Saturday, 22 March 2025 12:49

ሜሪጆይ ኢትዮጵያ የገቢ ማሰባሰቢያ ሩጫ መርሐ ግብር ያካሂዳል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 •ከ12 እስከ 15 ሺ የሚደርስ  ሕዝብ ይሳተፋል ተብሏል
                              ከሦስት ወራት በኋላ የድርጅቱ ሆስፒታል ይመረቃል


       ከተመሰረተ 31 ዓመታትን ያስቆጠረው ሜሪጆይ ኢትዮጵያ የበጎ አድራጎትና የልማት ድርጅት፣ ከብራይት  አድቨርትና ኢቨንት ጋር በመተባበር፣ የገቢ ማሰባሰቢያ ሩጫ መርሐ ግብር ሊያካሂድ መሆኑን ገልጿል።
ባለፈው ረቡዕ መጋቢት 10 ቀን 2017 ዓ.ም፣ በዮድ አቢሲንያ የባሕል ምግብ አዳራሽ ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የገቢ ማሰባሰቢያ ሩጫው መጋቢት 28 ቀን 2017 ዓ.ም. ጠዋት በዑራኤል አድርጎ ወደ ወሎ ሰፈር በሚወስደው የፒኮክ መናፈሻ አዲሱ አስፋልት መንገድ በመዝለቅ፣ የወሎ ሰፈርን አደባባይ ዞሮ በታችኛው አስፋልት ወደ መነሻው በመመለስ የሚጠናቀቅ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡  ሩጫው የሚሸፍነው አጠቃላይ ርቀት 5 ኪሎሜትር ሲሆን፣ በዚህ መርሐ ግብር ላይ ከ12 እስከ 15 ሺ የሚደርስ  ሕዝብ ይሳተፋል  ተብሎ እንደሚጠበቅ ተነግሯል፡፡
ለመርሐ ግብሩ ተሳታፊዎች የአዋቂና ሕጻናት ቲ-ሸርት መዘጋጀቱ የተገለጸ ሲሆን፤ ቲ-ሸርቶቹ ለአዋቂ 500 ብር፣ ለሕጻናት 300 ብር እንደሚሸጡ  ታውቋል፡፡  ቲ-ሸርቶቹን በሁሉም የሜሪጆይ ኢትዮጵያ ቢሮዎች  (በአስኮ ፣ በመገናኛ፣ በጊዮርጊስና ገዳም ሰፈር) እንዲሁም በዋና ዋና የዳሽን ባንክ ቅርንጫፎች (በልደታ፣ በጣና ገበያ ፣ በአድዋ አደባባይ፣ በፒያሳ፣ በጦር ሐይሎች፣ በቄራ፣ በንፋስ ስልክ፣ በቦሌ መድሃኒያለምና በሰሚት ቅርንጫፎች) ማግኘት እንደሚቻል ነው የተገለጸው።
የሜሪጆይ ኢትዮጵያ መስራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ ባስተላለፉት መልዕክት፤ “አረጋውያንን እመግባለሁ፣ ጤንነቴን እጠብቃለሁ” በሚል መሪ ቃል በሚካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ ሩጫ መርሐ ግብር ላይ፣ ሁሉም ለበጎ አድራጎት ስራ ተነሳሽነት ያለው ዜጋ እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።
 መቶ ሕጻናትን በመርዳት ሥራውን ሀ ብሎ የጀመረው ሜሪጆይ ኢትዮጵያ፤ በአሁኑ ወቅት ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ ወገኖችን እየረዳ እንደሚገኝ ሲስተር ዘቢደር ገልጸዋል። በተጨማሪም፣ “ኢትዮጵያውያን ለኢትዮጵያውያን” በተሰኘው የበጎ አድራጎት እንቅስቃሴ፣ ከ6 ሺ 500 በላይ ሕጻናት እርዳታ ማግኘታቸውን ጠቁመዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ፣ አስኮ አካባቢ የተገነባው የሜሪጆይ ሆስፒታል ከ3 ወራት በኋላ እንደሚመረቅ የገለጹት ሲስተር ዘቢደር፤ ሆስፒታሉ ለ25 ሺ ታካሚዎች ነጻ የሕክምና አገልግሎት እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም፣ ከአሜሪካ የሲያትል ከተማ የነርሶች ማሕበር ለሜሪጆይ ኢትዮጵያ 18 የዳያሌሲስ ማሽኖች እንደተላኩ፣ በእነዚህም ማሽኖች አማካይነት ሐዋሳና አዲስ አበባ የኩላሊት ሕክምና ማዕከላት እንደሚከፈቱ ሲስተር ዘቢደር አክለው ጠቅሰዋል። በሌላ በኩል፣ ወጣት ባለሃብቶች የሚሳተፉበት ለሜሪጆይ ኢትዮጵያ አጋዥ የሆኑ የድጋፍ ስራዎችን የማስተባበር እንቅስቃሴ፣ ሐዋሳና አርባምንጭ ከተሞችን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች በቅርብ ቀናት ውስጥ እንደሚከናወን ተናግረዋል።

Read 14792 times