ታዋቂዋ ድምጻዊት ቬሮኒካ አዳነ፣ የቤት እቃዎችን ለገበያ የሚያቀርበው የሚዲያ ኢትዮጵያ ብራንድ አምባሳደር ተደርጋ የተሾመች ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ብቸኛው የሚዲያ የቤት እቃዎች አስመጪና ዋና አከፋፋይ ከሆነው ከኬ.መቅድም ጄነራል አስመጪና ላኪ ድርጅት ጋር የአጋርነት ስምምነት ፈጽመዋል፡፡
ባለፈው ረቡዕ መጋቢት 10 ቀን 2017 ዓ.ም፣ ኬ.መቅድም አስመጪና ላኪ ድርጅት ከአርቲስት ቬሮኒካ አዳነ ጋር በመሆን በአጋርነት ስምምነታቸው ዙሪያ በስካይላይት ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ አርቲስቷና ድርጅቱ በአጋርነት ለመሥራት የሚያስችላቸውን የፊርማ ሥነስርዓትም አከናውነዋል፡፡
የሚዲያ ኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሲሳይ በየነ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ በሰጡት ማብራሪያ፤ “ቬሮኒካ ድርጅታችንን የበለጠ ታስተዋውቅልናለች ብለን ብራንድ አምባሳደር አድርገን መርጠናታል፤ ማህበራዊ ሃላፊነታችንን ለመወጣትም አብረናት እንሰራለን፡፡” ብለዋል፡፡
የሚዲያ ብራንድ አምባሳደር በመሆኔ በጣም ዕድለኛ ነኝ ያለችው ድምጻዊት ቬሮኒካ፤ ስሙን ባላውቀውም የሚዲያን የቤት እቃዎች መጠቀም የጀመርኩት ከሁለት ዓመት በፊት ነው ብላለች፡፡ “የምርቶቹን ጥራት በተመለከተ እኔ ምስክር ነኝ፤ ተጠቅሜበት አይቼዋለሁ” ስትልም ማረጋገጫ ሰጥታለች፡፡
ሚዲያ ኢትዮጵያ 12 ዘፈኖቿን ሙሉ ወጪውን ሸፍኖና የሚገባትን ክፍያ ፈጽሞ በጥራት እንዳሰራላት የገለጸችው ድምጻዊቷ፤ ይህም የአጋርነት ስምምነታቸው አካል መሆኑን ጠቁማለች፡፡
ባለፈው የፈረንጆች ዓመት በ”ፎርቹን 500”፣ በ227ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው የቻይናው የቤት እቃዎች አምራች ሚዲያ፣ የማንችስተር ክለብ ኦፊሴላዊ አጋር ሲሆን፣ የክለቡ ተጫዋች ERLING HALLAND ደግሞ የኩባንያው ዓለማቀፍ ብራንድ አምባሳደር መሆኑ ይታወቃል፡፡
ኬ.መቅድም ላለፉት 8 ዓመታት ጥራት ያላቸው የሚዲያ የቤት ዕቃዎችን በብቸኝነት በማስመጣት ሲያከፋፍል የቆየ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል ፍሪጆች፣ አየር ማቀዝቀዣዎች፣ የልብስ ማጠቢያ ማሽኖች፣ የውሃ ማከፋፊያዎች፣ እቃ ማጠቢያዎችና የውሃ ማጣሪያዎች ይገኙበታል፡፡ በተጨማሪም ኬ.መቅድም፤ ከ30 ዓመታት በላይ ሰሊጥ፣ የቅባት እህሎች፣ ጥራጥሬ፣ ቅመማቅመም፣ ጣሂኒ እና ቡና ለውጭ ገበያ ሲያቀርብ መቆየቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡
Saturday, 22 March 2025 12:47
ቬሮኒካ አዳነ ከMidea ኢትዮጵያ ጋር በብራንድ አምባሳደርነት ለመስራት ተስማማች
Written by Administrator
Published in
ንግድና ኢኮኖሚ

