Saturday, 22 October 2011 11:16

የዳቦ ታሪክ

Written by  ሌሊሣ ግርማ
Rate this item
(0 votes)

የአንድ ሰው የህልውና ሂደት ተጠናቅቆ የሚገኘው በህይወቱ መጨረሻ ላይ ነው ይላሉ ኤግዚዝቴንሻሊስቶች፡፡ በሂደት ላይ እያለ ማንነቱ “ነው” በሚል ማረጋገጫ መደምደም አይቻልም፡፡ በህይወቱ እያለ “በሁነት ወይንም መሆን ሂደት ላይ ነው” ይባላል እንጂ “ሆኗል” ብሎ በአለቀ-ደቀቀ የሰውዬውን ጉዳይ መዝጋት አይችልም፡፡ ይህ የሰውን ህልውና በተመለከተ ነው፡፡ የሰውን ታሪክ ለመናገር ስናስብ መጠናቀቁን መጀመሪያ ማረጋገጥ ግድ ነው ለማለት ነው፡፡

ግን ለሰው ብቻ ነው ይህ ፍልስፍና የሚሰራው? ለምሳሌ፤ የዳቦስ ታሪክ እንደ ሰው ህይወት ከተጠናቀቀ በኋላ ነው ልንተርከው የሚፈቀድልን? 
…ዳቦ በኢትዮጵያ ሀገር ላይ ከእናቱ አንባሻ እና ከእህቱ ሙሉሙል ከእ.ኤ.አ…. ዓ.ም ተወለደ፡፡ ሲወለድ ክብደቱ … ግራም ነበር… ሲሞት በአዲስ አበባ ከተማ ክብደቱ ዳቦ ቆሎ አክሎ ነበር፡፡ …. ብለን የዳቦን ታሪክ ለመፃፍ ግዴታ መሞት አለበት?
… ለማንኛውም የዳቦን ታሪክ ለመፃፍ በአዲስ እይታ መመልከት አስፈላጊ መሆኑን አመንኩበት፡፡ … የዳቦ ማዋለጃ (ዳቦ ቤቶች) እየተዘጉ ነው የሚል ወሬ የሰማነው ባለፈው ሳምንት ነበር፡፡ …የኑሮ ውድነቱን ከዳቦ ጋር እንዴት እንደተያያዘ ለማሰብ አዲስ መንገድ መረጥሁ፡፡ እንደሚከተለለው፡፡
በድሮ ዘመን ዋና መገበያያ ወርቅ እንደነበረው አሁን ደግሞ የሁሉም እሴት መወከያ (እንደ ገንዘብ) ዳቦ ቢሆን ብላችሁ አስቡት?
ብዙ ዳቦ ያለው ሀብታም ነው፡፡ የሌለው ደግሞ ደሀ ነው እንበል፡፡ የሀገራችን ጠቅላይ ሚኒስቴር ትልቁ ኃላፊነት ላይ የተቀመጡ ሰው ስለሆኑ የሚፈቀድላቸው የወር ተመን... ሰባት ሺ ዳቦ ነው (ሰባት ሺ ብር)
አራት ቤተሰብ አላቸው እንበል፡፡ እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ሁለት ዳቦ ለቁርስ ሁለት ዳቦ ለምሳ እና ሁለት ዳቦ ለእራቱ መመገብ አለበት፡፡ ውሻ እና ድመቷ አንድ አንድ ዳቦ በቀን ተመድቦላቸዋል፡፡ አስር ዳቦ በቀን የምግብ ወጪ አለባቸው፡፡ አስር ጊዜ ሰላሳ፣ ሦስት መቶ ነው፡፡ ግን ደረቅ ዳቦ ብቻውን እህል ተብሎ አይበላም፡፡ ከቁርስ ጋር ማርማላት፣ ወተት፣ ቂንጬ፣… ሌላም ብዙ ነገር ያስፈልጋል፡፡ …ይሄ ሁሉ የምግብ አቅርቦት በቤተሰቡ ውስጥ የሚሟላው ዳቦ እየተከፈለ ነው፡፡ ዳቦ ገንዘብ ነው፡፡ ዳቦ ወርቅ ነው፡፡
ገንዘብ እና ወርቅ የሆነው ዳቦ፣ ስንዴ እንደ መአድን ተቆፍሮ ከተዘራ በኋላ የሚገኝ ነው፡፡ አመታዊው ስንዴ ከተመረተ በኋላ ታጭዶ፣ ተወቅቶ፣ ተበራይቶ፣ ተፈጭቶ ባንክ ቤት ይገባል፡፡ ባንክ ቤት ዱቄቱን እየጋገረ ለህዝቡ ያከፋፍላል፡፡ እያንዳንዱ ሰው እንደ ችሎታው እያንዳንዱ ሰው እንደ ስራው ደመወዙ ተተምኖለት በዳቦ መጠን ይከፈላዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወር የሰባት ሺ ዳቦ ተከፋይ ናቸው፡፡ ጥያቄው ከች የሚለው እዚህ ገደማ ነው፡፡ …የአመታዊ የስንዴ ምርት ሳይቀንስ የዳቦ ዋጋ እንዴት አድርጐ ሊጨምር ቻለ? የሚል ነው እቅጩ ጥያቄ፡፡ ለካ የጥያቄ እንቅጭ የለውም፤ የመልስ እንጂ…፡፡
የዳቦው ወይንም የገንዘቡ ተመን ለምን ረከሰ?... በአንድ ዳቦ ይገዛ የነበረ የሆድ ጥጋብ… ሃያ ዳቦ ክፍያ አስፈለገው፡፡ …እንግዲህ እዚህ ላይ የዳቦውን ብዛት ለግለሰብ መጠን እንዲብቃቃ አዲስ አይነት ዘዴ መፈጠር አለበት፡፡ …አንድ ብርጭቆ ወተትን ለሃያ ብርጭቆዎች እንዲብቃቃ አድርጋችሁ አካፍሉ ብንባል… ማድረግ የምንችለው አንድ ብርጭቆ ወተቱን በዘጠኝ ብርጭቆ መበረዝ እና ለአስሩም ሰው ማዳረስ ብቻ ነው፡፡ ምንም አያጠያይቅም፤ መፍትሄው ይህ ብቻ መሆኑ፡፡
ዳቦውም ላይ የተከሰተው ተመሳሳይ ነገር ነው፡፡ ለግለሰቡ የዳቦ ደመወዙን ለመጨመር ድሮ የሚከፈለውን የዳቦ ቁጥር ዳቦውን ለመስራት የተጠቀመበትን ዱቄት ሳይቀየር ማብዛት፡፡ የአምስት መቶ ዳቦ ደሞዝተኛው የአንድ ሺ ብር ጨማሪ አግኝቶ የተሻሻለ ቢመስለውም… የአምስት መቶ ዳቦ ዱቄት እና የአንድ ያው ናቸው፡፡ እንዲያውም የአንድ ሺው ሳይቀንስ አይቀርም፡፡ … በአስማት ዳቦ ነው ደሞዙን ገበሬው የሚቀበለው፡፡ ገበሬ ማለት በዚህ መጣጥፍ ስራ ሰርቶ የስራውን ክፍያ በደመወዝ የሚቀበል ሁሉ ነው፡፡
የገበሬው መሬት በመንግስት እጅ ያለ ነው፡፡ በሊዝ የተያዘ ነው፡፡ በሊዝ ባይያዝም የስንዴ ምርቱን ወደ ብር ተመን የሚቀይረው በመንግስት ባንክ ቤት ነው፡፡ በዳቦ ትረካችን ቋንቋ፣ የብር ተመን ዱቄት ወደ ዳቦ የሚመነዘርበት ነው፣ ወይንም ስራን ወደ ገንዘብ፡፡ ዳቦ ቤቱ ባንክ ቤት ነው፡፡ ገንዘቡን ዳቦ ጋግሮ የሚሰጠው፣ የገበሬውን ስራ (ምርት) ወደ ዳቦ ገንዘብ የሚለውጠው ጋጋሪ ቤት ነው፡፡ ዳቦ ቤቱ የመንግስት ነው፡፡
ፋብሪካ የለንም፡፡ የእርሻ ምርት ማቀላጠፊያ ማሽኖች አላመረትንም፡፡ በአነስተኛ እና ጥቃቅን መሬቶች ላይ በሚሰራ ግብርና ስንዴን በብዛት ማምረት አልቻልንም፡፡ …ስንዴ ማለት ዳቦ ማለት ነው፡፡ ህዝብ አለን፣ መሬት አለን ግን በቂ ስንዴ የለንም፡፡ ስንዴን ቋሚ እሴት አድርገን ካየነው እንደ ወርቅ፡፡ ስንዴ አለ እና ስንዴ ሁሌም በአለም ላይ ተፈላጊ እስከሆነ ድረስ የስንዴው መወከያ የሆነው የዳቦ ዋጋም አይወድቅም፡፡ ስንዴ ነዳጅ ዘይት ይሆናል ያኔ፡፡
የህዝብ መጠን እየበዛ የስንዴ ምርቱ ግን መመጣጠን አልቻለም፡፡ ስንዴው ከህዝቡ እኩል ተመርቷል እያልን የምንከራከር ከሆነ … በአስፈለገው ሁኔታ የዳቦ ዋጋ ወድቋል የሚለውን እውነት ግን ይዘን ቢሆን ጥሩ ነው፡፡
ስንዴው በገበሬው ተመርቷል፤ ልማታዊ ስኬታማዊ ሆነናል፤ ግን ዱቄቱ በነጋዴ ተወስዶ መጋዘን ውስጥ ተቆልፎበታል ለሚሉትም ቢሆን የሚያቀርቡት ምክንያት ለችግሩ መፍትሄ እስካላመጣ ድረስ ዋጋ አይኖረውም፡፡ …ነጋዴውስ ዱቄቱን ወደ ዳቦ መቀየር ካልቻለ ምን ያደርግለታል፡፡ ዱቄት ውስጥ ተቀብሮ መቀመጥ?
ወይንስ ዱቄቱን ከገበሬው እና ከነጋዴው በዳቦ ዋጋ ቀይሮ መንግስት ይገዛና፣ ለህዝቡ የአንድ ዳቦን ዱቄት ለአስሩ እንዲበቃ አድርጐ ከጋገረ እና ካከፋፈለ በኋላ … የተረፈውን ዱቄት ለውጭ ሀገር የዳቦ ገበያ ያቀርበዋል፡፡ የስንዴ ዱቄት ነዳጅ ዘይት ነው ብያለሁ፡፡ ይኼንኑ የማይለወጥ ዋጋ ያለውን እሴት ለውጭ ዳቦ ጋጋሪዎች ሸጦ የፈረንጅ ዳቦን በተለዋጭ ያገኝበታል፡፡ የውጭ ዳቦ ማለት ዶላር ወይንም ዩሮ ማለት ነው፡፡
የውጭ ዳቦ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ የእንቅስቃሴ ደም ስር የሆነውን ቤንዚን እና ናፍጣ ወደ ሀገር ውስጥ ለማስመጣት የፈረንጅ ዳቦ ያስፈልጋል፡፡ በአበሻ ዱቄት የአበሻ ዳቦ ብቻ ነው የሚሰራው፡፡ በአበሻ ዱቄት ላብ ወይንም ምርት ግን የፈረንጅ ሀገር ዳቦ ቤቶች የፈረንጅ ዳቦ ያመርታሉ፡፡ መልሰው የራሱን ልፋት ለራሱ ለሀበሻው ይሸጡለታል፡፡ “በሀገር ምርት እንኩራ” ይላል የአበሻ ባህላዊ መፈክር፡፡ በሀገር ምርት ለመኩራት መጀመሪያ ነገር ምርቱ መኖር እንደነበረበት የጠየቀ ወይንም ያስጠየቀ እስካሁን የለም፡፡ ምርት የሌለባት ሀገር ላይ በሀገር ስንዴ መኩራት አይቻልም፡፡ …የስንዴ ምርት በሌለበት ሀገር ላይ በኤኮኖሚ መመንደግ አይታሰብም፡፡
በጥራት የተመረተ አንድ ኪሎ የሀገር ውስጥ ስንዴና የውጭ ሀገሩ አንድ ነበሩ በፊት፡፡ አንድ ብር ከአንድ ዶላር ጋር ምንም ለውጥ አልነበረውም እንደማለት ነው፡፡ በአንድ የአበሻ ዳቦ አንድ የፈረንጅ ዳቦ መቀየር ይቻል ነበር፡፡ ምናልባትም አንድ አበሻ ስለሀገሩ ያለው ኩራት ከአንዱ ፈረንጅ አይተናነስም - በዛ ወቅት፡፡
አስር ዳቦ ማስጋገር የፈለገ ሰው፣ አንድ ኪሎ ዱቄት ማምጣት መቻል አለበት፡፡ ወይንም በአንድ ኪሎ ዱቄት የሚተመን ዋጋ መለወጥ መቻል ግዴታ ነበር፡፡ በኋላ ህጉ ተቀየረ፡፡ …ምንም ዱቄት ሳይኖር ዳቦ ማስጋገር አሊያም ለአንድ ዳቦ መጠን በታቀደ ዱቄት አስር ዳቦ ማስመረት ተጀመረ፡፡ …አንድ ብር ይገዛ የነበረውን ዋጋ አስር ብሩ መግዛት አቃተው ማለት ነው፡፡
በአንድ ቀን ምሳ አስር ቀን እንደመቆየት ነው፡፡ ወይም አንዱን ለአስር እንደማካፈል፡፡ …ችግር አስከተለ… ችግሩ ኢንፍሌሽን ተብሎ ተጠራ፡፡ ችግሩ ውስጥ አሁን እየኖርን ነው፡፡ ይህንን ያህል ዳቦን በገንዘብ ተክቼ ካወራሁ ይበቃኛል፡፡ አሁን ወደ ትክክለኛው ዳቦ እንመለስ፡፡ በአንድ ብር ስለምንገዛው አንድ ዳቦ፡፡…
ዳቦ እኔ በማውቅበት እድሜ አስራ አምስት ሳንቲም ነበረ፡፡ በአንድ ብር ስድስት እና ሰባት ዳቦ ይገዛል፡፡ የዳቦዎቹ ክብደትም በተሰጣቸው ደረጃ መሰረት እንዲሆኑ ህጉ ያስገድድ ነበር፡፡
የዳቦዎቹ ዋጋ ከግዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ፤ ክብደታቸው ደግሞ እያነሰ መጣ፡፡ ዳቦው የተሰራበትን የዱቄት መጠን በቀጥታ የማይወክል ብር የዳቦው ዋጋ ሆነ፡፡ መሆንም ነበረበት፡፡ የመግዛት አቅም እና የማቅረብ አቅም አልተመጣጠኑም፡፡ …ወይንም እኛ በዶላር ዋጋ ወደ ውጭ የምንሸጠው እና በራሳችን ብር ከውጭ የምንገዛው እሴት አልተመጣጠኑም፡፡
ሰባት ሺ ብር በወር የሚቀበልም ሰውም በዶላር አለም ላይ የጥቂት መቶ ብሮች ደሞዝተኛ ነው፡፡ በጥቂት መቶ ብሮች የሚገዛው ጥራት የጠበቁ ዳቦዎቹም ከወር ወር በውጭ ሀገርም ቢሆን አያኖሩትም፡፡ ትልቁ የመንግስት ደሞዝተኛ መኖር ያልቻለበትን ትንንሾቹ እንዴት እንድንኖር ይጠበቃል፡፡ …ዳቦ ተጨባጭ ነገር ነው፣ በተስፋም ሆነ ታትሞ፣ ተባዝቶ (እንደ ፎቶ ኮፒ) ሊገመጥ አይችልም፡፡ ዳቦ ቤቶች የዳቦዎቹን ክብደት ወደ ህጋዊ ደረጃ እንዲመልሱ ተገደዋል፤ የሚል ወሬ እየተናፈሰ ነው፡፡ …ወደ ድሮ ክብደታቸው ከተመለሱ በድሮ ዋጋቸው እንደማይሆን ግልፅ መሰለኝ፡፡ የድሮ አንድ ብር የዛሬ አስር ብር ከሆነ፤ የድሮውን ክብደት ያለው ዳቦ የድሮውን አስር እጥፍ ብር ማስወጣቱ አይቀርም፡፡ አሊያም ዳቦውን ወደ ድሮው የ15 ሳንቲም ተመን እንመልሰው ከተባለ ደግሞ ዳቦው የዳቦ ቆሎ ክብደት እና መጠን ማከሉ አያጠራጥርም፡፡ … ይህም የዳቦ ሞት ነው፡፡ የዳቦ ሞት የረሀብ ትንሳኤ ነው፡፡

 

Read 3326 times Last modified on Saturday, 22 October 2011 11:20