮ በግል ትምህርት ቤቶች ክፍያ ላይ የዋጋ ተመን ማውጣት እንደማይችልና በነፃ ገበያ ሥርዓት መሰረት ት/ቤቶች የራሳቸውን የዋጋ ተመን ማውጣት እንደሚችሉ ገልፀዋል፡፡ ይሁን እንጂ ቀደም ሲል የዋጋ ተመናቸውን (ወርሃዊ ክፍያቸውን) አሣውቀው ምዝገባ ካካሄዱ በኋላ ቆይተው ጭማሪ አድርገናል ማለት እንደማይችሉና ይህ አሠራር ህገወጥ እንደሆነም ጨምረው ገልፀዋል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በዘንድሮው አመት ት/ቤቶች ለተማሪዎች የሚሸጡትን የመማሪያ መፃህፍት ት/ቢሮ በሚያወጣው የዋጋ ተመን ብቻ እንዲሸጡ መመሪያ ቢወጣም አንዳንድ ት/ቤቶች መመሪያውን በመጣስ በመፃህፍት ሽያጭ ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ እያደረጉባቸው እንደሆነ ወላጆች ገለፁ፡፡ የት/ቢሮው ምክትል ሃላፊ በበኩላቸው ቢሮው ካወጣው የመማሪያ መፃህፍት መሸጫ ዋጋ በላይ ሲሸጡ በተገኙ ት/ቤቶች ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ ተናግረዋል፡፡ ህብረተሰቡ እነዚህን ህገወጦች በመጠቆም ተሳትፎ እንዲያደርግም አቶ ኃይለስላሴ አሳስበዋል፡፡